የማለዳ ወግ…
=======================================
> በዓሉ እየተከበረ የቃረምነው መረጃ አለ …
=========================
> የሰማሁትን አካፍካችኋለሁ …
==================
> እናንተም ሀሳባችሁን አካፍሉን …
===================
* የኢድ በዓል በሳውዲ መካ ጸሎት ተጀምሮ ፣ በመላ አለም እየተከበረ ነው
* በሳውዲ ያለው አከባበር በሰላማዊ ሁኔታ ተጀምሯል ፣ ሰው የማለዳው የኢድ ጸሎት ከውኖና ቁርሱን ከቤተሰብ ጋር በሳቅ በደስታ ተቃምሶ በአብዛኛው እረፍት አድርጓል፣ እኩለ ቀን ላይም ተነቃቅቶ በዓሉን በዘመድ አዝማድ ጓደኛ ጥየቃ ይጀመራል: )
* በሳውዲ ማለዳ የተከወነው የኢድ ጸሎት ድባብም የተረጋጋና ሰላማዊ እንደነበር በተለያዩ ቦታዎች በመደወል ለማረጋገጥ ችያለሁ
* የምህረት አዋጁ የመጨረሻ ቀን ላይ ብንሆንም ከአጠቃላይ የዛሬ ማለዳና ረፋድ እንቅስቃሴ ከዓመት በዓል ውጭ ሌላ ስሜት አይነበብም
* በምህረት አዋጁ መገባደድ ስጋት የከረመው ነዋሪ ኢድን በሰላማዊ መንገድ ተረጋግቶ ማሳለፍ ጀምሯል
* በምዕራብ ሳውዲ የአሲር የአብሓ ከተማ ኢትዮጵያውያን የጣት አሻራ እስከ ዛሬ ሌሊት ሲሰጡ አምሽተዋል
* በአብሓ ዛሬ ማለዳም ጭምር አሻራ ለመስጠት በርካቶች ተገኝተዋል ፣ አሻራ መስጠቱ እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳለ በቦታው ያሉት ጉዳይ ፈጻሚ መረጃ አቀብለውኛል
* በቲኬት ምክንያት ጉዟቸው የተሰረዘበቸውና አንዳንድ ወደ ሀገር መግባት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በሪያድ ኮሚኒቲ እንዳሉ መረጃ ደርሶኛል
* በሪያድ ያለው የበረራ ችግር ባይቀረፍም መጠነኛ መሻሻል እየታየበት ነው ፣ ኢንባሲውና ነዋሪው በሚያደርገው ርብርብ ለመጓዝ የተሰረዙ ቲኬቶችን ወረፋ የማስያዙ ስራ ጥሩ ውጤ ማሳየቱን ሰምቻለሁ
* በጅዳ በቲኬት ዙሪያ ያለው ችግር አልተፈታም ፣ በአጠቃላይ ሂደቱ ከበፊቱ የተሻለ መሻሻል እየታዬ ነው ሲሉ መረጃ የሰጡኝ አሉ
* በጅዳ የሀጅ ተርሚናል ብዙ ተጓዥ አውሮፕላን በመጠበቅ ላይ ነው ። ተመላሾች ከትናንት ጀምሮ ማቀዝቀዣ ወዳለበት አዳራሽ ለመግባት እስከ 100 ሪያል ለሚያስገቧቸው የውጭ ዜጎች ለመክፈል አየተገደዱ እንዳሉ ሰምቻለሁ ፣ ሙስና መሆኑ ነው ! ግርግሩ ለዘራፊ ተመችቷልና የኃላፊዎችን ትኩረት ያሻል ! ሌላው አውሮፕላን ሲመጣ ቅድሚያ ለምዕራብ አፍሪካ ተጓዦች እየተሰጠ ነው በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ይሰማል !
* ይህ ጥንቅር እስከተሰራበት ሰአት ድረስ በምህረት አዋጁ ዙሪያ ከሳውዲ መንግሰት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም
* በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ያላችሁ ኢትዮጵያውያን በዓሉን እንዴት እያከበራችሁ ነው? እናንተ በምትገኙበት የሳውዲ ክልል ፣ አካባቢ ስላለው መረጃ ታካፍሉን ዘንድ እጠይቃለሁ
* በቲኬት እጦት በሪያድ ፣ በጅዳ ፣ በጀዛንና በደማም በእንግልት ላይ ስለሉት ወገኖች ምን አዲስ መረጃ አለ? የሚያውቁት ካለ መረጃውን ያካፍሉን ! ጥሩውን እናመስግን ስለጎደለብን አግልግሎት እንናገር !
የግርጌ ማስታዎሻ ፣
=============
በሀገር ቤትና በመላ አለም የሚትገኙ ኢትዮጵያውያን የሳውዲ የምህረት አዋጅን መገባደድ ተከትሎ ስጋት ላይ እንደሆናችሁ ከሚደርሰኝ ተደጋጋሚ መረጃ መረዳት ችያለሁ … በአረብ ሀገር ስደት እንግልት ላይ ያለ ወገናችሁ ላይ ስለሚሆነው ለማወቅና ለመረዳት ጆሯችሁ መስማት ፣ አይናችሁ ማየት የሚፈልገው በወገናችሁ ዙሪያ ስለሚሆነው መጭ እርምጃ ለማወቅ ነፍሳችሁ የምትሻ መሆኑም ጠንቅቄ ተረድቻለሁ ! ይህንን ከግምት በማስገባት አቅም በፈቀደ መጠን በሳውዲ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ትረዱ ዘንድ እነሆ መረጃውን ከምንጩ ከባለቤቶቹ ትረዱት ዘንድ በኢድ በዓል የአከባበር ውሏችን በቃረምነው መረጃ ጀምረናል !
በድጋሜ በዓሉን በማክበር ላይ ላላችሁ የተረጋጋ ፣ የሰከነና የደመቀ አውደ ዓመት ይሁንላችሁ ዘንድ ምኞቴ ነው !
ኢድ ሙባረክ 🙂
ነቢዩ ሲራክ
ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓም Updated … 2:00 PM
Average Rating