(የካቲት 20/2007) የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለዛሬ የካቲት 20 የተቀጠረው ቀሪ የአቃቤህግ የሲዲ ማስረጃዎችን ለማየት ነበር። በባለፉት ሁለት ችሎቶች 4ኛ ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ ላይ እና 5ኛ ተከሳሽ አብደታ ነጋሳ ላይ የቀረቡ የሲዲ ማስረጃዎች በችሎት ታይቷል። በ11ኛ ተከሳሽ የቀረበው የሲዲ ማስረጃ “ከተከሳሽሹ ላፕቶፕ የተገኙ ለቅስቀሳ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የኦሮምኛ ሙዚቃ ክሊፓች” እንደሆኑ አቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ በዛሬው ችሎት 11ኛ ተከሳሽ የሆነው በየነ ሩዶ ላይ የቀረበው የሲዲ ማስረጃ ታይቷል። ዛሬ በቀረበው የ11ኛ ተከሳሽ የሲዲ ማስረጃ ላይ ሁለት የኦሮምኛ ሙዚቃ ክሊፓች በችሎት ታይተዋል። በመጀመሪያ የታየው የአርቲስት ጫላ ቡልቱሞ “ማስተር ፕላኒ” የተሰኘው ዘፈን እና ክሊፕ ነው። ቀጥሎ የታየው የአርቲስት ሴና ሰለሞን ሙዚቃና ክሊፕ ነው።
ቀሪ የሲዲ ማስረጃ ተብሎ የነበረው 4ኛ ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ ለኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የሰጡት ቃለመጠይቅን የያዘ ሲዲ ነበረ። በባለፈው ችሎትም ሲዲው አልሰራ ብሎ ስለነበረ ነው ለዛሬው ቀጣይ ችሎት እንዲታይ መዘዋወሩ ይታወሳል ። ሆኖም ሲዲው በድጋ በዚህኛው ችሎትም ሊሰራ አልቻለም፡፡ ሲዲው የቪዲዮ ፋይሉ እንዳለ ቢያሳይም ሊከፈት አለመቻሉን ዳኞች ጠቅሰው የአቃቤ ህግን አስተያየት ጠይቀዋል። አቃቤ ህጉም በበኩሉ በባለፉት ቀጠሮዎች ስብሰባ ገብተው ስለነበር የሲዲውን ጉዳይ ተከታትለው የሚሰራ ሲዲ ቀይረው ማምጣት አለመቻላቸውን ገልፆ ሁለት ቀን እንዲሰጠው እና ከፓሊስ የሲዲ ማስረጃውን ኮፒ አድርገው እንዲያመጡ እንዲፈቀድላቸው ጠይቋል።
የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች በዛሬው እለት ባይቀርቡም አቶ ወንድሙ ኢብሳ ለዛሬ ወክለዋቸው ቀርበዋል። አልሰራ ያለው ሲዲ እንዲሰማ በሚል ተጨማሪ ቀጠሮ መጠየቁ ምክንያታዊ እንዳልሆነ፤ አቃቤ ህግ ያለውን ማስረጃ አዘጋጅቶ መጠበቅ እና ሲዲው በሚከፈት ወቅትም እንዲሰራ የማድረግ የራሱ የአቃቤ ህግ ስራ እንደነበር ተናግረው ተጨማሪ ቀን መጨመሩን ተቃውመዋል። አቶ በቀለም ” አለ የተባለው የቪዲዮ ማስረጃው ቢቀርብ ለኔም ይጠቅመኝ ነበር። አቃቤ ህግም ቢፈልግ እስከዛሬ ከዩቲውብም ቢሆን አውርዶ ማቅረብ ይችል ነበር። ስለሆነም አቃቤ ህግ ማስረጃውን ማቅረብ አልፈለገ ይሆናል ብዬ ነው የተረዳሁት እና እስከዛሬ በተሰማው ማስረጃ ብይን እንዲሰጠኝ” ብለው ሃሳባቸውን አቅርበዋል። ዳኞቹም የሁለቱንም ወገን ክርክር ከሰሙ በኋላ የሲዲው አልከፈት ማለት የቴክኒክ ችግር ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚገምቱ እና በሌላ በኩልም ለተከሳሹም (ለአቶ በቀለ ገርባ) ሊጠቅም ስለሚችል የተፈጣጠነ ውሳኔ ከማስተላለፍ፤ አቃቤ ህግ አንድ እድል ተሰጥቶት በቀጣይ ቀጠሮ የሚነበብ ሲዲ ይዞ እንዲቀርብ አዘዋል።
ቀጣይ ቀጠሮ ለመጪው እሮብ (የካቲት 22/2009) ተቀጥሯል።
በ11ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረቡትን ሁለት ክሊፓች ሊንክ ከዚህ በታች ይገኛሉ።
Average Rating