K. Teshome
ሰኔ 6/2009 ዓም
ወያኔ በመጻፍ እና በመናገር ለስልጣኑ ፈተና የሁኑበትን ሁሉ በካድሬዎቹ ሲያስፈራራቸው፣ ከዚያም አልፎ ሲያስራቸው እና
ሲያሰቃያቸው ይታያል:: ይሄንን በማድርጉ ያልተሳካለት ወያኔ አሁን ደግም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔ የውሸት
ፖለቲካን ከሚያስተላልፉ ሚዲያዎችን ገሸሽ ብሎ አይኑን፣ ጆሮውን፣ መላሱን እና ብእሩን ወድ ውጭ ሚዲያዎች ስላዞረ
እና ህዝቡን ሁሉ እስር ቤት ማስገባት እንደማይችል ሲያውቅ የህዝቡን የስሜት ህዋሳት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ማፈኑን
እና ማሰሩን ቀጥሉዋል:: በዚህች ጽሁፊ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የስሜት ህዋሳት መታፈን በትንሹ እገልጣለሁ::
ስለ ስሜት ህዋሳት የተማርኩት የመጀሪያ ደረጃ ተማሪ በሆንኩበት ወቅት ነበር:: ከዚያ ጊዜ ጀምሬ የሰው ልጅ 5 የስሜት
ህዋሳት እንዳሉት እና ተግባራችውም የተለያየ እንደሆነ አውቃለሁ:: አይን ለማየት፣ ጆሮ ለመስማት፣ እጅ ለመዳሰስ፣
አፍንጫ ለማሽተት እና ምላስ ለመናገር ያገለግላሉ::
እኔ እንደሚገባኝ እነዚህ የስሜት ህዋሳት በተፈጥሮ ወይንም በሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት ችግር ካልደረሰባቸው በስተቀር
በተፈጥሮ የተቸሩትን ተግባራት የማንንም ይሁንታና ፈቃድ ሳይፈልጉ እና ሳይጠይቁ ያከናውናሉ:: ጆሮ የሚሰማው፣ አይን
የሚያየው፣ አፍንጫ የሚያሸተው፣ ምላስ የሚቀምሰው፣ እጅ የሚዳስሰው የፖለቲካ ወይንም ዲሞክራሲ መብት በህገ
መንግስት ስለ ተሰጠው ሳይሆን የተፈጥሮ መብቱ ስለሆነ ነው:: የተወካዮች ምክር ቤት፣ ዳኛ ወይንም የፖለቲካ ሹማምንት
አይን ይህንን ይመልከት፣ ጆሮ ይህንን ይስማ፣ ምላስ ይህንን ይናገር፣ እጅ ይህንን ይጻፍ ብለው ሊወሰኑ አይችሉም:: ይህ
ማለት ጨንጓራ፣ ልብ፣ ኩላሊት እና ሌሎች ብልቶቻችን ስራቸውን የሚያከናውኑት የፖለቲካና ዲሞክራሲ መብት
ተሰጥቱዋቸው ነው በሎ እንደማሰብ ነው:: ስለዚህ የስሜት ህዋሳቱ ባለቤት ካልሆነ በስተቀር ሌላ አካል ድርጊታቸውን
ሊመርጥላቸው ወይንም ማእቀብ ሊጥልባቸው አይገባም ብየ አምናለሁ:: እንድህም ማድረግ ከጭቆና አፈና አልፎ ጸረ
ተፈጥሮ ያስብላል:: በተግባርም ሊሆን አይችልም:: የወያኔ መሪዎች ግን ከፍራሀቻቸው የመነጨ የህዝቡን የስሜት ህዋሳት
ማፈንና ተግባሮቻቸውን እስከ መወሰን ደርሰዋል::
ከጥቅምት 2009 ዓም በፊት የወያኔ ሰዎች የሚጽፉ፣ ያሚናገሩ እና የሚያትሙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ እንዳይናገሩ፣
እንዳይጽፉ እና እንዳያትሙ ከህገ መንግስቱ በተቃራኒ ማዕቀብ እና አፈና ሲያደርጉባቸው ቆይተዋል:: ማዕቀቡም
የሚመለከታቸው ወያኔን በመቃወም፣ በመተቸት እና የህዝብ መብት ይከበር ብለው የሚጽፉ እጆች እና የሚናገሩ መላሶች
ናቸው:: ይሄንንም ማዕቀብ የተላለፉ ብዙ እጆች እና መላሶች ወደ እስርቤት ተጥለዋል ከፊሎችም በስደትላይ ይገኛሉ:: እዚህ
ላይ እንደ አብነት በእስር ቤት ያሉትን እነ ተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንደር ነጋ እና በቀለ ገርባን ማንሳት ይቻላል::
አሁን ግን ሃግ ባይ ያጣው እና የዲሞክራሲ ነጋደው የወያኔ መንግስት በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን የህዝብ ልሳናታ
የሆኑ እንደ ኢሳት፣ ኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ እና ሌሎች ሚዲያዎችን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እየተራበ ሚሊዮን
ብሮችን ወጪ በማድረግ በተደጋጋሚ ጃም ለማድረግ ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር የእነዚህን ሚዲያዎች አድማጭ የሆነውን
የሰፌውን የኢትዮጵያ ህዝብ አይን እና ጆሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በማፈን ላይ ይገኛሉ:: የሚገርመው ደገሞ የወያኔ
መንገስት ይሄንን ያደረገው ደግሞ የተሻልኩ መሆኔን አውቆ ህዝብ 100% መረጠኝ፣ የህዝብ አገልጋይ ነኝ፣ ስልጣን የህዝብ
ነው ባለ ማግስት መሆኑ ነው::
የሃገራቸን ጸሃፍት፣ ምሁራን፣ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች ወይንም ማንኛውም ዜጋ በጋዜጣ፣ በራሪ ወረቀት፣ መጽሄት፣
ኢንተርኔት፣ ፌስ ቡክ ወዘተ ላይ ሰለ ሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በሀገር ቤትም ሆነ በውጪ ሚዲያዎች ላይ መጻፍ አይችሉም::
መጻፍም ብቻ ሳይሆን የተጻፉትን ጽሁፎች ያነበበ፣ ያስነበብ አመጽን በማነሳሳት እና መንግስትን በመገልበጥ ይከሰሳሉ::
ህዝቡ ስለ ኑሮ መክበድ እንኳዋን አማሮ ሲያወራ ከተሰማ መንግስትን በማማረር አመጽ ልታነሳሳ ነው ተብሎ ወደ እስር
ቤት ሊሄድ ይችላል:: በጣም የገረመኝ እና ምን ያክል በፍራቻ ውስጥ እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዳለን ያስተዋልኩት
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፌት ታክሲ ውስጥ የሰው ወሬ ፖለቲካ ነበር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ግን ታክሲዎች ሰው
የጫኑ እስካማይመስሉ ድረስ ትንፋሽ እንኳዋን አይሰማም ነበር:: እኔም ይህችን ጽሁፍ እየጻፍኩኝ እንኳዋን ሃገሬ ያለው
የፍረሃት አባዜ ስላልለቀቀኛ ይመስለኛል የፍረሃት ስሜት ይሰማኛል:: በተጨማሪ የወያኔ ሰዎች ኢንተርኔት እና ፌስ ቡክን
የተጠቀም፣ ኢሳት፣ ኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ እና ሌሎች ሚዲያዎችን ያዳመጠ እና የተመለከት የወያኔ ጠላት ነው በማለት
ህዝቡን ላይ ማዕቀብ ጥለዋል:: “ፈሪ ሜዳ አይበቃውም” እንደሚባለው ለስልጣናቸው የፈሩት የወያኔ ሰዎች ከዚህም
አልፈው ጣሪያ ላይ እየወጡ ዲሺ አውርደዋል፣ ወጣቶች መታወቂያቸው ታይቶ ኦሮሞ እና አማራ የሚል ከሆነ
ሞባይሎቻቸው ላይ የተጫኑት ነገር በጸጥታ ሃይሎች እየታየ ወደ እስር ቤት ይወሰዱነበር:: እኔም ምን አልባት ከተያዝኩኝ
የሚል ፍርሃት ሰለነበረኝ ሞባይሌ ላይ የነበሩ ሙዚቃዎችን፣ ጽሁፎችን እና የፌስ ቡክ ዱካዎችን ሁሉ ሰርዠ ነበር::
ጽሁፌን ለመደምደም ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብ ብቻ ነው የሚቻለው መክንያቱም አይታይምና:: ማሰብን የሚያሳይ
ቴክኖሎጂ ቢኖርም የእያንዳንዳችን አዕምሮ ጃም ተደርጎ ወይንም ለአፍ እና ለእጅ ተግባራት ምንጭ የሆነው አእምሮ እና
የአእምሮ ጓዳችን ሁሉ ተበርብሮ ወያኔዎች ብቻ እያሰቡ እኛ ሁላችን እስካሁን እስር ቤት ነበርን::: ስለዚህ ህዝቡ በአፈና፣
ሰቆቃ እና ፍርሃት እየኖረ ስለሆነ የነጻነት አየር የሚተነፍሰው በውጪ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የአለም አቀፍ ተቋማት እና
ድርጅቶች በችግሩ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንድሰሩ አበክረው መስራት ይገባቸዋል::
Average Rating