www.maledatimes.com በሁዳዴ ጾም የአህያ ልኳንዳ! ክንፉ አሰፋ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በሁዳዴ ጾም የአህያ ልኳንዳ! ክንፉ አሰፋ

By   /   April 6, 2017  /   Comments Off on በሁዳዴ ጾም የአህያ ልኳንዳ! ክንፉ አሰፋ

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 17 Second

 

 

“ደሳለኝ” ተብሎ ስለሚጠራው አህያ፤ በወያኔ ሜድያ የተተረከልን ታሪክ መሳጭ ነው። እነሱ  ጫካ ውስጥ በነበሩበት ወቅት፣ አስገደ ገብረስላሴ በ45 ብር ገዝቶ ለወያኔ ማጓጓዣ ይሆን ዘንድ አበረከተ። ይህ  “ደሳለኝ”  የሚባለው አህያ ከባድ ጭነት እየተሸከመ ያገለግላቸው ነበር። በአንድ ወቅት በጦርነት ተሸነፉና ይዘውት የነነበረውን  ስፍራ  ለቅቀው ተበታተኑ። ከቀናት በኋላ አንዳንዶቹ ወደቀድሞ ምሽጋቸው ተመልሰው ለመምጣት እንኳን ሲቸገሩ ደሳለኝ ግን መንገዱን ሳይስት እዚያው ስፍራ ይጠብቃቸው ነበር።  በመጨረሻም የአህዮች አለቃ ተባለና  “ብፃይ” (ጓድ) የሚል የማዕርግ  ሹመትን አገኘ።

አሁን ደሳለኝ በህይወት የለም። ወያኔዎች ግን በበኩር ልጁ እየተጽናኑ እንደሆነ ይናገራሉ። አባቱ አብሮን ብዙ ተጉዟል ሲሉ፣ “ለልጁ” የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሹመት ሰጥተውታል።

ሃይለማርያም “ደሳለኝ” ይባላሉ።  ሹመት እንጂ ስልጣን የላቸውም።  “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው?” ሲባሉ ” ምንም!”  ብለው የተቀመጡ ሰው ከእንሳው በተሻለ እንዴት ሊያስቡ ይችላሉ?  ስልጣኑ ቢኖራቸው ኖሮ በኢትዮጵያ የአህያን እርድ ባልፈቀዱ ነበር። እምነታቸውም ይህንን ለማድረግ የሚከለክል ይመስለኛል።

የሚገርመው ግን ወያኔዎቹ ባለውለታቸው የሆነ ሁሉ ላይ ቢላ መሳላቸው ነው።  ባለውለታቸውን ያርዳሉ። ሊበሉትም ይችላሉ! ህወሃቶች ይሉኝታና ውለታ የሚባሉትን ነገሮች ጨርሰው አያውቋቸውም።…  ጀግና በመባል የተዘመረለት  ብጻይ ደሳለኝ፤ መሳርያ ተሸክሟል፣ በጦር አውድማ ውሏል፣ መንገድ መርቷል… ዛሬ ግን እንዲታረድ ፈርደውበታል። … ስንቱን አረዱ፣ ስንቱን አፈኑ፣ ስንቱ ባለውለታቸውን አሰቃዩ! …

አስደንጋጩ የአህያ ቄራ ዜና በምድራችን በታወጀ ማዕግስት፤ አንዱ ባለ ጊዜ አደባባይ ወጥቶ እንዲህ አለ።

“በሬ ከበላህ አህያ በምንም ነውር አይሆንም። ሳይንሳዊ ምክንያት የላችሁም። አገሪቱ ደግሞ በሃይማኖት ሕግ አትተዳደርም።  ቆሻሻ የሚበላ ሕዝብ ይዘን አህያ ለምን – ስትሉ አታፍሩም? እሱን በልተን ከረሃብ በወጣን በማን እድል! …”

የአህያ ቄራው የመከስት ጉዳይ አስደምሞን ሳያበቃ፣ ጭራሽ የአህያ ስጋ ብሉ እያሉን ነው ሰዎቹ።ከየትኛው ህብረተሰብ እንደወጡ፣ የትኛው ማህበረሰብ እንዳሳደጋቸው ከቶውን ሊገባን ባይችልም፤ ድፍረትና ንቀታቸው ግን አዲስ ነገር አይደለም።

ዛሬ፤  ግዜ ጥሎት የእነሱን ቆሻሻ እየበላ የሚኖረው ሕዝብ ላይ ጣቱን እያወጣ ሲናገር፤ ነገን ጨርሶ የረሳው ነው የሚመስለው። የቆመ የመሰለው እንደሚወድቅ፣…  እነሱ ጥለውት የወደቀ ወገን ሁሉ ነገ እንደሚነሳ ዘንግቷል።

ይህ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያለው ህዝብ ግን፤ ቅዱሳን መጽሃፍት(ሰኮናው ያልተሰነጠቀ እንስሳ በክርስትናም ሆነ በሙስሊም እምነት አይበላም።) የሚከለክለሉትን የአህያ ስጋ ከሚበላ፤ ቆሻሻውን ቢለቅም ይመርጣል።  እቤቱ ተወልዶ ያደገን እንስሳ አርዶ ከመብላት ይልቅ ሞቱን የሚመርጥ ሕዝብ እንደሆነ ወያኔዎች መቼም ሊገባቸው አይችልም። አንድ ሰው ይህ እንዲገባው ኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባር፣ ከፍ ሲል ደግሞ ስበዕና ሊኖረው ይገባል። እነሱ ደግሞ ለሁለቱም ያልታደሉ፤ በአስተሳሰባቸውም ለእርድ ከሚያቀርቡት አህያ ያልተሻሉ ናቸው። ስለዚህ አይገባቸውም። ሕዝቡን አናውቀውም ብሎን የለ አቦይ ስብሃት ነጋ። “እብድና ሰካራም የልቡን ነው የሚናገረው።” የሚለው አባባል አንዳንዴ ልክ ነው።

የአህያ ቄራ በደብረዘይት መከፈቱን ጉዳይ ስናወጋ የሰሙ አንዲት አዛውንት፤ በቁጣ ተናገሩን። “እረ እሱ ይቅር ይበላችሁ። ምን የሚሉት ቀልድ ነው የምታወሩት?   አሁን በዚህ  የአብይ/ሁዳዴ  ጾም  እንዲህ እየተባለ  ይቀለዳል?”  አሉ። ነገሩ ቀልድ መምሰሉ አይደንቅም። ለእኝህ ወይዘሮ ቀልድ የመሰለው ይህ መራራ ሃቅ እኛንም ያሳመነው የደብረዘይቱ የአህያ ቄራ ተከፍቶ አራጆቹ ቢላ መሳል ሲጀምሩ ነው።  መቼም የሁዳዴ ጾም ላይ ናቸውና ከዚህ በላይ ተናግሮ ስሜታቸውን የበለጠ መጉዳት አስፈላጊ ባይሆንም፤ እውነቱን ማወቅ ስለነበረባቸው ዜናውን አሰደመጥናቸው። ለደቂቃ ዝም ካሉ በኋላ ይህችን ቃል ተናገሩ። “እግዚዖ የፈጣሪ ቁጣ!”

ይህችንም የተናገሩት ባህር ማዶ ስላሉ ነው። ሃገር ቤት ቢሆኑ ኖሮ በዚህ ንግግራቸው በአሸባሪነት ወይንም ደግሞ በጸረ-ልማት ሊከሰሱ ይችሉ ይሆናል።

ባለ “ራዕዮቹ” እኝህን እናት “ወግ አጥባቂ” ይሏቸዋል። ግና እምነታቸውን፣  ወጉን፣ባህሉን እና ከሁሉም በላይ ፈጣሪያቸውን የሚያከብሩ መሆናቸውን የሚገነዘቡላቸው ከከርሳቸው በላይ ሊያስቡ የሚችሉ ሰዎች ብቻ ናቸው።  እንደ አጋሰስ ሳይሆን እንደ ሰው ቢያስቡማ ኖሮ ይህንን  ዜና ቢያንስ ከሁዳዴ ጾም ፍቺ በኋላ ይለቅቁት ነበር።

እንዲህ አይነት ነውር እና ርኩሰት መታየት ከጀመረ ቆየ። አንዳንዶቹን ነውሮች ሕዝብ እንደዋዛ እየለመዳቸው የመጣ ይመስላል። ግብረሰዶምን በጳጳሱ ቡራኬ ሲያስገቡ አይተናል፣  ጄሶ እና ሰጋቱራ በቴፍ እንጀራ ውስጥ እየደባላቁ የሚሸጡትም እነሱ ናቸው፤ ካንሰርና ሄፒታይተስ የሚያመጣ አደገኛ ንጥረ ነገር በበርበሬ ውስጥ እየጨመሩ ሕዝብን መፍጀታቸውን ሰሞኑን  ያጋለጠው የጀርመን መንግስት ነው።…

“አገሪቱ ደግሞ በሃይማኖት ሕግ አትተዳደርም።” ብሎናል። ይህ ሰው እዚህ ላይ እርግጥ ተናግሯል። ስለ ሃይማኖት የምናወራው ፈጣሪያቸውን የሚያከብሩ፤ ሃይማኖት ካላቸው ሰዎች ጋር እንጂ ከአረመኔዎች ጋር አይደለም።  እምነት ቢኖራቸውማ፤ በስነምግባር እሴቶቻችን ሃገሪቱን ያስተዳድሩ ነበር። የሃይማኖት ሕግ ማለት ሌላ ነገር አይደለም። ፈሪሃ-እግዚአብሄር ያለው ሰው ሁሉ የሚያደርገው ነገር ነው።   ሃገሪቱ በስነ-ምግባር በታነጹት እሴቶችዋ ሳይሆን ይልቁንም አንባገነኖቹ በፈቀዳቸው ግዜ በሚያወጡት አዋጅ ነው እየተዳደረች ያለችው።… ይህም ያልፋል፤ እስኪያልፍ ግን ያለፋል። ስመ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ደራሲ የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ክቋጠራቸው ማራኪ ስንኞች አንድዋን እዚህ ላይ ልዋስ፤

ማሽላና ስንዴ በአንድ አብረን ስንቆላ፣

እያረረ ሳቀ የባህር ማሽላ።

ከሰል የሚሆኑ ብዙ እንጨቶች ሳሉ፣

ዝግባ ለምን ይሆን ይቆረጥ የሚሉ።

 

ባሳለፍነው አመት አጋማሽ ላይ የቡርኪና ፋሶ መንግስት የአህያ ስጋ ኤክስፖርትን የሚከለክል ህግ ባጸደቀ ግዜ፤ ቻይና እጅግ ተቆጣች።  ያለ ምንም ልዩ ማደለብያ፣  የተፈጥሮ ሳር ብቻ እየበላ የሚያድገው የአፍሪካ አህያ ስጋ ፍላጎት በታላቋ ቻይና እየጨመረ በመጣ ግዜ ነው ቡርኪና ፋሶ አህያ እንዳይታረድ የከለከለችው።  ያም ሆኖ ቻይኖች እጅ ወደ መጠምዘዙ አልገቡም። የቡርኪና ፋሶ መንግስት ለሕዝቡ ሞራል ሲል የብዙ ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጣ ያውቃሉ። በብዙ ነገር መደለል ይሞክሩ ነበር።   ግን ሌላ የተሻለ አማራጭ አለ።  ከገዛ ዜጋው የሞራል እሴት ይልቅ፣  ለከርሳቸው እና ለኪሳቸው ብቻ የሚያስቡ ጉዶች በአፍሪካ ቀንድ ላይ አሉላቸው።   እናም ቻይኖቹ የማረጃ ካራቸውን ይዘው ወደኛ ብቅ አሉ። ወያኔም በአንድ ሳይሆን በሁለት እጆቹ ጨብጦ ተቀበላቸው።  ባህያ የተጀመረው የእርድ ዘመቻ ወደ ውሻና ድመትም በቅርቡ  እንደሚዛመት መገመት አያዳትም።

በኢ-ሰብአዊነት ላይ የተሰማሩ የውጭ “ኢንቨስተሮች” ከሌላ ሃገር በተለያየ ምክንያት ሲባረሩ ኢትዮጵያ የመጨረሻ አማራጫቸው ሆናለች።  እንደ ባጣ ቆይህ ወደ ሀገራችን ሲሮጡ  ይህ የአህያ እርድ የመጀመርያው አይደለም።   የሆላንድ የምርመራ ጋዜጠኞች በሀገሪቱ ብሄራው  ቴሌቭዥን ባለፈው አመት ያቀረቡትን ዘጋቢ ፊልም ብቻ መጥቀሱ ጉዳዩን በደንብ ያስረዳዋል።

ሼር የተባለው የአበባ አምራች ኩባንያ ከኬንያ እንደተባረረ፤ ጓዝና መርዙን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ አለ። ዶላሩን ብቻ ያዩ የኛዎቹ ጉዶች አይናቸውን ሳያሹ ነበር የተቀበሉት። ይኸው ኩባንያ የአበባ እርሻ በኬንያ ጀምሮ ከባቢውን በመበከሉ እና የሃገሪቱን ውሃ ሃብት በማምከኑ መባረሩን ያውቃሉ። ለወያኔ ከዚህ ሁሉ ዶላር ይበልጣል።

የሆላንድ ጋዜጠኞች ያቀረቡት የምርመራ ዘገባ እጅግ ዘግናኝ ነበር።  አንዲት ጽጌሬዳ ለማምረት በአማካኝ 7 ሊትር ውሃ ይፈጃል። የአካባቢው ሕዝብ  ግን አንዲት ሊትር ውሃ በቀን ለማግኘት በሚቸገርበት አካባቢ ነው።  የአበባ አምራቹ በቀን ከ 3 እስከ 4 ሚሊዮን እግር ጽጌሬዳ ያመርታል። መሬቱ ዳግም ሌላ ነገር አያበቅልም።  ከዝዋይ ሃይቅ ውስጥ የሚገባው መርዝ ደግሞ አሳ ተመጋቢ ዜጎች ልጅ እንዳይወልዱ መካን  ያደርጋቸዋል።  የህክምና ባለሙያዎች እንዳጋለጡት ከሆነ ደግሞ መርዙ በዜጎች ላይ ከዚህ በፊት ተከስተው የማይታወቁ በሽታዎችን (ምናልባት ካንሰር)  እንዳስከተለ አልሸሸጉም።…

ለሆዱ እንጂ ለዜጋው ግድ የሌለው ቡድን በህዝቡ አናት ላይ መቀመጡን ነጮቹም ያውቃሉ።

ሕዝብ የአህያ ስጋ እንዲበላ ያሳሰበው ካድሬ የኦሪት ህግ ከሙሴ ጋር እንደተቀበረ ይነግረናል። የፈጣሪ ህግ ዘላለማዊ ነው። እነሱ እንደሚሉት የሚሻር፣ የሚቀየር ወይንም የሚቀበር አይደለም። ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ህግን ሊሽር ሳይሆን ሊፈጽም እንደመጣ አስተምሯል። የሙሴ ህግ አልተሻረም። ህወሃት ሽሮት ከሆነ ግን አናውቅም።  ሙሴ ከፈጣሪ ያገኘውን ቀል ነው ህግ ያደረገው።

አህያ  ለአገልግሎት እንጂ ለምግብነት አልተፈጠረም።  ፈርሃ እግዚአብሄር ያለው ህዝብ ደግሞ አህያ አያርድም። አህያም አይበላም። አህያን ጅብ ብቻ ሲበላው ነው የምናውቀው።

ከህብረተሰቡ ሞራል ይልቅ ዶላሩ ቢበልጥባቸው እንኳን የአህያ ቄራ ከመገንባት፣ አህያውን በቁሙ ወደ ቻይና መላኩ የተሻለ አማራጭ ነበር። የአህያ ጭንቅላት እንኳን ባነሰ የሚያስቡ ሰዎች ስልጣን ላይ እስከተቀመጡ ድረስ ከዚህ የባሰ ነገርም ሊመጣ እንደሚችል መገመት አይከብድም።  እነዚህ ሰዎች ለዘለዓለሙ የምኒሊክ ቤተ መንግስት ውስጥ እንደማይኖሩ እርግጥ ነው። የማይለወጥ ነገር የለም። ትእቢት የውድቀት ምልክት ናት። እነሱም አንድ ቀን ይወድቃሉ። ግን ይህንን ሁሉ ግፍ፣ ይህንን ሁሉ ንቀት፤ ይህንን ሁሉ ወንጀል ተሸክመው የትኛው ምድር ይቀበላቸው ይሆን?

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on April 6, 2017
  • By:
  • Last Modified: April 6, 2017 @ 9:44 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar