www.maledatimes.com ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር 6ኛ ክፍል (በግሩም ተ/ሀይማኖት) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር 6ኛ ክፍል (በግሩም ተ/ሀይማኖት)

By   /   October 9, 2012  /   Comments Off on ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር 6ኛ ክፍል (በግሩም ተ/ሀይማኖት)

    Print       Email
0 0
Read Time:26 Minute, 8 Second

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል 6ኛ
እንደጅብ ቆዳ ቅኝቱ ሁሉ ‹‹እንብላው..እንብላው..›› ብቻ ሆንብኝ
በግሩም ተ/ሀይማኖት


ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር

ሰላም ወዳጆቼ ነዛር የተባለ ወዳጄ የሰጠው አስተያየት ላይ …ወዳጄ ግሩም ባለህበት ቦታ ሰላምታዬ ይድረስ፡፡ /እፍኝ ሙሉ ስላምታህ ደርሶኛል/ በጽሁፍህ መግቢያ የገለጽከውን የኩዌት የሞተውን ልጅ ሀዘን ጨምሮ እስከመጨረሻው ያለው ጽሁፍ በጣም ያሳዝናል፡፡ በእርግጥ የኩዌቱ ልጅ ሞት የቅርብ ጊዜ ሀዘን ነው፡፡ እኛም እስከመጨረሻው የማንረሳው ወንድማችን ነበር፡፡ በሀዘን በመረረ ቃልም ነው ሞቱ እውን አልመሰል ቢለኝ በጽሁፍ ያቀረብከውን የሀዘን እሮሮ የጻፍኩት፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ወንድማችንን አጣነው፡፡ ይህ እንግዲ በኔ የደረሰ የቅርብ እውነታ ነው፡፡ ዛሬም ግን ኩዌት ውስጥም ሆነ የተቀረው አረብ ሀገር የዜጎቻችን ግፍ፣ በደል፣ ሞት፣ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሁኖ አንድም ጥሩ ነገር ለመሰማት ጆሮአችን አልታደለም፡፡ እኔማ አንዳንዴ በቃ ሀበሻ ዋጋው እንዲህ ሆነ፣ ማነው ይህንን በደል የሚያስቆም? መቼ ነውስ በየአረብ ሀገሩ ለሚንገላታው ዜጋ መላ የሚሰጠው? የውስጤ መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡

ከመቼውም በተለየ መልኩ እርስ በእርሳችን ተጨካከንን ድህነታችንም ከፋ፡፡ ለማንም አረብ መጫወቻ ሆንን፡፡ ታዲያ የዚህ ችግር መፍቻ ቁልፉ ምንድነው፡፡ በ2004 ወደ አረብ አገር የተሰደደውን ሰደተኛ ብዛት ለአንተ አልነግርህም፡፡ /እሱ ለእኔ ባይነግረኝም እኔ ልንገራችሁ፡፡ በ2011 ብቻ 103.000 ኢትዮጵያዊያን ወደ የመን ገብተዋል፡፡ ይሄ አንድ ሀገር ነው በአጠቃላይ አረብሀገር አስሉት፡፡/ ለኔ ጉድ ያሰባለኝ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ እየተመለስኩ ኤርፖርት ያገኘኋት አንድ የቅርብ ወዳጄ ግን ውስጤን ይበልጥ እንዲሰበር ነበር ያደረገችኝ፡፡ ነርሰ ናት፡፡ በሙያዋም ተቀጥራ ትሰራ ነበር፡፡ አንድ ወቅትም የድግሪ ትምህርቷን ቀጥላ እንደነበረ አጫውታኛለች፡፡ በዛን ሰዓት ሳገኛት ግን በሀገሯ መኖር አማሯት ሳውዲአረቢያ የቤት ሰራተኛ ሆና ለመሄድ ስትል ነበር ኤርፖርት የተገናኝ ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንግዲ ምንም የለም፡፡ መጪው ጊዜ ግን እንዲህ አይነት የዜጎች ሰቆቃ ፡ የማናይበት እንዲሆን የዘውትር ምኞቴ ነው………ብሏል፡፡ የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡

ያን ተከትሎ አንዲት ልጅ ቻት ስታደርገኝ የመምህራን ኮሌጅ ዲፕሎማዋን ይዛ ታስተምርበት የነበረውን ትምህርት ቤት ተሰናብታ ወደ አቡዳቢ መንጎድዋን ስትነግረኝ መሪር ሀዘን ነው የተሰማኝ፡፡ ሀገር ውስጥ የተማሩት ስራ አጥተው ኮሊንስቶን ይሰራሉ ተብሎ በሚዲያዎች ገኖ መውራቱ ገርሞኝ ነበር፡፡ የገረመኝ መስራታቸውን ተቃውሜ አልነበረም፡፡ ሀገራቸው ሆነው ቢሰሩ ምናለበት በሚል ነው፡፡ ዲፕሎም እና ዲግሪ ይዘው እንደዚህ በሰው ሀገር መገረድን ሲሰማስ ምን ይባላል? በሀገር የተገኘውን መስራት ክብር መሆኑ ይሰመርበት፡፡ ጀምሬው የነበረውን ሀበሻዎች በሉብናን ያላቸውን ህይወት የሚዳስስ ታሪክ ልመለስበት ወደድኩ…. ከዛ በፊት ግን አዜብ የተባለች የፌዝቡክ አንባቢዬ ስልኬን አንኳኳች፡፡ ስከፍተው ጠላታችሁ ክፍት ይበል ልብ የሚያለሰልስ ብርጭቆ ወረቀት የሆነ ድምጽ በጆሮዬ ተንኳለለ፡፡ ‹‹ግሩም ተ/ሀይማት ነህ?›› ስሜን ከእነአባቴ ግሩም ተ/ሀይማት ብላ ስትጠራ..ት/ቤት ክፍል ውስጥ የሚደረግ ስም ጥሪ መስሎኝ ‹‹አቤት!›› ብዬ በጩኸት ላደምቀው ስል ‹‹..ነህ..›› የሚለውን ጨመረችልኝ፡፡ አቤት የኔ ቆንጆ ቲቸር ማን ልበል? አልኳት፡፡ የተደወለልኝ ቁጥር ከየመን ስለሆነ የሚያውቁኝ ናቸው ብዬ ለመቀለድ፡፡

የሆነ ደስ በሚል ቅላፄ ‹‹አታውቀኝም እዚህ የመን መጥቼ ነው፡፡ ችግር ገጥሞናል፡፡…›› ሳግ ነገር የተናነቃት መሰለኝ፡፡ ‹‹..ሸሽሽ…›› የሚል ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ‹‹..የለ ተሀረኩ..የለ..›› የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ ‹‹አናግሪው ቶሎ በይ..›› የሚል ድምጽ ከጀርባ በደከመ ሁኔታ ይሰማል፡፡ ‹‹ሄሎ ከኤርፖርት ይዘውን ሚግሬሽ እስር ቤት ሊወስዱን ነው፡፡ ምን ትረዳናለህ..እባክህ እርዳን ወደ ሀገር ሊመልሱን ነው፡፡ መመለስ አልፈልግም እባክህ…›› በለቅሶ ታጀበ፡፡ አይኔ ባያነባም ውስጤ ግን አብሯት አነባ፡፡ ቢሆንም መጠየቅ ስለነበረብኝ ከየት ኤርፖርት ነው የያዟችሁ ወዴት ስትሄዱ..

‹‹ሰነዓ ኤርፖትርት ላይ ነው የያዙን ወደ ቤይሩት እየሄድን ነበር…›› ተቋረጠ፡፡ ሜግሬሽን ሄጄ ላገኛቸው ፈለኩ፡፡ ያለሁበትን ሱቅ የሚጠብቅልኝ ሰው ስፈልግ ቆየሁና አገኘሁ፡፡ በዚህ አገር አጠራር ጀዋዛት የሚባለው እስር ቤት ሄድኩ፡፡ አሁን ስላወኩት ከፊት ተጠቀምኩኝ እንጂ በሰዓቱ ስሟን ስላልነገረችኝ ማን ብዬ ላስጠራት፡፡ ተጠጋሁና ተደወሎልኝ ነበር ማን ነው የደወለልኝ ስል ‹‹አዜብ..›› አሉ እና ጠሯት፡፡ ትንሽዬ ልጅ መጣች፡፡ እድሜዋ ያለማጋነን 16 ወይም 17 ቢሆን ነው፡፡ ግራ መጋባትና ፍርሃት የተራኩቱት ፊቷን ሳይ አሳዘነችኝ፡፡ ተጨባበጥንና ‹‹ስሜ አዜብ….ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ጓደኛህ ነኝ፡፡ የምትጽፋቸውን ባይም ያለኝ አማራጭ ነው እና ቤይሩት ለመሄድ መጥቼ ኤርፖርት ላይ የእናንተ ቪዛ የተስተካከለ አይደለም ብለው 15 የምንሆነውን ያዙን አሁን ወደ ሀገር ሊመልሱን ነው እባክህ አግዘኝ ስንት ከስክሰን…›› እንባ ቀደማት፡፡ ለስደት ህይወት ማጀቢያው እንባ፣ ብስጭት፣ ፀፀት እና ጭንቀት ናቸው፡፡ የጀመረችውን ትጨርስ ብዬ በዝምታ ዝምታ ውስጥ ሰፍሬ አይኔን ከአንዳቸው አንዳቸው ላይ እያንቀዋለልኩ ጠበኳት፡፡ ብዙ አወራን፡፡

ይመለከተዋል ያልኩትን ሰው ፈልጌ ላናግር ሞከርኩ፡፡ እንደጅብ ቆዳ ቅኝቱ ‹‹እንብላው..እንብላው..›› ብቻ ሆንብኝ፡፡ እዚህ ሀገር ግልጽ ሙስና ነው ያለው፡፡ ያበደረህን ገንዘብ የሚጠይቅህ ነው የሚመስለው፡፡ ‹‹ለአንድ ሰው 400 ዶላር ክፈል እና እፈታልሀለሁ..›› ተባልኩ፡፡ ኪሴ ያለችኝ 4000 ሪያል ናት፡፡ በዶላሪኛ ስትሰላ 20 ዶላር ማለት ነው፡፡ አስቡት ልዩነቱን፡፡ ተመለስኩኝ እና ያሉኝን ነገርኳት፡፡ የሚበሉ የሚጠጡት ነገር ገዛዝቼ አቀበልኳቸው እና ብር ከላኩልኝ ደውልላቸው ላለችኝ ሰዎች ደዋወልኩኝ፡፡ አንድ ብር ያሰከረው ጉንጩን በጫት የወጠረ ሰው መጣና ‹‹አንተነህ ያናገርከው?›› አለኝ፡፡ ቢጨንቀኝ እንጂ የማወጣበት ገንዘብ እንደሌለኝ ነገርኩት ‹‹…ሁሉን ከፍዬላቸዋለሁ ማታ ወደ ቤይሩት ይሄዳሉ…›› ማንም አይወጣም ሲል ድንፋታ የምትመስል ነገር ወርውሮልኝ ሄደ፡፡

ውስጤ እያዘነ ተሰናብቻቸው ከሚግሬሽን እስር ቤት ወጣሁ፡፡ መቼ ነው ፈጣሪ የሚሰማን? መቼ ነው እንባችን ስፍሩን የሚሞላው? መቼ ነው በቃ! የሚለን? እውን መንግስት ቤይሩት መሄድን አስቦበት ነው የከለከለው? ከሆነ ይህን አይነት ድርጊት ሲፈጸም እንዴት አያውቅም? በኬንያ ቪዛ እንዴትስ የመን ሊመጣ ይችላል? የመሳሰሉትን አሰብኩ፡፡ ከማሰብ ውጭ ግን ምን አመጣለሁ? በቀረችኝ ሳንቲም ታክሲ ተሳፍሬ ጉዞዬን ስቀጥል ስለ ቤይሩት የሰማሁትን ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ያሰላሰልኩት ብዙ ነው ባለፈው ወደጀመርኩት ታሪክ ልንጎድ…..

በተከታታይ በቻት ሳጥኔ ሳትታክት እየጻፈችልኝ ያለችውን እህታችን ደግሜ ላመሰግናት ወደድኩ፡፡ ቀጠልኩ.. ከላይ እንደገለጽኩልህ ልጅቷ የተሰጣት መልስ ጥሩ ስላልሆነ መፍትሄም ስላጣች ያላት አማራጭ መጥፋት ነበርና ጠፋች፡፡ ጠፍታም ለረጅም ጊዜ የተለያየ ቤት ሰርታለች፡፡ ካንዱ ስትወጣ ስራ አጥታ ረጅም ጊዜ ስትቀመጥ ብዙ ተቸግራለች፡፡ አሁን ያለችበት ቤት ሁለት አመቷ ነው፡፡ ሰውዬው ደስ ሲለው ይከፍላታል ሲያጣ ይከለክላታል፡፡ እንደዛም ሆና እንደነገረችኝ ልጅዋን በጥሩ ሁኔታ እያስተማረች ነው፡፡ ወላጆች ግን ልጄ ምን ሰርታ ነው ብሩን ያመጣችው አይሉም፡፡

የእኔውን ቤት ጉድ ደግሞ ልንገርህ…እኔ የነበርኩበት ቤት 3 ሰው ብቻ ነው ያለው፡፡ ቀን ቀን አይውሉም፡፡ ሴትዮዋ መጥፎ የምትባል አይደለችም፡፡ ልጁ ተማሪ ነው፤ እሷ ስራ አላት፡፡ ወንድሟ ደግሞ የቤተሰብ ድርጅት ውስጥ ይሰራል፡፡ ታዲያ ግን ቤት ውስጥ ስራው ማለቂያ የለውም፡፡ የምተኛው ሌሊት 7 ሰዓት ነው፡፡ የቀኑን ወደ ሌሊት ገልብጠውታል፡፡ ቀን ቀን ቤት ስለማይውሉ ስራ ብዙም አያስቸግረኝም፡፡ ከ10 ስዓት በኋላ ግን መቀመጥ እስኪያቅተኝ በስራ ያጣድፉኛል፡፡ በዛ ላይ ከ7 ሰዓት በኋላ ያለውም ቢሆን መተኛት አትበለው፡፡ ልጇ ቀበጥ ነገር ነው፡፡ የ11 አመት ልጅ ቢሆንም አጠገቡ ያለውን ውሀ ማንሳት አይፈልግም፡፡ መጥሪያውን ተጭኖ ይጣራል፡፡ እንደሰው መተኛት ያለብኝ አይመስለውም፡፡ እሱስ ባልከፋ እንቅልፍ ነው የነሳኝ ሱሰኛ የሆነው ወንድሟ ሌላ ፈተናዬ ነበር፡፡ ፍላጎቱ የተወጠረ ስሜቱን ማርገብ ነው፡፡ ለእኛ ያለው አመለካከት በንቀት የተሞላ ነው፡፡ በቃ! ለስሜት ማስከኛ የተፈጠርን እቃዎች ነው የምንመስለው፡፡

አንዳንዶቹ በፍርሃትም ይሁን በፍላጎት ፍቃደኛ ስለሚሆኑላቸው መሰለኝ ‹‹..አንቺ ከሌሎቹ በምን ትበልጫለሽ? በፊት ከነበሩት ውስጥ እከሊትን..እከሊትን እንዲህ አደርግ ነበር ይለኛል ስማቸውን እየጠራ፡፡ እሺ እንደማልለው ሲያውቅ ሁሌም ይዝትብኛል፡፡ ለሴትዮዋ የሆነ ያልሆነውን ይነግራታል፡፡ በዚህ ምክንያት ከማንም ጋር እንዳልገናኝ ቤት ትቆልፍብኝ ነበር፡፡ በዚህ በጣም ስማረር ቢሮ ሌላ ቦታ እንዲቀይሩኝ ነገሬ ተቀየርኩ፡፡ የተቀየርኩበት ቤት የሚገርምህ ጥቁር አትወድም፡፡ የወሰደኝ ባልዋ ነበር፡፡ ከእኔ በፊት የነበረችው ማዳጋስካራዊ ቀላ ያለች ነበረች፡፡ ከእኔ ጋር አንድ ፊሊፒኒሳዊ ተቀጥራለች፡፡ ሁለት ነን ማለት ነው፡፡ እኔ 4 ልጆቿን እይዛለሁ ፊሊፒንዋ ቤት ታጸዳለች፡፡ ምግብ ቤት ውስጥ አይሰራም፡፡ እዛ ፎቅ ላይ ያሉት ሁሉ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ልጆቹ አያቶቻቸው የሰሩትን ነው የሚበሉት፡፡ አባትየው የት እንደሚበላ አናውቅም፡፡ እሷ ከልጆቹ ጋር ትበላለች፡፡ እኔና ፊሊፒኗ በመሀል ፍዳችንን በላን፡፡ አንድ ሴጣናም ልጅ አላቸው እሱን ይዤ ስንቀዋለል ነው የምውለው፡፡ ከፊሊፒንስዋ እንዲያውም እኔ እበላለሁ፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ አያት ቤት ያለችው ሀበሻ ነች፡፡ እስዋ ትሰጠኛለች፡፡ የምግቡ እና የልጁ ሁኔታ ሲመረኝ ጠፋሁ፡፡

ከመጥፋቴ በፊት እሰራበት የነበረው ቦታ ከፊት ለፊት ያለው አፓርትማ ላይ ያለችው ደግሞ ጠዋት11 ሰዓት ተነስታ ስራ ትጀምር እና ሌሊቱን ሁሉ አትተኛም፡፡ ስራ ባይኖር እንኳን እህቶቿ ጋር ትወስዳታለች፡፡ ሌላም እታች ያለች ኢትዮጵያዊት አለች፡፡ እሷ ደግሞ ከማንም ጋር እንድትገናኝ አትፈቅድላትም፡፡ መውጫ ሰዓታቸውን ጠብቃ ነው ወደ እኛ የምትመጣው፡፡ የእሷ አሰሪ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ፓንቷን እንኳን ማውለቅ አትፈልግም፡፡ ለሁሉ ነገር ጥሪ ነው፡፡ ቤቱን ካጸዳች በኋላ ሴትዮዋ ቼክ ታደርጋለች፡፡ በዚህን ጊዜ አውቃ ግርግዳው ላይ ወይም ሶፋ ስር ቆሻሻ ታደርግና አልጸዳም ብላ ታሰቃያታለች፡፡ ከጨረሰች እኛ ያለንበት አፓርትማ ላይ እህቷ ስላለች እሷም ጋር ታሰራታለች፡፡ ከጠፋሁ በኋላ ግን ምን ላይ እንዳለች አላየኋትም፡፡

አሁን የምሰራው ከከተማ ወጣ ያለ ቦታ ነው፡፡ ያለሁበት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ስራቸው ግን ያስጠላል፡፡ ሴትነታቸውን ይሸቅጣሉ፡፡ ከተማውን እንደጨረስክ ያለው ቦታ ነው የሚሰሩት፡፡ እዚህ ያሉት ሶሪያዊያን ሲነግሩኝ በ50.000 የሉብናን ገንዘብ ነው የሚሰሩት፡፡ ይህ ማለት 27 ዶላር አካባቢ ባለ ዋጋ ራሳቸውን ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዴ ግን ቢዝነስ ቢሰሩ አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱን ቤት ሰራተኛነት ከጀርባው ያለውን ችግር ስታይ የግድ የሚገፋቸው ነገር ታያለህ፡፡ የዛኑ ያህል የሚያናድዱኝ በነጻ ቪዛ መጥተው በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩት ናቸው፡፡ አሁን የምሰራበት ቦታ ሶስት ወንዶች ናቸው የሚሰሩት እኔ ብቻ ነኝ ሴት በየአመቱ ለሶስት ወር የሚያግዛቸው አንድ ሴት ይቀጠርላቸዋል፡፡ ልክ አሁን እኔ እንደተቀጠርኩት፡፡ ታዲያ ከባንግላዲሾች እና ሶሪያዎች ጋር በማይረባ ብር ይተኛሉ፡፡ ሁሉ እንደ እነሱ ስለሚመስላቸው በእርካሽ ትገኛላችሁ ይላሉ፡፡

ይወራ ከተባለ ለጉድ ይወራል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ ካሉት መካከል ወገናቸውን የሚሸጡ የመኖራቸውን ያህል ለሰው ችግር ቆዳቸውን የሚገፈፉ ጥሩ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ ኤቢ ደመቀ በአብዛኛው የመን ባለ እና የመን በነበረ ሰው ዘንድ የሚታወቅ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ዮሀንስ ተስፋዬ /ጆኒ/ የሚባል ልጅ አለ፡፡ ከረንቦላ ቤት ስለነበረው ጆኒ ከረንቡላ ይሉታል፡፡ ከባህር የመጡትን ከረንቡላ የሚያጫውትበት ቤት ውስጥ ከማሳደር አንስቶ የማይሰራው በጎ ስራ የለም፡፡ በተጨማሪ ኩሩቤል የሚባል ኢትዮጵያዊ UNIDOM የተባለ ድርጅት አዋቅሮ ብዙዎችን ለመርዳት ሞክሯል፡፡ ስለእነዚህ ሰዎች በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ አሁን ያነሳኋቸው ቀጣይ ለማቀርበው ታሪክ ምክንያት ስለሆኑኝ ነው፡፡ በሚቀጥለው በቀጠሮ እንገናኝ
ሰላም ሰንብቱ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 9, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 9, 2012 @ 6:25 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar