ተሻለ መንግሥቱ (teshalem1@gmail.com)
ከዐይን በላይ የሚታመን ባለመኖሩ “ማየት ማመን ነው” ይባላል፡፡ እኔም አየሁ፤ አመንኩም፡፡ እናም አልሁ – “ወያኔ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን በተለይም በአማሮች ላይ የሚፈጽመው ድንበርየለሽ ግፍና በደል በመጨረሻው የዞረ ድምር ምን ያመጣብን ይሆን?” አሳሳቢና አስጨናቂ ጥያቄ ነው፡፡ የዚህን የወያኔን ዘመን ፍጻሜ ለማየት ብዙዎቻችን የችግሩ ገፈት ቀማሾች ብንጓጓ እስካሁን ከምናውቀውና ከዚህ በታች ከምነግራችሁ አስደንጋጭ መረጃ አንጻር አይፈረድብንም፡፡
እንደአጠቃላይ እውነት ጨካኝ መንግሥታት የሚዘወሩት(የሚመሩት) በክፉ መንፈስ ነው፡፡ ከመነሻው መናፍስት ሁለት መሆናቸውን ልብ ይሏል – ያዋጁን በጆሮ እንዳትሉኝ እንጂ፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ሚዛን በደፋ ሁኔታ ዓለምን እያንቀጠቀጠ በመግዛት ላይ የሚገኘው መንፈስ ከሁለቱ አንዱ የሆነው ክፉው መንፈስ መሆኑን ለመረዳት ዓለምን ለአፍታ ያህል በምናባችን ቃኘት ማድረግ ብቻ በቂ ነው፡፡ እዚች ግድም /Positive Energy and Negative Energy የሚባሉትን ፈረንጅኛ ጽንሰ ሃሳቦች አስታውሱልኝ፡፡/ የጨካኙ መንፈስ ብርታትም የደጉ መንፈስ – በተወሰነ ደረጃ ከመከላከል ውጪ – ለማጥቃት ክንዱን አለመሰንዘሩ ነው፡፡ ለዚህም ነው በቅጽበት ውስጥ ጠላቶቹን ድባቅ መምታት እየተቻለው “ጠላትህን ውደድ፤ እጅ ጠባብህን ለሚፈልግ መጎናጸፊያህንም ጨምርለት፤ ግራህን ለሚጠፋህ ቀኝህንም አዙርለት፤ የሚሰድቡህን መርቅ፣ ወዘተ.” የሚል የፍቅርና የትህትና አስተምህሮ አስተላልፎ ራሱም በመስቀል ተቸንክሮ የሞተው – የዓለም ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትም በዚህ አስተምህሮ ምዕመኗን በመግራቷ ይመስላል ሕዝቡ ሁሉንም ነገር በ”አንተው እንዳመጣኸው አንተው መልሰው” ጸሎት ለፈጣሪ ከመስጠት ውጪ በራስ ተነሳሽነት በጠላትነት የተፈረጀን ኃይል በመጣበት የኃይልና የክፋት መንገድ ለመቋቋም ያለው ፍላጎት እጅግ አነስተኛ ነው፤ ይሄም መንገድ ብዙ እንደጎዳን በጣም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ዘመኑን ያልዋጀ አካሄድ ለዘመናችን አካይስቶች የተመቻቸው ይመስላል፡፡ በዚህን ዓይነት ትምህርት የታሸ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እፍኝ በማይሞሉ ሞራለቢስና ሃይማኖተቢስ ወያኔዎች ሕይወቱ ሲመሰቃቀል ማየት እንግዲህ የሃይማኖትን ካባ እስከማስወለቅ ለሚደርስ የአእምሮ ህመም ቢዳርግ ለፍርድ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ ለነገሩ በዘመነ ግርምቢጥ የዘመን ፍጻሜ ላይ ተቀምጠን ፍትህን መመኘት ሞኝነት ነው፡፡
ይህ ክፉ መንፈስ በሰዎች ሰውነት ውስጥ ግዛት ፈጥሮ ሰዎቹን የርሱ ባሪያ በማድረግ እርሱ የፈለገውን እንዲያደርጉለት የጨለማው ንጉሥ ምድራዊ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮችና በመጨረሻውም የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎ ይሾማቸዋል፡፡ በዚህ የሹመት ዘመናቸው አንዳችም ሥጋዊ ነገር እንዳይቸግራቸው የምኞታቸውን ጣሪያ እስከማሳካት በሚደርስ አለኝታነት ከነርሱ ጋር ይቆማል፡፡ እነሱም እርሱ የሚፈልገውን የደም ግብርና የስቃይ ቁልል በማስቆጠር ወሮታውን ይከፍላሉ፡፡ መጨረሻቸው ግን በርግጠኝነት አያምርም ብቻ ሣይሆን ከሠፈሩበት ቁና በበለጠ ይሠፈርላቸዋል፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ነጥብ አኳያ ወያኔም ሆነ አይሲስ የሚባሉት የመካከለኛው ምሥራቅ ጭራቆችና መሰሎቻቸው (የሀሽሽ ንግድ ካርቴሎችን ጭምር) ቀን ከሌት የሚባዝኑት ርኩሳን መናፍስት አለቆቻቸውን ለማስደሰት ነው፡፡ በተለይ አሁን ሊደበቅ የማይችል እውነት፡፡
በዚህ መሀል ኢትዮጵያና አማራ በግላጭ ተገኙ፡፡ ለክፉ መናፍሰት ጭዳነትም በክፉው የዐውሬው መንፈስ ታጭተው እሳቱ ለማይበርድ፣ ስለቱ ለማይዶለዱም የመከራና ዕልቂት አዙሪት ተጋለጡ፡፡ ይሄውናም እነሱን ያለና ስለነሱ የዘመረ ትግሬም ይሁን ኦሮሞ፣ ጉራጌም ይሁን ከምባታ፣ ወላይታም ይሁን ሳሆ፣ አሪም ይሁን ቦዲ፣ ጠምባሮም ይሁን ሃዲያ… መላው የሀበሻ ምድር ዜጋ የነሱን ዕጣ ፋንታ ሊያገኝ የግድ ሆነ፡፡ “ሀበሻ አይደለሁም፤ ቀብራራ እንቶኔ ነኝ!” የሚለኝ የዘመነ ዕንቆቅልሽን ዝልል ጠጥቶ በሥነ ልቦና የሰከረ ገልቱ መኖሩን አልዘነጋሁምና ለዚህ ዓይነቱ ወፍ ዘራሽ ሰው ይቅርታ መጠየቅ ካለብኝ እዚቺው አደረስኩ፡፡
ክፉ መንፈስ – እየመሰለንና በሁኔታዎች አስገዳጅነት እየተገፋን እንጂ- ዘርና ጎሣ አይለይም፤ የገዛ ልጅንና የቅርብ ዘመድን ሣይቀር ግብር የሚያስገባ(የሚያሳርድ) ዐውሬ መንፈስ በቋንቋና በዘር ልዩነት ያምናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ የሰው ግርድና አመሳሶ በክፉ መናፍስት የጥቃት ዒላማ ውስጥ ቦታ የላቸውም፡፡ እርግጥ ነው – እንደ ሥልትና ሰውን ለማጭበርበር ያህል ይጠቀሙበታል፡፡ ክፉ መናፍስት የዘር ሐረግ ቢለዩ ኖሮ ወያኔ – ከመነሻው አንስቶ – “ለምን እንደኛ ‹ጨካኝ› አልሆናችሁም፤ ለምን የነገዳችሁን ውድብ አልተከተላችሁም፤ ለምን እንደኛ አማራን አልጠላችሁም፤ ለምን ከነፍጠኞች ጋር ትሻረካላችሁ፤ አርቀን እየቀበርነው ያለነውን ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን ታሪክ ለምን ታነሳላችሁ…” በሚል እጅግ ብዙ ትግሬዎችን ያለ ርህራሄ ባልጨፈጨፉ፣ ባላሰሩ፣ ባላደኸዩና ከሥራና ከኑሮም ባላፈናቀሉ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ መስዋዕትነታቸው እምብዝም ያልተዘመረለት ኢፍትሃዊነትን በመታገል ሕይወታቸውን ለሀገራዊ አንድነትና ለፍትህ የሰው ትግሬዎች ወደፊት በታሪክ ማኅደር ይነግሣሉ፡፡ እናም ምንም እንኳን ብዙ የወያኔ አጫፋሪ ትግሬ መኖሩ ሃቅ ቢሆንም “ዐይቡን ሳያዩት አጓቱን ጨለጡት” እንዲሉ እንዳይሆንብን ፍርዳችንን እያስተካከልን እንድንራመድ ማስታወስ እፈልጋለሁ – እንዲሁ አሁን ብልጭ ያለብኝ ሃሳብ ነው፡፡ ለማንኛውም ይህን የክፉ መናፍስት ባሕርይ ልብ እንድንል እያሳሰብኩ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልንደርደር፡፡
ደርግ ክፉ ነበር፡፡ (ይህ ነገር ሊሰፋብኝ ነው መሰል) ባይሆን ላሳጥረውና በርሱው ልነሳ ከጀመርኩ አይቀር፡፡ እናም ደርግ እጅግ ክፉ ነበር፡፡ የአገዛዝ ሥልቱ ወታደራዊ ወገናዊነት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይሁንና በዘር የተመረዘ አስተዳደር አልነበረውም – ቢያንስ እስከመጨረሻዎቹ ዓመታት ድረስ፡፡ Give the devil its due. ክፋቱ ግን የወያኔን አያክል እንጂ ከዚያ በመለስ ወደር የለውም፡፡ ሁለቱም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ናቸውና – ከክፋት ምንጭ፡፡እናም ደረጃቸው ይለያይ እንጂ ሁለቱም ዐረመኔዎች ናቸው፡፡
ብዙዎቻችን የምናውቀውን የደርግን ጨፍጫፊነት፣ አሳሪነት፣ ገራፊነት(ወፌላላን የቀመሰ ያውቃታል)፣ ኢ-ሃይማኖታዊነትና ያን ተከትሎ ብዙዎችን ማበለሻሸቱን፣ ግትርነቱን፣ ድንቁርናውን፣…. እንርሳው፡፡ ግን ግን በአሳቻ ሰዓት በዜጎች መኖሪያ ሠፈር ላይ እሳት እየለቀቀ በተለይ ብዙ ሀብትና ንብረት ያወድም እንደነበር መዘንጋት የለብንም – ያ ጠባዩ ከወያኔ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ እንዲያ ያደርግ የነበረውም ቦታውን ይፈልገው ስለነበር ነው፡፡ ምሣሌ – ማርካቶ ቅ. ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢና ድሬዳዋ ውስጥ፡፡
ወያኔ፡፡ ህም! የወያኔ ሁልአቀፍና ወደር የለሽ ጭካኔ ተወርቶ አያልቅም፡፡
በአማሮች ላይ ያወጀውን እስካሁን ያልተነሳ የዘር ፍጅትና የዘር ማጽዳት ዐዋጅ እዚህ አናነሳም፡፡
ልባቸው ከአለት ድንጋይ የተሠራው ወያኔዎች አንድን ቦታ መቀማት ሲፈልጉ ወይም አንድን ሕዝብ መበቀል ሲፈልጉ አካባቢውን በእሳት ያጋዩታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያን ያነደዱ መስሏቸው ብዙ ደኖችንና ጫካዎችን ነዳጅ በመድፋትና አብሪ ጥይት በመተኮስ እንዳቃጠሉ ይታወቃል፡፡ የወያኔዎች ጥፋትና የእግዜሩ ትግስት ደግሞ እጅግ የሚገርሙ ናቸው፡፡ እግዜር የወያኔን ያህል በምድር የታገሠው ቢኖር ምናልባት የሰሜን ኮሪያን የኪም ኢል ሱንግ ሥርዎ መንግሥት ብቻ ነው – በኔ እምነት፡፡ እነሱም እንደኛው ከሦስት ትውልድ በላይ በናቡከደነፆራዊ የቀጥቅጥ አቅልጥ አገዛዝ ሥር ናቸው – እናም እነሱም እንደኛው እጅግ ያሳዝኑኛል፡፡ የእግዚአብሔርንም ትግስት ገደብየለሽነት እንድማር የሚያደርጉኝ እነዚህ ሁለት የዓለማችን ዕንቆቅልሾች ናቸው፡፡ እነሱን ሳስብ – ሁሌም – “እግዜር የት ሄደ?” እያልኩ ክፉኛ እጨነቃለሁ – ግን አማኝ ነኝ ታዲያ፤ ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚጋጭ እኔም ከፈጣሪ ጋር በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ጊዜ “እነታረካለሁ”፡፡ በኛና በርሱ መካከል ያለውን የጊዜ ዳይሜንሽናዊ ልዩነት በመጠኑ ስለምረዳ ግን ለጊዜው እጽናናለሁ፡፡ የሀገሬ ሙስሊም “‹አላህ ዳተኛ ነህ ታስጨርሰናለህ!› የሚለው ለካንስ ወዶ አይደለም”ም እላለሁ፡
በወያኔው ሥውር ትዕዛዝና የወንጀል አቀነባባሪነት በቅርቡ በጎንደር ከ420 በላይ ሱቆች በእሳት ነደዋል፡፡ በዚያው የአማራ ክልል ተብዬው አካባቢ የሕዝብን የመጠጥ ውኃ መርዘዋል፤ ለመመረዝ ሲንቀሳቀሱም እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡ እሥር ቤቶችን በአሳቻ ሰዓት በማጋየት የሚፈልጋቸውን ዜጎች አንድዶ ይፈጃል፡፡ በደመ ነፍስ ከእሳት ለማምለጥ የሚሮጡትን ታሳሪዎች ቀድመው በተዘጋጁ ነፍሰ ገዳዮች ይገድላቸዋል፡፡ ይህ የክፋት ዓይነት ዘርን ከመፍጀት ባለፈ ልዩ ስም ሊሰጠው የሚገባው ነው፡፡ ሰለጠነ የሚባለው ዓለም ለእንስሳት መብት ሲቆረቆርና ምግባቸውም ሆነ መጠጣቸው ከሰው ሳይለይ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ሲጥር እዚህ ያሉ ገዢዎቻችን ከእንስሳትም በታች ይቆጥሩናል፤ ድንቁርናቸውና ዕብሪታቸው መለኪያ የለውም፡፡ ወይ ፍርጃ! ምን አጥፍተን ይሆን እነዚህን ዐረመኔዎች እግዜር የሰጠን? ራሳችንን እንጠይቅ፡፡
ወያኔዎች ዜጎችን በእሳትና በናዳ ከቀያቸው ማፈናቀል በጣም የለመድነው የዕለት ከዕለት ተግባራቸው ነው፡፡ አንድን የሚፈልጉትን ቦታ ከነዋሪዎች ለማጽዳት ሲፈልጉ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ውስጥ በትንሽ ገንዘብ ደልሎ ወይም አስገድዶ ማባረር በአንጻራዊነት “ቅዱስ” ሊባል የሚችል ዘዴያቸው ነው፡፡ ከዚህ የከፋው ግን ጦር ሠራዊት መጠቀም፣ በድንገተኛ እሳት አካባቢውን ማያያዝና የእሳት አደጋ ሠራተኞችና የአካባቢው ሰዎች እሳቱነን እንዳያጠፉ በማገድ ሰውና ንብረትን ማጋየት፣ “ህገ ወጥ ናችሁ” ብሎ በማዋብ ማስለቀቅ… ዋና ዋናዎቹ የዐውሬዎቹ ወያኔዎች ዜጎችን ከርስታቸው የማፈናቀያ ሥልቶች ናቸው፡፡
አሁን ሰሞኑን ደግሞ በዓይነቱ ለየት ያለ ምናልባትም ሰይጣን ራሱ ሣይቀር ብዙ ሊማርበት የሚችል አዲስ የዕልቂት ሥልት አቀናብረዋል፡፡ ይህም ዜጎች በሥራ ድካም የናወዘ ሰውነታቸውን አረፍ አድርገው በሰላም ሊተኙ ሲሉ ከነመላ ቤተሰብ የሚያዳፍን ልዩ መሬት ሰርጓጅ ቴክሎጂ በመጠቀም መጨረስ ነው – ተራራ ደርማሽ ድማሚት አጥምዶ አፍሪካዊ ሂሮሽማና ናጋሳኪን በታሪክ ለማስመዝገብ ፈር ቀዳጅ የሆነውን ሙከራ ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ አካሂደዋል፡፡ “ቆሼ ተራ” በሚባው አካባቢ የታየው ዕልቂት የዚህ አዲስ ሥልት የሙከራ ጅማሮ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ጊዜ ካገኙ አዲስ አበባ ሥር አንዳች ነገር አጥምደው ሳይፈጁን አይቀሩም – ቻይና ደግሞ ሣንቲም ካየች የማትታዘዘው ነገር የላትም፤ ነፍሰ በላ የትልቁ ዐውሬና የትንንሾቹ የአጋንንት መንፈስ ታዛዦች ቀኝ ክንድ ናት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን መቼም ቤተ ሙከራ ከሆንን ቆየን፡፡ ፈረንጆቹ በዐይጥና በጅንጀሮ አንድን ነገር ይሞክራሉ – ወደኛ ሲመጣ ግን በኛው በዜጎች እንዲሞከር ልጆቻቸውን ያዛሉ፤ ክፉ መንፈስ የተጣባቸው ልጆቻቸውና “ልጆቻችን” ደግሞ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም – በሆዱ የማለ አድርግ ያሉትን ያላንዳች ማመንታት ያደርጋል፡፡ “ሴትና ሆድ የላኩት ሞትን አይፈራም” ብዬ ተረታችንን ባሻሽለው የሴቶች መብት ተከራካሪዎች(ፌሚኒስቶች) እንደማይቆጡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ – የሆኖ ሆኖ “ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅም”ና ገና ብዙ አሣር አለብን፡፡ ወያኔዎች ሁሉንም የአለቆቻቸውን ትዕዛዛት ካለማቅማማት ይፈጽማሉ – ምክንያቱም በደማቸው ውስጥ የተዋሃደው የአጋንንቱ መንፈስ ካለደም ግብር አይጸናላቸውም፤ የሥልጣን ማቆያ ማኅተማቸውም የሰው ደም ነው፡፡ አበቅቴው እስኪሽር የፈለጉትን ቢያደርጉ ከልካይ የለባቸውም፤ የደም ግብሩን እስካላቋረጡና ከትዕዛዝ እስካልወጡ ድረስ ደግሞ ወይም በተቃራኒው እኛ የደጉን መንፈስ ቀልብ የሚስብ አንዳች መልካም ነገር ማድረግ እስካልጀመርን ድረስ አለቃቸው የሆነው የዐውሬው መንፈስ ጦር ከጥፋት ይታደጋቸዋል – በራሳቸው ጊዜ በንነው እንደማይጠፉ ግን እንወቅ – ያ ምኞት ነው፡፡… ለማንኛውም ፈጣሪ የወገኖቻችንን ነፍስ ይማር – ለነገሩ እንዲህ ባልልም ዱሮውን ተምረዋል፤ ሰማዕት ናቸውና፡፡ በግፍ የምትጠፋ ነፍስ የኃጢኣት ሥርየትን በቀላሉ እንደምታገኝ በበኩሌ አምናለሁ፡፡ ግን ወዮ ለግፈኛው! ”በቅሎ ገመዷን በጠሰች” ቢሉ “ማሰሪያዋን አሳጠረች!” ይባላልና እያንዳንዷ የምናደርጋት ክፉም ሆነች በጎ ነገር ዙራ ተመልሳ ከእኛው ደጅ አትጠፋም፡፡
በአማራው አካባቢ እንዲህ ይደረጋል፡፡ ይህን ግፍ ታዘቡ፤ ሁሉም ወገን እንዲያውቀውም አድርጉ፡፡
ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በተለይም የፖሊስና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተብዬው የአማራ ጎሣ ባልደረቦች፣ የመስተዳድር አካላት ሠራተኞችና የጸጥታና ደኅንነት ባልደረቦች በተልዕኮም ሆነ በምሽት የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲማሩ ፈጽሞ አይፈቀድም – ይህ ዕገዳና ክልከላ ደግሞ በምንም ዓይነት መንገድ ለድርድር አይቀርብም፡፡ እንደሰማሁት በሌሎች በተለይም በትግራይ ክልል ይህ ዓይነቱ ነገር አይታወቅም፡፡ እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ በሀሰትም ይሁን በእውነት ማንኛውም ዜጋ ዲግሪ እንዲኖረው ይበረታታል፡፡ ይህ double standard በአንዲት “ፌዴራላዊት” ሀገር ውስጥ እውን ሆኖ ማየት ከግርምት በላይ ነው፡፡ አንዱን ማስተማር ሌላውን ማደንቆር፡፡ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ፤ አንዱ ዘመድ ሌላው ባዕድ፡፡ ፋሽዝምና ናዚዝም ከዚህ በላይ የለም፤ አፓርታይድ ከዚህ የከፋ በደል በሕዝቦች ላይ አላደረሰም፡፡ ቀን ይፍረድ!
ምሥጢር ማውጣት እንዳይሆንብኝ እንጂ አንዳንድ ሠራተኞች እንዴት ባለ የረቀቀ ዘዴ የርቀት ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ከራሳቸው ከሰዎቹ አንደበት ሰምቻለሁ፡፡ በፈተና ወቅት እንኳ ማንነታቸውን ለመደበቅ የሴት ቀሚስ ለብሰውና እንዳረብ ሴት ፊታቸውን በሂጃብ ሸፍነው እስከመሄድ እንደሚደርሱ ነግረውኛል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን? ቢማሩ ሀገርንና ወገንን ይጠቅማሉ እንጂ ማንን ይጎዳሉ? ግን ሀገሪቱን የሚገዛው በተግባሩ ባዕድ ኃይል ሆነና ችግሩ ከዚያ መነጨ፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን አደንቁሮ ለመግዛት ማንም ዜጋ ከሀሁ ባለፈ እንዳያውቅ ያደርግ ነበር፡፡ መማር ራስን ያሳውቃል፤ መማር አካባቢን ያሳውቃል፤ መማር ዓለምንና ከዚያም ባለፈ እንድናውቅ ያደርጋል፡፡ ያወቀ ሰው ደግሞ ለውስጣዊ ኅሊናው እንጂ ለውጫዊ እንቶ ፈንቶ አያጎበድድም፡፡ ስለዚህም ጨቋኞችና ቅኝ ገዢዎች ዜጎች እንዲታወሩ እንጂ በብርሃን እንዲመላለሱ አይፈቅዱም፡፡ የኛ ነው የሚሉትን ግን ብዙም ባይሆን በተወሰነ ደረጃ ለቀቅ ያደርጉታል፤ ማኪያቬሊያዊ የአገዛዝ ሥርዓት እንዲህ ነው፡፡ በወንድማማቾች መሀል ይህን መሳይ ሽብልቅ የሚቀበቅቡ እነዚህ እርጉም ወያኔዎች ዘር አይውጣላቸው – ለነገሩ እንዴት ብሎስ ይወጣላቸዋል?
አመራሮቹ ግን ይደበቁ አይደበቁ አይታወቅም እንደፈለጉ ይማራሉ – መማር ተብሎ፤ ማይምነት በአሥር ዲግሪ ቢጀቦን ከማይምነቱ ፈቀቅ አይልም፡፡ እነዚህ የወያኔ አሽከሮች ከፈለጉ ከውጪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያሻቸውን ዓይነት ዲግሪ በግዥም ይሁን በእጅ መንሻ ስጦታነት ይጭናሉ – አብዛኞቹ ግን ውስጣቸውም ውጫቸውም ገለባ ነው፤ ዱሮውንስ ሰውነቱን ለእህል ሲል ለወያኔ ያከራዬና የገዛ ወገኖቹን የሚጨፈጭፍና የሚያስጨፈጭፍ ባንዳ ሰው ምኑን ሰው ሆነው?
ዲግሪን ባወጣ የሚቸበችቡ የግል ተቋማት ደግሞ ከገጠር እስከከተማ ሞልተዋል፡፡ ከነዚህም ብዙዎቹ የነሱው የወያኔዎቹ ናቸው፡፡ ከወቅቱ የሀገራችን ራስ ምታቶች አንዱ በተለይ በመንግሥት ተብዬው የወያኔ አስተዳደር ውስጥ ከተራ የቀበሌና የወረዳ ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ላይኛው የዕዝ ጠገግ ድረስ የሚመደቡ ዜጎች በፎርጅድ ዲግሪ የተጥለቀለቁ መሆናቸው ነው፡፡ ከጋሪው ፈረሱን እያስቀደሙ በባዶ የዲግሪ ወረቀት መንበሽበሻቸው ለደረጃ ዕድገትና ለደመወዝ ማስተካከያነት ካልሆነ በስተቀር በሥራው ላይ አንድም ነገር አይፈይድም፡፡ ሀገሪቱ በባዶ ጭንቅላት ተወርራ ሥራ እየተበላሸ ተገልጋይ ዜጎችም እየተማረርን ነው፡፡ የስብሰባው ጋጋታ ደግሞ አይጣል ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ሶደሬ ላይ ቀሚስ አያማረጠ አንሶላ ሲጋፈፍ የቢሮው ጸሐፊ ግን “ስብሰባ ላይ ናቸው!” እያለች ሕዝብን ታታልላለች፡፡ ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ የሚያስቸግር የዘመንና የትውልድ ኪሣራ ገጥሞን ግራ ተጋብተናል፡፡
በአማራ አካባቢ ተዘዋወሩ፡፡ ከጥቂት የሆቴልና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች በስተቀር እንደሌሎች ክልሎች በተለይም እንደ‹ኦሮሚያ›ና እንደ ትግራይ የመሰለ የተለዬ የልማት አውታር አታዩም፡፡ መንገድ የለም፡፡ ገበሬው በከፋ ድህነት ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ልጆቹ አይማሩም፤ ተማሩ ቢባልም አሥረኛና አሥራ ሁለተኛን ሳይቀር ዘለቁ ተብለው ፊደልን መለየት አይችሉም፡፡ ዕውር ዕውርን እየመራ ገደል በመግባት ላይ ነው፡፡ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች(mega projects) በአማራው አካባቢ ህልም ናቸው፡፡ አንድ የዚያው አካባቢም ይሁን የሌላ አካባቢ ተወላጅ በአማራው ክልል መራቆት ተቆርቁሮ በልማት ልሠማራ ቢል የመጨረሻ ዕጣ ፋንታው ዕድለኛ ከሆነ በሆነ ሰበብ ወህኒ ቤት ወርዶ እስከወዲያው መማቀቅ ወይም የባሰው ከመጣ “ሀንቲ ጥይት ሃቦ” የምትለዋን በጣም የምናውቃትንና የተለማመድናትን ስብሃት ነጋዊ ገጸ በረከት ሳይወድ የግዱን መሸለም ነው፡፡ ስንክሳራችን ብዙ ነው … ይሁንና ይህ ቀን ያልፋል ጎበዝ! ሲያልፍ ግን ለልጆቻችን ምንና እንዴት እንደምናወራቸው ነው የሚጨንቀኝ፡፡ በተደጋጋሚ እንዳልኩት በቅዠት የመኖር ያህል ነው የአሁኑ ኑሮ፡፡ የሚገርመው ደግሞ የመከራ ሌሊት በቶሎ እንዳለመንጋቱ የኛም የስቃይ ዘመን እጅግ መርዘሙ ነው – ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኢዮባዊ ቁስል መንፈር ለሰሚ ግራ የሆነ መርገምት ነው፡፡ የክርስቶስ ስቃይ እንኳን ከረቡዕ እስከ ዓርብ ነበር – ለሦስት ቀናት ብቻ፡፡ ለምን የኛን አረዘመብን ታዲያ? ራሳችንን እንጠይቅ፡፡
አማራ በግብርም በነቢብም እንዲጠፋ እየተደረገ ነው፡፡ ልማቱን ተውት፡፡ መንገዱን ተውት፡፡ የንጹሕ ውኃ አቅርቦቱን ተውት፡፡ ትምህርቱንም ተውት፡፡ የጤና ክብካቤውም እርሱት፤ እዬዬም ሲደላ ነውና፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው እንግዲህ አማራው በገዛ ቀየው በወያኔዎች እየተተካ የከተማዎች ዐይን ዐይን ቦታዎች ሁሉ ለምርጥ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች እየተሰጡ አማራው በሥነ ልቦናም በኅሊናም በአካልም በመንፈስም ቅስሙ እየተሰበረ ከመጠነኛ መኖር ወደለየለት አለመኖር እየተሸጋገረ መሆኑ ነው፡፡ ወኪሉ ነን የሚሉት አብዛኞቹ የብአዴን ሰዎች ደግሞ ሆዳቸው ከሞላ ለወገኖቻቸው የሚያስቡ አይመስሉም – የአጥንትና የደም ሥሪታቸው ከጅብ ይሁን ከዓሣማ ወይንም ከግዑዙ ድንጋይ ገና በውል አልታወቀም፡፡ ይህ ሁሉ ዐይን ያወጣ መድሎ ሲፈጸም ባይናቸው በብረቱ እያዩ የነሱ ከርስ ባለመጉደሉ ብቻ ለወያኔ እሽክርና ገብተው ወገናቸውን በወያኔ አጋዚ በማስጨረስ ላይ ይገኛሉ – “በሬ ካራጁ” እንዲሉ ነውና የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ጭዳነቱ ለነሱም አይቀርም፤ ትንግርተኛ ዘመን ነው በደፈናው፡፡ የሆነ ሆኖ እነሱም ዋጋቸውን ያገኛሉ – ሊያውም ከዋናዎቹ በባሰ፡፡ ያየሁትን ተናገርኩ፡፡ ኃጢኣቱ በኔ ነው፡፡
መቀሌ ፒያሳ ላይ “ሰውነት ክንዴ ወርቅ ቤት” ወይም “ደርበው ሞላልኝ ሥጋ ቤት” የሚል የንግድ ተቋም ካለ ጥሩ ነው፡፡ ወልዲያ ውስጥ መቻሬና ሙጋድ ላይና ደብረ ታቦር ፒያሳ ላይ ግን “ሐጎስ ተወልደ ወርቅ ቤት” እና “ኅሩይ ግደይ ሥጋ ቤት” የሚል ማስታወቂያ እንዳለ በዐይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ – በዚህም የማምነውን ነው የምላችሁ በጣም ተደስቻለሁ (የሰዎቹ ስምና የንግድ ዓይነቶቹ ላይ መጠነኛ መሻሻል እንደተደረገባቸው በትህትና እገልጻለሁ)፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር ግን ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን ያሰፈልግ ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ታዲያን “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ”ን አዘውትሮ የሚጠቀምባት ወያኔ የኔ ናቸው የሚላቸው ወገኖቻችን በየትም ሥፍራ ምርጥ ምርጡን እንዲይዙ የህግና የጸጥታ ሁነታዎችን ሲያመቻች ለሌሎች ግን የመጫወቻ ሜዳው ሰበርባራና የጠርሙስ ስብርባሪ የተደፋበት እንደሚያደርገው ሰማይና ምድር ሳይቀሩ በሚገባ ያውቃሉ፡፡
በአማራው አካባቢዎች መብራት ከሚመጣባቸው ጊዜያት ይልቅ የማይመጣባቸው ይበዛሉ፡፡ በዚህን ዘመን በተለይ አማራው እንደ ዜጋ አይታይም – በገዢው መደብ እንደቀንደኛ ጠላት ስለሚቆጠር በተገኘበት ሁሉ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ተፈርዶበታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ይቅርና እንደ አንድ መጻተኛ ርሁቅ ብዕሲ እንኳን በዚህች የጋራ ሀገሩ እንዲኖር አይፈቀድለትም፡፡ በገዛ አገሩ በስደት እንዲኖር፣ እየተሸማቀቀ እንዲኖር፣ ሀብት ሳያፈራ በድህት እየማቀቀ እንዲኖር፣ በማይምነት ጥቁር መጋረጃ ተሸብቦ በኤሎሄ እንዲቃትት የውጭና የውስጥ ጠላቶቹ ፈርደውበታል፡፡ ደግ ነው፡፡ ከመግፋት መገፋት፣ ከመግደል መሞት፣ ከማሳደድ መሳደድ የማታ ማታ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ ስለሆነም በተለይ በዚህ የመጨረሻ በሚመስል የመከራ ወፍዳ ዘመን፣ በዚህ ዘመነ መንሱት ለቃላት የሚከብድ ስቃይና እንግልት እየደረሰበት የሚገኘው አማራ እንኳንስ አሳዳጅ አልሆነ፣ እንኳንስ ዘር አጥፊ አልሆነ፣ እንኳንስ ዘር አጽጂ አልሆነ፡፡ እንኳስ የዲያብሎስ ቀኝ እጅ ሆኖ የእግዜርን ፍጡራን አለአበሳቸው ጨፍጫፊ አልሆነ፡፡ የተበዳዮች ወገን መሆን የሚያኮራ ቢሆን ኖሮ ለመንጠባረር የሚቀድመኝ ባልነበረ፡፡ ግን ግን ምድር ጊዜያዊ የስደት ቦታ መሆንዋን እረዳለሁና፣ ይህ ሁሉ ግርግርና ህንፍሽፍሽም አላፊ ጠፊና ይዋል ይደር እንጂ በሌላ ያማረ ነገር እንደሚተካም እገነዘባለሁና በማየው ሁሉ ብዙም አይሞቀኝም፤ አይበርደኝምም፡፡
ከፍ ሲል በጠቀስኩት የአማራው አካባቢ ሕዝቡ እንኳንስ መብራት ጠፋብኝ ብሎ እንደመብት ሊጠይቅ ይቅርና ፀሐይን በሰፌድ ቢጋርዱበት፣ የሚተነፍሰውን አየር በማራገቢያ ቢከሉበት ትንፍሽ አይልም፤ ሁሉንም ችግሩን ለሰጠው ሰጥቶ መልሱን እየተጠባበቀ ያለ ይመስላል – ያም መልስ ቢያንስ እኔን ጨምሮ ለጥቂት ዜጎች ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ጉራ አይደለም፤ ትምክህትም አይደለም፡፡ ይልቁናስ “የሚመካ ሁሉን ማድረግ በሚችል በሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይመካ፡፡” የሰው ኃይል ከልኩ አይዘልም፡፡ እስኪበቃን አየነው፡፡ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ይበልጥ ኃይለኛና አስፈሪ፣ ጨካኝና ልበደንዳና በኢትዮጵያ አልነበረም – እርግጥ ነው እስከ 1983ዓ.ም ድረስ! እርሱ እንኳን ላይመለስ አልፏል፡፡ ዕድሜም እኮ ወሳኝ ነው፡፡ የሚያረጀው ሰውና ሕይወት ያለው ፍጡር ብቻ አይደለም – ጀግንነትና ፍርሀትም ያረጃሉ፡፡ ጉብዝናና ውርዝትናም በጊዜያቸው ያልፋሉ፡፡ ዝናና ክብርም ጠውልገው ይከስማሉ፤ሞትም ራሱ አርጅቶ ይሞታል፤ ታዲያ የማያልፍ ነገር ምን አለ? ምንም! ሰላም ለኢትዮጵያ፡፡
“ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፉም፡፡”(ማቴ. 24፡ 35)
“ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፤
መልካም መሥራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት፣ ስለ መበለቲቱም ተሟገቱ።” (ትንቢተ ኢሣይያስ 1፡ 16-17)
Average Rating