Read Time:3 Minute, 37 Second
የማለዳ ወግ ... ታላቁን የዓድዋን ድል ለማክበር ቢሮን መዝጋት በቂ ነውን ? ========================================= * ስለ መከረኛዋ ኢትዮጵያ ስትሉ እንደ ድርጅታችሁ በዓላት ሰለ ዓድዋም ድል ሰባስቡን ... * ዓድዋን በፊስታ ዳንኪራ ማክበሩ ቀርቶ ፤ በክብር ለሞቱልን ሰማዕታት ሻማ አስበሩን ... * የስደት ፍሬዎቻችን ታሪክ እናስተምራቸው ፤ የጀግኖች አባቶችን ታሪክ እናውርሳቸው ... * ዓድዋ ከውጭ ወራሪ ጋር በተደረገ ትግል የደም መስዋዕት የተከፈለበት ታሪካቸን ነው ... * ስለ ኢትዮጵያ ታደሱ ... * ዓድዋን ለማሰብ ቢሮ መዝጋት በቂ አይደለም ... በታላቁ የዓድዋ የነጻነት ድል ቀን ዋዜማ ... ======================= አዎ ልክ የዛሬ 121 ዓመት የሀገሬ ሰው በዓድዋ ዘር ሀይማኖት ሳይለያይ የሀገሬ ሰው ውርደትን አሻፈረኝ ብሎ ክተት ብሎ ፣ በአጭር ታጥቆ ፣ ጦር ሰብቆ ፣ የራሱን ወንድም ሳይሆን ነጭ ወራሪ ሰላቶ ጣልያንን ዓድዋ ላይ ገጥሞ ድል ያደረገበት እለት ነው ። እኒያ አይበገሬ ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ፣ በጣሻ ዱር ሸንተረር ፣ በተራራ በወንዝ በየስርቻው ወጥተው ወርደው ፣ ታግለው አታግለው ፣ ጥ ለው ወድቀው አጥንታቸውን ከስክሰው ፣ ደማቸውን አፍሰው ይህችን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አስረክበውናል ። ... ይህ ታላቅ የትውልድ መስዋዕትነት የተከፈለበት የደመቀ የዓድዋ ድል በዓልን ከብላቴና እድሜ እስከ ጎልማሳ እድሜ በሀገሬ በኩራት ሲከበር ደርሻለሁ ። ከዚያም ወዲህ ታሪካችን የመቶ አመት ተደርጎ ሲነገረን የአደዋው ጦርነት አዝማች መሪው ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምሊሊክ ባማስፋፋት ዘመቻ እየተወገዙ ስማቸው ሲረክስ በታላቁ የዓድዋ ድል አከባባር ድባብ ደስ ባይልም ኢትዮጵያን ለምንወድ ከየትኛውም ድል ቀዳሚ የሀገር ኩራት ድላችን ሆኖ እስከ ዛሬዋ ቀን ቀጥሏል ። የዓድዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከገዥው ስልጣንና ከግለሰቦች በላይ የህዝብ ትግል ውጤት ነውና የማንነታችን መሰረትና የህልውናችንም መገለጫ ነው ። የዓድዋ ድል ከዳግማዊ እምዬ ምኒሊክና ከንግስት እትጌ ጣይቱ ግለሰባዊ ታሪክ በላይና ከኢትዮጵያ ኩራትነት አልፎ ተሻግሮ ለመላው የጥቁር ህዝብ የነፃነት ተምሳሌትና የአርነት መገለጫ ታሪክ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት እማኝና ዋቢ ናቸው። በዓድዋ የጥቁር ዘር " አትንኩኝ !" ባይበት ሲረጋገጥ የጥቁር ዘር ለነጻነቱ ቀናኢ መሆኑን ለአለም የተመሰከረበት ጉልህ የታሪክ አሻራም ነው ፣ ዓድዋ ! ጎልማሳ ልጅ ባደረሰ የስደት እድሜየ የዓድዋን በዓል ያለፈውን እያስታወስኩ በታላቁ የዓድዋ የነጻነት ድል ቀን ዋዜማ ለስደት ፍሬዎቻችን የጎደለው ይሞላላቸው ዘንደ የማለዳ ወጌ ትኩረቴን በክፍተቶቹ ላይ አተኩር ዘንድ ግድ ብሎኛል ! ዓድዋና ዝካሬው በአረብ ሃገራት .... ==================== ላለፉት 20 ዓመታት የዓድዋ ታሪካዊ የድል በዓልን በየአመቱ ሲዘከር እኔም በሳውዲው ስደት ነው ያሳለፍኩት ፤ ምንም እንኳን የታላቁ የዓድዋ ደል በአል አከባበር እዚህ በስደት ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ቢሮ በመዝጋት በአሉን ያሳልፉታል ፡ በሃገር ቤትም በሃገር አቀፍ ደረጃ የዓድዋ በአል በመንግስት እገዛ ሞቅና ደመቅ ብሎ ባይስተዋልም የማይተው ታሪክ ነውና “ አድዋ ታሪኬ ነው “ በሚለው ትውልድ በተለያየ መንገድ መከበሩና መታሰቡ ግን ተስተጓጉሎ አያውቅም ። ከግማሽ ሚሊዮን የማያንስ ኢትዮጵያውያን በምንገኝበት በሳውዲ አረቢያና በቀሩት የአረብ ሃገራት ኢንባሲና ቆንስል መ/ቤቶች ላለፉት 21 ዓመታት ዓድዋን በማሰብ ቢሮ ሲዘጋ እንጅ በውል ሻማ አብርተው እንኳ ዓድዋ እንደ አኩሪ ብሔራዊ በዓል ተከብሮ አይቸ አላውቅም ... እርግጥ ነው ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ይዘጋሉ … ሲዘጉ ደግሞ በሚለቀቀው ማስታዎቂያ ላይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ስራ ዝግ ነው ግልጋሎት አንሰጥም ከማለት ባለፈ በማስታዎቂያው ግርጌ እንኳ ሰማዕታቱ በክብር አይወሱም ከማስታወቂያ ግርጌ “ ክብር ለጀግኖች አርበኞች !” የምትል ስንኝ ለመጻፍ ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶቻችን ከገደዳቸው አመታት ነጉደዋል ። የድርጅትና የፖርቲ ብሎም የብሔር ብሔረሰብ በአላትን ሲያከብሩ ማድምቂያ የሚያደርጓቸውን ታዳጊ የስደት ፍሬ ለሆኑት በአረብ ሃገር ተወልደው ለሚያድጉ ልጆቻችን የዓድዋን የአባቶቻቸውን አንጸባራቂ ድል እንዲያውቁት ማስተማሪያ የሚሆን ዝግጅት ያደርጉ ዘንድ ዘወትር ብንወተውትም ሰሚ አላገኘንም ። ዓድዋን እንደ ድርጅት ፓርቲና ብሄር ብሄረሰብ በዓላት ወይፈን አርደው ፤ ከበሮ እየደለቁ በደመቀ ሆታና ጭፈራ ማክበሩ ቀርቶባቸው ስለ በአሉ ምንነት ገላጭ የሆነ ትምህርት በብጣቂ ወረቀት ግንዛቤ እንዲሰጥ ቢደረግ አስተምሮቱ ከፍ ያለ መሆኑ ሊያከራክር የሚገባ አይመስለኝም ። ዓድዋ ከቢሮ መዝጋት ባለፈ ሃበሾች በነጭ እብሪተኞች ላይ የተቀዳጀነው ድል ለመሆኑን ከእኛ አልፎ ለነገ ሃገር ተረካቢ ታዳጊዎች ገላጭ መረጃዎችን መሰናዳት ግድ ይለናል ። ዛሬ በአረቡ አለም የተወለዱ ታዳጊዎች ሊኮሩበት ከሚገባው የሃገራቸው ታሪክ ይልቅ ስላደጉበት አገር በአላት የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው እየገፋናቸው በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ። ልጆቻችን አኩሪውን የሀገራቸውን ታሪክ አክብረውና ጠብቀውት እንዲኖሩ ታሪክ የማውረስ ኃላፊነቱን ደግሞ በመንግስት ተወካይ ዲፕሎማቶች፤ የሚሲዮን መስሪያ ቤቶቻች እና የአለም አቀፍ ት/ቤቶቻችን ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል ። አኩሪ ታሪክን ማዘከር ታሪክን ከማወራረስ አንጻር ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነውና ሊታሰብበት ይገባል ። ዓድዋን በክብር እናዘክረው ዘንድ ሰባስቡን ... ========================= በአረብ ሀገራት የዓድዋን ታላቅ ሃገር አቀፍ የድል በዓል እንደ ድርጅት ፣ የፖርቲ ፓርቲ ብሎም የብሔር ብሔረሰብ በአላት ኢትዮጵያውያን በአዳራሾቻቸው ተሰባስበን እንድናከብረው ሊደረግ ይገባል ። ዲፕሎ ማቶቻችን "ለዓድዋ ድል መታሰቢያ ቢሮ ዘጋን " ከማለት ባለፈ ነዋሪውን ወደ አዳራሹ ጥሩት ፣ ቢያንስ ከበሮ ባይደለቅ ለዚህች መከረኛ ሀገር ለኢትዮጵያ ጀግኖች ሰማዕታት ሻማ አስበሩንና እንመናችሁ ፤ ዘር ሃይማኖት ሳትለዩ ሰባስባችሁ የጀግኖቻችን ታሪክ ላንድ አፍታ እያነሳሳን እንድናዘክር ፣ እንድንማማርና ጀግኖቻችን እንድናመሰግን አድርጉን ፤ እንኩራባችሁ ! ስለ ኢትዮጵያ ስትሉ በጥልቀት ታድሳችሁ እንያችሁ ! የቀደመው የማይመች አካሄድ በቀጣይ ሊታረምም ግን ይላል … አምናም የተማጸንኳችሁ ይህን ነበር ዘንድሮም እንዳምና የምማጸናችሁ ይህንኑ ነው ! ይስረስ ለክቡራን ሰማዕታት ... ================= በዱር በገደል ፣ በጣሻ ዱር ሸንተረር ፣ በተራራ በወንዝ በየስርቻው ፣ በከተማ በገጠር በየጉራንጉሩ ለተንከራተታችሁ ፣ ደማችሁን አፍሳችሁ ፣ አጥንታችሁ ከስክሳችሁ ክብር የህይወት መስዋዕትነትን ለከፈላችሁ የሀገሬ ጀግኖች አባቶች ከብር ይገባችኋል ! የዓድዋን አንጸባራቂ ድል በደማችህ ዋጅታችሁ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን አልፎ ለአፍሪካን ነጻነት ተምሳሌት ድል አብቅታችሁናልና እናመሰግናችኋለን ! ቁርጥ ቀን አርበኞቻችን እናንተ ናችሁና በክብር እናስባችኋለን ! ክብር ለዓድዋው ድል አጥንታቸው ለከሰከሱና ደማቸውን ላፈሰሱ ሰማዕታት ! ነቢዩ ሲራክ የካቲት 22 ቀን 2009 ዓም
Average Rating