www.maledatimes.com በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አማካይነት በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ ለመምከር በኖርዌይ ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያዉያን አቶ ሌንጮ ለታ ያደረጉት ንግግር - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አማካይነት በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ ለመምከር በኖርዌይ ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያዉያን አቶ ሌንጮ ለታ ያደረጉት ንግግር

By   /   June 18, 2017  /   Comments Off on በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አማካይነት በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ ለመምከር በኖርዌይ ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያዉያን አቶ ሌንጮ ለታ ያደረጉት ንግግር

    Print       Email
0 0
Read Time:14 Minute, 38 Second

 

በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አማካይነት በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ ለመምከር በኦስሎ (ኖርዌይ) ቅዳሜ June 17, 2017 ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያዉያን አቶ ሌንጮ ለታ ያደረጉት ንግግር

ዉድ ወገኖቼ፡-

በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አማካይነት በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ ለመምከር በኦስሎ (ኖርዌይ) ቅዳሜ June 17, 2017 ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያዉያን አቶ ሌንጮ ለታ ያደረጉት ንግግር

ከሁሉም አስቀድሜ በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ስም የተደረገላችሁን ጥሪ ተቀብላችሁ በአገራችሁ ጉዳይ ላይ ለመወያየትና ሁላችንም የምንፈልገዉን ነፃነት በኢትዮጵያ ዕዉን ለማድረግ የሚረዳ አስተዋፅኦ ለማበርከት በዚህ ዝግጅት ላይ በመገኘታችሁ በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ እና በራሴም ስም ልባዊ ምሥጋናዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ፡፡

የዛሬዉን ንግግሬን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጥሞና ሊያስብበት የሚገባዉ ነዉ ብዬ የማምንበትንና እኔን ግን እጅግ በጣም የሚያሣስበኝን መሠረታዊ ጥያቄ በመጠየቅ ለመጀመር እፈልጋለሁ፡፡ እስከአሁን ካየናቸዉና አሁንም ከምናያቸዉ ዕዉነታዎች አንፃር ስናይ የሕወሐትን መዉደቅ ተከትሎ በኢትዮጵያ ሊከሠት የሚችለዉ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል አስባችሁ ታዉቃላችሁ? ሊፈጠር የሚችለዉስ ሁኔታ አሣስቧችሁ ወይም ዕረፍት ነስቷችሁ ያዉቃል? እኔን በኢትዮጵያ ሊፈጠር የሚችለዉ ሁኔታ እጅግ በጣም ያሣስበኛል፡፡ ምክንያቱም ከወጣትነት ዕድሜዬ ጀምሬ ያየሁት የመንግሥት ሥርዓት በተቀየረ ቁጥር ነገሮች ከመጥፎ ሁኔታ እጅግ በጣም ወደከፋ ሁኔታ ሲለወጡ ስለአየሁ ነዉ፡፡ በእኔ የዕድሜ ክልል እንዳሉት የእኔ ትዉልድ አባላት ሁሉ ስለፖለቲካ ማሰብ የጀመርኩት በቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሤ ዘመነ-መንግሥት ነበር፡፡ በወቅቱ ከንጉሡ የዘዉድ አገዛዝ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ወደ ሥልጣን የሚመጣ መንግሥት በየትኛዉም መልኩ ከቀደመዉ ሥርዓት የባሰ ይሆናል ብለን አስበን አናዉቅም ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ግን ከንጉሡ ሥርዓት የባሰ ሆነና ግምታችን የተሣሣተ መሆኑን አሣየን፡፡ ከዚያ በኋላም ደግሞ ከደርግ ሥርዓት ቀጥሎ የሚመጣዉ ሥርዓት በብዙ መልኩ ከደርግ የሚሻል ይሆናል የሚል ግምት ነበረን፡፡ ይሁን እንጂ በሕወሐት የሚመራዉን ጨቋኝ፣ ግፈኛ፣ ጨፍጫፊ እና ዘራፊ የአገዛዝ ሥርዓት ካየን በኋላ ግምታችን ትክክል እንዳልነበረ አረጋገጥን፡፡

የደርግ መንግሥት የሚወስዳቸዉን ኢሰብዓዊ ዕርምጃዎች ሁሉ ይወስድ የነበረዉ “የፊየል ወጠጤ …” የሚል መዝሙር እያስዘመረ በግልፅ እና በአደባባይ ስለነበር ምን ያህል ዜጎች እንደታሠሩ፣ እንደታፈኑና እንደተገደሉ ማወቅ ይቻል ነበር፡፡ የህወሐት አገዛዝ ግን የሚወስዳቸዉን የግፍና የጭካኔ ዕርምጃዎች ሁሉ የሚወስደዉ ድብቅ እና ፍፁም ምስጢራዊ በሆኑ መንገዶች ስለሆነ ምን ያህል ወገኖቻችን እንደታፈኑና ከታፈኑትስ ዉስጥ ምን ያህሎቹ እንደተገደሉ ማወቅ አልቻልንም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ግን በጣም እርግጠኞች ሆነን መነጋገር እንችላለን፡- በሕወሐት አገዛዝ ሥር የታፈኑትና በግፍ የተጨፈጨፉት ወገኖቻችን ቁጥር በደርግ ሥርዓት ሥር ከታፈኑትና ከተገደሉት ጋር ሲመዛዘን እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ፡፡ ይህን እያወቅን ግን ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወደ መንግሥትነት ሥልጣን የሚመጣዉ ኃይል አሁን አራት ኪሎ ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠዉ የሕወሐት የጥቂቶች የግፍና የጭቆና አገዛዝ የባሰ አይሆንም ብለን ራሣችንን እናታልላለን፡፡ ካለፉት ተሞክሮዎቻችን ተነስተን ግን ከሕወሐት የባሰ ሥርዓት እንዳይመጣብን በጣም መጠንቀቅ አለብን፡፡ አሁን እንዲያዉም ባለፉት ተከታታይ አገዛዞች ካየናቸዉ ሁኔታዎች እጅግ በጣም የባሰ አደጋም ሊመጣብን ይችል ይሆናል እንድንል የሚያደርጉንን አንዳንድ ምልክቶች እያየን ነዉ፡፡ በበኩሌ እጅግ በጣም ሣሣቢ ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበዉ ችግር ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል እንዳትችል የሚያደርግ ችግር ነዉ፡፡ ከሁሉም ችግሮች የሚብሰዉ ደግሞ የኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል አለመቻል ነዉ፡፡

ያለምንም ማጋነን ይህ አሁን በሥልጣን ላይ ያለዉ የጥቂቶች ቡድን በሚወስዳቸዉ ጭፍን እርምጃዎች ምክንያት በኢትዮጵያ ሥርዓተ-አልበኝነት እንዲሰፍን እና አገር እንድትበታተን የሚያደርግ ዘግናኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በበኩሌ የወጣትነትና የጉልምስና ዕድሜዉን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ እንዳሣለፈ ሰዉ ሆኜ ሣየዉ መጪዉ ጊዜ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያሣስበኝና የሚያስጨንቀኝም “ይህቺ አገር ተበታትና እንዳልነበረች ትሆን ይሆን?” በሚለዉ ስጋቴ ምክንያት ነዉ፡፡

ሩቅ መሄድ ሣያስፈልገን በቅርባችን በአፍሪካ ቀንድ ዉስጥ እንኳን አገሮች ሲበታተኑና እንዳልነበሩ ሲሆኑ አይተናል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት ለመጣል የሚታገሉ ኃይሎች የሚስመሙበት አንድ ብቸኛ ጉዳይ ሊጥሉት ለሚታገሉት መንግሥት ያላቸዉ ጥላቻ ብቻ የመሆኑ ዕዉነታ ለአገሮች መበታተንና ወደባሰ ችግር ዉስጥ መግባት አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በሌላ አባባል ተቃዋሚ ኃይሎች የሚግባቡበት ወይም የሚስማሙበት አንድ ብቸኛ ጉዳይ እናስወግደዋለን ለሚሉት መንግሥት ያላቸዉ ጥላቻ ብቻ መሆኑ አገራት ወደባሰ ችግር እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡

በጥቂት ጊዜ ዉስጥ መንግሥት-አልባ በሆነችዉና እስከዛሬም ድረስ ከገባችበት ዉስብስብ ችግር ባልወጣችዉ በጎረቤታችን በሶማሊያ ያየነዉ ይህንን ነዉ፡፡ የሶማሊያዉያን ዋነኛ እና ጠንካራ ብሔራዊ መግባቢያ ለኢትዮጵያ ያላቸዉ ጥላቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ሶማሊያዉያን ኢትዮጵያን በኃይል ለማንበርከክ ተባብረዉ ነበር፡፡ ይህንን የምለዉ በግምት ወይንም በሰሚ ሰሚ ሣይሆን በአካል ተገኝቼ ያየኋቸዉን አንዳንድ ዕዉነታዎች መሠረት በማድረግ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ጦርነት እንዳበቃ በ1978 የኢትዮ – ሶማሌ ጦርነት እንዳለቀ የኢሣን የሰፈራ መንደሮች በእግር አቋርጬ ወደ ጅቡቲ ተጉዤ ነበር፡፡ በጉዟችን ላይ ያገኘናቸዉ የኢሣ ሶማሌ ጎሣ አባላት – በዕድሜ የገፉ መሃይማን አሮጊቶችን ጨምሮ – “ሃበሻ” ብለዉ ለሚጠሩት ሕዝብ ያላቸዉን በጣም ሥር የሰደደ ጥላቻ አሣይተዉናል፡፡

ይህ ሌላዉን ሕዝብ የመጥላት አባዜ ነበር የ1978 የሶማሌ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ ወደራሣቸዉ የአድርስ በእርስ ጥላቻ የዞረዉ፡፡ በሌላ አነጋገር ሶማሌዎች “ሃበሻ” ብለዉ ለሚጠሩት ሕዝብ ያላቸዉን ሥር የሰደደ ጥላቻ ወደራሣቸዉ የእርስ- በእርስ የጎሣ ጥላቻ አዞሩት፡፡ ከዚያ በኋላ የሶማሌ አገራዊ ስሜት በቅፅበት ተቀየረ፡፡ በመጨረሻም የተለያዩ የጎሣ ቡድኖች ሁሉንም ነገር ትተዉ የዚያድባሬን አምባገነናዊ ሥርዓት ወደመጣሉ ላይ ብቻ አተኮሩ፡፡ በዚያድባሬ አምባገነናዊ አገዛዝ ላይ ከነበራቸዉ ጥላቻ እና አገዛዙንም ተባብረዉ ለመጣል ከነበራቸዉ ፍላጎት ዉጭ ሌላ የጋራ የሆነ አጀንዳ ያልነበራቸዉ እነዚህ የጎሣ ቡድኖች ዚያድባሬ በ1991 ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ እርስ በእርሳቸዉ ወደ መጠፋፋት አመሩ፡፡ ዛሬም ድረስ ሶማሊያ ከዚያ ችግር ሙሉ በሙሉ አልወጣችም፡፡

የደቡብ ሱዳን ሁኔታም ሌላዉ ሩቅ መሄድ ሣያስፈልገን ከቅርባችን ልናነሠዉ የምንችለዉ ጥሩ ምሣሌ ነዉ፡፡ ዓመታትን በፈጀ ትግል የሚፈልጉትን ድል ከተጎናፀፉ እና ነፃነተቸዉን ካወጁ በኋላ በጣም ዉስብስብ፣ ምስቅልቅልና ተስፋ አሰቆራጭ ሁኔታ ዉስጥ ከገቡት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች አንዷ ደቡብ ሱዳን ናትና፡፡ የሰሜኑን የበላይነት ከመጥላት ሌላ የጋራችን የሚሉት መግባቢያ ነጥብ ያልነበራቸዉ የደቡብ ሱዳን ነፃነት ታጋዮች የሚጠሉትን ጨቋኝ ሥርዓት በጋራ ካስወገዱ በኋላ እና ነፃነታቸዉን ካወጁ በኋላ በአንድነት እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸዉ የጋራ አጀንዳ አልነበራቸዉም፡፡ ስለሆነም ያገኙትን ድል ማጣጣምና ያላቸዉን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመዉ በዕድገት ጎዳና ላይ ተባብረዉ መጓዝ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም አንዱ የሌላዉ የበላይ ለመሆን በሚደረግ የእርስ በርስ ግጭት ዉስጥ በመግባት ከራሣቸዉም አገር አልፈዉ የመላዉ አፍሪካ ቀንድ አገሮች ስጋት ለመሆን ችለዋል፡፡

እንደእኔ እምነት ከእነዚህ የቅርብ ጎረቤቶቻችን የተማርናቸዉ ጠቃሚ ትምህርቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ትምህርቶች ሦስት ነጥቦችን ጨምቀን ማዉጣት እንችላለን፡-

  1. በፍፁም አምባገነንነትና በአንድ ሉዓላዊት አገር መበታተን መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖሩን ተረድተናል፡፡ አንዱ ለሌላዉ መኖር ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነም አረጋግጠናል፤
  2. አንዴ ወደ ዉድቀት ጎዳና መሄድ የጀመረን ሥርዓት ለማቆም የሚቻልበት ቦታ እንደሌለም አዉቀናል፤
  3. በአገር ደረጃ ሲታይ ወደ ዉድቀት ጎዳና መሄድ በጣም ቀላል መሆኑንና ከሂደቱ መመለስ ግን እጅግ በጣም ከባድእንደሆነ የእነዚህ ጎረቤቶቻችን ተሞክሮ በግልፅ አሣይቶናል፡፡

ስለሆነም እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበትና የአገራችንን ወደ ዉድቀት ማምራት የምንጠብቅበት ምክንያት ስለሌለ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የምንል ወገኖች ሁሉ ጉልበታችንን፣ ዕዉቀታችንን፣ ሃብታችንንና ጊዜያችንን ብሎም ማሣደር የምንችለዉን ተፅዕኖ ሁሉ አቀናጅተንና አስተባብረን አገራችንን ከመበታተን አደጋ መታደግ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ምሥረታ እንደ ጥሩ ተስፋ ሰጭ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ሁለችንም እንደምናዉቀዉ ለኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ምሥረታ ምክንያት የሆኑት የመግባቢያ ነጥቦች የተወሰኑ ናቸዉ፡፡ እንዲያዉም አንዳንዶቹ የንቅናቄዉ መሥራች ድርጅቶች ከሚግባቡባቸዉ የጋራ ነጥቦች ይልቅ የሚለያዩባቸዉ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ሊበዙ ይችላሉ፡፡ የአገራዊ ንቅናቄዉ ጥሩና ጠንካራ ጎን አድርገን ከምንወስዳቸዉ ነጥቦች አንዱና ዋነኛዉም ልዩነቶቻችንን ወደጎን አድርገንና አቻችለን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት መስማማታችንና የሚያግባቡንን ጉዳዮቸ በሂደት እያበራከትን እንደምንሄድ ተስፋ ማድረጋችን ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በግልፅነት፣ በመከባበር፣ በቅንነትና ኃላፊነት በተመላበት ስሜት በጥልቅ መወያየት፣ መመካከርና መከራከር አለብን፡፡ የኢትዮጵየ አገራዊ ንቅናቄን የመሠረትነዉ አራት ድርጅቶች ይህንን በተግባር እያደረግን መሆናችንን ስገልፅ ደስታ ይሰማኛል፡፡

እንደሚታወቀዉ አንዱና ዋነኛዉ የልዩነታችን ምክንያት አንዳንድ ወገኖች “የጎሣ ፖለቲካ” ብለዉ የሚጠሩት ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሂደት ነዉ፡፡ በነገራችን ላይ “የጎሣ ፖለቲካም” ሆነ አንዳንዶች ደግሞ እንደሚሉት “የዘር ፖለቲካ” የሚሉት አጠራሮች እንደ እኔ እምነት የተሣሣቱ አጠራሮች ናቸዉ፡፡ “ጎሣ” የሚለዉ ቃል ከአፋን ኦሮሞ የተወሰደ ቃል ሲሆን በኦሮሞ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ክፍፍሎች ዉስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነዉ፡፡ “ዘር” የሚለዉ ቃል ደግሞ የቆዳ ቀለማችን ጥቁር የሆነዉን ሁላችንንም በጥቁርነታችን አንድ ላይ የሚገልፀን ወይንም ደግሞ የሰዉ ዘር አባላት በመሆናችን እንደ “የሰዉ ዘር” በአንድነት የሚገልፀን ሰፊ የሆነ ቃል ነዉ፡፡ ስለሆነም በማንነት የተደራጀንን ወገኖች “የጎሣ ፖለቲከኞች” ወይም “የዘር ፖለቲካ አራማጆች” ብሎ መፈረጅና ትናንትም ስላልነበረዉና ዛሬም ስለሌለዉ “አንድነት” ደግሞ ደጋግሞ ማንሣት ትርጉም የለዉም፡፡ በዲሞክራሲያዊ መርሆ የምናምን ከሆነና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በነፃነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት በአንድ የጋራ አገር አብሮ መኖር አለባቸዉ ብለን ከልብ የምናምን ከሆነ የምንፈልገዉ በጉልበትና በመሣሪያ ኃይል የሚከበር የመልክዓ-ምድር አንድነት ሣይሆን የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትን መሆን ይኖርበታል፡፡ በቅንነት ከተነሣንና በግልፅነት ከተቀራረብን የዚህ ዓይነቱ የሕዝብ ለሕዝብ አንድነት በአገራችን እንዲኖር ማድረግ እንችላለን፡፡

በመሠረቱ በጠመንጃ ኃይል የተመሠረተና በኃይል እየተጠበቀ ያለ የመልክዓ-ምድር አንድነት እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ እዉነተኛ አንድነት ባልነበረባትና አሁንም በሌለባት ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የዲሞክራሲ ጭላንጭል እንዲታይ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በብሔር ስም በማንነታችን ተደራጅተን የምንታገለዉና “የአንድነት ኃይሎች” ተብለዉ የተፈረጁት ወገኖች ከምንፈልገዉ ግብ ለመድረስ ከምንም በፊት “የኢትዮጵያ አንድነት” ለሚለዉ ፅንሰ ሃሳብ በምንሰጠዉ ትርጉም ላይ መግባባት መቻል ይኖርብናል፡፡

በኢትዮጵያዊ ማንነት ወይንም በ“ኢትዮጵያዊነት” ፅንሰ-ሃሳብ ላይም በትርጉም ያለመግባባት ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ግራ የተጋባ እና ግራ የሚያጋባ የግንዛቤ ችግር መዉጣት የምንችለዉ በሁለት መንገዶች ብቻ ነዉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በፖለቲካ ክርክሮቻችን ዉስጥ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” የሚል ማስጠንቀቂያ መሰል ነገር ማስገባትን ማቆም መቻል አለብን፡፡ በበኩሌ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሚጫንብኝን አንድነት የማልደግፈዉንና የማልቀበለዉን ያህል የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ባካተተ መንገድ የኢትዮጵያን አንድነትም ሆነ የኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉዓላዊት አገር መቀጠል አልቃወምም፡፡ ይህን አቋም እንድይዝ ያደረገኝ ደግሞ እስከዛሬ የምናዉቀዉ “የኢትዮጵያ አንድነት” በጉልበት፣ በጠመንጃ ኃይልና በማስፈራራት ተጠብቆ የቆየ የዉሸት አንድነት መሆኑን ማወቄ ነዉ፡፡ በተቃራኒዉ ግን በሕዝቦች ስምምነትና በመግባባት ላይ የተመሠረተ አንድነትን በደስታ እቀበላለሁ፤ ከልብም እደግፋለሁ፡፡

ይህ በስምምነትና በመግባባት ላይ የተመሠረተ እዉነተኛ የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትን የመመሥረቱ አዝማሚያ ደግሞ እጅግ በጣም በሚያበረታታና ተስፋ በሚሰጥ መንገድ በአገር ቤት ባሉት ወገኖቻችን መካከል ተጀምሯል፡፡ ይህ ዕዉነታ የሕወሐትን የግፍ አገዛዝ በመቃወም ከፍተኛ የሕዝባዊ አመፅ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ በነበረበት ወቅት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል፤ በተለይም በጎንደር እና በጎጃም በሚገኘዉ የአማራ ወገናችንና እንዲሁም በኦሮሞ ሕዝብ አማካይነት በማያሻማ መንገድ ተሰምሮበታል፡፡ እንግዲህ ይህን ተስፋ ሰጪ እና በጣም አበረታች የሆነ ጅምር በተቻለን መንገድ ሁሉ ማጠናከር ይኖርብናል፡፡

በተከታታይ የኢትዮጵያ ገዢ ሥርዓቶች በጉልበት ተጭኖብን የኖረዉን ዓይነት የግዴታ አንድነት የማልቀበልባቸዉ ግልፅ ምክንየቶች አሉኝ፡፡

የዚያ ዓይነቱ የጉልበት አንድነት የአንዳንድ ማህበረሰቦችን የሌላዉ አካል አለመሆን አጉልቶ በሚያሣይ መንገድ የተገነባ ብቻ ሣይሆን አንድን ሕዝብ ራሱ የሚያለያይ “አንድነት” ነበር፡፡ አንዳንዶች ጮክ ብለዉ የሚዘምሩለት የእስከዛሬዉ “የኢትዮጵያ አንድነት” አንዱን የበላይ ሌላዉን ደግሞ የበታች፣ አንዱን ልጅ ሌላዉን የእንጀራ ልጅ በሚያደርግ ከፋፋይ የጭቆና አገዘዝ ላይ የተመሠረተ ነበር፤ ዛሬም ቢሆን በሕወሐት አገዛዝ ሥር ያለዉ “የአገር አንድነት” ጥቂቶችን ተጠቃሚና አንደኛ ደረጃ ዜጎች የሚያደርግ የዉሸት “አንድነት” መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር የእስከዛሬዉ “የኢትዮጵያ አንድነት” የተወሰኑትን ሕዝቦች የተደበቁ እንዲሆኑ ያደረገና ስልታዊ በሆነ መንገድ ያገለለ፣ ጥቂቶችን ግን ተጠቃሚ እና ጎልተዉ እንዲታዩ ያደረገ መሆኑ ለብዙዎቻችን ግልፅ ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ “አንድነት” በየትኛዉም መስፈርት ሚዛናዊነት ያለዉ ካለመሆኑም በላይ ወደዳር የተገፉትን ሕዝቦች ልብ ያሸፈተ የዉሸት አንድነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ልምሣሌ፡- ከላይ ለመግለፅ የሞከርኩት የእስከዛሬዉ “የኢትዮጵያ አንድነት” ኦሮሞዎችን፣ ከምባታዎችን፣ ጉራጌዎችን፣ ሃዲያዎችን፣ ሲዳማዎችን፣ አኝዋኮችን፣ አፋሮችንና ሌሎችንም ሕዝቦች እርስ በእርስ የሚያቃቅር እና የሚያለያይ የከፋፍሎ መግዛት ፖሊሲ የሚንፀባረቅበት “አንድነት” ነበር፤ ዛሬም በህወሐት አገዛዝ ሥር የተለወጠ ነገር የለም፡፡

ሕዝቦችን ስልታዊ በሆነ መንገድ እርስ በእርሣቸዉ የሚያለያይ የዉሸት “አንድነት” አንድ መሆን በሚገባቸዉና መሆንም በሚፈልጉ ሕዝቦች መካከል ስምምነትና መተባበር እንዳይኖር የሚያደርግ ሲሆን በተቃራኒዉ ግን የአገዛዙ ጥበቃና ድጋፍ የማይለያቸዉንና ዉስጣዊ አንድነታቸዉ ያልተበረዘዉን የአገዛዙ ተጠቃሚ ወገኖች የበለጠ እንዲተሣሰሩና አንድነታቸዉንም ጠብቀዉ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሚዛናዊ ካለመሆኑም በላይ በአብሮነት ላይ የተመሠረተ የሁሉም ሕዝቦች እዉነተኛ አንድነት እንዳይኖር የሚያደርግ ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ከፋፋይ የሆነ የስም ብቻ አንድነት በምንም መልኩ የሚደገፍ አይሆንም፡፡

የበለጠ ተቀባይነት የሚኖረዉና የተለያዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የሚያስተሣስረዉ እዉነተኛ አንድነት ልዩነቶቻችንን የሚያከብርና በመፈቃቀድና በመተባበር ላይ የሚመሠረት ከመልክዓ-ምድር አንድነት የዘለለ የሕዝብ ለሕዝብ አንድነት ነዉ፡፡ ስለዚህ የየትኛዉንም ወገን የበላይነት የማይቀበሉ ሕዝቦች በመተባበር፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀድና በመስማማት በቅንነትና በግልፅነት ተቀራርበዉ ወደ አንድነት ጎዳና ለመሄድ ተባብረዉ የጋራ ጠላታቸዉን እንዲታገሉ ብናደርግ ሁላችንም ለምንቀበለዉና ለዘላቂነቱም ለምንታገልለት አዲስ የኢትዮጵያ አንድነት ጠንካራ መሠረት ልንጥል እንችላለን፡፡ ከዚህ ዉጭ የሆነዉ የእስከዛሬዉ “የኢትዮጵያ አንድነትም” ሆነ “ኢትዮጵያዊነት” የሕዝቦችን ማንነት ማለትም፡- ኦሮሞነትን፣ አኝዋክነትን፣ ጉራጌነትን፣ ሲዳማነትን፣ ከምባታነትን፣ ከፊቾነትን፣ ዳዉሮነትን፣ ሃዲያነትን፣ ጋሞነትን፣ ወላይታነትን፣ አፋርነትን፣ ወዘተ የጨፈለቀ የመልክዓ-ምድር “አንድነት” ነበር፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝቦች ማዕከል አድርጎ በቆመ የኢትዮጵያ አንድነት ዉስጥ ግን የሕዝቦች ማንነት የሚጨፈለቅበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማንነታቸዉን እንደያዙ ኢትዮጵያዊ ሆነዉ ወይም የኢትዮጵያዊነትን ማንነት በኩራት ተላብሰዉ ሊታዩ የሚችሉት መሬታቸዉን ሣይሆን እነሱን ራሣቸዉን ማዕከል አድርጎ በተመሠረተ የኢትዮጵያ አንድነት ዉስጥ ብቻ ነዉ፡፡ ያኔ ነዉ የቋንቋ፣ የባህል፣ የዕምነት፣ እና ሌሎችም ልዩነቶቻችን የዉበታችን ምንጮች መሆናቸዉን አምነን ዉብ የሆነና ሕዝቦችን ማዕከል ያደረገ የኢትዮጵያ አንድነት ፈጥረናል ወይም መሥርተናል ማለት የምንችለዉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ራሣቸዉን ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ወዘተ ማለት የማይፈልጉና ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ዉጭ ሌላ ማንነት የለንም የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ያታወቃል፡፡ በእነዚህም ላይ ቢሆን የብሔር ማንነታቸዉን በግድ እንዲቀበሉ ለማድረግ አላስፈላጊ ጫና ማሣደር የለብንም፡፡ እነዚህ በ“ኢትዮጵያዊነት” ብቻ መታወቅና መገለፅ የሚፈልጉ ወገኖች እኛን በማንነታችን መታወቅና መታገል የምንፈልገዉን ወገኖችን “የለም አፋርነታችሁን፣ ኦሮሞነታችሁን፣ ሲዳማነታችሁን፣ አማራነታችሁን፣ ጉራጌነታችሁን፣ አኝዋክነታችሁን፣ ወዘተ ወደዚያ ጥላችሁ “ኢትዮጵያዊ ነን” ብቻ በሉ” ሊሉን አይገባም፡፡

ጠቅለል ባለ አነጋገር እኔ በዚህ ንግግሬ ዉስጥ ይስማማኛል ብዬ የምገልፀዉ የኢትዮጵያ አንድነትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ያለፉት ገዢዎቻችን ሊጭኑብን ሞክረዉ ካልተቀበልነዉና አምርረንም ከታገልነዉ ዛሬም ድረስ እየታገልነዉ ካለነዉ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ፍፁም የተለየ ነዉ፡፡

የቀድሞዉ “ኢትዮጵያዊነት” የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሁሉ ያካተተ ወይንም በትክክል ያቀፈ አልነበረም፡፡ ስለሆነም የእስከዛሬዉ አንድነት ጥቂቶች ራሳቸዉን የሚያዩበትና የሚገልፁበት የነበረ ሲሆን ብዙሃን ግን በፍፁም ራሣቸዉን የማያዩበት ነበር፡፡ እነዚህ ትናንት በነበረዉና አሁንም ባለዉ የጥቂቶች “ኢትዮጵያዊነት” ዉስጥ ራሣቸዉን ፈልገዉ ማግኘት ያልቻሉ ወገኖች ፍትሃዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎችን አንስተዉ ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ትግል ለማፋፋም ተገደዱ፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ አንስተዉ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴዎችንም አስፋፉ፡፡ እነዚህ የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን ሕዝቦች ያነሷቸዉ ፍትሃዊና ተገቢነት ያላቸዉ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ አጥጋቢ መልስ ስላላገኙ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት እና ዲሞክራሲ ፈላጊ ሕዝቦች ከዓመታት በፊት የጀመሩትን ትግል ዛሬም ድረስ በተለያየ መልኩ እንደቀጠሉ ናቸዉ፡፡

እንግዲህ ኢትዮጵያን አንድነቷ የተጠበቀ ሉዓላዊት አገር አድርጎ ማስቀጠል የሚቻልበት ብቸኛዉ መንገድ ኢትዮጵያዊነትን የአንድ ወገን ብቻ መገለጫ ከመሆን አላቆ የሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ማንነቶች ጎልተዉ የሚታዩበትና የሚገለፁበት የልዩ ልዩ ማንነቶች ድምር ዉጤት እንደሆነ አድርጎ በመተርጎም ነዉ፡፡

እንደእኔ እምነት ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል፡፡ ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን ደግሞ የትኛዉንም ወገን አይጎዳም፤ ብዙዎቻችን ለምንመኘዉ ዓይነት የአገር አንድነት ግን ይበጃል፡፡ ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፣ ሲዳማ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፣ አማራ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም የሚለዉ ጭፍን አቀራረብ ማንነታችንን መሠረት አድርገን የጋራችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንደ አዲስ እንመሥርት የሚል ግልፅ አቋም የያዝነዉን ወገኖች ከሁለቱ አንዱን እንድንመርጥ ያስገድደናል፡፡ ያ አስገዳጅ ሁኔታ ከተፈጠረ ደግሞ ብዙዎቹ ብሔረተኞች – በተለይም የኦሮሞ ብሔረተኞች ኢትዮጵያዊነትን እርግፍ አድርገዉ ጥለዉ የብሔር

ማንነታቸዉን ብቻ ይዘዉ መቅረትን እንደሚመርጡ አልጠራጠርም፡፡ ይህ የግዴታ ምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያን አንድነቷ እንደተጠበቀ ለማስቀጠል ጥሩ ሊባል የሚችል አማራጭ አይደለም፡፡

የቋንቋ ጉዳይም ሌላዉ የማያዳግም ዕልባት ሊሰጠዉ የሚገባ ቁልፍ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ እጅግ መሠረታዊ ከሆኑት የዲሞክራሲ መብት ጥያቄዎች አንዱና ዋነኛዉ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሂደት፣ በአስተዳደር፣ በፍትህ፣ በጤናና በሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ የመንገሥት ተቋማት ዉስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመገልገሉ አስፈላጊነት እና እንደ አፋን ኦሮሞ ያለዉን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገራችን ሕዝቦች (በትዉልድ ኦሮሞ ያልሆኑትን እጅግ በጣም ብዙ ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ጨምሮ) የሚገለገሉበትን የአገሪቱ ትልቅ ሕዝብ ቋንቋ አማራጭ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን አለማድረግ ለምንመኘዉ የኢትዮጵያ አንድነት ዕንቅፋት መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ዕዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሚገለፅባቸዉ ባህሪያት አንዱ ለሥርዓቱ ተገልጋዮች ክፍት መሆኑና ተገልጋዩ ሕዝብ መንግሥትን ወክለዉ የተቀመጡትን አገልጋዮቹን አግኝቶ በቀጥታ ማነጋገር መቻሉ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ ተገልጋይንም ሆነ አገልጋይን ያቀራርባል፣ ያስተሣስራል፡፡ በሌላ አባባል ሕዝብን ከመንግሥት ጋር፣ መንግሥትንም ከህዝብ ጋር በጥሩ መንገድ ያቆራኛል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች ሲደረግ እንደነበረዉ በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል አስተርጓሚ ለማቆም መሞከር በትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዉስጥ ሊኖር የሚገባዉን የአገልጋይና የተገልጋይ ቀጥተኛ ግንኙነት ያደናቅፋል፡፡

ኢትዮጵያ ዉስጥ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በተራዉ ሕዝብ መካከል አስተርጓሚን ማቆም የተለመደ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡ ይህ አስተርጓሚን የማቆም ሥርዓት “ስማ በለዉ!!” በመባል ይታወቃል፡፡ ልጅ እያለሁ በፍርድ ቤት የችሎት ሂደት ላይ ተገኝቼ ለአንድ የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወደ አማርኛ ቋንቋ የሚያስተረጉምለት ሰዉ ተመድቦለት የችሎቱ ሥነ-ሥርዓት በ“ስማ በለዉ!!” ሲካሄድ የመከታተል ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ተርጓሚዉ – ሌላ ተልዕኮ ኖሮት ይሁን የአፋን ኦሮሞ አባባሎችን በትክክል መተርጎም አቅቶት እንደሆነ እስከአሁን ድረስ ባልተረዳሁት ምክንያት – የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዉ ያለዉን ለዉጦ ባለጉዳዩ ካለዉ ለየት ባለ መንገድ ለችሎቱ ሲተረጉም ታዝቤ ነበር፡፡ ይህ የትርጉም ስህተት እንደ አንድ ኦሮሞ በጣም ከሚያንገበግቡኝና እስከዛሬም ድረስ ከአዕምሮዬ ሊጠፉ ካልቻሉ አሣዛኝ ክስተቶች እንደ አንዱ ሆኖ ይሰማኛል፡፡

ማንኛዉም በሕዝቦች የመብት ጥያቄ ምክንያት ሥራ ላይ የዋለ ነገር ጎጂ ነዉ ሊባል የሚችለዉ በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ ሌላዉን ወገን የሚጎዳ ሆኖ ከተገኘ ነዉ፡፡ ለምሣሌ፡- በቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት በየትኛዉም ወገን ላይ እንደማይደርስ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ ኦሮሞዎች የፍትህ አገልግሎት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ አስተዳደራዊ አገልግሎት፣ የጤና አገልግሎት፣ ወዘተ በትክክል ለማግኘት በራሣቸዉ እናት ቋንቋ በአፋን ኦሮሞ ቢጠቀሙ ማነዉ የሚጎዳዉ? ባለፉት ሥርዓቶች ኦሮሞ ወገኖቻችን በ“ስማ በለዉ!!” ሲዳኙ የተጠቀመ ወገን ነበረ? ሌሎች ኢትዮጵያዉያንስ የአገራችን የጀርባ አጥንት የሆነዉን የዚህን በቁጥሩ የአገራችን ብዙሃን፣ በመሬቱ አቀማመጥ ደግሞ የመላ አገሪቱ ዕምብርት የሆነ ሕዝብ ቋንቋ እንዲያዉቁ ቢደረግ ጉዳቱ ምኑ ላይ ነዉ?

የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ገዢዎች የወረሷቸዉና በትክክል ከመፍታት ይልቅ የባሰዉኑ ያወሳሰቧቸዉ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ተደላድለዉ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ብለዉ የፈጠሯቸዉ ችግሮችም አሉ፡፡ እንፍታም ቢሉ ደግሞ በቀላሉ ሊፈቷቸዉ የማይችሏቸዉ ችግሮች አሉ፡፡ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመር የዛሬዎቹ ገዢዎችም ሆኑ የነገዎቹ መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ሊገቷቸዉ ወይንም ሊቆጣጠሯቸዉ ከማይችሏቸዉ ችግሮች አንዱ ነዉ፡፡ የዛሬዎቹ የሕወሐት ገዢዎች ከሩብ ምዕተ- ዓመት በፊት ወደሥልጣን ሲመጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ50 ሚሊዮን ትንሽ ከፍ ያለ ነበር፡፡ ዛሬ የአትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ወደ 100 ሚሊዮን ተጠግቷል፡፡ ይህ በጣም ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር በጣም ዉስን በሆነዉ የአገሪቱ ሃብት አጠቃቀም ላይም ሆነ በአካባቢ ብክለት ረገድ የሚያስከትለዉ ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ይህን የሕዝብ ቁጥር ችግር የትኛዉም ከሕወሐት ቀጥሎ ወደ ሥልጣን የሚመጣ መንግሥትም ሣይወድ በግድ ይወርሰዋል፡፡ በጣም የሚደንቀዉ ነገር ይህ የሕዝብ ቁጥር ጉዳይ በተቃዋሚ ወገኖች ዘንድ እንደ ችግር ተወስዶ ዉይይት ሲደረግበት ወይም መፍትሔ ሲፈለግለት አለመታየቱ ነዉ፡፡ ስለሆነም ለሕዝብ ቁጥር ፈጣን ዕድገት ትኩረት ሰጥተን መነጋገር አለመቻላችን በጣም ያሣስበኛል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱን ወደ ጥፋት ሊመሯት ከሚችሉት ችግሮች አንዱ ይህ የሕዝብ ቁጥር ጉዳይ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ሁላችንም ዝምታን የመረጥን እንመስላለን፡፡ በሕዝብ ቁጥር ፈጣን ዕድገት ምክንያት ሊመጡብን ስለሚችሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ምንም የምንጨነቅ አንመስልም፡፡ ለዚህም ነዉ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ ሆኜ ይህን አሣሣቢ ጉዳይ እያየንና እየሰማን ዝምታን የመረጥነዉ ለምንድነዉ? ብዬ መጠየቅ የፈለግኩት፡፡

ዛሬ በአገራችን መዲና የሚኖሩ ሰዎች የሕዝብ ብዛት ምን ያህል ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሌላዉን ሁሉ ትተን የከተማዋ መንገዶች ሁሌም በሰዎች ተሞልተዉና መፈናፈኛ አጥተዉ ሲታዩ በሕዝቡ ዘንድም ሆነ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሙያ ማህበራት ወይም በሌሎች ማህበራዊ ተቋማት እና በግለሰብ ኢትዮጵያዉያን አማካይነት ጥያቄ ማስነሣት ነበረባቸዉ፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የዕለት ተዕለት ወንጀሎች እስከአሁን ድረስ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሣቸዉ አልተሰማም፡፡ የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድኖች ከቁጥጥር ዉጭ ሆነዉ ሕዝብን እያስቸገሩ መሆኑን አንሰማም ወይንም አናይም፡፡ ይህ ደግሞ አንድ መታለፍ የሌለበት ጥያቄ እንድናነሣ ያደርገናል – የሕዝብ ብዛት፣ በሕዝብ ብዛት የተጨናነቀች መዲና፣ ከመጠን ያለፈ ድህነት፣ ማመን የሚያስቸግር የኑሮ ዉድነት፣ ወዘተ በመሣሪያ ወደተደገፈ ዝርፊያ እና ወደሌሎችም ወንጀሎች ያላመሩት እንዴት ነዉ? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ፡፡ መልሱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልዩ የሆነ ባህሪ ከማወቅ ይገኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እዉነትም እጅግ በጣም ጨዋ የሆኑ ሕዝቦች ናቸዉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማንም ሣይነግራቸዉና ሣያስገድዳቸዉ እንዲሁ በተፈጥሮአቸዉ ህግን ያከብራሉ፡፡ አብዛኞቹ ሕዝቦቻችን ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረባቸዉ ናቸዉ፡፡ ከሕወሐት የመሣሪያ ጋጋታ እና ወታደራዊ ጡንቻ በላይ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የሕዝቦቻችን ጥሩ ጎኖች ናቸዉ የኢትዮጵያን ሕዝቦች በሰላም ዉለዉ እንዲገቡና ተከባብረዉ አብረዉ እንዲኖሩ ያደረጓቸዉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ አንድ ቀን ሊቀየር ይችላል፡፡ ችግሮች ገፍተዉ እና ክልክ አልፈዉ ሲመጡ በቀላሉ ማቆሚያ መንገድ አይኖርም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሙያ ማህበራት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወዘተ ከቁጥጥር ዉጭ የሆነ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ ይቻል ዘንድ በተገኘዉ መንገድ ሁሉ ሕዝብ ዉስጥ ገብተዉ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችን ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮች ከፊታችን ተደቅነዉ ይጠብቁናልና ከአሁኑ ጀምረን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ሥራ መግባት ይኖርብናል፡፡

በመጨረሻም በጋራ አገራችን ለሁላችንም የሚበጅ ዕዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕዉን ለማድረግ እንድንችልና ሕዝቦቻችን በጨቋኝ ሥርዓት የግፍ አገዛዝና ጭፍን አካሄድ ምክንያት ከሚፈጠር መከራና ስቃይ ተላቀዉ ሰላም የሰፈነበት የተረጋጋ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ለማድረግ ልዩነቶቻችንን ሁሉ አቻችለን ቢያንስ ቢያንስ በምንስማማባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ በመቀራረብ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከመታገል ዉጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ለአንድ አፍታ እንኳን እንዳንዘነጋ አበክሬ ላስገነዝባችሁ እወዳለሁ፡፡ የለንም፡፡ ስለሆነም ከሰባት ወራት በፊት በታዋቂ ኢትዮጵያዉያን ያልተቆጠበ ጥረትና በአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነት በይፋ ተመሥርቶ ቅንነት፣ ግልፅነትና አርቆ አስተዋይነት ባልተለየዉ ሁኔታ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለዉን የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ እንድትቀላቀሉና በተቻላችሁ መንገድ ሁሉ ደግሞ ከጎኑ እንድትሰለፉ በራሴና በንቅናቄዉ መሪዎች ስም ጥሪዬን ሣቀርብላችሁ በምትችሉት መንገድ ሁሉ ከእኛ ጋር እንደምትተባበሩና አገራዊ ንቅናቄያችንን በሁሉም መስክ እንዲጠናከር እንደምታደርጉ በመተማመን ነዉ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on June 18, 2017
  • By:
  • Last Modified: June 18, 2017 @ 5:02 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar