ዳዊት ከበደ ወየሳ
ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ
የኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ ሲነሳ፤ በግንባር ቀደም ከሚጠቀሱት መካከል ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በዋናነት ይጠቀሳሉ። – በአባታቸው ኦሮሞ፣ በናታቸው የጉራጌ ተወላጅ የሆኑት ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ) በተለይ በ1888 ዓ.ም. በአድዋ ጦርነት ወቅት በአጼ ምኒልክ ስር ሆነው በመድፍ አስተኳሽነት በሰሩት ጀግንነት ይታወሳሉ። እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያ ለአገራቸው እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያደረጉት ታላቅ ጀብዱ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል። ስለስራቸውም ክብር ታላላቅ ቦታዎች በስማቸው ተሰይመዋል። ከነዚህም መካከል በሩስያውያን እርዳታ የተገነባው ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል፣ ደጃዝማች ባልቻ መንገድ፣ ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። ጀግኖች ሲፈክሩና ሲያቅራሩ ስማቸውን እየጠሩ… “ዘራፍ የባልቻ አሽከር!” ብለውላቸዋል። በስማቸው መጽሃፍት ተጽፈዋል። ድምጻውያን አንጎራጉረውላቸዋል።
አሁን ወሊሶ በሚባለው ቦታ፣ በነሃሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት፣ በ1854 ዓ.ም. ነበር የተወለዱት። እናም ይህ ሳምንት የልደት ቀናቸው የሚከበርብ ሳምንት ስለሆነ፤ ወደ ኋላ ተመልሰን ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶን እናስታውሳቸዋለን።
የትውልድ ዘር ሃረጋቸው ጉዳይ ብዙ ጊዜ አነጋጋሪ ስለሆነ፤ እዚህ ላይ መልስ ሰጥተንበት እናልፋለን። ባልቻ ሳፎ በአባታቸው የኦሮሞ ተወላጅ ሆነው የሮቢ የልጅ ልጅ ሲሆኑ፤ በናታቸው በኩል ደግሞ ጉራጌ የጭረት ከንፈሴን ናቸው። እኚህ ታላቅ ጀግና ገና በልጅነት እድሜያቸው በጦር ሜዳ ውስጥ የተገኙ ሰው ነበሩ። ነገሩ እንዲህ ነው። በድሮ ጊዜ ጦርነት ሲደረግ፤ አሸናፊው ወገን የተሸናፊውን ብልት መስለብ እንደጀግንነት ይቆጠራል። ምንም እንኳን ምኒልክ እንዲህ አይነቱን እርምጃ የሚደግፉት ባይሆንም፤ ከአቅማቸው በላይ በሆነ ሁኔታ ወታደሩ በጦርነቱ ወቅት ያገኛቸውን ወንዶች፤ የሚገደሉትን ገድለው በህይወት የተረፉትን መስለባቸው የተለመደ የጦርነት ባህል ሆኖ ቆይቷል። በዚህም ጦርነት ወቅት በታዳጊው ወጣት ባልቻ ላይ የደረሰበት ይህ አስከፊ ቅጣት ነበር።
በጦርነቱ የምኒልክ ሰራዊት ማሸነፉ ሲበሰር፤ ስለሞቱት እና ስለተማረኩት ሰዎችም ተነገራቸው። ከነዚህ ምርኮኞች መካከልም ብልቱን ተቆርጦ የተገኘ ብላቴና መኖሩ ሲነገራችው ምኒልክ እጅግ አድርገው አዘኑ። ከነዚያ ሁሉ ምርኮኞችም መካከል ይህንን ልጅ ወደሳቸው እንዲያቀርቡ አደረጉ። ብዙዎቹ ምርኮኞች በምህረት ሲፈቱ፤ ባልቻ አባ ነፍሶን ግን ምኒልክ ሊያሳድጉ ሃላፊነት ወስደው ወደ አዲስ አበባ ይዘውት መጡ። በዚህ አይነት ሁኔታ… ባልቻ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በምኒልክ ቤተ መንግስት የአጼ ምኒልክ የቅርብ አንጋች ሆኖ፤ በጦር ሞያ ተኮትኩቶ አደገ። በጎልማሳነቱም ወቅት የመድፍ ተኩስ ተምሮ… አጼ ምኒልክ ከፈረንሳይ አገር የተሰጣቸውን መድፎች የሚተኩስ እና የሚያስተኩስ ጎበዝ ጀግና ወጣው።
(ባልቻ የሚለው የኦርምኛ ስማቸው ትርጉም “ምትክ” ማለት መሆኑን እዚህ ጋር ጠቅሰን ብናልፈውስ)
በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉት ጦርነቶችም፤ መድፉን ወደ ጠላት ወረዳ ተኩሶ… ጠላትን የሚያርበደብድ ጀግና ሆነ። በተለይም ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር ባደረገችው የ1888 ዓ.ም. ጦርነት ወቅት፤ በመቀሌ፣ በአዲግራት እና በአድዋ ተራሮች መድፉን ጠምዶ፤ የጣልያንን ጦር ከርቀት በመምታት ዝናን ያተረፈ ጎበዝ ተሰኘ። በማዕረግ ላይ ሌላ ማዕረግ ተጨምሮለት… ደጃዝማች ተብሎ ስማችው በወርቅ ቀለም ከተጻፈላቸው ጀግኖች መካከል አንዱ ሆኖ ተጠራ። ከጦርነት እና ከጀግንነት ውጪ ሌላ ህይወት ለሌላቸው ለነደጃች ባልቻ አይነቶቹ ጀግኖች እንዲህ ተባለላቸው።
ለበኑም፥ መውዜሩም፥ መድፉም፥ መትረየሱም፥ አንድ ነው ብረቱ፤
ቈራጥ ያስፈልጋል ክትት ያለ ዐሞቱ።
————————————————
ጦር መጣ፤ ጦር መጣ፤ ጫፉን ነቀነቀው፤
ጐበዝን ደስ አለው፤ ፈሪንም ጨነቀው።” ተብሎላቸዋል— የዘመኑ ጀግኖች።
ሊቀመኳስ አባተና ባልቻ አባ ነፍሶ በመድፍ ስላደረጉት ፍልሚያ ቤርክሌይ ሲጽፍ፤ “ጣሊያኖች እንዳስላሴ ወጥተው ‘የእየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ልቀቁ፤ ጦርነቱ ሲያልቅ በትልቅ ህንጻ እንሰራላችኋለን።’ አሏቸውና አንድ ሺህ ብር ሰጧቸው። ሁሉም ቤተክርስቲያኑን ሲልለቁ አንድ የሃምሳ አመት ቄስ ግን እምቢ አሉና ወዲያውኑ ተገደሉ። ከዚያም ቤተ ክርስቲያኑንና ቦታውን ጣልያኖች ተቆጣጠሩት። ሆኖም ክርስቲያን የሆኑ የጣሊያን ወታደሮች ‘ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን አንዋጋም’ በማለታቸው ክርስቲያን ያልሆኑ ወታደሮች እዚያ ገብተው ጦርነቱ ቀጠለ… ያ ቀን መጥፎ እለት ነበር። በጣሊያኖቹ ወገን ከእንዳስላሴ የሚተኮሰው መድፍ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ጨረሰ። በኢትዮጵያ በኩል የተተኮሰው የመድፍ ጥይት፤ የጣሊያኑ መድፍ አፍ ውስጥ ገብቶ ሁለት ወታደሮች አቆሰለ… እሳትም ተነስቶ አፈር የተሞሉ የምሽግ ጆንያዎች ተቃጠሉ።” ብሏል።
በነገርዎ ላይ አሁን አሁን በዘፈን፤ “ባልቻ አባ ነፍሶ መድፉን ጣለው ተኩሶ” ቢባልም፤ በትክክል መድፍን በመድፍ ተኩሶ የጣለው ግን ያኔ 25 አመት ወጣት መድፈኛ የነበረው አባተ ቧያለው (አባ ይትረፍ) ነበር። በዚያን ጊዜ ነው፤
“አባተ አባ ይትረፍ፣ ነገረኛ ነው፤
ይህን መድፍ፣ ከዚያ መድፍ፣ አቆራረጠው።” ተብሎ የተገጠመው።
(ደጃች ባልቻ በወቅቱ የ36 አመት ጎልማሳና የሊቀ መኳስ አባተ አዛዥ ነበሩ)
የካቲት 23 ቀን፣ 1888 ዓ.ም. የአድዋ ጦርነት እለት…. የጦሩ ዋና ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው በጦርነቱ ላይ ሲሰዉ አጼ ምኒልክን ጨምሮ ብዙዎች አዘኑ። በዚህን ጊዜ ምኒልክንም ሆነ ህዝቡን ለማጽናናት፤ “ገበየሁ ቢሞትም ባልቻ አለልዎ” ለማለት ጭምር እንዲህ ተባለ።
ገበይሁ ቢሞት፣ ተተካ ባልቻ፤
መድፍ አገላባጭ፣ ብቻ ለብቻ። ተብሎ ተፈከረ።
እንግዲህ የደጃዝማች ባልቻ የጀግንነት ታሪክ በተለይ ከአድዋ ድል በኋላ እየገነነ መጥቶ የመድፈኛ ክፍል ሃላፊ ከመሆን ጀምሮ፤ በኋላም በአጼ ምኒልክ ዘመን የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲቋቋም፤ የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ሆነው ዛሬ ከበቅሎ ቤት በታች ይገኝ ከነበረው ስፍራ ላይ፤ የኢትዮጵያን ጦር መሳሪያ በአይነት ባይነት ማቀመጥ መጀመራቸው ይታወቃል።
(የጦር ግምጃ ቤቱ ከምኒልክ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የነበሩ መድፍ እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን እንደያዘ፤ ግንቦት 27፣ 1983 ዓ.ም. መቃጠሉ ይታወሳል – የበቅሎ ቤቱ ፍንዳታ መሆኑ ነው)
እዚህ ላይ አንድ ሌላ ታሪክ እንጨምርልዎ። የደጃች ባልቻ ታሪክ ሲነሳ ይህ ታሪክ ሁሌ ይነሳልና… ይህን ፈገግ የሚያሰኝ ገጠመኝ ሳንነግራችሁ እንዳንቀር በሚል እነሆ አቅርበነዋል። ታሪኩ እንዲህ ነው።
ቀደም ብለን እንደገለጽነው…. ባልቻ አባ ነፍሶ በልጅነታቸው ብልታቸውን ጦር ሜዳ ላይ ስላጡ፤ ውስጥ ውስጡን ሚስጥሩ መወራቱ አልቀረም። ደግሞም መሞት የፈለገ ካልሆነ በቀር፤ ማንም ደፍሮ ይህን ጉዳይ እሳቸው ፊት አያነሳም። አንድ ቀን የሚነሳበት አጋጣሚ ሊፈጠር ሆነ።
አዎ ከእለታት በአንዱ ቀን አጼ ምኒልክ…. ደጃዝማች ባልቻን ምርጥ የሆነ ጎራዴ ሸለሟቸው። የቤተ መንግስት ሰዎችም ጎራዴውን አደነቁላቸው። አንዳንድ ጓደኞቻቸው ግን፤ “ይህንን የጎራዴ ስጦታ የማያደንቀው አለቃ ገብረ ሃና ብቻ ነው።” አሏቸው። ባልቻ አባ ነፍሶም “ጃንሆይ የሰጡኝን ጎራዴ እንዴት ነው የማያደንቀው?” ብለው ተቆጡ። አለቃ ገብረሃና እቤታቸው ድረስ እንዲመጡ አደረጉና… ከጋበዟቸው በኋላ፤ “ሰው ሁሉ የምኒልክን ስጦታ ሲያደንቅ አንተ የማታደንቀው ለምንድነው?” አሏቸው።
አለቃ ገብረሃናም “የታለ ስጦታው?” ይላሉ።
ደጃች ባልቻም ጎራዴውን መዘው ለአለቃ ገብረሃና ሰጧቸው። በአሽሙር ንግግራቸው የሚታወቁት አለቃ ገብረሃናም ጎራዴውን ተቀብለው አገላብጠው ካዩ በኋላ፤ “አይ ጎራዴ! አይ ጎራዴ! ጥሩ ጎራዴ!” ካሉ በኋላ ጎራዴውን መለሱላቸው። ደጃች ባልቻም በአለቃ ገብረሃና ንግግር ተደስተው ተለያዩ።
በኋላ ላይ የደጃዝማች ወዳጆች፤ “አለቃ ገብሃና ምናለ?” ይሏቸዋል።
ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶም «በደንብ ነው ያደነቀው» ብለው ይመልሳሉ፡፡
«እስኪ ምናለ?» ይላሉ ወግ ፈላጊዎቹ፡፡
«አይ ጎራዴ፣ አይ ጎራዴ ብሎ አደነቀ» ይሏቸዋል፡፡
ያ ሁሉ ሰው በሳቅ ያወካና «እንዴ ደጃዝማች ባልቻ … በቅኔ እርስዎን እኮ ነው የተናገረው» ብለው …አለቃ… ‘ጎራዴ’ ያሉት ደጃዝማቹን መሆኑን ያስረዷቸዋል፡፡ ያን ጊዜ ጀግናው ደጃች ባልቻ፤ አለቃ ገብረሃናን እገላለሁ ብለው ተነሱ። የአገር ሽማግሌዎችም በስንት አማላጅ እና ልመና “በመጀመሪያ ደረጃ አለቃን ቤትዎ ድረስ የጠሩት እርስዎ ነዎት። አሁን የናንተ መጣላት ወሬውን ላልሰማ ማሰማት ነው” ብለዋቸው፤ ደጃች ባልቻም የሽማግሌዎቹን ምክር ሰምተው አለቃ ገብረሃናን እንደሸሹ ኖሩ ይባላል። ለነገሩ ደጃች ባልቻ በኋለኛው ህይወታቸው ዘመን፤ ከነገር እና ከርስ በርስ ጸብ ሲርቁ እንደኖሩ ቀጣዩ የህይወታቸው ታሪክ ያመለክታል።
በእድሜ እና በእውቀት መጎልበት ሲመጣ… በመጀመሪያ ሲዳሞን እንዲያስተዳድሩ ተደረገ። በኋላም የራስ መኮንን የመጀመሪያ ልጅ ደጃች ይልማ ሲሞቱ፤ የሃረር ገዢ ሆነው ሐረርጌን እንዲያስተዳድሩ… በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾሙ። ተፈሪም ከሲዳሞ ማዶ ያለውን የጊሚራ መሬት እንዲያስተዳድር፤ በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾመ። በእርግጥ ልጅ እያሱ ይህንን ያደረጉት ገና ከመጀመሪያው በተፈሪ እና በባልቻ መካከል ቅሬታን በመፍጠር፤ ሁለቱን ትላልቅ ሃይሎች ከፋፍለው መግዛት እንዲችሉ ነበር።
እናም ደጃች ባልቻ አባ ነፍሶ ሐረርጌን ለአራት አመታት ሲያስተዳድሩ፤ ተፈሪ ደግሞ፤ “የአባቴ አገር ሐረርጌን ላስተዳድር?” የሚል ጥያቄ ለእቴጌ ጣይቱ እያቀረቡ፤ ወደተሾሙበት ደቡብ ኢትዮጵያ ሳይሄዱ አዲስ አበባ ላይ ከረሙ። በርግጥም… ሐረርጌ ሊሰጥ የሚገባው ለሌላኛው የራስ መኮንን ልጅ፤ ለደጃች ተፈሪ መሆን ሲገባው ለባልቻ አባ ነፍሶ መሰጠቱ፤ በኋላ ራስ ተፈሪ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በሆኑት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መካከል ቅሬታን ፈጠረ።
በስተበኋላም ላይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንጉሠ ነገሥትነቱን ዙፋን ሲይዙ፤ ባልቻ አባ ነፍሶን ከቀድሞ የአገር አስተዳዳሪነት ሹመት አነሷቸውና ደጃች ብሩ ወልደገብርኤልን ሾሟቸው። ይህም ሆኖ ግን ባልቻ አባ ነፍሶ በወቅቱ በነበሩት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንደተከበሩ፤ በዘመዶቻቸው አገር ተቀመጡ። ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ባልቻ ከነ ሙሉ ክብራቸው፤ በአካባቢው ህዝብ እንደተወደዱ፤ ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ጋር ወደ ሌላ ጸብ ሳይገቡ፤ ከነልዩነታቸው በሰላም ተለያይተው መኖር ጀመሩ። ቀዳማዊ ኃይለስላሴም አገር እያስተዳደሩ፤ ደጃች ባልቻም የተጣላ እያስታረቁ፤ እስከ ሁለተኛው የጣልያን ወረራ 1928 ዓ.ም. ድረስ ዘለቁ።
ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲወር፤ ከአጼ ምኒልክ ጋር ሆነው በጀግንነት የተዋጉት፤ አሉላ አባ ነጋ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ራስ አባተ እና ሌሎችም ጀግኖች በእርጅና አንድ በአንድ ሞተው አልቀው ነበር። ከዚያን ዘመን ጀግኖች መካከል የቀሩት… አንድ ሰው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ብቻ ነበሩ። እሳቸውም ቢሆን አርጅተዋል። በዚያ ላይ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጋር በነበራቸው ጸብ ምክንያት ንጉሠ ንገሥቱ ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ጄኔቭ ሲሄዱ፤ ደጃች ባልቻ ከጣልያን ጎን ሊሰለፉ እንደሚችሉ የጣልያኖች ግምት ነበር። ደጃች ባልቻ ግን በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ላይ ቅሬታ ቢኖርባቸውም፤ በአገር ጉዳይ ሌላ ድርድር ውስጥ መግባት አልፈለጉም። ስለሆነም ጦራቸውን ማሰባሰብ ጀመሩ። እናም ከነደጃች ኃይለማርያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ እና አቡነ ጴጥሮስ ጋር የሚስጥር ደብዳቤ መለዋወጣቸውን ቀጠሉበት።
በወቅቱ አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ በጣልያን አገዛዝ ስር ወድቃለች። ንጉሠ ነገሥቱም በአገር የሉም። በማይቸው ጦርነት ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን በጣልያን አውሮፕላን፤ በአየር በሚጣል ቦንብ እና የመርዝ ጢስ አልቀዋል። ከዚያ የተረፉት ግን እጃቸውን ለመስጠት አልፈለጉም። ጣልያን የከተመበት አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ለመፋለም ወሰኑ። በእቅዳቸውም መሰረት የራስ ካሳ ልጆች ከፍቼ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ፤ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞም ጦሩን ይዞ ከነ አቡነ ጴጥሮስ ጋር ሆኖ አዲስ አበባ እንዲገባ፤ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶም አምስት ሺህ ያህል ጦራቸውን ይዘው በአዲስ አበባ ደቡብ በኩል በእኩል ቀን ገብተው የጣልያንን ጦር ለመምታት ተዘጋጁ። ደጃች ባልቻ ጦራቸውን አምጥተው አሁን “አየር ጤና” ከሚባለው ሰፈር ማዶ ካለው ረጲ ጋራ ላይ መሸጉ።
ይህን ታሪክ ለማሳጠር ያክል የሆነውን በአጭሩ እንዲህ ልግለጸው። …የራስ ካሳ ልጆች አዲስ አበባ ሳይገቡ ሶስቱም ተገደሉ። ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ አዲስ አበባ ዘልቀው፤ አሁን እንግሊዝ ኢምባሲ ያለበትን አካባቢ አልፈው እስከ ቀበና ድረስ ዘልቀው፤ ብዙ ወታደሮቻቸው አልቀው እሳቸው ተሰዉ። አቡነ ጴጥሮስ በጣልያኖች ተይዘው ታሰሩ (በርግጥ በኋላ ላይ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ)… ደጃዝማች ባልቻ ከትውልድ መንደራቸው… ከአገምጃ ሶዶ ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ። ከዚያም ረጲ ጋራ ላይ ሆነው፤ መድፋቸውን ጠምደው የሌሎቹን አርበኞች ሁኔታ እና መልዕክት መጠባበቅ ጀመሩ። ሁኔታውን ለመሰለል ለሊቱን ወደ አዲስ አበባ የላኳቸው ወታደሮቻቸው፤ ጣልያኖቹ ጋር ሳይደርሱ በባንዳዎች ተይዘው ተገደሉባቸው። ሲነጋ ጣልያን በአውሮፕላን ሆኖ፤ የደጃች ባልቻን ጦር እየተከተለ በጣም ብዙ ሰው ፈጀባቸው። በህይወት ዘመናቸው ጣልያንን ሁለት ጊዜ የተዋጉትና ብዙ ሺህ ተከታይ የነበራቸው ባልቻ አባ ነፍሶ ብቻቸውን ቀሩ። በመጨረሻ ጥቂት ወታደሮቻቸውን ይዘው ወደ ኋላ አፈገፈጉ።
የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ታሪክ በጣልያኖች ዘንድ ሲወራ ብዙዎችን አስገረመ። የጣልያን ጋዜጦች… “በአድዋ ጦርነት ወቅት ከምኒልክ ጋር ሆኖ ከተዋጉት ሰዎች መካከል ባልቻ አባ ነፍሶ የሚባል የ75 አመት ሽማግሌ ሰው አሁን በህይወት አለ። በደቡብ በኩል ጦር እያደራጀ ነው።” ተብሎ እየተጋነነ ሲወራ፤ የጣልያን መንግስት፤ “ይህን ሰው እንፋረደዋለን። ከነህይወቱ ይዛቹህ እንድታመጡት።” የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈ።
በነገርዎ ላይ ደጃች ባልቻ ሁለት ወንድሞች ነበሯቸው። አንደኛው ፊታውራሪ ሳህለሚካኤል ነው። በአድዋ ጦርነት ላይ ተሰውቷል፤ 2ኛውን ፊታውራሪ ገብረመድህንን ደግሞ በሰገሌ ጦርነት ወቅት በጦር ሜዳ ህይወቱ አልፏል። እናም በወቅቱ ብቻቸውን የነበሩት ደጃች ባልቻ….
“ጦር መጣ ይላሉ፤ እኔ ምን ቸገረኝ፤
እናቴም ልጅ የላት፤ ለኔም ወንድም የለኝ።” አሉ ይባላል።
ከዚህ በኋላ የሆነውን እኛ ከምንተርከው ይልቅ፤ በወቅቱ በአርበኝነት ጫካ ገብተው ሲዋጉ ከነበሩት መካከል ሻለቃ መስፍን ስለሺ የጻፉትን ደብዳቤ እናካፍላቹህ። ሻለቃ መስፍን ስለሺ ደብዳቤውን የጻፉት እንግሊዝ አገር ለነበሩት ለቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ነበር።
“…የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወድሚኖሩበት እስከ ጉራጌ አገር ድረስ በመዝለቅ በሳቸው ላይ ዘመተባቸው። ህዝቡ ከዳቸው፤ ወታደሮቻቸውም ለህይወታቸው ሲሉ ሸሹ። እሳቸው ደጃች ባልቻ እና ሁለት አሽከሮቻቸው፤ ከሳቸው ጋር ሶስት ሰዎች ብቻ ቀሩ። ያ ሁሉ የጣልያን ጦር ከበባቸው። ወዴትም መሄድ አልቻሉም። በመጨረሻም አንድ ነጭ ፈረንጅ ወደጃች ባልቻ ዘንድ መጣ። ከዚያም… “ደጃዝማች ባልቻ ማለት አንተ ነህ?” አላቸው።
ደጃዝማቹም “አዎ እኔ ነኝ!” ሲሉ፤ ፈረንጁ “በሉ ይማረኩ። ሽጉጥዎትንም ያስረክቡኝ።” አላቸው።
ደጃዝማች ባልቻም፤ “እኔ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም። ትጥቄንም አልሰጥህም!” ብለው ሽጉጣቸውን አውጥተው፤ ነጩን የጣልያን ጦር መኮንን ገደሉት። ከዚያም በራሳቸው ሽጉጥ የራሳቸውን ህይወት አጠፉ። ከደጃዝማች ባልቻ ጋር አብረው የነበሩትም ወታደሮች ስቃይ ሳይበዛባቸው በየተራ ወደቁ።” በማለት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ገልጿል።
እናም የጣልያን ጦር በቾ አበቤ ድረስ ዘምቶ ከደጃች ባልቻ አባ ነፍሶ ጋር ተዋግቶ፤ ሳያሸንፍ ተሸነፈ። እጃቸውን ይዞ ሊወስዳቸው ቀርቶ፤ ህይወታቸውን እንኳን ሳያጠፋው በራሳቸው ጥይት ራሳቸውን ሰዉ – ጥቅምት 27፣ 1929 ዓ.ም.።
በሁለተኛው የጣልያን ጦርነት ወቅት ብቻቸውን መሆናቸውን የተመለከተ አዝማሪ….
