www.maledatimes.com ለካስ ኢህአዴግ ፈሪ ናት! | አቤ ቶኪቻው www.abetokichaw.com - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ለካስ ኢህአዴግ ፈሪ ናት! | አቤ ቶኪቻው www.abetokichaw.com

By   /   October 20, 2012  /   Comments Off on ለካስ ኢህአዴግ ፈሪ ናት! | አቤ ቶኪቻው www.abetokichaw.com

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 54 Second

ሽመክት ውድነህ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቴኳንዶ ክለብ ምክትል አሰልጣኝ ነበር። በቴኳንዶ “ሶስተኛ ዳን” በሚባል ደረጃ ኢንተርናሽናል ቀበቶ አግኝቷል። በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2009 ዴንማርክ የቴኳንዶ ስፖርት ክለቡን ይዞ ሄዶ ተስፋ ሰጪ የሚባል ውጤት ይዞ ተመለሶ ነበር። (ይቺ ተስፋ ሰጪ… ከስፖርት ጋዜጠኞቻችን ኮርጄ ነው። ብቻ ከተስፋ አስቆራጭ ተቃራኒ የሆነ ውጤት ማለት ናት!)

በአዲስ አበባ ከተማ ወደ አስራ አምስት ሺህ የሚጠጉ ወጣት ልጆችን በቴኳንዶ ማሰልጠኑን አውግቶኛል። ሽመክት ከአምና በፊት የነበረው አምና (ካቻምና ማለት ነው) ግንቦት ሃያ ሊቃረብ አካባቢ ግን አንድ ፈታኝ ነገር ገጠመው።

በግል ክለቡ ቴኳንዶ የሚያሰለጥናቸውን ተማሪዎች ጠርጣራው መንግስት “ግማሹን በኦነግነት ግማሹን በግንቦት ሰባትንነት እጠረጥራቸዋለሁ” አለው። በዚህም የተነሳ የደህንነት ሰዎች ነን የሚሉ ሰዎች “የምታሰለጥናቸው ለግንቦት 20 ላሰባችሁት አመፅ እና ብጥብጥ ነው” ብለው ስለጥናውን እንዲያቆም አስጠነቀቁት።

ከማስጠንቀቂያው ብዙም ሳይቆይ የቀበሌው ሊቀመንበር አምስት ኪሎ አካባቢ የነበረውን ማሰልጠኛው ሊዘጉበት መጡ። አሻፈረኝ ብሎ ሲሟገት ስምንት የሚሆኑ ፌደራል ፖሊሶች ስድስት ኪሎ አምበሳ ግቢ አጠገብ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ካምፕ ውስጥ አስገብተው ክፉኛ ደበደቡት። በዚህም የተነሳ ሁለት ወር ያህል አልጋ ይዞ ተኝቶ ነበር።

ያ ሰሞን ኢህአዴግ “ጭንቅ ጥብብ” የሚለውን ዘፈን ድምፁን ከፍ አድርጎ ይዘፍን የነበረበት ሰሞን እንደነበረ እኔም አስታውሳለሁ። “የድል ቀን” በሚል የፌስ ቡክ ግሩፕ አማካይነት “በቃ” የሚል እንቅስቃሴ በሰፊው ታዋቂነት አግኝቶ ነበር።

ይህ እንቅስቃሴ፤ “ኢህአዴግ ግንቦት ሃያ በዓልን ሲያከብር አብዮት አደባባይ አብረን እንውጣ እና ለእስካሁኑ “ቴንኪው!” ከአሁን በኋላ ግን “ቻው” ብለን እናሰናብተው” በሚል፤ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በወላይትኛ፣ በአፋርኛ፣ በትግርኛ ብቻ በሁሉም ቋንቋ “በቃ” እያለ በርከቶችን ሲያስተባብር ነበር! ጊዜውም የአረቡ አገር አብዮት በየቦታው ይቀጣጠል የነበረበት ግዜ ነው።

ይሄኔ “ባለ ራዕዩ” ራዕይ ታያቸው አንድ ብልሃትም ወለዱ! እርሱም ግንቦት ሃያን የአባይ በዓል ማድረግ። እውነትም ግንቦት ሃያ የድል ቀንነቱ ቀርቶ የአበይ በዓል ሆነ። አባይ ይገደብ ይገደብ ከተባለ ያኔ ገና ወራት ብቻ ነበሩ የተቆጠሩት። ታድያልዎ በዚህ ዝግጅት ላይ አንድም መስሪያ ቤት ሳይቀር ሰልፍ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር። ሁለት ሰራተኞች ብቻ የነበሩት የሰፈራችን ፀጉር አስተካካይ ቤት ራሱ ከመስሪያቤት ተቆጥሮ ሰራተኞቻችሁ በሰልፉ ላይ እንዲገኙ የማይገኙ ከሆነ የማይገኙበትን ምክንያት እንዲያሳውቁ የሚል ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር። (እዝች ጋ ለጨዋታ ማጣፈጫ ታህል ትንሽ አጋንኛለሁ!)

የሆነው ሆኖ የዛን ግዜው ግንቦት ሃያ ኢህአዴግን ክፉኛ ሲያስጨንቀው ሰንብቶ በሰላም አለፈ። እንቅስቃሴው ከሁሉ በላይ ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር እንቅልፍ ነስቷቸው እንደከረመ ወሮ አዜብን ሳንጠይቅ እንዲሁ መረዳት ችለን ነበር። “እንዴት?” ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው…! ግንቦት ሃያው በአባይ ተሳቦ ድምቅ ብሎ በሰላም ተጠናቀቀ። በነጋታው አቶ መለስ ሆዬ የዝግጅቱ አስተባባሪ የነበሩ ወደ አስር ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን በሚሊኒየም አዳራሽ ራት ጋብዘው ነበር። (በቅንፍ እነዚህ አስር ሺህ ወጣቶች ባለፈው ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብር አስፈፃሚነት ስራ ላይም ተመድበው ነበር። እነዚህ ወጣቶች ሲያረጁ ኢህአዴግ ምን ይውጠው ይሆን? ብሎ ማሽሟጠጥ ይቻላል) ታድያ ያኔ ሟቹ ባደረጉት ንግግር “አንዳንዶች የግንቦት ሃያን ክብረ በዓልን ወደ ብጥብጥ ሊቀይሩ ቆርጠው ተነስተው ነበር!” ብለው ቃል በቃል ሲናገሩ ሰምቻቸዋለሁ። ይሄንን ስሰማ “ቀላል” ተጨናንቀው አንዳልነበር ግንዛቤ አገኘሁ! አሁን አሁን ሳስበው ይሄ ይሄ ተጨማምሮ ነው ለዚህ ያበቃቸው!

በነገራችን ላይ ኢህአዴግዬ ድንጉጥ ነው። ኮሽታ ሁሉ የምታስደነግጠው ድርጭት። በዛን ሰሞን በርካቶች የ“በቃ” እንቅስቃሴ ደጋፊ ናችሁ ተብለው አበሳቸውን ያዩ ነበር። አንዱም እኔ ነበርኩ። የእኔን እናቆየው፤

የቴኳንዶ አሰልጣኙ ሽመክትም በማሰልጠኛ ክለቡ የሚሰለጥኑ ልጆች ለዚሁ አላማ ነው የምታሰለጥነው ተብሎ ብዙ ፍዳዎችን እንዳየ፣ በዛም የተነሳ የሚወደውን እና ብዙ ገቢ ያገኝበት የነበረውን ስራውን ትቶ መሰደዱን ሲነግረኝ ደነቀኝ! ለካስ ኢህአዴግ ፈሪ ናት! ስል እንዳስብ አደረገኝ! በዛች የፌስ ቡክ ኮሽታ ስንቱን አመሰችው!?

በመጨረሻም

በዚሁ በ ”በቃ” ሰበብ እነ ውብሸት ታዬ ርዮት አለሙ አቶ ዘሪሁን እና ሂሩት ክፍሌ ታስረው ፍርድ ቤት ሲመላለሱ በነበረ ጊዜ የተሰጠ የምስክርነት ቃል እስከመቼም አይረሳኝም…! እስካሁን ለምን እንዳላወራዎት እግዜር ይወቀው! ቆይ፤ ተየብ፣ ተየብ አድርጌው አስነብብዎት የለ! ተገርመውም አያባሩ!

እስከዛም አማን ያድርገን!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 20, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 20, 2012 @ 9:53 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar