# ዝክረ-አድዋ 18
የኢትዮጵያ ልጆች ነጻነታቸውንና ብሔራዊ አንድነታቸውን ለማስከበር ባህር ተሻግረው ድንበር ጥሰው ከመጡ አያሌ የውጭ ወራሪዎች ጋር ከፍተኛ ፍልሚያቸውን አካሂደዋል ።ከነዚህ ከባድ ወታደራዊ ፍልሚያዋች ውስጥ ኢጣሊያ ኢትዮጲያን በሀይል ለማንበርከክ ያደረገችውን ወረራን ለመመከት ኢትዮጲያውያን ያደረጉት ፍልሚያ አንዱና ተጠቃሹ ነው ፤ በኢትዮጵያ ረጅም የታሪክ ዘመን ውስጥ በተለይም ከ 16ኛው መቶ ክፍለዘመን ወዲህ የተለያዮ የውጭ ወራሪዎች አገሪቱን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ተከታታይ የሆኑ ሙከራዎች አድርገዋል ።
እያንዳንዱ ወራሪ ሀይል በየወቅቱ ይዞት የተናሳው ልዮ ዓላማና ባህሪ ነበረው ።ቱርኮችና ግብጾች በአካባቢው የበላይነትን በመያዝ ንግድን ለመቆጣጠርና ግዛቶችን ለማስፋፋት በነበራቸው እቅድ መሰረት የተነሱ ሲሆን፤ ፓርቱጋሎች ፣ፈረንሳዮች ፣ እንግሊዞችና ጣሊያኖች ደግሞ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የነበረው የካፒታሊዝም እድገት መነሻ በማድረግ በየደረጃው ከዚህ እድገት ጋር የመነጩትን የቅኝ ግዛትና የብዝበዛ ፍላጎቶች ለማሟላት በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ ተሰልፈዋል ።
ኢትዮጲያን የቅኝ ግዛት አድርጎ ለመያዝ ብዙ ሀገሮች ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው እንደቀረ የአለፈው የነጻነት ትግላችን ይመሰክራል ።የኦቶማን ቱርክና የግብጽ ተስፋፊዎች የፓርቱጋል ቅኝ ገዢዎች የመሃዲስት ወራሪዎች የኢጣሊያ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ሀይሎች በተከታታይ ያደረጉዋችው ግልጽና ስውር ደባን ኢትዮጲያውያን በተባበረ ክንዳቸው አክሽፈዋዋል ።
እነዚህ ወራሪ ሀይሎች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዳደረጉት ሁሉ ኢትዮጵያን ለመውረር ካደረጉት ሙከራዎች በአብዛኛው የተፈጸመው በስውር ነበር ፤ ይህም ሚሲዮናውያንና ቆንስላዎችን አስቀድመው በመላክ ቦታውን ካስጠኑ በኃላ ወታደሮችን በመላክ የሚያደርጉት የወረራ ሙከራ ነው ።ይህንን አስመልክተው አጼ ቴዎድሮስ ሊዥን ለተባለው ፈረንሳዊ ሚሲዮን ለምን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንደማይፈቅዱ ሲገልጹ ፦
” የአውሮፓ መንግስታት የምስራቅ ግዛታችንን ለመያዝ ሲሹ የሚጠቀሙበትን በዘዴ አውቃለሁ ። መጀመሪያ ሚሲዮናውያንን ይልካሉ ፤ ቀጥለው ደግሞ እነሱን እንዲረዱ በማለት ቆንስላዎችን ይልካሉ ። በማከታተልም ቆንስላዎችን እንዲረዱ በማለት ወታደሮች ይልካሉ.. ……..እኔ እንደ ሂንዱስታ ገዥ እንዲህ የሚቀለድብኝ እይመስልህ.. ….ይህንን ከማደርግ ከጦሩ ጋር ግንባር ለግንባር መግጠሙን እመርጣለሁ “……ብለዋል ።
ቅኝ ገዢዎች በሚሶናውያን ፊታውራሪነት በቆንስላዎች ጋሻ ጃግሬነት ግልጽ ወረራ በማድረግ ኢትዮጲያን ለመያዝ ከ 1557 /እ.ኤ.አ/ ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ። የቀደምትነቱን ቦታ በመያዝ የወረራው በር ከፋች የሆኑት የኦቶማን ቱርክ ፓሻ ኡትማን በቀይ ባህር አካባቢ ያሉትን ሀገሮች በቁጥጥር ሥር ሲያደርግ የኢትዮጵያን የባህር በር ከ1557/ እ.ኤ.አ/ ጀምሮ እስከ አስራ ዘጠነኛው ምዕት አመት አጋማሽ ከፊላዊ ሥልጣን /Nominal Authority /በመያዝ ሲቆጣጠር ቆይቷል ።
የኦቶማን መንግስት ኃይል ሲዳከም አካባቢውን በተተኪው ለመያዝ የሞከረው በመሐመድ አሊ የተገነባው የግብጽ መንግስት ነበር ። የግብጽ ተስፋፊዎች እንደ ኦቶማን ቱርኮች በምጽዋ ወደብ ብቻ ሳይወሰኑ ወደ መሀል አገር ዘልቀው በመግባት ግዛት ለማስፋፋት ቆርጠው ተነሱ ። በዚህ ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ ጀምረውት የነበረው ማዕከላዊ መንግስትን የማጠናከሩ ተግባር እየጉለበተ በመምጣቱ ወራሪው ኃይል እንዳሰበው ግዛቱን ለማስፋፋት ሳይችል ቀረሽ። በዚህ መሰረት በ1876/እ.ኤ.አ/ ጉንደትና ጉራዕ ላይ በአጼ ዮሐንስ በሚመራው ጦር ተከታታይ ድል በመመታታቸው የወረራ እቅዳቸው ሊከሽፍ ችሏል ።
የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች በሱዳን የመሐዲ ንቅናቄ ካሰጋቸው እንግሊዞች ጋር የውስጥ ስምምነት በማድረግ በ1885/እ.ኤ.አ/ አካባቢ የምጽዋን ወደብ ያዙ ።ይህ ድርጊት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሎ ሁለቱም ወገኖች ጦርነት እስከማወጅ ደረጃ ተዳርሰው በ1887 /እ.ኤ.አ/ ዶጋሊ ላይ በተደረገው ጦርነት ኢትዮጲያውያን አሳፍረው መለሷቸው ።
አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በሁዋላ ነጥረው መውጣት የቻሉት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ጠንካራ መአከላዊ አስተዳደር ለመመስረት ችለዋል ፤ይህም የውጭ ጠላቶችን ለመከላከል ቀድሞ ከነበረው ይበልጥ አመቺ ሁኔታ ሊፈጥር ቻለ ።
ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ በአንድ በኩል ለአስተዳደራቸው ጠንካራ መሰረት ለመጣል ሲጥሩ በሌላ በኩል ደግሞ ከጠላት ጋር ላለመጋጨት ሰላማዊ የሆነ የዲፓሎማሲ ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ፤በመሀከሉም በኢሊጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል የውጫሌ ውል ተፈረመ ።ይህ ውል በተለይም አንቀጽ አስራ ሰባት በኢጣሊያኛ ቋንቋ ትርጉም በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጲያን የቅኝ ግዛት የሚያደርግ ነበር። የአንቀጹን አሻሚነት የኢጣሊያንን መሰሪነት የተረዱት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ውሉ መሰረዛቸውን ለኢጣሊያ መንግስት በግልጽ አሳወቁ ።
በሽፍጥ ኢትዮጲያን ለመያዝ ያልተሰካላቸው የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች በኃይል ከመጠቀም ሌላ አማራጭ በማጣታቸው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የጦር ዝግጅት ማድረግ ቀጠሉ ።የኢጣሊያ ያልታሰበ አገርን የመቁረስ ሙከራ ያሰጋቸው ዳግማዊ አጼ ምኒሊክም የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ የበኩላቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ቀጠሉ ።
ከዛሬ 121 አመት በፊት በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የቋያው እሳት ነደደ ፤ አድዋ ላይ የኢትዮጵያ ልጆች ከኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ጦርነት ገጠሙ ፤ ውጊያው እጅግ ከባድ ቢሆንም ድል ለኢትዮጲያ ልጆች ሆነ ፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የኢጣሊያ ጦር ከ 1,000 ኪሎ ሜትር በላይ፤ በእግሩ ተጉዞ በመጣው በገበሬ ጦር ቆሰለ ፣ተገደለ ፣እንዲሁም ተማረከ ።
የአድዋውን የድል ዜናን ተከትሎ በሮምና በተለያዮ የኢጣሊያ ግዛቶች አመጽ ተቀሰቀሰ ፤ ከ100,000 ሰዎች በላይ petition በማሰባሰብ ኢጣሊያ ከአፍሪካ ቅኝ ግዛቶቿ ትውጣ ሲሉ ጥያቄያቸውን አቀረቡ ፤ሰልፈኛቹም viva Menlik እያሉ ሲጮሁም ተደመጡ ። የወቅቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት ሲኛር ክሪስፒም በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ ።
የኢትዮጵያ ልጆች የኢጣልያንን ወራሪዎች አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት በጥቁር አለም ታይቶ የማይታወቀውን ድል ተጎናጸፋ ፤አድዋ ላይ የቅኝ ገዢዎች ቅስም ተሰበረ ፤ኃያላን የሚባሉ ሁሉ ሀይላቸው የቱን ያህል እንደሆነ ዞር ብለው እንዲያዩ አስገደዳቸው ።
ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር!!!!
ያለ ምኒሊክ ጠንካራ አመራር የአድዋ ድል አይታሰብም!!!!!!!
ክብር ለአድዋ ጀግኖች !!!!!
Average Rating