www.maledatimes.com የዳላሱ መንፈስ ,ከዳንኤል ገዛኽኝ (ከዳላስ መልስ አትላንታ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የዳላሱ መንፈስ ,ከዳንኤል ገዛኽኝ (ከዳላስ መልስ አትላንታ)

By   /   July 14, 2012  /   Comments Off on የዳላሱ መንፈስ ,ከዳንኤል ገዛኽኝ (ከዳላስ መልስ አትላንታ)

    Print       Email
0 0
Read Time:30 Minute, 20 Second

የዳላሱ መንፈስ

ዛሬ በዚ ከላይ ባሰፈርኩት ርዕስ ስር የምጽፈው ጽሁፍ ዋናው ምክንያት ላለፉት 29 አመታት በሰሜን አሜሪካ ከሃያዘጠኝ አመታት በፊት ተቁዋቁሞ በስደት ሃገር ኢትዮጵያውያንን በባህል፤ በስፖርት አቆራኝቶ መገናኛ ድልድይ አድርጎ የዘለቀው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌደሬሽን የ 2012 በዳላስ ለሃያዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደውን ዝግጅት የሚመለከት ነው።

ምንም እንኩዋን ፌደሬሽኑ ለተጉዋዘባቸው ሃያ ዘጠኝ አመታት የሚያስመሰግን ታሪክ ባለቤት ቢሆንም በዚያው መጠን በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጠ እዚህ መድረሱን ነው በተለይ ለፌደሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በ አጽንኦት የሚያስረዱት። ባለፈው አመት ከተከሰተው የፌዴሬሽኑ አስቸጋሪ እክል ባሻገር የዘንድሮው በተለይም ፌዴሬሽኑ የ 2012 ዝግጅቱን በዳላስ ለማከናወን ወስኖ፤ ሆኖም ግን የቀጣዩን ስራ የማከናወን ሃላፊነት የሚጣልባቸውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ምርጫ ካከናወነ በሁዋላ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽኑ ሲከሰቱ ነበሩ ከሚባሉቱ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ግን ይህኛው በ 2012 የዳላሱ ዝግጅት ዋዜማ የተከሰተው ችግር ግን በተለይ ለፌዴሬሽኑ አዲስ ተመራጮችም ሆነ ለፌዴሬሽኑ ግልጋሎት ትልቅ እይታ እና ቦታ ለሚሰጡ ኢትዮጵያውያን ከፈተናም የከፋ ፈተና ነበረ። ነገር ግን የዚህ የዳላሱ ዝግጅት ዋዜማ የተፈጠረው አስቸጋሪ ችግር ግን ጭራው ላለፉት ጥቂት አመታት በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያቆጠቆጠ ግን በወሳኙ ጊዜ አፍጥጦ የወጣ መሆኑን ነው ስማቸውን እንዳልጠቅስ ያስገነዘቡኝ የፌዴሬሽኑ አንድ ስራ አስፈጻሚ የገለጡልኝ።

በተለይ በተለይ የስራ አስፈጻሚ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ለመመረጥ በርካታ ገንዘብ ለግለሰቦች በመርጨት በፌዴሬሽኑ ያሰቡትን ቦታ ያጡት በተለይ አቶ ብስራት ደስታ እና አቶ ተድላ ገሰሰ የመጀመሪያ እርምጃቸው ያደረጉት 29 አመታት የኢትዮጵያውያን ኩራት ሆኖ የዘለቀውን የባህል እና ስፖርት ፌዴሬሽን ህልውና የሚፈታተን እርምጃቸውን መጀመር ነው።

ምንም እንኩዋን እርምጃቸው እነሱ እንዳሰቡት ተሳክቶ ከጫፍ ሳይደርስ በህግ አደባባይ ሽንፈት ቢከናነቡም። የሰዎቹ ሙከራ የነባሩን ፌዴሬሽን ስም እና ሎጎ ESFNA የሚለውኝ መጠሪያ መቶ በመቶ አመሳስለው በመያዝ አዲስ ከትርፍ ነጻ የሆነ ድርጅት ለመመስረት ያደረጉት ሙከራ ክልከላ ተጥሎበት ተዋርደዋል። ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲሉ ስያሜውን እና ሎጎውን ቢከለከሉም ሌላ ስም ሰይመው AESA ONE የሚል ስም በመስጠት በማቁዋቁዋም ዋናውን ፌዴሬሽን ለሁለት በሚከፍል መልኩ ስራቸውን ጀመሩ።

በተለይ አያያ በሚባለው ግለሰብ ተላላኪነት እና በ ሳውዲው ቱጃር ሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲን አቃቢ ነዋይ አብነት ገብረ መስቀል አማካኝነት በቱጃሩ ሰው ገንዘብ ነባሩን ፌዴሬሽን ከ ኢትዮጵያውያን ለመለየት 6 ሚሊዮን ዶላር በማስመደብ በገንዘብ ወደ አዲሱ ዝግጅታቸው የቻሉትን ሰው ሁሉ ለመሳብ ሲንቀሳቀሱ ቆዩ። እነሆም እርግጠኛው ጊዜ ደረሰ እና ኢትዮጵያውያን “እምቢ ለከፋፋዮች…እምቢ ለሆዳሞች…” ሲሉ በ አንድነት በመዘመር ዋናው 29 አመታት ከነችግሮቹ ወደዘለቀው ዝግጅት ወደ ዳላስ በ አንድ ድምጽ ተመሙ።

ገንዘብ ሃይል እንዳለው ሁሉ በማሰብ በሙሉ ሃይላቸው የተንቀሳቀሱት የገዳዩን…የ አፋኙን እና የጨቁዋኙኝ መንግስት አቁዋም በሚደግፉ ጥቅመኞች ስብስብ የተዋቀረው አሳ ዋን እንደ ስሙ ከባህር የወጣ አሳ የሆነበት ሂደት የተከሰተበትን የዲሲው RFK ስታድየም የተካሄደውን አፍራሽ ተልዕኮ ያነገበውን ዝግጅታቸውን በተመለከተ ወረድ ብዬ የምለው ይኖራል። አሁን ግን የዳላሱን አዲስ መንፈስ በተመለከተ ጥቂት ልበል።

ጁላይ 1 እለተ ሰንበት 2012 በዳላስ ሙቀት ታጅቦ ከቀትር በሁዋላ የመክፈቻ ስነስራቱን በ አልፍሬድ ጄ. ሎስ ስታድየም የጀመረው የ ኢትዮጵያውያን የባህል እና ስፖርት ፌዴሬሽን ዝግጅት ድባቡን ባደመቀው የወጣቶች የፈረስ ላይ ትርኢት ብዙዎችን በሲቃ ስሜት ውስጥ ከቶዋል። ያንን በፈረስ ላይ ወጣቶች አረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችንን ይዘው በካባ ተንቆጥቁጠው፤ ጦር እና ጋሻ አንግበው ያሳዩት ትዕይንት በእውነት በተለይም ፈተናውን አልፎ ለዚያ ክብር ህዝቡን ላበቃው ፌዴሬሽን ሁላችንም ክብር እንድንሰጥ የጋበዘ ሂደት ነው።

በተለይ በዚህ ዘመን በውጪው አለም የሚገኘው ወጣት የምዕራቡ አለም ባህል ምርኮኛ በመሆኑ የተነሳ በሃገሩ ጉዳይ ላይ የሩቅ ተመልካች እንጂ ተሳታፊ አይደለም የሚለውን አስተያየት ተቀባይነት ባሳጣ መልኩ በሰሜን አሜሪካ አካባቢዎች ተወልደው ያደጉ ህጻናቶች እና ወጣቶች በጥቁር ሰው የቴዎድሮስ ካሳሁን ወኔ ቀስቃሽ እና የ አባቶቻችንን የጀግነነት ታሪክ በምልሰት ከ እዝነ-ልቦና በሚደቅነው ዜማ ታጅበው ባቀረቡት የ አደባባይ ላይ ሙዚቃዊ ድራማ ያልተማረከ አልነበረም፤ የደስታ እምባ ያላፈሰሰ፤ ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ያልተንቆራጠጠ የለም ማለት ይቻላል።

ያቺን ወድቃ የተነሳች ባንዲራ በዚህ ዘመን ሃገራዊ ጉዳይ ውስጥ የለም ተብሎ የሚታማው አዲሱ ትውልድ አንግቦ የሩቅ ተመልካች ሳይሆን የሃገሩ ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት የሚመለከተው መሆኑን ያሳየበት ሂደት አስደናቂም አስገራሚም ብቻ ሳይሆን መቼም መቼም የማይረሳ አንድ የታሪክ ምዕራፍ ነው። ከነበሩት ልዩ ልዩ ዝጅግቶች በተለይ ሚዛን የደፋው የኢትዮጵያውያንን አትንኩኝ ባይነት የጀግነነት ታሪክ የሚያወሳው ትርኢት በመሆኑ በአይረሴነቱ ይወሳል።

ከመክፈቻው ቀን አንስቶ እስከ ማጠቃለያው የመዝጊያው ዝግጅት የነበረው የዘንድሮው የሰሜን አሜሪካ የባህል እና የስፖርት ፌዴሬሽን ዝግጅት ሌላው አንድ አስገራሚ ጎን አለው።  አስገራሚ እና የፌዴሬሽኑ በጽናት የታገዘ ጠንካራ ጎን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በየአመቱ እንደሚደረገው ከነበሩት የተለየዩ ቡድኖች አንዱም የ እግር ኩዋስ ክለብ ሳይጎድል ውድድሩ  በፍጹም ሰላማዊ እና ስፖርታዊ ጨዋነት ያለምንም እንከን መካሄድ መቻሉ ሲሆን የ ፌዴሬሽኑ አመራር አካላትም ለዝግጅቱ መሳካት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰውተው የሰጡት ግልጋሎት የሚመሰገን ሲሆን ጥቂት ችግሮች እንደነበሩ የሚካድ ባይሆንም።

ዞሮ ዞሮ ግን ከፌዴሬሽኑ ጉያ ወጥተው ያፈነገጡ ጥቂት ጥቅመኛ ህሊና ቢሶች በፈጠሩት የመከፋፈል ስራ አንጻር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተልዕካቸውን ከመወጣት አንጻር አመራሩን ማመስገን አስፈላጊ ነጥብ ነው። ይህንን ስል ታዲያ ለዚህ የዳላሱ ዝግጅት መሳካት ስራቸውን በተግባር ካስመሰከሩት የስራ አመራር አባላት ጀርባ የ አንድ ጠንካራ ሰውን ብቃት እና ጥንካሬ ለማይት ተችሎዋል። እኚህ ሰው በዳላስ እና አካባቢዋ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቁት አቶ ዘውገ ቃኘሁ ናቸው። በ ESFNA የህዝብ ግንኙነት ስር በተዋቀረው ንኡስ ኮሚቴ ውስጥ ተመድበው የህዝብ ግንኙነት ስራውን በማቀላጠፉ በኩል የዳላሱ ኮምዩኒቲ ሬድዮ አዘጋጅ የሆኑት አቶ ዘውገ ቃኘው የዳላስ ኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበርን ወክለው ሚናቸውን የተወጡ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ይመሰገናሉ።

በሌላ በኩል ለሚዲያ ሰዎች የሚዘጋጀውን የማለፊያ መታወቂያ ባጅ እንዲያዘጋጅ ለፌዴሬሽኑ መረጃዎች የተላኩት ከወር በፊት እንደሆነ በግሌ ያለኝ መረጃ ቢያመለክትም እኔን ጨምሮ በርካታ የፕሬስ ሰዎች መግቢያ ለማግኘት ደጅ ጠንተናል። የህዝብ ግንኙነት ሃላፊውን አቶ ዮሃንስ ብርሃኑን እና ምክትል ፕረዚዳንቱን አቶ አብይ ኑርልኝን ስናስጨንቅ ጭራቸውን ስንከታተል ነበረ የሰነበትነው። የሆነው ሆኖ ለዚህ ጉድለት ተጠያቂው ማን እንደሆነ መናገር ባይቻልም እንደ አንድ ድክመት ከሚነሱት ነጥቦች ይሄኛው አንዱ ነበር።

ለሳምንት ያህል በዘለቀው በዚህ የደመቀ ዝግጅት ላይ ከ35 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በላይ ይኖሩባታል ተብላ በምትገመተው ዳላስ ከተማ ከስታድየሙ ውጪ ኢትዮጵያውያን የሚያንቀሳቅሱዋቸው የፖለቲካ እና የሲቪክ ማህበራት ግቡን የመታ ስራቸውን በተለያዩ ቦታዎች እና ቀናት አከናውነዋል። በአመት አንድ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በአንድ ስፍራ በሚገኙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ዝግጅታቸውን ካካሄዱት ድርጅቶች መካከል የበቃ ዘመቻ ድርጅት አባላት፤ የኢትዮጵያ የሽግግር ምክር ቤት ጠንሳሾች ምርጫ እና ምስረታቸውን ያካሄዱ ሲሆን እንደ አጥቢያ ኮከብ እየጎመራ የህዝብ አይን እና ጆሮ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረው ኢሳት ቴሌቪዥን ያከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ እና የቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ ጉልህ ሚና ያላቸውን ኢትዮጵያውያን የማክበር ዝግጅት በዳላስ የኢሳት ድጋፍ አሰባሳቢ አባላቶች የተካሄደው እጅግ ስኬታማ ዝግጅት ይጠቀሳል።

እዚህ ጋር ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ ይህንን የሃያዘጠኝ አመት ፌዴሬሽን ለሁለት የከፈሉት ወገኖች ፍላጎት በአደባባይ እንደታየው የገዢውን የወያኔን ፍላጎት እና ጥቅም በፌዴሬሽኑ ውስጥ ማራመድ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቶዋል። በዚህ የተነሳም ፌዴሬሽኑ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ ኢትዮጵያውያን በአመት አንድ ጊዜ የሚሰባሰቡበትን ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊ መንፈስ የተላበሰ ስሜት ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ከመቼውም በበለጠ አኩሁዋን የተሳካ ሆኖዋል። ዝግጅቱ በተከናወነበት ስታድየም ምንም አይነት ወገንተኝነት፤ የፖለቲካ፤ የጎጥ እና የቡድንተኝነት ስሜት ሳይፈጠር ነው ዝግጅቱ ሲካሄድ የሰነበተው።

ከመክፈቻው ዝግጅት ለጥቆ ኢትዮጵያውያን እጅ ለ እጅ መያያዛቸው ግድ ያላቸው ወቅት ላይ ደርሰዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ብዙዎቻችንን ያደረሰው አርብ ጁላይ 6/2012 በሎስ ስታድየም ልዩ ሜዳ ውስጥ የተካሄደው የ ኢትዮጵያውያን ቀን ዝግጅት ነው። ይሄ ዝግጅት የተከናወነበት ሜዳ ሙሉ ለሙሉ ክብ እና ታዳሚው በክብ ቅርጽ የስታድየሙ ልዩ ቦታ ተሰባስቦ ዝግጅቱን የታደመበት ሁኔታ ለቀኑ እና ለዳላሱ መንፈስ ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል።

በፌዴሬሽኑ ፕረዚዳንት አቶ  ጌታቸው ተስፋዬ ንግግር የተጀመረው መርሃ ግብር በራሱ በአንድ ጊዜ ገና ከጅማሬው ድባቡን ለወጠው። ይኽውም ፕረዚዳንቱ የፌዴሬሽኑን ውስብስብ ተግዳሮቶች በግርድፉ ከመጥቀስ ባሻገር በዚያ የከተሙ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ሴራ ስላሴሩት ጥቅመኞች አለመናገራቸው ኢትዮጵያዊነት እና ትግስት ሁሉን ለማሸነፉ ማሳያ መሆኑን የተገነዘበው ታዳሚ በአንድ ድምጽ እዚያው በፈጠረው የጋራ ዜማ ከዳር እስከ ዳር በጋራ የአቶ ተስፋዬን ንግግር አጀበው።

አንሄድም ዲሲ አንሄድም

አንሄድም ዲሲ አንሄድም…

እኛ ሆዳም አይደለንም።

ሲል ህዝቡ የፕረዚዳንቱን ንግግር በልዩ ህብረ-ዜማ አጀበው። ፕረዚዳንቱም አቶ ተስፋዬ የህዝቡ መል ዕክት ስለገባቸው ንግግራቸውን ገታ በማድረግ ዝማሬው እስኪቆም ጠብቀው የጀመሩትን ንግግር አጠናቀቁ።

ይህ በዳላስ እየሆነ ባለበት ወቅት ታዲያ 6 ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰበት የዲሲው RFK ስታድየም ከባህር የወጡት አሳዎች ዝግጅት በዲሲ ሜትሮ የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች እና አውቶቡሶች ላይ ሳይቀር የቅስቀሳ ማስታወቂያ ተረጭቶ በስፍራው የተገኘው ህዝብ 300 ነበር። በዚህ አላበቃም “ዋሽቶ ለመኖር ልቤ” በተሰኘው የቴዲ ዜማ ከሜዳው ውጪ ተቃውሞዋቸውን ያካሂዱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የዲሲ፤ የሜሪላንድ እና የቨርጂኒያ አካባቢ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ከታዳሚው የሚልቅ ቁጥር እንደነበራቸው ሲታይ ነገሩን አስገራሚ ብቻም ሳይሆን የነዚህ አፍራሾች ስራ እንደተነቃባቸው ያሳያል። ሌላም አለ ጉዳዩ ሳይገባቸው ከመደበኛዎቹ ክለቦች በስፖርት ስም በገንዘብ የተሳቡ ስፖርተኛዎች የተገዛላቸውን የስፖርት ቱታ እንደለበሱ ተቃውሞውን መቀላቀላቸው ደግሞ ሌላው ክስተት ነበረ። ምንም እንኩዋን ገንዘባቸውን መርጨታቸውን የሚያሳብቀው ሌላው ሂደት ከ ኢትዮጵያዊነት ባህል ታሪክ እና የስፖርት ክንውን ጋር ምንም ቁርኝት የሌላቸው ኢሜሪካውያን ራፐሮች መጋበዛቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ከመጠን በላይ ገንዘብ የተረጨበት ይህ ዝግጅት ከዋናው ፌዴሬሽን የተገነጠለ እንደሆነ እና ያልተሳካ መሆኑን እንደ ዩ.ኤስ ቱዳይ፤ ዋሽንግተን ፖስት የመሳሰሉ ዝነኛ ሰፊ ስርጭት ያላቸው ጋዜጠች ዘግበውታል።

ወደ ዳላሱ መንፈስ ስንመለስ ታዲያ  ዝግጅቱ በቅኝት የባህል ቡድን ደምቆ ባህላዊ ጭፈራው እና ውዝዋዜው ከአፍ እስከ ገደቡ ጢም ብሎ የሞላውን ኢትዮጵያዊ በባንዲራው እንደተሸለመ አነቃነቀው። አስገራሚው ነጥብ እዚህ ጋር ይጠቀሳል … እንደዚያ እስከ አስር ሺህ የሚገመት ህዝብ በዚያች አነስተኛ የቤት ውስጥ ስታድየም የኢትዮጵያዊነትን ቀን ሲያከብር በዋናው ስታድየም ደግሞ የዚያን ህዝብ ከሁለት እጥፍ በላይ የሚልቅ ህዝብ በተለያዩ ሁኔታዎች በድንኩዋኖች እና በሜዳው ዙሪያ መገኘቱ ነው።

ወጣም ወረደ ከሚጻፈው… ከሚነገረው የበለጠ በዝግጅቱ ወቅት ስፍራው ላይ ተገኝተው የነበሩ የአይን ምስክሮች ከበቂ በላይ የመሰከሩለት የ 2012 የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ሳምንት በዳላስ ከስኬትም በላይ በሆነ ስኬት ተከናውኖዋል። የዝግጅቱን መጠናቀቅ በሚያመለክተው የመዝጊያው የፌይር ፓርክ ዳላስ ዝግጅት ላይ በትንሹ ከአራት ሺህ በላይ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ድምጻዊ ጸሃይ ዮሃንስ፤ ማህሙድ አህመድ፤ ሄኖክ አበበ፤ ጎሳዬ ተስፋዬ ሃገር ሃገር…ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ የሚሸቱ ዜማዎቻቸውን በባንዲራችን ተሸልመው ለህዝቡ አቅርበዋል።

በዝግጅቱ መሃልም በጉጉት ይጠበቅ የነበረውን  የፌዴሬሽኑን ፕረዚዳንት ልዩ መልዕክት ለማቅረብ ወደ መድረክ የመጣው ምክትል ፕረዚዳንቱ አቶ አብይ ኑርልኝ የሚያቀርበው መልዕክት የቀጣዩን 30ኛ አመት ዝግጅት የሚከናወንበትን ስፍራ መጠቆም በመሆኑ በጉጉት የሚጠብቀው ህዝብ በፉጨት እና በሆታ ነበር የተቀበለው። አቶ አብይ የመጣበትን በድጋሚ አስታውሶ 30ኛው አመት የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ሳምንት በልዩ ድምቀት በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ዜናውን ሲያበስር ለደቂቃዎች ያ አምስት ሺህ ሰዎችን ጢም አድርጎ የመያዝ ብቃት ያለው አዳራሽ ውስጥ የታደመ ህዝብ ደስታውን በጩኽት እና በሆታ ገለጸ። አቶ አብይ… “ዲሲ…እንገናኝ!” በማለት መልዕክቱን አድርሶ ተሰናበተ።

በመጨረሻም ሃገራዊ ጉዳያችንን በተመለከተ ደከመኝ ሰለቸን ሳይሉ ለሚለፉ፤ በሃገራችን የኪነትበብ ስራ በተለይም የሙዚቃው ገበያ በኮፒራይት ችግር ምክንያት አደጋ ተጋርጦበት ሳለ፤ የድምጻዊያኖቻችን የገቢ ዋስትና በሙዚቃ የመድረክ ዝግጅቶች ላይ ጥገኛ በሆነበት በዚህ ወቅት፤ ከዘረኛዎች እና ጥቅመኛዎች ዝግጅት አስተባባሪዎች የቀረበላቸውን ኪስ የሚያደልብ ገንዘብ ወዲያ ብለው ወደ ቀዳሚው ፌዴሬሽን ዝግጅት መጥተው ኢትዮጵያዊነታቸውን ላስመስከሩ ድምጻዊያን ከፍያለ ምስጋና ማቅረባችንን መዘንጋት የለብንም። በዚሁ ልክ የአንድ ወገን አፍራሽ ቡድንን እኩይ ተግባር ደግፈው፤ ተባባሪ በመሆን፤ ሆዳቸውን እና ገንዘብ ወደው፤ ጥቅምን ብቻ በማለም ኢትዮጵያዊነታቸው ላይ አፈር የነሰነሱትን ሆድ አምላኪዎችን ደግሞ ልናወግዝ እና ልናገላቸው ይገባል እላለሁ አበቃሁ።

——————————-

* ዳንኤል ገዛኽኝ…በስደት የሚገኝ ጋዜጠኛ ሲሆን ሲዋን የተሰኘው መጽሃፍ ደራሲ ነው!!

 

About Post Author

Abby

Internet reporter, freelancer and webmaster.
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 13 years ago on July 14, 2012
  • By:
  • Last Modified: July 14, 2012 @ 2:46 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

About the author

Internet reporter, freelancer and webmaster.

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar