www.maledatimes.com ፊደላዊ ምሁሩ ሐይለማርያም ደሳለኝ የመራሹ ደርግ ዋና አቀንቃኝ የኢሰፓ አባል ነበር:: - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፊደላዊ ምሁሩ ሐይለማርያም ደሳለኝ የመራሹ ደርግ ዋና አቀንቃኝ የኢሰፓ አባል ነበር::

By   /   October 8, 2012  /   Comments Off on ፊደላዊ ምሁሩ ሐይለማርያም ደሳለኝ የመራሹ ደርግ ዋና አቀንቃኝ የኢሰፓ አባል ነበር::

    Print       Email
0 0
Read Time:29 Minute, 5 Second
በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን ትምህርታቸውን ተከታትለው በማዕርግ መመረቅ ከቻሉ የዐመድ አፋሿ እናት ሃገር ልጆች መካከል አንደኛው ነበር። ጥሎበት  የመረጠውንና የዕለት እንጀራዬን ያሳምርልኛል ያለውን ሙያ ብቻ መከታተልን እንጂ ፖለቲካ ይሉትን ነገር እነደኮረንቲ ሲሸሽ ነው የኖረው። ጨዋነት ተፈጥሮው ነው። “እሺ” ባይነት መለያ ባሕርይው።
በስተኋላ እራሱ በአንደበቱ እንደመሰከረው የታናናሾቹን ቤተሰባዊ ሸክም መሸከም ነበረበትና የታላቅነቱን ድርሻ አቅሙ በፈቀደው መጠን ለመወጣት ከማለዳው አንገቱን ደፍቶ መማሩንም ይሁን “ሲጠሩት አቤት! ሲልኩት ወዴት?” ባይነትን ሳያውቀው ልዩ መታወቂያው አደረገው፡፡ በዚህ ላይ የሚከተለው የክርስትና ዕምነት አክራሪነቱ፤ማለትም “ክርስቶስ የፈቀደውንና እሱ የወደደውን የታዛዥነት ተግባር ብቻ መፈጸም ነው ጥሩ…” የሚለው ህይወታዊ መርሁ በዓለም ምርጫ ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን “እንደ ዕባብ ብልህ፣እነደ ዕርግብ የዋህ” የመሆንን ሚዛን አሳተው።
ሚዛኑን ከማለዳው በመሳቱም እንደ ካለብሬስ  ተሳቢ ወይም እነደ ጋሪ ተጎታች ለመሆን ተገደደ፡፡ ድንገት መርጦ ዘው ያለበትን መድረክ አውጥቶና አውርዶ፣አይቶና ገምቶ መተውን ወይም ለመለወጥ መሞከርን እንደአስተውሎት ሳይሆን “እንደክህደት” የሚቆጠርበት ሆኖ ተሰማውና “እሺ ባዩ” ልጅ እንደወጣ ቀረ፡፡ የብሔር ልክፍተኛ፣የጎጠኞች ታማኝ መልዕክተኛ ብቻ ሳይሆን ዋንኛ ጉዳይ አስፈጻሚ መሆን የጉልምስና ዕድሜው ዕጣ ፈንታ ሆነና አረፈው።
ይህ ሰው ለወንድም እህቶቹ የሚያደርገው፣ለእናት ለአባቶቹ ልጆች  ጥቅም ሲል ብቻ የሚፈጽመው ማናቸውም የ “እሺ” ባይነት ተግባር ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ እንደፈጸመው ታላቅ ሥራ ሆኖ የሚሰማው ተላላ ቢጤም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ብዙውን ግዜ ሲናገር የሚሰማውም እንደዚህ ዓይነት ሰው ለመሆኑ አስረጅ ነው። “ወንድሞቼ አባ ነው የሚሉኝ፣የዚህም ምክንያቱ የሞተውን አባቴን በመተካት ለቁም ነገር ያበቃኋቸው እኔ በመሆኔ ነው…” ማለትን ማዘውተሩ፤ከሃገራዊ አመለካከቱ ይልቅ ከጎጠኝነትም፣ከመንደርተኝነትም ደረጃ እጅግ ዝቅ ብሎ ከራሱ ቤተሰብ ሃሳብ የማይላቀቅ “ቤተኛ” አድርጎ አስቀርቶታል።
ይሄም ሁሉ ሆኖ ይህን ሰው በዘመነ መንግሥቱ ኃይለ-ማርያም ዘመን፤ በትምህርቱ ደካማ ነው፣የመጠጥ፣ ያልባሌ ልማዶችና ሱሶች ተገዥ ነበር…ብሎ ሊያማው የሚችል ሰው አልነበረም፡፡ በእርግጥ እሱ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ “ፊደላዊያን” እንደሚላቸው ዓይነት ተማሪ መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ የሙጥኝ ብሎ በያዛት ሙያ ውጤት ለማምጣት ዕንቅልፍ አጥቶ የሚያጠና፣ከቤተ-መጽሐፍት የማይጠፋ ተማሪ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከውሃ ምህንድስና ሙያው ውጭ ያችኑ መጽሐፍ ቅዱሱን ብድግ ያደርጋል እንጂ ሌላው ሌላውን ዕውቀት ምንአልባት ይጠቅመኝ ይሆናል እንኳ በማለት በተጓዳኝነት መመልከቱን ወይም አብስሎ መመርመሩን አልመረጠም፡፡
ዛሬ ላይ ሆኖ “ያለ ፈቃዴ ነበር የተመደብኩት…” ገለመሌ እያለ ለመዘላበድ ቢሞክርም የአዲስ አበባ የከፍተኛ ትምህርት ግዜውን ሲያጠናቅቅ ወደ አርባ ምንጭ የውሃ ኢንስቲትዪት ተቋም በመምህርነት ተመደበ፡፡ ግን እሱ የምህንድስናን ሙያ አጥንቶ ሲያበቃ ወይም ምስኪኗ እናት ሃገር “ለወደፊቱ ዘመን ዜጎቼ ሊጠቅም ይችላል” በምትለው የተግባር ሙያ እንዲማር ካደረገቸው በኋላ ጎንደር ቸቸላ ወይም ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ወይስ አዲስ አበባ መቀመጠን ነበር የፈለገው? ለነገሩ የሰው ልጅ መብት ሲለጠጥ የሕክምናን ሙያ የመረጠ ሰው ሲፈልግ በሽተኛ ወይም ዕብድ ሆኖ መኖርን ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር የሌላውን መብት እስካልተጋፋ ድረስ ነው…እንዳሉት ወደማይቀረው መንገድ “ያለግዜው” ሄደዋል…የተባሉት ሰው፡፡
እሺ ባዩ ሰው ከአርባ ምንጭ የተሻለ ለትውልድ መንደሩ ለአረካ የሚቀርብም የሚመችም ሥፍራ እንደሌለ ዛሬ ብቻም ሳይሆን ያኔም ልቦናው ነግሮታል፡፡ ግን “ታሞ የተነሳ ፈጣሪውን ረሳ” ነውና በወጣትነቱ ዘመን በአርባ ምንጭ የውሃ እንስቲትዩት መመደቡን ዛሬ ላይ ሆኖ በግዳጅ እንደተመደበበት መጥፎ ነገር ቆጥሮታል፡፡ ሰውዬው እዚያ ባይመደብ ኖሮ ከዛሬው እሱነቱ አንድ ነገር ይጎልበት እንደነበር ግን አልተገነዘበም መሰል፡፡ የትላንት ማንነት  ለዛሬ ምንነት መስታወትና የጥንካሬ ምርኩዝ መሆኑን ሰው እንዴት ይስታል?
ያም ሆነ ያም ሆነ ያ ወጣት አርባ ምንጭ በመምህርነት ሲመደብ ከተመዳቢዎቹ ስድስተኛው ነበር፡፡ አምስት የዩንቨርስቲ ተመራቂዎች ከእሱ ጋር ስድስት ማለት ነው የኢንስቲትዩቱ ቀዳማይና ኢትዮጵያውያን አስተማሪዎች ሆኑ፡፡ ከእሱ ጋር በተቋሙ ተመድበው የማስተማር ሥራቸውን ጀምረው ከነበሩት  ተማሪዎች መካከል  አራቱ ለሙያቸው ብቻ ሳይሆን ለአፍለኛው የወጣትነት ስሜታቸው ተገዥዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው በትምህርት ችሎታውም ይሁን በትጋቱ ከእሱ የማይተናነስ ቢሆንም በጥቂቱም ቢሆን የአራቱን ባልደረቦቹን ፈለግ በትርፍ ግዜው የሚከተል፣ለማህበራዊ ግንኙነት መዳበር ሲል ዋጋ የሚከፍል ዓይነት ሰው ነበር፡፡ “እሺ” ባዩ ሰው ግን መዝናናት ብሎ ነገርንም ሆነ ማህበራዊ ግንኙነት መፍጠር የሚባሉትን ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ግዜ ያጠረው ነው፡፡ ትምህርት ያስተምራል፣ከትምህርት ክፍለ ግዜው ውጭ በቤተ-መጽሐፍ ውስጥ ይመሽጋል፡፡ ምናልባትም ወደ ቤተሰቦቹ መልዕክት ለመስደድ ወረቀት ላይ ይሞነጫጭራል፡፡ ስልክ መቶም “እንዴት ናችሁ!” ይላል፡፡ የማስተማር ተግባሩን በተመለከተም ይሁን በሙያው ጉዳይ ሲጠሩት “አቤት” ለማለት ከሌሎቹ ሁሉ የተፋጠነ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡
“መምህር እንደዚህ አድርግ!” “እሺ ጌቶች…” “አንተ ልጅ ይህን ነገር ሠርተህ እንድታሳየን!” “እሺ…እሠራዋለሁ…” ብሎ ማለት ከትህትናው ጋር ለዚያ ወጣት የአርባ ምንጭ ውሃ ኢንስቲትዩት መምህር ደስ የሚያሰኘው ነገር ነበር፡፡ የሚሆንለትንም የማይሆንለትንም ነገር ቢሆን እሺን ነው እንጂ “ዕምቢን” እና “አይሆንልኝምን” ከቶ አያውቅም፡፡ ታዲያ ይህ ሰው፤ ለተቋሙ መምህራን ከወደ ፊላንድ መጥቶ የነበረው የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆን ቻለ፡፡ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ መሆን የቻለውም ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ሆኖ በመገኘቱ ነበር፡፡
የአረካው ልጅ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆኑ ከመረጋገጡ በፊት የተቋሙ ኃላፊዎች “ማንን ብንልክ ጥሩ ነው?” የሚል ውይይት ቢጤ አካሂደው ነበር፡፡ ከውይይቱም በኋላ ወደ ፊንላንድ ለትምህርት የሚላከውን ሰው ለመወሰን እንዲያስችል በሚል በአርባ-ምንጭ የውሃ ኢንስቲትዩት የሚገኙት አስራ አንድ ሕንዳዊያን መምህራን አስተያየት እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡ በሚገርም ሁኔታ አስራ አንዱም ሕንዳዊያን  ልጁ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ሃሳባቸውን አቀረቡ፡፡ በቀረበው ሃሳብ መሰረትም በእሺ ባይነቱ፣ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ በመመሸጉና ተግቶ በማስተማሩ…የሚታወቀው ልጅ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ተወሰነ፡፡
ከውሳኔው በኋላ ሽቁጥቁጡና “እሺ” ባዩ ወጣት መምህር  ስለጉዳዩ እንዲያውቅ ተጠራ፡፡ ለምን እንደተጠራ ያላወቀው ልጅ ጥሪውን አክብሮ ከቢሮ ተገኘ፡፡ እንደተገኘም “ለተቋሙ መምህራን ስለመጣው የትምህርት ዕድል የምታውቀው ነገር አለን?” የሚለው ጥያቄ ነበር በቅድሚያ የቀረበለት፡፡ “ሲወራ ሰምቻለሁ…” የሚል መልስ ሰጠ፡፡ “የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንድትሆን መታጨትህን ብታውቅ ምን ይሰማሃል…?” የሚለው ጥያቄ ገና ከመከተሉ  ልጁ ፈጥኖ ወደ ቢሮው ኃላፊ እግር ስር በመወርወር “ጋሼ እንዴት ሊሆን ቻለ…” እያለ ምስጋናውን አዥጎደጎደው፡፡ ዕድሉ ሊያመልጠው የማይፈልግ መሆኑን…አጠቃላይ ድርጊቱ የሚሰብቅበት ያ ወጣት መምህር በወቅቱ የነበሩትን የቢሮ ኃላፊ እንደ መለኮት አድርጎ በመመልከት በተማጽኖ ዓይነት ስሜት ዓይኑን አንከራተተባቸው፡፡…
ቅድመ ትዕይንቶቹ እንዳለቁ  በኢሠፓ አባልነትና  በሌሎች ጉዞውን የተመለከቱ ሠነዶች ላይ ስም፣ፊርማውንና የመጠይቆቹን ምላሽ ካሰፈረ በኋላ ሃገሩን እንደማይከዳ፣ትምህርቱን እንደጨረሰ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ቃል ገብቶ ወደ  ፊላንድ በረረ፡፡ በሮም አልቀረ መምህሩ ተማሪ ወጣት ትምህርቱን አጠናቆ ወደ እናት ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ በነበረበትም የትምህርት ተቋም ተግባሩን ቀጠለ፡፡
ቀን አለፈ ቀናቶችም ተተኩ፡፡ የመምህር ደሳለኝ ልጅ በዕድሜውም በሥራ ዘርፍ ደረጃውም ከፍ ከፍ አለ፡፡ ግዜ አለፈ ግዜ ተተካ፡፡ ሥርዓት ተሽሮ ሥርዓት መጣ፡፡ ያለፈው “ነበር” ሲባል ደንቢጦችም “ወፍነን ወፍነን…” እያሉ ቦታቸውን ያዙ፡፡ የአረካው ልጅ በትምህርትና በማስተማር የጎለመሰበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንደሌሎች መሰሎቹ በለውጡ ነፋስና ነፋሱም ባስከተለው ማዕበል ሲታመስ፤ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” ባዩ የደሳለኝ ልጅም ከመጣው ጋር ተመቻመቸ፡፡  ለጥቂት  ጊዜያት በአርባ-ምንጭ ዩንቨርስቲ አድፍጦ ከረመና በ “እሺ”ባይነቱ ወጥመድ ተጠልፎ የጎሰኝነት ደዌ ተጋባበት፡፡ “ከለማበት የተጋባበት” እንዲሉም የምሕንድስናው ተማሪና መምህር የለየለት የመንደርተኝነት አቀንቃኝ ሆነ፡፡ መለስ “ዋናው ታማኝነቱ ነው፤ዘበኛም ቢሆን ሚንስትር መሆን ይችላል…” ያሉት ሆነና ኃይለማርያም ደሳለኝ የደህዴን ሊቀመንበር፣ቀጥሎም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድር ሆኖ ብቅ አለ፡፡
ምስኪኑ “እሺ” ባይ ሳሩን እንጂ ገደሉን አላየውምና በደህዴን ሊቀመንበርነቱና በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድርነቱ ጦስ የአዋሳው ዕልቂት ሰለባ ለመሆን ተገደደ፡፡ እሱ ሰለባ የሆነበት ድርጊት ኃይለማርያምን ላዘመቱት ጎጠኖች “ጥቅም” ሰጥቷልና ስለውለታው ብለው አዝማቾቹ የአረካውን ልጅ ከአዋሳ ወደ አዲስ አበባ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ በአማካሪነት ስም ገለል አደረጉት፡፡ ስለማንም ቢሆን ውለታ የመሰለው ነገር እንጂ አደጋው ፈጥኖ የማይታየው “እሺ” ባዩ የአረካ ልጅም በይበልጥ ታማኝ ሆኖ ለመገኘት በአጎብዳጅነቱና በ“አቤት!ወዴት?…” ባይነቱ ቀጠለ፡፡ በዚህም ሂደቱ ለአፍታ እንኳን ሳይጠራጠር የኢሕአዴግን ዓላማ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ፣ሟቹን የድርጅቱን ሊቀመንበርና የኢሕአዴጉን መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር ደግሞ እንደ ክርስቶስ ተቀብሎ በመንጎዱ የምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነትንና የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነትን አክሊል ተቀዳጀ።
ደግሞም ግዜ መጣ፡፡ ጳሱና ንጉሱም ተከታትለው አሸለቡ፡፡  “እሺ” ባዩ ምስኪን ግን ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ እነሆ ሃዘኑም ለቅሶውም አልፎ ኃይለማርያም በመለስ መንበር ላይ የተቀመጠው የሕወሓት ኢሕአዴግን መንግሥታዊ መሠረት ባጸኑት ሰዎችና የመለስ የስልጣን ተገን በሆኑት ምዕራባዊያን መልካም ፍቃድና በ “እሺ” ባይነቱ ፈርቱና እንጂ በፖለቲካዊ ብልሃቱ ወይም ብስለቱ እንዳልሆነ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ “ኧረ አይደለም የጠላት ወሬ ነው፤ የአረካው ልጅ አሁን ያለበት ቦታ ላይ የደረሰው በብልሃቱና በብስለቱ ነው” የሚል ተሟጋች ከመጣም የኛን ስህተት የእነሱን አስተዋይነት ወደፊት እናየዋለን፡፡ ዕድሜና ጤና ካደለን፡፡
ያም ሆነ ያም ሆነ ከአዋሳው ዕልቂት ጉዳይ አስፈጻሚነት አምልጦ በቤተ-መንግሥት ተሸሽጎ የቆየው ሰው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኗል ተብሏል፡፡ የአርባ ምንጩ የውሃ ምሕንድስና ባለሙያና በ “እሺ” ባይነቱ ብቻ የሚታወቀው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መንበረ ጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሲረከብ “የአቶ መለስን ውርስ ለማስቀጠል…ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እገባለሁ…” ማለቱን እንጂ ካቢኔ ስለመሻር ስለመሾሙ፣የኔ ነው የሚለውን ጉዳይ ለማስፈጸም ዓላማ ያለው ስለመሆኑ ፍንጭ አልሰጠንም፡፡ ምንም እንኳ የቸኮልን ቢመስለንም ከአቶ ኃይለማርያም የነበረ ስብዕና ስንነሳ፤በችግር ቋፍ ላይ ያለውን የሃገሪቱን ውስብስብ ችግር በ “እሺ” ባይነታቸው ጠባይ  ግፊት  ጭራሽ ገደል ይገፈትሩታል የሚል ስጋት ይኖረናል፡፡ ስጋታችን ደግሞ እንደው ዝም ብሎ ከምድር የበቀለና በሬ ወለደ ዓይነት ነገር አይደለም፡፡
ሃገርና ሕዝብን ለማስተዳደር ብቃት፣ለበሳል ፖለቲካዊ ስብዕና መኖር፣ጥቅምን ለሚያስከብር ዲፕሎማሲያዊ ችሎታ…መሐንዲስ መሆን ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡  “ፊደላዊ ምሁርነትም” አደጋ አለው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ “እሺ” ባይነት ቀሳፊው ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የሚመዘነው የአቶ ኃይለማርያም ስብዕና ለኢትዮጵያ ታላቅ አደጋ፣ታላቅ የፈተና ግዜ አለመሆኑን አለመገንዘብ በራሱ የዋህነት ነው፡፡ በእስካሁኑ ድርጊታቸው ርዕይ አልባ ወራሽ ሆነው በሚታዩት ተተኪው ጠቅላይ ሚንስተር ዙሪያ የሚስተዋለው አደጋና ፈተና ደግሞ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን መሆኑ አጠራጣሪ አይሆንም፡፡ ምን አልባት ይህ ጥርጣሬ ፍሬ ቢስ የሚሆነው “እሺ” ባዩ ሰውና በእስከ አሁኑ የነጠረ እውነት ርዕይ አልባ ወራሽ ሆነው የሚታዩት ሰው ከ “እሺ” ባይነታቸው ጀርባ የሸሸጉት አሻፈረኝ ባይነት፣ፖለቲካዊና ብሔራዊ ቁርጠኝነት ወይም ለሃገርና ለወገን የተቆርቋሪነት ስሜት ካላቸው ነው፡፡ ይህ መገለጥ እስኪመጣ ግን የአረካው ልጅ ርዕይ አልባ ወራሽ መሆናቸውን መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ታላቅሰው ምንአለ ራዕይ አልባው ወራሽ!
MS
ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን  ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 8, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 8, 2012 @ 10:24 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar