www.maledatimes.com ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ለመቼ ሊሆን ነው? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

  ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ለመቼ ሊሆን ነው?

By   /   December 15, 2016  /   Comments Off on   ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ለመቼ ሊሆን ነው?

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 17 Second

              

ግርማ በላይ – gb5214@gmail.com

“ዝምታ ወርቅ ነው” – ጥሩ አባባል ነው፡፡ “ዝም አይነቅዝም” – ይሄኛውም ግሩም አባባል ይመስላል፡፡ “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ” – ጠንከር ያለ ሀበሻዊ መልእክት ያለው ነው፤ ፀረ ዴምከራሲያዊነቱም እንዲሁ ከሌሎቹ አየል ይላል፡፡ አዎ፣ የሀገራችን ሥነ ቃላችንም ሆነ አጠቃላይ ባህላዊ ትውፊታችን መናገርንና ሃሳብን በነፃነት መግለጽን አያበረታታም ብቻ ሣይሆን ክፉኛ ይኮንናል፡፡ በዚህም ሳቢያ ይሉኝታ እየገነነና ሀፍረትን እየወለደ “የዝምታ የዝምታ” የሚል አንደርብ የተደገመብን ይመስል ውስጥ ለውስጥና በየመሸታ ቤቱ እየተማማን እንኖራለን፡፡ ይህ ይትበሃል ደግሞ በሌላ በኩል ለአምባገነኖች ምቹ እየሆነና ለተተኪ ደቀ መዛሙርታቸውም መድረኩን እያበጃጀ በመረረ የጭቆናና የአፈና አዙሪት እንደተዘፈቅን የመከራ ሕይወት እንድንገፋ ያደርገናል፡፡ አሣዛኝ ዕጣ፡፡ ዘመን የማይሽረው የትውልድ መርገምት፡፡ ተራማጅና ተስፋ ሰጪ ልጆቻችንን በየዘመኑ እየቀጠፈ በስ(ዕ)ለትም ሆነ በጸሎት ሊለቀን ያልቻለ መጥፎ ሾተላይ፡፡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያለውም፣ ወደ ቤተ መንግሥት ለመግባት ወር ተራውን የሚጠብቀው ተስፈኛም የተሸመደመዱበት አገር አጥፊ ልክፍት፡፡

በዝምታ ዙሪያ የተነገሩ ፈረንጅኛ አባባሎችን ለዚህ መጣጥፍ ፈርጥነት ብዬ ድረገፅ ስዳስስ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ተናግሮታል የተባለ ይህን ጥቅስ ሳገኝ ከሌሎቹ ይበልጥ ሳበኝ፤“Remember not only to say the right thing in the right place, but far more difficult still, to leave unsaid the wrong thing at the tempting moment.” በግርድፉ ወዳማርኛ ሲተረጎም “በትክክለኛው ቦታና ጊዜ ትክክለኛ ነገር መናገርህን ብቻ ከቁም ነገር አትቁጠር፤ ይልቁንም ፈታኝ በሆነ ወቅት አንተ እውነት ነው የምትለውን ነገር በዝምታ ማለፍህ ትክክል እንዳልሆነ አስታውስ፡፡” ትርጉሙን አወላግጀው ከሆነ ይቅርታ፡፡

