‹‹ESAT›› እና ‹‹OMN›› በሽብር ተከሰዋል ከ1 ቢ. ብር በላይ ንብረት እንዲወድም አስደርገዋል ተብሏል
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በሽብርተኝነት ቡድን ከተፈረጀው የግንቦት 7 ሊ/መንበር ፕ/ር ብርሀኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሀመድ ጋር አመፅ በማነሳሳት፣ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም በማድረግ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን ኢሳትና ኦኤምኤን የተባሉት የመገናኛ ብዙኃን የሽብር ጥሪ ልሳን በመሆን፣ ከትላንት በስቲያ በልደታ ፍርድ ቤት የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ዶ/ር መረራ፣ ፕ/ር ብርሀኑና አቶ ጀዋር መሀመድ ከቀረቡባቸው የወንጀል ክስ መረዳት እንደተቻለው፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት በህገ መንግስት የተቋቋመውን ስርአት በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ፤ በመንግስት ላይ ተፅእኖ በማሳደር ወይም የህብረተሰቡን ክፍል በማስፈራራት፣ የሁከትና የብጥብጥ ጥሪ በማስተላለፍ፣ አንዳንድ የኦሮሚያና አማራ ክልል ህብረተሰብን ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት እንዲጠፋና መሰረተ ልማት እንዲወድም፤ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን -የክስ መዝገቡ ይገልፃል፡፡
በመዝገቡ 1ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ኦፌኮ የተባለውን የፖለቲካ ድርጅታቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ የስራ ክፍፍል በመፍጠር፣ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ደጋፊዎቻቸው ወደ ሁከት እንዲገቡ በማድረግ፣ በመንግስትና በህዝብ ንብረቶች ላይ ውድመት እንዲደርስ እንዲሁም በሰውና በአካል ላይ ከባድ የአካል ጉዳትና ሞት እንዲደርስ ማስደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
ተከሳሾቹ ባስነሱት ሁከትና ብጥብጥ ከ2 ሚሊዮን – 1.1 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሀብትና ንብረት በተለያዩ አካባቢዎች እንዲወድም አስደርገዋል የሚለው አቃቤ ህግ ፤ በተጨማሪ ኦኤምኤን በተባለው ሚዲያ የሁከት ጥሪ አስተላልፈዋል ብሏል፡፡
ዶ/ር መረራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍና ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ሀሰተኛ ወሬዎችን በማውራት ተጨማሪ ክሶች ቀርቦባቸዋል፡፡
በመዝገቡ 2ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፤ ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለማስወገድ፣ የሽብር ተልእኮ በመስጠት፣ አርሶ አደሩ በመንግስት ላይ እንዲያምፅና ለፍትህ ስርአቱ እንዳይገዛ፣ ለዳኝነት በየፍርድ ቤቱ እንዳይሄድ በመቀስቀስና የሁከት ጥሪ በማስተላለፍም፣ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል ይላል፡፡ በተጨማሪም በመንግስት ላይ ጦርነት በመክፈት የሚያሸንፉበትን አቅጣጫ መቀየሳቸው በክሱ የተጠቀሰ ሲሆን የማሰልጠኛ ማእከላት እንዲከፈቱ ተልእኮ እንደሰጡም ተመልክቷል፡፡
በሚኖርበት ውጭ ሀገር የሽብር ቡድን አባል በመሆን፣ የሽብር ቡድኑን ተልእኮ ለመፈፀም የሁከትና የብጥብጥ ጥሪ በኦኤምኤን በኩል በማስተላለፍ፤ የልማት ተቋማትና ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሁም፣ የኢንቨስተሮች ንብረት ላይ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ንብረት እንዲወድም አስደርጓል የተባሉት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ጀዋር መሀመድ ናቸው። ግለሰቡ በሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳትም መድረስም ተጠያቂ ተደርገው፣ በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ቀርቧል፡፡
በሽብር የተከሰሱት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ፤ በሽብርተኝነት የተፈረጁት የአርበኞች ግንቦት 7 እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፤ የሁከት ብጥብትና ማስተላለፊያ ልሳን በመሆን፣ ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ አድርገዋል በሚል ተከሰዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ክሱን በንባብ በማሰማት፣ መዝገቡን ለየካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
Average Rating