(ዜናውን በምስል ለማየት እዚህ ይጫኑ) በህወሓት ጄኔራሎች የሚመራው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ለሚቀጥለው ዓመት የበጀት ጭማሪ ተደረገለት፡፡ ሚኒስቴሩ አንድ ቢሊዬን ብር ጭማሪ የተደረገለት ቢሆንም፣ ጭማሪው የተደረገበ ምክንያት ግን አልታወቀም፤ ወይም በይፋ አልተነገረም፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት ከተያዘው አጠቃለይ 321 ቢሊዬን ብር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ጥቂት መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እንደገለጹት ከሆነ፣ የቀጣዩ ዓመት የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በጀት ከ12 ቢሊዬን ብር ወደ 7 ብሊዬን ብር ወርዷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በጀት ከነበረበት 11 ቢሊዮን ብር ወደ 12 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ሆኖም ሚኒስትሩ የመከላከያ ሚኒስቴር በጀት በምን ምክንያት እንደጨመረ የተናገሩት ነገር የለም፡፡
ከላይ እስከ ታች በህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመራው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በ2008 በጀት ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ ካጭበረበሩ ወይም ገንዘቡን የት እንዳደረሱት ካልታወቁ የመንግስት ተቋማት አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ያለፈውን ዓመት የፌደራል መስሪያ ቤቶች የበጀት አጠቃቀም አስመልክቶ ምርመራ ካደረገባቸው 155 ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች መካከል፣ መከላከያ ሚስቴር ቀዳሚው ገንዘብ አጥፊ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሣብን በተመለከተ በተደረገው የኦዲት ምርመራ የሀገር መከለከያ ሚኒስቴር ብር 172,017,623.31 ጉድለት ተገኝቶበታል፡፡ በፌዴራል መንግሥት መ/ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ወቅት የታዩ ዋና ዋና ግኝቶች በሚለው የዋና ኦዲተሩ ርዕስ ስር ደግሞ መከላከያ ሚኒስቴር ዋነኛ ገንዘብ በዝባዥ ሆኖ ተቀምጧል፡፡
ህንጻ ስራ ተቋራጮች እና ዕቃ አቅራቢዎች በገቡት ውል መሰረት ባለመፈጸማቸው ያልሰበሰቡት የጉዳት ካሣ ወይም ቅጣት ብር 226,318,955.97 ሆኖ የተገኘ ሲሆን፣ የጉዳት ካሣውን ካልሰበሰቡት መ/ቤቶች መካከል ደግሞ ዋናው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት መስሪያ ቤቱ ሊሰበስብ የሚገባውን ብር 44,825,207.62 ገንዘብ ሳይሰበስብ ቀርቷል፡፡ በተጨማሪም የዕቃና አገልግሎት ግዢ በመንግሥት ደንብ እና መመሪያ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ79 መ/ቤቶች እና 4 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያለ ጨረታ ቀጥታ ግዥ በመፈጸም ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች መካከል በህወሓት የሚመራው መከላከያ ሚኒስቴር ይገኝበታል፡፡
በዚህም መሰረት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ከደንብ ውጪ ወይም በህገ ወጥ መንገድ ብር 24,606,609.47 ወጪ አድርጓል፡፡ እንዲሁም በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሂሳብ ከታየባቸው መ/ቤቶች የሀገር መከላከያ ሚኒስቴርብር 159,561,189.14 በማጭበርበር ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡ መስሪያ በቱ ባለፉት አራት ተከታታይ የኦዲት ዓመታት ማለትም በ2005፣ በ2006፣ በ2007 እና በ2008 ከፍተኛ ገንዘብ ከተመዘበረባቸው እና በየዓመቱም አልታረም ካሉ መስሪያ ቤቶች ዋነኛው ነው፡፡ እንዲሁም ገንዘብ ወጪ የተደረገባውን የሂሳብ ሰነዶች ለኦዲት ምርመራ ለማቅረብ እንኳን ሲያመነታ የነበረ ሲሆን፣ ሰነዶቹን ለኦዲት መስሪያ ቤቱ ያቀረበውም በ24/4/09 ነው፡፡ ሆኖም በህጉ መሰረት አንድ ሰነድ ለኦዲት ሪፖርት መቅረብ ያለበት የበጀት ዓመቱ በተዘጋ በሶስት ወራት ውስጥ ነው፡፡
በ113 መ/ቤቶች እና በ28 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 5,262,275,550.73 (አምስት ቢሊዬን ሁለት መቶ ስልሳ ሁለት ሚሊዬን ሁለት መቶ ሰባ አምስት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ ብር ከ73 ሳንቲም) በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱን የገለጸው ኦዲተሩ፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በማጭበርበር የተቀመጠው መከላከያ ሚኒስቴር መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ‹‹ከዚህ ውስጥ ብር 375,557,284.38 በ6 መ/ቤቶች እና 6 ቅ/ጽ/ቤቶች ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተመዘገበ፤ ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ሊቀርብለት ያልቻለ ሂሳብ በመሆኑ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ ተሰብሳቢ ሂሳብ ተገኝቷል፡፡›› ሲልም ኦዲተሩ ገልጽዋል፡፡ በአጠቃለይ መከላከያ ሚኒስቴር በ2008 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዬን ብር በላይ በመመዝበር ቀዳሚውን ስፍራ ቢይዝም፣ ለሚቀጥለው ዓመት ግን አንድ ቢሊዬን ብር ተጨማሪ በጀት ተፈቅዶለታል፡፡
SOURCE: BBN news June 15, 2017
Average Rating