የዛሬ አራት ይሁን አምስት ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ ነፃነት እንደሸቀጥ ከየትም ሀገር በባቡርም ይሁን በመኪና ተጭኖ ሊመጣ እንደማይችልና በተለይም ከኤርትራ ደግ ነገር መጠበቅ የዋህነት መሆኑን በቁጭት ስናገር የደረሰብኝ ውርጅብኝ አሁን ድረስ ይታወሰኛል፡፡ እኔ ብቻ ሣልሆን በአገላለጻችን ክረት እንለያይ እንደሆነ እንጂ ደምስ በለጠ የሚባል ጋዜጠኛ እንደሆነ የሚናገር አንድ ዲያስጶራና አቶ ጌታቸው ረዳ የተባለ የአንድ ድረገፅ አዘጋጅ ጨምሮ አንዳንድ ወገኖች በጊዜው በዚህ ጉዳይ ይጮኹ ነበር፡፡ ግን ሰሚ አልተገኘም፡፡ ይባስ ብሎ እነሱን በእርጋታ ከማስረዳት ይልቅ በነገር ጦር ቀንድ ቀንዳቸውን የሚመታ ነውጠኛ የድርጅት አፍቀሪ ይበዛ እንደነበር ትዝ ይለኛል – ለማንኛውም ሌላ ምርጫ ስላልነበረን “ይሁንላቸው” ብለን ዝም አልን፤ ዝምታችን ግን ዋጋ ቢስ ሆኖ እነዚያ በረሃ ወረዱ የተባሉ ነፍጥ አንጋች ወንድምና እህቶቻችን በነዚህ ሁሉ የትግል ዓመታት ከአዲስ አበባ ታክሲዎች የጥቅስ ትግል ያልዘለለ እንዲያውም ያነሰ ውጤት ማስመዝገባቸውን ስንረዳ ዝምታችንን መስበርን ወደድን፡፡ አዎ፣ “ከላይ ነው ትዛዙ ብለን ዝም አልን” ወይም “ይህም ሁሉ ያልፋል” የሚል ጥቅስ የለጠፈ ሚኒባስ ታክሲ በረሃ ወረድኩ ካለና በአሥር ዓመት ውስጥ አንድም የሙሽት ሊሆን የሚበቃ የድል ብሥራት ሊያሰማ ካልቻለ ወይም እንዲያሰማ “ካልተፈቀደለት” ታጋይ የበለጠ ሥራ ሠርቷል ቢባል ማጋነን አይደለም ፡፡ የአእምሮ ዕድገት መገለጫው አንዱ በንግግር መግባባት መቻልና አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን በሃሳብ ተግባብቶ ላለመደራረስ በጨዋ ደንብ መለያየት ነው፤ ከዚህ ውጭ ግን በነገር ጅራፍ እየተሞሻለቁ በጎራዎች መፈራረጅ ባህላችን ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡ በጤናማ አካሄድ የማትስማማበት ሃሳብ እንጂ የማትግባባው ሰው ሊኖር አይገባም፡፡ ሳትስማማ ስትቀር ደግሞ “እሱ ወያኔ ነው፤ እሷ ሻዕቢያ ናት፤ እነሱ አሸባሪና ትምክህተኞች ናቸው …” እየተባባሉ በርስ በርስ ግፍትሪያ መቆራቆሱ የምክንያታዊነትና የተጠየቃዊ አመክንዮ ጉድለት ማሳያ ነው፡፡