የባልቻ ወንድሞች ጥይቶቹ ናቸው፤
እዚህ ተቀምጦ፣ እዚያ የሚልካቸው፡” ብሎ ገጥሞላቸው ነበር።
በነገርዎ ላይ ደጃች ባልቻ በሞቱ በ11ኛው አመት፤ አሁን ከልደታ ማዶ የሚገኘውና በስማቸው የተገነባው ዘመናዊ ሆስፒታል በጥቅምት ወር መጨረሻ 1940 ዓ.ም. ተመርቆ ተከፈተ። ሆስፒታሉ በመጪው ጥቅምት ወር 45 አመት ይሞላዋል። (በዚያው አጋጣሚ ደጃች ባልቻን ቢያስቧቸው መልካም ነበር)
የታሪክ ወጋችንን ልናጠናቅቅ ነው።
በአምስቱ አመት የአርበኞች ትግል ወቅት… አንበሳው የኢትዮጵያ ጦር ተመልሶ አገሩን እንደሚያስተዳድር የታወቀ ነበር። አርበኞችም እንዲህ እያሉ ይፎክሩ ነበር።
“ባንበሳው መኝታ፣ ጅቡ ተኝቶበት፥
ብንን ብንን ይላል፣ በ’ልሙ እየመጣበት።”
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1933 ዓ.ም. በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ፤ የሞቱትን የኢትዮጵያ ጀግኖች አሰቧቸው። ለሰማዕታቱ መታሰቢያ ሃውልት ቆመ። አቡነ ጴጥሮስ ከተገደሉበት ስፍራ ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ሃውልት በስማቸው ተቀርጾ ቆመላቸው (አሁን ለጊዜው ተነስቷል)። ለደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶም በስማቸው በተወለዱበት ወሊሶ፤ ባደጉበት አዲስ አበባ በስማቸው ትምህርት ቤቶች ተከፈቱላቸው፤ መንገድ ተሰየመላቸው፤ ሆስፒታልም ተሰራ። በነዚህ ጊዜያት በሙሉ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በስፍራው እየተገኙ መንገዱን መርቀዋል፤ ሆስፒታሉ ሲከፈትም ንግግር አድርገዋል። ይህ ብቻ አይደለም። ባልቻ አባ ነፍሶ በተወለዱበት ስፍራ ጭምር ሃውልት ተሰርቶላቸዋል።
ባልቻ አባ ነፍሶ በአካል ጉድለት ምክንያት፤ ልጅ ወልደው ዘራቸውን ባይተኩም፤ የጀግናን ውለታ የማይረሳው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ልጅ ሆኗቸዋል። አጼ ምኒልክ “ከትልቅ መወለድ ሳይሆን፤ ራስን ከትልቅ ነገር መውለድ ሞያ ነው” እንዳሉት፤ ደጃች ባልቻ ከትልቅ ስለተገኙ ሳይሆን፤ ትልቅ ስራ ስለሰሩ… በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በስማቸው መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት ከተሰራላቸው ሌሎች ጀግኖች ይልቅ ብዙ የተባለላቸው – ባልቻ አባ ነፍሶ ናቸው።
ታሪክ በመሰንቆ (3)
ባልቻ ፈረሱ ነፍሶ
መድፉን ጣለው ተኩሶ
ባልቻ ሆሆ !
ባልቻ ሆሆ?
ባልቻ አባ ነፍሶን በታሪክ ውስጥ ስመጥር ያደረገው አድዋ ላይ የፈፀመው ጅብድ ብቻ አይደለም። ምን የመሰለ ጀብድ ሰርተው ፣እንዳዘቦት ቀን የተረሱ ጀግኖች ሞልተዋል። የወሎየው አዝማሪ፣ የሀሰን አማኑ መሰንቆ፣ ለባልቻ ሳፎ ህያውነት ትልቅ ድርሻ አለው።
“ገበየሁ ቢሞት ፣ ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ፣ብቻ ለብቻ
አሻግሮ ገዳይ፣ዲብ አንተርሶ
የዳኘው አሽከር ፣ባልቻ አባ ነፍሶ”
ብሎ የዘፈነው ሀሰን አማኑ፣ባራት መስመሮች ከባልቻ ጋር እንዳንፋታ አድርጎ ያቆራኘን ይመስለኛል።
ባልቻ የድል ሰንደቅ ለሚያውለበልቡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ፋና ወጊ ነው። ፀሀፌ ትዛዝ ገብረስላሴ በመቀለ ድል መባቻ የተደረገውን ሲፅፉ” በጅሮንድ ባልቻ መቀሌ እርዱ ውስጥ ገብቶ የኢትዮጵያን ባንዲራ ተከለበት “ይላሉ። በዚህ አጋጣሚ ፣ ያን ግዜ የነበረው ባንዲራ ፣ ዛሬ ከምንፎካከርባቸው ባንዲራዎች ጋር በቅርፅም ሆነ በቀለም ቅንብር እንደማይመሳሰል ይታወቅልኝ። በረጅም ሸንበቆ ጫፍ የሚታሰር፣እንደ ሹካ ጥርስ በተነጣጠሉ ሶስት የሀር ጨርቆች የተቀናበረ ከላይ ቀይ ፣ከማህል ብጫ ፣ከታች አረንጏዴ ቀለማት የተላበሰ ነበር።
ባልቻ አባ ነፍሶ በቁመቱ ዘለግ ያለ፣ ቀጭን ሲሆን በባህርይው ለባልንጀሮቹ ለጋስ ፣ለባላጋራዎቹ ደግሞ ሞገደኛ ነበር ይባላል።
ካድዋ ድል በሁዋላ አርባ አመታት አለፉ።
ጥልያን በሽንፈቷ እየተንገበገበች፣ ጦቢያም ድሏን እየገረበች ዘመናቸውን ገፉ።
ጣልያኖች በሙሶሎኒ አነቃቂነት ተጠናክረው ሲመለሱ ባልቻ እድሜ እንደ ቀንበር የተጫነው ሽማግሌ ነበር። ይሁን እንጂ ሰውየው የሚያረጅ ገላ እንጂ የሚያረጅ ወኔ አልነበረውም። በትውልድ ስፍራው ፣ከጥቂት ተከታዮቹ ጋር ሆኖ በጣልያን ላይ ሸፈተ፤ ተዋጋ፤ ተከበበ።
ከበደ ሚካኤል የጥንቱ የካርታጎ የጦር መሪ ፣ አኒባልን የሚዘክር ውብ ተውኔት በግጥም ደርሷል። አኒባል ከሮማ ወታደሮች ጋር በተፋጠጠ ጊዜ ፤እንዲህ ያሰኝዋል፤
“ካርታጎን ከሮማ ገጥማ ስትታገል
እጣችን ነበረ ፤ መሞት ወይም መግደል”
የአኒባል እጣ ከባልቻ እጣ ጋር ተገጣጠመ።
የከበደ ሚካኤልና የባልቻ እጣ ግን ለየቅል ነበር።
ከቤ ፣ከመሞት እና ከመግደል ውጭ የተለየ እጣ ደርሶታል።
ደራሲ ግርማቸው ተክለሃዋርያት ፣ባልታተመ ግለታሪኩ የባልቻን አሟሟት እንዴት እንደሰማ ይተርክልናል።
ከለታት አንድ ቀን፤ ግርማቸው በጠላት ቁጥጥር ስር በነበረችው አዲሳበባ እየተዘዋወረ ነበር። አንድ ጎረምሳ ባንዳ ፣ህዝቡን በዙርያው ሰብስቦ በድምፅ ማጉያ ” ባልቻ የተባለ ስልብ ሽፍታ ዛሬ በጀግናው የጣልያን ሰራዊት ተድምስሱዋል” እያለ ይልፍፋል። ያ ጎረምሳ ብንዳ፣በነፃነት ማግስት የተከበረ ደራሲና ያገር ፍቅር ሰባኪ ለመሆን የበቃው፣ከበደ ሚካኤል ነበር።
Average Rating