Read Time:4 Minute, 2 Second
*የሳውዲ ምህረት አዋጅ ሲገባደድ የተባለውና እየሆነ ያለው !
* የታቀደውና የሆነው …
* በጅዳ ፣ ሪያድ ፣ መዲናና ጄዛን የበረራ ችግር …
* ለሳውዲ ኢትዮጵያ ካርጎ ስራውን ካቆመ ወር ደፍኗል…
* የምህረት አዋጁ መገባደድና ተስፋው ስጋቱ …
የታቀደውና የሆነው …
=============
ከሳውዲን ስደተኛ አልፎ ከሳውዲ ውጭ ያሉ ወገን ወዳድ ዜጎችና ቤተሰብን ሲያሳስብ የነበረው የሳውዲ ምህረት አዋጅ እየተገባደደ ነው። በ 90 ቀናቱ የሳውዲ የምህረት አዋጅ ዲፕሎማቶች በሳውዲ መንግስት ትብብር እየተደረገላቸው ከዚህ ቀደም ሲጣሩ የማይሰሟቸውንና “ የት ናችሁ ?” ብለው የማያውቋቸው ዜጎቻቸውን ይገኛሉ በተባሉባቸው ከተሞች ሁሉ በመሰማራት ከፍ ያለ ቅስቀሳና የሰነድ ማቀበል ስራን ሰርተዋል። በሳውዲ የሚኖሩ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ወደ ሀገር እንዲገቡ ላለፉት ሶስት ወራት ታዋቂ አርቲስቶች ሳይቀር በተሳተፉበት ፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በፈሰሰበት ዘመቻ የተሳካ ውጤት ስለመገኘቱ ይነገር እንጅ የውጤቱ ስኬት በተመላሽ ቁጥር አይታይም ። በመላ ሳውዲ 400 ሽህ ህገዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች መኖራቸውን ደጋግሞ በተነገረ ማግስት ከ 50 ሽህ ከፍ አለማለቱ እውነት ነው። ወደ ሀገር ለመግባት ሰነድ የተሰጣቸው ቁጥርም ቢሆን እስካሁን 100 ሽህ አልደረሱም ።
ዛሬ ላይ የምህረት አዋጁ 90 ቀናት ጊዜው ሲገባደድ “የተመላሽ ቁጥር አነሰ !” እያልን በምንነጋገርበት ጊዜ መሬት የሚታየው እውነት የታቀደውና የሆነውን ያሳይ ይመለኛል። ከአንድ ወድ ተኩል በላይ የካርጎ አገልግሎት የተቋረጠ ቢሆንም በማስከፈቱ ሂደት እስካሁን ውጤት አልታየም። ትናንት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ባቆመው የአሻራ አሰጣጥ በተለይም አብዛኛው ስደተኛ ባለበት በጅዳ ብዙዎች በደረሰባቸው እንግልት ለከፍተኛ ወጭ ተዳርገዋል። የተሳካላቸው ቢኖሩም ያልተሳካላቸው ተስፋ ቆርጠው የመጣው ይምጣ በማለት አሻራ ሳይሰጡ ወደ የቤታቸው የተመለሱት ቁጥር ቀላል አይደለም። ሌላው ከአሰሪዎች ጋር ሲሰሩ በተፈጠረ አለመግባባት ከስራ ሲጠፉ ክስ የተመሰረተባቸው ዜጎችም ጉዳያቸውን የሚያስጨርስላቸው አጥተው ተመልክተናል። ተሳክቶላቸው አሻራ የሰጡና የመጓጓዣ ሰነድ የያዙት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቲኬት ገዝተው ወደ ሀገር ለመመለስ የሚፈልጉ ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ ችግር ከጉዞ ተሰናክለው ተመልክተናል። ካሳለፍነው ሳምንት ወዲህ ደግሞ የቲኬቱ መታጣት ተባብሷል !
ጅዳ ፣ ሪያድ ፣ በመዲና ፤ ጄዛን ፤ የበረራ ችግር…
===========================
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ እጦት በጅዳ ፤ በሪያድ፤ በደማም ፤ በመዲናና በጄዛን ከተሞች ዜጎች እየተንገላቱ ለመሆኑ ተጨባጭ መረጃዎች ደርሰውኛል። ዜጎች የምሬት ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። ጅዳ ፣ ሪያድ ፣ መዲናና ጄዛን የበረራ ችግር በበሪያድምና በድንበር ከተማዋ በጄዛንም በተመሳሳይ ችግሮች እንግልቱ ቀጥሏል። ተቸገርን ፣ ተንገላታን ያሉ ዜጎች በሪያድና በጅዳ ብሎም በጄዛን የምስልና የድምጽ መረጃዎችን ልከውልኛል። በሪያድ የምህረት አዋጁን ተከትሎ ካለው ስጋት አንጻር የቀጣዩ ቀን በረራ ያላቸው ሳይቀር አየር መንገዱን ማጨናነቃቸውን ለመረዳት ችያለሁ ። በምዕራብ ሳውዲ የድንበር ከተማዋ ጄዛን ፤ በመዲናና በምስራቅ ሳውዲ በደማም በተመሳሳይ ሁኔታ የአውሮፕላን እጥረት ምክንያት ዜጎች በመንገላታት ላይ መሆናቸው ይጠቀሳል። የአውሮፕላን ቲኬት ጉዳይ በቦታው ከሚገኙት የጅዳ ቆንስል ተወካይ ጋር ነዋሪው ” ለምን ቃላችሁን አትጠብቁም ” በሚል አንባጓሮ ፈጥሮ እንደነበር ከቦታው የደረሰኝ መረጃ ያመለክታል። በሁኔታው የተማረሩ የጄዛን ነዋሪዎች ወደ ጅዳና መዲና ቢያቀኑም ለከፍተኛ ወጭ ተዳርገውም አልተሳካላቸውም ። ጅዳ ውስጥ ቲኬት ቆርጠው ዝግጅት ከጨረሱ በኋላ ጉዟቸው ለተሰርዘባቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆቴል እንዲያርፉ አድርጓል ። ይህ ድጋፍ ግን ለእነሱ መፍትሔ አይደለም። ለቀናት መንገላታታቸው አማርሯቸው “…የአውሮፕላን አለመኖር ብቻ ሳይሆን ምን እየተሰራ እንዳለ የሚነግረን የሰሚ ተወካይ እጦት አያንገላታን ነው ፣ ደምጻች አሰማልን !” ብለውኛል ።
ለሳውዲ ኢትዮጵያ ካርጎ ስራውን ካቆመ ወር ደፍኗል …
==============================
በምህረት አዋጁ 90 ቀናት ሂደት ፤ ኢትዮጵያ ሀገሬ ዜጎቿን ልትቀበል መደገሷ ሲነገር ፤ የጨነቀው ስደተኛ ያፈራውን ንብረትና ጨርቅ ማቁን ይዞ ወደ ሀገር ለመግባት የቀረጥ ነጻ ተፈቀደለት ። በፈቃዱ ማግስት ግን ከሳውዲ አረቢያ አዲስ አበባ የካርጎ አገልግሎት ተስተጓጎለ የሚለው ደስ የማይል ዜና ተሰማ ። በመጀመሪያው 30 የምህረት አዋጅ ቀናት ወደ ሀገር ለመግባት እቃቸውን በካርጎ የላኩት እንደ እድል ሆኖ መረከብ ቻሉ ። ካሳለፍነው ሁለት ወር ወዲህ ባለው ግዜ ካርጎ ተዘግቶ እያለ ” የከፈታል ” እና ” ሌላ መንገድ አለን” በሚሉ አታላይ የእኛ ዜጋ የካርጎ ባለቤቶች የተረከቡት እቃቸው የውሃ ሽታ ሆኖባቸው ቀርቷል። ረመዳንን ሰርተው ገንዘብ ለመቋጠር ብሎም ሌላ የምህረት ተስፋ ካለ በሚል የዘገዩት ወደ ሀገር ለመግባት ሲዘገጃጁ በስግብግብ ነጋዴዎች ተታለው ካርጎ በማስገባት ላይ ቢሆኑም እቃቸው የትም ተወርውሮ መገኘቱ የሚያም እውነት ነው ። በዚህ መልኩ ሁለት ወር ሙሉ ካርጎ ተዘግቷልና ሀገር ቤት ሆኖ የሚንገላታውን ዜጋ ቤቱ ይቁጠረው ። ሀገር ቤት ያልገባው ተመላሽ ለክፉዎች ባለ ካርጎዎች እቃውን በትኖ እጅ እግሩን ይዞ ወደ ሀገር ልግባ ሲል ደግሞ በአውሮፕላን እጥረት እንግልቱ ብሶበት የምሬት ድምጹን እያሰማ ይገኛል ።
የምህረት አዋጁ መገባደድና ተስፋው ስጋቱ …
=========================
” ወደ ሀገሬ እገባለሁ ” ያሉ ዜጎች በቅድሚያ ዝግጅትና ቅንጅት ጉድለት በመንገላታታቸውን ለታዘበ አብዛኛው ሰው ወደ ሀሩ ለመግባት ፈቃደኛ ቢሆን ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ መገመት ይቻላል። 400 ሽህ ዜጋን ወደ ሀገር ግባ ብሎ ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል በተባለበት ሰማይ ስር በሸዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የካርጎ፤ በአሻራና በበበረራ ችግር ሲከላተሙ መመልከት በእርግጥም ያሳዝናል። ይህም ኩነት የሚወራውና የሚሰራው መሳ ለመሳ ስላለመሄዱ እማኝነት የማይካድ እውነት ሆኗል። ሁሌም እንደምናውቀው እየሆነ ያለው የሚነገረውንና የተነገረውን ያህል አይደለም እላለሁ 🙁
የምህረት አዋጁ መገባደድን ተከትሎ የነዋሪው ዘንድ ጊዜው ይራዘማል የሚለው ተስፋ ከፍ ያለ ነው ። የኢትዮጵያ መንግስ ተወካዮች የሳውዲ መንግስት ጊዜ እንዲያራዝም ጠይቀናል ብለዋል ። እኔ በምኖርበት ጅዳ የሚገኙ አንድ የጅዳ ቆንስል የሽሜሲ ተወካይ የምህረት አዋጁ ይራዘም እንደሆነ ጠይቄያቸው ” ይህ የምህረት አዋጅ ይራዘማል ብዬ አልጠብቅም ” ብለውኛል ! በዚያው በሽሜሲ የአንድ እስያ ሀገር ተወካይ በበኩላቸው የምህረት አዋጁ የመራዘም ተስፋ እንዳለው ከቀናት በፊት አስረግጠው ከነምክንያቱ ጠቁመውኛል ። እንዲህ አይነቱ መረጃ በሳውዲ የተለመደ ነው ። ያም ሆነ ይህ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ብዙ ጠብቆ ጥቂት የሚባል ተመላሽ ያስተናገደው የሳውዲ መንግስ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆንን የውጭ ዜጋ በአሰሳና በወህኒ አጉሮ ይዘልቀዋል ብሎ መገመት ይከብዳል ። አቅምና ዝግጅት ተደርጓል እንኳ ቢባል ግማሽ ሚሊዮንን ያህል ቁጥር ያለው የውጭ ዜጋ አስሮ ለወራት ለመቀለብ ፤ በእስርና በገንዘብ ከመቅጣቱ የከበደ እርምጃ በፊት ሌሎች አዋጭ አማራጮችን ከመጠቀም ይቆጠባል ብየ አልገምትም !እናም የሚመጣውን እንደቀደመው በምስጋናና በተስፋ እየተገፋ ነው ! ሳይውል ሳያድር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የተመላሽ ዜጎች እንግልት መላ ሊበጅለት ይገባል ! .
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓም
የማለዳ ወግ …በሳውዲ የኢትዮጵያውያን ተመላሽ ዜጎች ፈተና ! Ethiopians returnee suffer in Saudi
Average Rating