ያኔም ሆነ አሁን የኔ አቋም እንደያኔው ነው፡፡  በማይጨበጥ ተስፋ የሕዝብን ሆድ ከመቀብተት ባለፈ ከኤርትራ አቅጣጫ የሚመጣ ነፃነትና የነፃነት ዜና ከንፋስነት አያልፍም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ችግር የተፈጠረበት ቤት ውስጥ መፍትሔ አይገኝም፡፡ ይህ አካሄድ የሚታመን መስሏቸው ወደዚያ አካባቢ በመሄድ ሕወታቸውን ለሻዕቢያ ጊሎቲን የሰጡ ንጹሓን ዜጎችን እግዚአብሔር በምሕረቱ ይጎብኛቸው፤ ኢትዮጵያ ብዙ ልጆቿን በሻዕቢያ ዐረመኔያዊ ውሳኔ አጥታለች – ሳያቀስ በማይለቅ ያደቆነ ሰይጣን የሚምልና የሚገዘት ጠላት መቼም ወዳጅ ላይሆን ብዙ የዋሃን ዜጎቻችን ውድ ሕይወታቸውንና ውድ ጊዜያቸውን ሰውተዋል – አሁንም ድረስ፡፡ የትሮይ ፈረስ ለመሆንና ላለመሆን ከሻዕቢያ ጋር በተደረገና በሚደረግ ግብግብ የጠፋው ነፍስና የኮሰመነው ስብዕና፣ የታየው ፈተናና የጫጫው የጋመ ተስፋ ይህ ክፉ ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን ሲተካ በተራፊዎች መነገሩ አይቀርምና ለዚያ ያብቃን፡፡ አሁንም ለጭዳነት የተዘጋጁ ወገኖቻችንን አንድ መላ ፈጥሮ ፈጣሪ ከዚያ ምድራዊ ሲዖል ያውጣልን፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና ሁለቱንም ወንድማማችና እትማማች ሕዝቦች እግር ተወርች የፊጥኝ ከታሰሩበት የእሳት ሰንሰለት ፈልቅቆ አውጥቶ ለሚፈልጉት የነፃነት ዓይነት ያብቃልን፡፡ በተረፈ አሁንም ይህን ላም አለኝ በሰማይ አንጋጣችሁ የምትጠብቁ ሞኞች ካላችሁ መጠበቁ መብታችሁ ሆኖ እውነቱን ግን አድምጡ፡፡ ሻዕቢያ ውሉን የማይስት የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን ካልተረዳን ሀገራችን መቼም ነፃ አትወጣም፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በአንድ ታጋይ መታፈን ምክንያት የነፃነት ትግሉ በአንድ ዓመት እንዳጠረ በግልጽ ተነግሮን ነበር፡፡ ስለአፈናውና አፈናውን ተከትሎ ስለወጡ የአፋኝ አሳፋኝ ድራማ ትንታኔዎች ውስጥ አንገባም፡፡ ሕዝብ እንደአጠቃላይ የዋህ ነውና የቁርጥ ቀን ልጁን የመታፈን አሳዛኝ ዜና በሆዱ ዋጥ አድርጎ ይዞ የተገባለትን ቃል በጉጉት መጠባበቁን ቀጠለ፡፡ ያ አሳዛኝ ጊዜ ካለፈ ሁለት ዓመት ከሦስት ወር ገደማ ሆነው፡፡

“ቂጣም ከሆነ ይጠፋል፤ ሽልም ከሆነ ይገፋል” ይባላልና ያን ተስፋ ብንጠብቅ ብንጠብቅ ዐርባ ምንጭ አካባቢ የሆነች ኦፕሬሽን ተከናወነች ከመባል ውጪ አንድም ነገር ሳይታይ ጊዜው ክንፍ እውጥቶ ነጎደ፡፡

ይህ ትግል ከተጀመረ አሥር ዓመታትን ሊደፍን የቀረው ጊዜ ጥቂት ነው ወይም ደፍኖም ይሆናል፡፡ የጦር ሜዳ ውሎን ያካተተ አንድ ሁለገብ ትግል ፍሬ እስኪያፈራና ተጨባጭ ውጤት እስኪያሳይ ስንት ጊዜ እንደሚያስፈልገው በውል ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ እርግጥ ነው- – ሎራን ካቢላ የተባለ የኮንጎ ኪንሻሳ ዲታ ተጋዳላይ በ11 ወራት ውስጥ የሞብቱ ሴሴኮን መንግሥት ገልብጦ የሀገሪቱን ዘውድ ጭኗል፤ አሁንም እርግጥ ነው – ይሄው ሰውዬ ለላኪዎቹ የገባውን ቃል ባለማክበሩ ይመስላል በገዛ ታጣቂዎቹ እንዲገደል በዝግ ችሎት ተፈርዶበት በልጁ በጆሴፍ ካቢላ እንዲተካ ተደርጓል፡፡ እንደሰብኣዊና ቁሣዊ አቅርቦቱና እንደየታጋዩ የወኔ ልዩነት እንዲሁም እንደዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችና እንደሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዓይነት አንድ የነፃነት ትግል ከጥቂት ቀናትና ሣምንታት ጀምሮ እስከ ሃያና ሠላሣ ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ከታሪክ መዛግብት እንገነዘባለን፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ የፈጀው የኤርትራ “ነፃነት”ና 17 ዓመታት ያህል የጠየቀው “የትግራይ ሪፐብሊክ ነፃነት” ለዚህ አባባል ጥሩ አብነቶች ናቸው፡፡ “ሕወሓት” የሚለው መጠሪያ የአነጋገሬን ትክክለኝነት የሚያሳይ ይመስኛል፤ አጠቃላይ ዝግጅታቸውም ወደዚያ የሚያመራ ስለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣል፡፡

የኛ ግን ከዘጠኝና አሥር ዙር ሥልጠናዎችና ተያያዥ ምረቃዎችም በኋላ እዛው በረሃ ውስጥ ነን፡፡ ምሥጢሩ ምን ይሆን? የሰው ኃይል ችግር? የገንዘብ ችግር? የዕውቀት ችግር ? የሕዝብ ድጋፍ ዕጦት? የውጊያ ሞራል ማነስ? የወኔ ችግር? የአመራር ችግር? የመሣሪያ ችግር? ወይንስ ምን?… እውነቱን እንነጋገር፡፡ መሰዳደብና መፈራረጅ የትም አያደርስም፡፡ ሕዝብ ደግሞ የዝምብ ልጃገረድ ለይቶ የሚያውቅበት የግንዛቤ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሕዝቡ አሁን ቆርጦ የተነሣው እንዲያውም ነፃ አውጪዎቹን ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድም ይሁን በጦር ትግትግ ሕዝቡን ከወያኔ “ነፃ ሊያወጡት” የቆረጡትን ንቅናቄዎችንና ፓርቲዎችን በሙሉ ነፃ ሣያወጣ ይህ በየአካባቢው ከወያኔ የአጋዚ ጦር ጋር የሚፋለም ሕዝብ ወደ ቤቱ የሚመለስ አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ የተቃርኖዎች ሀገር ናት፤ “ነፃ አውጭዎች” በዚህና በዚያ ቀያጅ አስተሳሰብና ጠንጋራ አመለካከት ተጠልፈው ሲሽመደመዱ ሕዝቡ ሊታደጋቸው ቆርጦ ተነሣ፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እነዚህ ሁሉ በመቶዎች የሚገመቱ በሀገር ውስጥም በውጪም እንደጉንዳን የሚርመሰመሱ “ነፃ አውጭዎች”ና የሲቪክና የሃይማኖት ተቋማት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከየታጎሩበት እሥር ቤት ነፃ ሲወጡ ይታየኛል – በሕዝብ ትግል፡፡

ያልተቀየደ ነፃ አውጪ ጦር ቢኖረን ኖሮ ታጋዩ ጦር ሠፍሯል ከተባለበት የኤርትራ ግዛት በጥቂት ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ውስጥ ወያኔ ያፈናቸው ወጣቶች በርሀብ፣ በዱር ዐውሬ፣ በግርፋትና በጥይት እያለቁ ባልተገኙ ነበር – ይህንንም ውሸት በሉና አስደምሙኝ፡፡ የጎንደርና የጎጃም ጠቅላይ ግዛቶች ግዳጅ የሚሰጠው አጥቶ በረሃ ውስጥ “ለሚርመሰመሰው” ነፃ አውጪ ጦር በጣም ቅርብ ናቸው፡፡ መቼም ከዐርባ ምንጭ ይልቅ መተከል ለኤርትራ በረሃዎች ሳይቀርብ አይቀርም፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ይልቅ ብር ሸለቆ ለሰሜን ኢትዮጵያ ይቀርባል፡፡ ምናልባት እኮ ወጣቱ ሆ ብሎ በወያኔ ላይ የእምቢተኝነት ዐመፅ የጀመረው ነፃ በሚባሉ የተቃውሞው ጎራ ሚዲያዎች የሚናፈሰውን የሁለገብ ትግል ቅስቀሳ አዳምጦና በዚያ ተመክቶም ሊሆን ይችላል – ስለዚህ ለሕዝባዊ መነሳሳቱ አስተዋፅዖ ያደረገ አካል ስቃይና መከራውንም ሊጋራው በተገባ ነበር(እነዚህ ሚዲያዎች ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ጉልኅ አወንታዊ ሚና መጫወታቸውን እዚህ ላይ መግለጽ ይኖርብኛል – ችግሩ በተግባር አለመደገፋቸው ነው)፡፡ እንግዲህ እንደንብ ከቀፎው ያወጣነው ወጣት በዐረመኔው የወያኔ አጋዚ ጦር ሲገደልና ሲሰቃይ አሁን ያልደረስንለት መቼ ልንደርስለት ነው? ሕዝብ በባዶ እጁ እየወጣ ካለቀ በኋላ ማንን ነው ነፃ የምናወጣው? አሁን ጥያቄው የነፃነት ጉዳይ ብቻ አይደለም – የተቃዋሚዎች የራሳቸው ኅልውና ጥያቄም ጭምር ነው፡፡ ከወረቀትና ከአልፎ አልፎ መግለጫ ባለፈ በርግጥም “እንዲህ እንዲህ ያለ አበረታች እንቅስቃሴ አለ ወይ?” ተብሎ ቢጠየቅ መልስ እንዳይቸግረን እፈራለሁ፡፡ ቀናት ሣምንትን፣ ሣምንታትም ወራትንና ዓመታትን እየተኩ በአበበ ተ/ሃይማኖት አነጋገር እንዲሁ እየተበሳበሱ መኖር ከተፈለገ ያ ሌላ ነገር ነው፡፡ እውነቱን መናገር ካስፈለገ ግን ከዚህ ጊዜ ሌላ ምቹ የትግል ወቅት ሊኖር ስለማይችል በረሃ የወረደና መሬት ላይ የሚታይ የነፃነት ትግል ቢኖር ኖሮ በአሁኑ ሰዓት ወያኔ ቀርቶ የሥምሪት ኃላፊዎቹ አብርኆታውያን ተብዬዎቹ ራሳቸው ሳይቀሩ ኢትዮጵያን አይረግጡም ነበር፤ ለነገሩ ለማንም ደንታ ባይኖራቸውም ሕዝባዊ ጅራፉን እነሱም እየቀመሱት ነው ፡፡

 

እንደኔ የዚህ ዕንቆቅልሽ መሠረት እንዲህ ይመስለኛል፤ ይህን ግሩም ጥቅስ እናንብ፡፡

 

የሕወሓት ከፍተኛ ልዑካን ከሻዕቢያ ተወካዮች ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ለሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ሲሰጡ፣ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ሻዕቢያዎች የመሣሪያ ዕርዳታ ሲጠይቋቸው፣ በተለይ ኢሳይያስ አፈወርቂ “የማይቆጣጠሩትን ድርጅት መርዳት አይቻልም፤ ዕርዳታ ሲሰጥ ከበስተጀርባው የፖለቲካ ዓላማህን የማስፈጸም አንድምታ መኖር አለበት፡፡” ብሎ እንዳለ ገልጸው ነበር፡፡ ይህ የኢሳይያስ አባባል በወቅቱ ክብደት ባይሰጠውም የሻዕቢያዎች ፍላጎት የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ደርግን ለማዳከም ሕወሓትን ሊጠቀሙበት እንጂ ጠንክሮ ራሱን የቻለ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ እንዳልነበር በግልጽ ያሳያል፡፡ ( አፅንዖት የተጨመረ) ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፣ ገብሩ አሥራ፣ ገጽ 92

 

ይህ ጥቅስ ብቻውን ብዙ መጻሕፍትን ያህል ብዙ ነገር በግልጽ ይናገራል፡፡ ኤርትራ የገቡ የነፃነት ታጋዮችም የውኃ ሽታ እየሆኑ መቅረት ከዚሁ የሻቢያ ሊለወጥ የማይችል ግትር አቋም ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ኅያው ማስረጃ የለም፡፡ ቀደም ሲል የወጡ “ጥቁር ጫካ” በሚል ብዕር የወጡ ጽሑፎችም ሆነ በኢሳይያስ ሣንጃ ታርደው በኤርትራ በረሃ የወደቁ ኢትዮጵያውያን ደም የሚመሰክረውም እውነት ይህንኑ ነው፡፡

በመሠረቱ የሚሳካላቸው መስሏቸው የሞቀ ቤታቸውንና የሞቀ ትዳራቸውን እርግፍ አድርገው ጥለው ወደዚያ የሄዱ ወንድሞቼንና እህቶቼን አደንቃለሁ – እኔ ላደርገው ያልደፈርኩትን በማድረጋቸው የኔን መስቀል ተሸክመዋልና እመብርሃን ከነልጇ ትራዳቸው፡፡ የእናታቸውን በወያኔ መታረድ ያስጣሉ መስሏቸው፣ የተሻለ ሌላ አማራጭም አጥተው ለከፋ አራጅ በመዳረጋቸው ግን ሊታዘንላቸው እንደሚገባ እረዳለሁና በጸሎታችን ዘወትር እናስባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት መቼም ቢሆን እንደተደበቀ አይቀርምና ያኔ እነዚህ ወገኖች በዚህ ሙከራቸውና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ባደረጉት ጥረታቸው ብቻ የግርማ ሞገስ አክሊል እንደሚጎናጸፉ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ወገኖች ከአጋም ተጠግቶ እንደበቀለ ቁልቋል የገና ዳቦ ሆነው ከሁለት ወገን በሚደርስባቸው ስቃይ ሲያለቅሱ መኖርን የመረጡት ሌላ አማራጭ ከማጣት አንጻር መሆኑን እንረዳላቸዋለን፡፡ ነገር ግን የሻዕቢያን ተፈጥሮ ለሚያውቅና ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ ያዘጋጀላትን የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ለሚገነዘብ ወገን በኤርትራ በኩል መልካም ነገር ይገኛል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ጊዜ ራሱ በግልጽ እየነገረን ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ በላይ ምቹ የትግል ወቅት እንዳለመኖሩ ሌላው ቀርቶ 40 እና 50 ሺህ ጦር እንዳለው የሚነገርለት ዴምህት የሚባለው ሌላው ላም አለኝ በሰማይ አሁን የት እንዳለና ምን እየሠራም እንደሆነ ከሰይጣን ምናልባትም ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው ይሄ ዶሮ ማታ ዓይነት ፖለቲካ እንደማያዋጣና እውነቱን መጋፈጥ ብቻ ተገቢ እንደሆነ ብዙ ወገኖች በድፍረት የሚናገሩት – (ዶክተር አሰፋ ነጋሽም አሁን ትዝ አለኝ)፡፡ ባህላችን ደግሞ አሣሪ እየሆነ ተቸገርን፡፡ “ዝም በል” እየተባለ ያደገ “ዝም በል!” ይላል እንጂ ሊያዳምጥህ አይፈልግም፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም የስሜት አምባላይ ፈረስ እየጋለበና በራሱ ጠባብ ዓለም እየተመመ አንዱ ሌላውን ማዳመጥ አልቻለም፡፡ ደግነቱ ፈጣሪ ጥሎ እንደማይጥለን አምናለሁ እንጂ ተያይዘን ወደገደል እየገባን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ …

ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ከቅርብ ወራት ወዲህ ሕዝቡ ራሱ ፖለቲከኞችን ሳይቀር ከየተረፈቁበት የጎጥና የሸጥ እንዲሁም ያረጀና ያፈጀ ሸውራራ አመለካከት ነፃ ሊያወጣቸው የራሱን እርምጃ መውሰድ ጀምሯል፡፡ በፊት ፊት ፊት ጡዝ ጡዝ ይል የነበረ ከውካዋ የፖለቲካ ድርጅት ሁላ ዛሬ ዛሬ በሀፍረት ጅራቱን ወትፎ ከሕዝቡ ኋላ ቱስ ቱስ ማለት ይዟል፡፡ ወደፊት ብዙ የሚታይ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡

ምሥረታው ከሻዕቢያም ቀደም ይላል የሚባልለት ኦነግ በዚህ በ50ዎች ዓመታት በሚቆጠር ዕድሜው አንዲትም ወረዳ ሊይዝ ያልቻለበት ምክንያት የዓላማና ግቡ ልልነት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአእምሮ መዳበር ያልተመሠረተ ነገር ሁሌም እንደጫጫና መጫጫቱንም ለመሸፈን ሁሌም ጉልበት እንደተጠቀመ መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ የሀገራችን ፋኖዎች በሙሉ በዚህ ይታወቃሉና እማኝ መቁጠር አያስፈልግም፡፡

ኦነግ ከወያኔ ጋር ተሻርኮ አዲስ አበባ እንደገባ ያኔ በ83 ግድም እንዲህ ሆነ አሉ፡፡ አንድ አካባቢ ቡና ቤት ውስጥ ጓደኛሞች ያወራሉ – መጠጥ ላይ፡፡ በወሬያቸው መሀል ላይ አንደኛው “ኤዲያ፣ ኦነግ ማለት እኮ ደካማ ድርጅት ነው …” ሲል አጠገብ የነበረ የኦነግ አባል ሰምቶ ኖሮ ድርጅቱ “ጠንካራነቱ”ን ሳይውል ሳያድር አሳዬ፡፡ የሆነው ምንድነው – ያ ኦነግን የተቸው ሰው ቤቱ አልገባም፡፡ ተከታተሉና አርደው በድኑን በማዳበሪያ ከትተው ጉድባ ውስጥ ጣሉት፡፡ የድርጅት ዕድገትና ጥንካሬ ማለት እንዲህ ነው እንግዲህ፤ ሕዝብን ነፃ ለማውጣት የቆመ፣ ለሕዝብ የመናገርና የመጻፍ መብት የተነሣ ድርጅት ማለት እንዲህ ነው፤ ለዚህ ለዚህማ ደርግና ከርሱም በፊት የነበረው የዐፄው መንግሥት ይሻሉ አልነበረምን? “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ይባላል፡፡ እንደዚህ ያሉ ደመ ሞቃት ድርጅቶች ገና ከአሁኑ እንዲህ የጨከኑ ሀገራዊ ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይታያችሁ፡፡ የአንድን ነገር ጅማሮ መድረሻውን ለመገመት መነሻውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ በዚህ ቅኝት የሚጓዙ ድርጅቶችና ተከታዮቻቸው ሞልተዋል – ዋጮን ለመገልበጥ ባለ በሌለ ኃይላቸው የሚጓዙ ደምባራ ፈረሶች ሕዝብን ጉዳት ላይ እንደሚጥሉ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ይህ ዓይነቱ የየጁ ደብተራ ዓይነት ዕድገት በሁሉም የፖለቲካና የሃይማኖት ድርጅቶቻችን ዘንድ በስፋት የሚዘወተር ነው፡፡ ሃሳብን በሃሳብ፣ ነገርን በነገር፣ ዕውቀትን በዕውቀት፣ አመለካከትን በአመለካከት እንደመሞገት ቅኔው ጎድሎበት ቀረርቶ ጨመረበት ተብሎ እንደሚቀለድበት የፈረደበት የየጁ ደብተራ የጎፈነነ ስሜታችንን ሲቻል በግድያ ያ ሳይቻል ሲቀር በስድብና በዛቻ የምናወጣ ገልቱዎች ቁጥር ሥፍር የለንም፡፡ ይህ የውርደት እንጂ የዕድገት ምልክት አይደለም፤ የዝቅጠት እንጂ የብስለት ማሳያም አይሆንም፡፡

ለማንኛውም ኦነግም ቢሆን በእስካሁን አካሄዱ ሕዝብን አስተባብሮ የመነሣትና ለድል የማብቃት ተፈጥሯዊ ችሎታው ዝቅተኛ ነው፡፡ ከሕዝብ በሚያንስ የፖለቲካ ድርጅት ሀገርና ሕዝብ ነፃ አይወጡም፡፡ ሕዝብን በዘርና በጎሣ፣ በጎጥና በቋንቋ፣ በባንዲራና በሃይማኖት እየከፋፈሉ ወያኔን አስወግዳለሁ ማለት ቅዠት ነው፡፡ የጠገበ አንበጣ አንስተህ የተራበ መዥገር በመትከልም ነፃነትን እውን አታደርግም፡፡ የሰከነ ፖለቲካ ለማምጣት ከስሜትና ከሆይሆይታ በመራቅ በአስተውሎት መራመድን፣ ከሁሉም ጋር መመካከርንና መግባባትን ይጠይቃል፡፡

የሆኖ ሆኖ ለኔ እንደሚታየኝ ነፃነታችን በአንድዬ እጅ ናት፡፡ የነፃነት መምጣት ደግሞ የቀን ጉዳይ እንጂ ማንም ሊያስቀራት አይችልም፡፡ ሕዝቡ በጀመረው ፍልሚያ ይቀጥል፤ የበቁ አባቶች በየበዓታቸው ልባዊ ጸሎታቸውንና ምህላቸውን ያድርጉ፤ ከክፋትና ከተንኮል ርቀን ወደፈጣሪያችን እንመለስ፤ አንዱ አንዱን አይበድል፤ የተጣላንና በነገር የተቋሰልን  በይቅርታና በዕርቅ ቁስሎቻችን እንዲሽሩ እናድርግ፣ ከሁሉም በላይ ፍቅርና መተዛዘን ይኑረን፤ ነጋዴው በአንድ አዳር ለመክበር የሚያደርገውን ማተብየለሽና ይሉኝታቢስ ሩጫ አቁሞ የሸማቹን የመግዛት አቅም ይመልከት፤ሥራችንን እናክብር፣ ለትውልድና ለሀገር የመቆርቆር ነባር ልማዳችንን እንመልስ፤ ከተናጠል ሩጫ ሶበር ብለን ለጋራ ሕይወት በጋራ እናስብ፣ ሞልቶ ለማይሞላ ሆድ ስንል ሀገርንና ወገንን አንክዳ፣ አንገትም ዐይንም ይኑረን … ያኔ እግዚአብሔር ፊቱን ወደኛ ይመልስልናል፤ ያኔ በምሕረት እጆቹ ይዳብሰናል፤ ያኔ “የአንዲት ላም ወተትና የአንድ ማሣ ሰብል” ለብዙዎች የሚበቃበት የበረከት ጊዜ ይመጣልናል፡፡ በያዝነው መንገድ ከቀጠልን ግን እመኑኝ ዕድሜያችን ግፋ ቢል አምስት ወይ አሥር ዓመት ቢሆን ነው፡፡ አሁንም ቢሆን እንዳን አንቆጠርም – ካልዋሸን በስተቀር ጠፍተናል፤ እንደሀገርም ሆነ እንደሕዝብና እንደማኅበረሰብ በቁማችን ሞተናል …

መልካም አዲስ ዓመት፡፡ ዓመቱ የነፃነትና የብልጽግና ይሁንልን፡፡ በ2010 አንደኛው የመባቻ ወር ላይ “አምና ወያኔ ከሥር መሠረቱ የተነቀለበትና ነፃነታችን የተበሠረበት ዓመት ነበር” ብለን የመጀመሪያውን እውነተኛ የነፃነት ክብረ በዓል በድምቀት ለማክበር ያብቃን፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on December 15, 2016
  • By:
  • Last Modified: December 15, 2016 @ 10:31 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar