www.maledatimes.com ይህም ደግሞ ያልፋል! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይህም ደግሞ ያልፋል!

By   /   October 8, 2012  /   Comments Off on ይህም ደግሞ ያልፋል!

    Print       Email
0 0
Read Time:11 Minute, 27 Second

ይህም ደግሞ ያልፋል

HMriam“እኔ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በዛሬው ዕለት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርቤ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ፌዴራል ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኜ ስሰየም፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ በመሆን ከአገሪቷና ከሕዝብ የተጣለብኝን ኃላፊነት፣በቅንነት፣ በታታሪነት፣ እንዲሁም ሕግንና ሥርዓትን መሠረት በማድረግ፣ ሥራዬን ለመፈጸም ቃል እገባለሁ።”

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር፣ መስከረም 11/2005 ዓ.ም፣ ይህንን መሓላ ከፈጸሙ በኋላ፣ ቀጥለው 18 ደቂቃ የፈጀ ንግግር አሰምተዋል። እኛም፣ በሥርዓቱ ላይ የታዘበነውን ሁለት ጉልህ ጉዳይ ለማንሳት ተገደናል። የመጀመሪያው፣ በአብዛኛው የዓለም መንግሥታት ዘንድ እንደሚደረገው በመሓላው ላይ የእግዚአብሔር ስም አለመጠራቱ ነው። የእግዚአብሔር ስም ክብር እንጂ ማፈሪያ ሊሆን አይገባም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በሚያውቀው መንገድ ከዳር እስከዳር የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሕዝብ ሆኖ ሳለ፣ መሪዎቻችን የሕዝቡን ስሜትና ፈቃድ ለመወከልና ለማክበር ያለመፍቀዳቸው ጉዳይ ነው። አውስትራልያ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ወዘተ፣ መሓላቸውን፣ “እግዚአብሔር ሆይ፣ እርዳኝ” ብለው ሲደመድሙ። ጋና፣ ግብጽ፣ ሕንድ፣ ወዘተ፣ ደግሞ ከመነሻው “በእግዚአብሔር ስም” ወይም “በኃያሉ እግዚአብሔር ስም” ብለው ይላሉ። ቻይና የእግዚአብሔርን ስም ከማይጠሩ ጥቂት አገሮች መካከል ነች። ታዲያ በቻይናም እንኳ የሥልጣንን አታላይነት ለመግታት፣“ቃለ መሓላዬን ባፈርስ፣ መንግሥት የሚሰጠኝን ጽኑ ቅጣት ለመቀበል ቃል እገባለሁ” ይላሉ። መሓላቸውን ለሚያፈርሱም የሚሰጠው ጽኑ ቅጣት በአብዛኛው የሞት ቅጣት ነው።

በኮስታ ሪካ ደቡብ አሜሪካ ደግሞ፣ መሓላው የሚፈጸመው ከሐተታ ይልቅ በጥያቄና መልስ መልክ ነው፦ መሓላ አስፈጻሚ፦ “በእግዚአብሔር ፊት … ቃል ትገባለህ?”። ፈጻሚ፦ “አዎን”። አስፈጻሚ፦ “ቃልህን ከጠበቅህ፣ እግዚአብሔር ይርዳህ፣ ካፈረስክ፣ እግዚአብሔርና አገሪቱ ይፋረዱህ።”

ከላይ በተዘረዘሩት አገሮች ሕገ-መንግሥት ላይ ሃይማኖትና መንግሥት የተነጣጠሉ ለመሆናቸው በግልጽ ሠፍሯል። በዚያው ልክ፣ ሃይማኖትም መንግሥትም የሕዝብና ከአምላክ ሥልጣን ሥር እንደሆኑ አልተዘነጋም። የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ለምን አስፈለገ? በመጀመሪያ፣ ሥልጣን ከርቀት እንደሚያዩት ስላልሆነ፤ ሕዝብን ማስተዳደር ቀላል ስላይደለ። እንኳንስ ሕዝብ፣ ቤተሰብ ማስተዳደር ከባድ ስለሆነ። የመንግሥት አስተዳደር የእግዚአብሔር እጅ ካልገባበት በሰው ብርታትና ብልሃት ብቻ የሚሞከር ስላይደለ። ለዚህ ነው የመንግሥታት መሪዎች ከጥንት እስከ ዛሬ ከራሳቸው ውጭ ወደ ሆነ ኃይል የሚጣሩት። መሣሪያ የሚያነሱት። አንዳንዶችም ወደ ጠንቋይ ቤት የሚመላለሱት። እግዚአብሔር ሰው ስላልሆነ፣ ለሰው የማይቻልና የማይታይ ሁሉ ለርሱ የሚቻልና የሚታይ ስለሆነ። እግዚአብሔር በስውር የሚደረገውን ሁሉ የሚያይ፣ አድልዎን የማያውቅና የማይወድ አምላክ ስለሆነ። የሚያይ ብቻ ሳይሆን የሚፈርድም ስለሆነ። “ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል” [ማቴዎስ 12፡36]። “ሰዎች” ሲል ሁሉን ይጨምራል፤ ሰዎች አመኑ-አላመኑ ቅንጣት ታክል ለውጥ አያመጣም፤ ስለ ሠሩትና ስለ ተናገሩት መልስ ይሰጡበታል። እግዚአብሔር ሲፈርድ፣ አንዳንዴ ቆይቶ፣ አንዳንዴ ፈጥኖ ነው። ሳይፈርድ የቀረበት ጊዜ ግን አንድም የለም። የፍርዱ አመጣጥ መቸና እንዴት እንደሆነ ስለማይታወቅ ዘወትር በጥንቃቄ መጓዝን ይጠይቃል። እግዚአብሔር ለባልቴቱና ለደሃ አደጉ ዳኛ ነው። በሥልጣን ላይ ያሉ በስውር መማለጃ [ጉቦ] ሲቀበሉ፣ ድንበር ሲገፉ፣ ሲከፉ፣ ሕዝቡን ሲያንገላቱ ያያል ማለት ነው። ራሳቸውን ከሕግ በላይ እንደሆኑ ሲያስቡ፣ ፍትሕን ጥለው የሕጉን ሚዛን ሲያጋድሉ ያያል፣ ይጸጸቱ እንደሆነ ይታገሳል። በሥልጣን ላይ ያስቀመጣቸው እርሱ ሆኖ ሳለ፣ ራሳቸው እንደሆኑ፣ የወገን የጥበብ የሃብት ብርታት እንደሆነ ማሰብ ሲጀምሩ፣ ነገሩ ይኸ እንዳልሆነ ለማሳየት በሰው ሁሉ ፊት ያወርዳቸዋል።  

ሁለተኛው ጉዳይ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ባሰሙት ንግግር ላይ “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለታላቁ መሪያችን ይሁን!” የማለታቸው ጉዳይ ነው። “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ” ማለት ምን ማለት ይሆን ብለን ስናሰላስል ከርመን ፍቺው ስላለተገለጠልን ጥያቄአችንን ለመለጠፍ ተገድደናል። ይህ መሰል ውዳሴ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚቀርብ ስለሆነ አጠቃቀሙ ጥንቃቄ ያሻዋል እንላለን። በመጽሐፈ ራእይ ምዕራፍ 5፡ከቁጥር 13-14 ላይ እንዲህ ተጽፎአልና፦ “ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጡራንም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤‘በዙፋኑ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።’ አራቱ ሕያዋን ፍጡራንም፣ “አሜን” አሉ። ሽማግሌዎቹም በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።”

ወቅቱ መሪ ሞቶ በሌላ መተካቱ የታየበት ወቅት ስለሆነ፣ በአገራችን ታሪክ ውስጥ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ንጉሥ፣ ከዐይኑ ፊት የሚያኖረውና ለሁሉ ሰዓትና ሁኔታ የተስማማ ቃል ጽፈው እንዲያመጡለት አማካሪዎቹን አዘዛቸው ይባላል። በመጨረሻም መክረው ያቀረቡለት ቃል፣ “ይህም ደግሞ ያልፋል” የሚል ነበረ። አዎን፤ ይህም ደግሞ ያልፋል። ሰው ያልፋል፤ ሥልጣን ያልፋል፣ ባለሥልጣን ያልፋል። ውበትና ጉብዝና ያልፋሉ። ዘመንና ትውልድ ያልፋሉ። የማያልፍ እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ረድዔት ያለበት ብቻ ነው። መሓላ በሚፈጸምበት ሰዓት የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው።       ምንጩ www.Ethiopianchurch.org   

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 8, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 9, 2012 @ 12:31 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar