የመቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን “ነፃ” ነት
መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን በአማራ ክልል፤ ምዕራብ ጎጃም ዞን የመኢአድ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ነበር። ከዚህ በፊት በ1989ዓ.ም‹‹የመአድ አባል በመሆን መንግስት ለመገልበጥ ሞክረሃል››በሚል ከነፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጋር ተከሶ 20 ዓመት ተፈርዶበት፤በአመክሮ 14 ዓመት ከ6 ወር ታስሮ በ2003 ዓ.ም ነበር የተፈታው፡፡ በእስር ሳለም ‹‹ከእስር ቤት ልታመልጥ ሞክረሃል›› ተብሎ በጥይት እግሩን ተመቶ ለረጅም ጊዜ ይሰቃይ ነበር። ከተፈታ ከአራት ዓመታት በኋላ፤ በ2007ዓ.ም በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ከታሰሩት በአማራ ክልል የሚገኙ 16 የመኢአድ፣ የአንድነት እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አንዱ ነው። በአሁኑ ሰአት እድሜው 48 የደረሰው መቶ አለቃ ጌታቸው፤በእስር ላይ እያለ የልጅ አባት ሆኗል:: መቶ አለቃ ጌታቸው ከታሰረ ከአንድ አመት ከስምንት ወራት እስር በኋላ ጉዳዩን የሚከታተለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 9/2009ዓ.ም ቀን በሰጠው ብይን”ነፃ” ተብሎ ዳግም ከ”እስር” ተፈቷል።
የክሱ ሒደት
በመዝገቡ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ከሌሎቹ 15 የተቃዋሚ አመራሮች ጋር ‹‹የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናችሁ›› ተብለው የፀረ ሽብርተኝት አዋጁን አንቀፅ 7(1)ን በመተላለፍ በሚል ክስ ተመስርቶበታል። ከአራት ወር በላይየማዕከላዊ የስቃይ ቆይታ በኋላ ግንቦት 18/2007 ፍርድ ቤት ቀርቦ የተነበበለት ክስ የአርበኞች ግንቦት 7 አባል በመሆን የፀረ ሽብር ህጉን አንቀፅ 7(1)ን በመተላለፍ፡
“ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ(አዴኃን) አባል በመሆን እንዲሁም ጥር ወር 2006 ላይ በሑመራ በኩል ኤርትራ እንዲገባ እና ከሽብር ድርጅቱ ጋር እንዲቀላቀል የቀረበለት ጥያቄ በመቀበል በየካቲት ወር 2006 የሽብር ድርጅቱን በአባልነት በመቀላቀል፤ ከባህር ዳር ከተማ በመነሳት ወደ ኤርትራ በመሄድ ከሽብር ድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገናኘት የሽብር ድርጅቱ አባል በመሆን፤ ከዛም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ አባላትን መልምሏል።”
የሚል ነው። አቃቤ ህግ ክሱን ያስረዳልኛል ብሎ ያቀረበው ማስረጃ በማዕከላዊ የሰጠውን 10 ገፅ የእምነት ቃል እና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ የቀረበ የስልክ ልውውጥ ብቻ ነበር።
መቶ አለቃ ጌታቸው ማዕከላዊ ከመምጣቱ በፊት የነበረበት ደህንነት ቢሮም ሆነ ማዕከላዊ ከባድ ድብደባ ተፈፅሞበታል፡፡ ማዕከላዊ እያለ ብልቱ ላይ ሁለት ሊትር ‹የሃይላንድ ውሃ› አስረውበት መርማሪዎች አድርገሃል ያሉትን እንዲያምን ያሰቃዩት እንደነበረ፤ በዚህም ብልቱ እንደቆሰለ እና ሕክምና እንዳያገኝ ተከልክሎ እንደቆየ ግንቦት 18/2007 ቀን ክሱ በችሎት የተነበበ ቀን ለዳኞች አስረድቷል። በድብደባ የደረሰበትን አደጋ ለማሳየት ዳኞችን ሲጠይቅ በመከልከሉ ሱሪውን አውልቆ ብልቱ ላይ ያለውን ቁስለት ለዳኞችና ችሎቱን ለታደሙ ማሳየቱና ዘሩን መተካት እንዳይችል መደረጉን መናገሩ የሚታወስ ነው። ከማዕከላዊ ወጥቶ ቂሊንጦ ከተዛወረ በኋላ ለመንቀሳቀስ እጅግ ይቸገር እንደነበር ይናገራል።
ፍርድ ቤቱ ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓ.ም ቀን በዋለው ችሎት የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል በተበየነው መሰረት አራት የሰው ምስክሮችን አስደምጧል። ምስክሮቹ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ማዕከላዊ እያለ ለፓሊስ የሰጠው ቃል በግዳጅ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱ ናቸው።
ጉዳዩን የሚከታተለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ችሎት ዳኞች የጥፋተኝነት ፍርድ ሰኔ 9/2009 ቀን ባሰሙ ወቅት መቶ አለቃ ጌታቸውን በተመለከተ ያነበቡት ብይን በአጭሩ እንዲህ የሚል ነው
“ተከሳሹ በማዕከላዊ እያሉ አካላቸው [ብልታቸው ለማለት ነው። ዳኞች የአካሉን ስም እንደማይጠቅሱ ተናግረዋል።] በድብደባ የተጎዳ መሆኑ እና በዛ አካላታቸውም መገልገል እንደማይችሉ ፍርድ ቤቱ እየከለከላቸውም ቢሆን በችሎት ያሳዩት ጉዳይ በመሆኑ፤ ከፊሎቹ መከላከያ ምስክሮችም አብረዋቸው በማዕከላዊ ‹ሳይቤሪያ› የሚባለው ጨለማ ክፍል የነበሩ ሲሆን ብልታቸው ላይየደረሰውን መቁሰልያዩ እናበድብደባ ሳቢያ ‘ከምትሞት የሚሉህን ፈርም‘ ብለው የቀረበበትን ክስ አምኖ ቃል እንዲሰጥ መምከራቸውን የመሰከሩ በመሆኑ እንዲሁም የተቀሩት ምስክሮች በማዕከላዊ ለመከሰስ የሚዘጋጁ እስረኞች በሚቀመጡበት ‹ሼራተን› ክፍል ተከሳሹን ያገኙት መሆኑን ገልፀው ‘ከምሞት ብዬ ያሉኝን ፈረምኩ‘ ብሎ እንደነገራቸው በመመስከራቸው”
በማዕከላዊ የሰጠው ቃል በግዳጅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው በማለት አቃቤ ህግ ያያዘውን የመቶ አለቃ ጌታቸው ቃል ውድቅ እንዳደረጉት ገልፀዋል። ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ የቀረበው ማስረጃን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ፡”ከኤጀንሲው የቀረበው ማስረጃ ላይ የስልክ ልውውጡ የተደረገበት ስልክ ባልተጠቀሰበት ሁኔታ” የስልክ ልውውጡ መቶ አለቃ ጌታቸው ያደረገው ነው ለማለት እንደሚያስቸግር በመግለፅ፤ አቃቤ ህግ ያቀረበበትን ማስረጃ በበቂ ሁኔታ በመከላከሉ በነፃ እንዲሰናበት ውሳኔ ተሰጥቷል።
አስገድዶ የእምነት ቃል መቀበል
መቶ አለቃ ጌታቸው ብቻ አይደለም “መርማሪ” ባደረሰበት ድብደባ አካሉ የጎደለ። በተመሳሳይ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ የሆነው አወቀ ሞኝሆዴም በ “ምርመራ” ወቅት ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶበት በተመሳሳይ “ነፃ” ተብሎ ከእስር ወጥቷል፡፡ መቶ አለቃ ጌታቸው እና አወቀ ሞኝሆዴም ብቻ አይደሉም፤ በ “መርማሪዎች” ድብደባ ህይወታቸውን ያጡ፣ አካላቸው የጎደለ፣ የእድሜልክ በሽታ የሸመቱ፣ አካላቸው እንዲጎድል የሆነ፤የስነ ልቦና ችግር ተጠቂ የሆኑ በርካቶች ናቸው። የወንድ ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠል፣ የውስጥ እግር መግረፍ፣ ሃይለኛ ጥፊ፣ ከባድ ድብደባ፣ የሴት ጡት መግረፍ፣ ማህፀን ውስጥ ባእድ ነገር ማስገባት፣ መድፈር፣ እርቃን ማስቆም፣ ስፖርት ማሰራት፣ ጥፍር መንቀል፣ ማዋረድ፣ መስደብ፣ ማስፈራራት፣ መዛት፣ ቤተሰብ እና ጠበቃ አለማገናኘት፣ እና ስነ ልቦናዊ ጫናዎች የሚያደርሱ ሌሎች መሰል ኢ-ሰብአዊ እንዲሁም ኢ- ሕገመንግስታዊ ድርጊቶች በ ”ምርመራ” ወቅት “መርማሪዎች” ጠርጥረናችኋል የሚሏቸው ግለሰቦች ላይ የሚፈለገውን ‹ወንጀል ሰርተናል› ብለው እንዲያምኑ እና ቃል እንዲሰጡ የሚፈፅሟቸው ወንጀሎች ናቸው። ይህ አይነት ወንጀል በአብዛኛው በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የሚፈፀም ቢሆንም በሌላ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ግለሰቦች ላይም ወንጀሎቹ የሚፈፀሙባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።
ሕጉ ምን ይላል?
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስተ አንቀፅ 19(5) ላይ፡ “የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም። በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም።” ይላል። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕጉም በተመሳሳይ አንቀፅ 27(1) ላይአንድ ግለሰብ ለቀረበበት ክስ ወይም የክስ አቤቱታ ቃሉን ለመስጠት እንደሚጠየቅ ይገልፃል፤ አንቀፅ 27(2) ደግሞ፡ “ሰውየው ምላሽ እንዲሰጥ ለማስገደድ አይቻልም። ነገር ግን ምላሽ ለመስጠት ነጻ እንደ ሆነና ፈቅዶ የሚሰጠው ማናቸውም ቃል በማስረጃነት የሚቀርብ መሆኑ ጠያቂው ፓሊስ ለተጠያቂው መንገር ይገባዋል።” በማለት ይገልፃል። በቅርቡም ከሰበር ሰሚ ችሎት በተሰጠ ብይን (ያልታተመ)፤ ተጠርጣሪዎች ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡት በማስረጃነት የሚቀርብ መሆኑ ሳይነገራቸው ከሆነ ማስረጃው (ቃሉ) ተቀባይነት እንደማይኖረው የሕግ ትርጓሜ ተሰጥቶበታል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ በምርመራ ወቅት በሕግ የተከለከሉ ተግባራትን የሚፈፅሙ ፖሊሶች በወንጀል እንደሚጠየቁ ይደነግጋል።
ይሁን እንጂ በሕጎቹ ላይ የተደነገጉት የተከሰሰ ወይም የተጠረጠረ ሰው መብቶች ከወረቀት ባለፈ ሲተገበሩ ማየት የማይታሰብ ነው።
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ
በሕገ መንግስቱ እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕጎ ላይ ላይ ከተደነገገው በተፃራሪ የማስረዳት ሸክምን በሚያቀል መልኩ፤ በ2001 ዓ.ም የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀፅ 23 ላይ ተቀባይነት የሚኖራቸው ማስረጃዎችን ይዘረዝራል። በአዋጁ አንቀፅ 23(5) ላይ “በሽብርተኝነት ድርጊት ከሚጠረጠር ሰው በፅሁፍ፣ በድምፅ መቅረጫ፣ በቪዲዮ ካሴት፣ ወይም በማናቸውም ሌላ ሜካኒካል ወይም ኤሌክትሮኒክ መሳሪያ የተቀረፀ የእምነት ቃል።” ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት ያለው ማስረጃ መሆኑን ያትታል፡፡በዚህም ምክንያት አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት የሚከሱትን ግለሰብ በግዳጅ የተቀበሉትን የ ”እምነት” ቃል ብቻ [ሌላ ምንም ማስረጃ ሳይኖረው] በማያያዝ ክስ ለመመስረት ያስችለዋል። በተግባርም እየሆነ ያለው ይሄው ነው።
የፍርድ ቤት ውሳኔ
አንድ ግለሰብ የፀረ ሽብርተኝት አዋጁን በመተላለፍ የተከሰሰ እንደሆነለ “መርማሪ” ፖሊስ ወንጀል እንደሰራ አምኖ በግዳጅ የሰጠው ቃል ማስረጃ ሆኖ ይቀርብበታል፤ ክሱንም እንዲከላከል ለማስፈረድ የሚያስችል ማስረጃ ነው። ተከሳሹ በሚከላከልበት ወቅት በማስረጃነት የቀረበበት ቃል በግዳጅ ወይም በኃይል የተሰጠ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት። አለበለዚያ ተከሳሹ ለ “መርማሪ” ፖሊስ ወንጀል እንደሰራ አምኖ በግዳጅ በሰጠው ቃል ብቻ ጥፋተኛ ተብሎ የእስር ቅጣት ይበየንበታል።
በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው እንደ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ቃላቸውን መከላከል ችለው ከክሳቸው “ነፃ” ሲባሉ ያየኋቸው ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። ተከሳሹ በማስረጃነት የቀረበበት ቃል በግዳጅ የሰጠው ስለመሆኑ “መርማሪ” ፖሊስ አስገድዶ ቃሉን ሲቀበል በአይን ያዩምስክሮችን ማቅረብ ይኖርበታል። ከተከሳሹ ጋር አንድ ክፍል የነበሩ ምስክሮች፤ ለምርመራ ሲጠራ ጤነኛ እንደነበረ ሲመለስ ግን እመን እየተባለ በደረሰበት ድብደባ አካላቱ ቆስሎ/ጎድሎ እና መራመድ እያቃተው መመለሱን ማየታቸውን እንዲሁም እርዳታ ያደርጉለት እንደነበረ ሲመሰክሩ“መርማሪው ሲደበድበው አይተኻል ወይ?”፣ “የእምነት ቃል እንዲሰጥ መገደዱን እንዴት አወቅክ?” እና “አደጋው የደረሰበት ወደ መርመራ ማዕከሉ [ማዕከላዊ] ከመምጣቱ በፊት የተከሰተ ነገር አለመሆኑን በምን እርግጠኛ ሆንክ?”የሚሉ መስቀለኛ ጥያቄዎች ከአቃቤ ህግ እንዲሁም ተመሳሳይ ማጣሪያ ጥያቄዎች ከዳኞች በተለያዩ መዝገቦች ላይ ሲሰነዘሩ እንደ መስማት የሚያሳምም ነገር ምን አለ? እንዴት አንድ የፍትህ ስርዓትአካል የሆነ [ዳኞች እና አቃቢያን ህግ] ይህን መሰል ታሪክ ለብዙ ዓመታት እየሰማ እንዳልሰማ በዝምታ ማለፍ ይቻለዋል?!
ጥቂቶቹ፤ የደረሰባቸውን ቋሚ ጉዳት በችሎትለማሳየት የደፈሩ፣ በአይን የሚታይ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ወንጀሉ በተፈፀመባቸው ወቅት እድለኛ ሆነው የህክምና ማስረጃ ማግኘት የቻሉ እና“መርማሪ” ፖሊስ በግዳጅ ቃላቸውን ሲቀበላቸው በአይን ያየ/ዩ ምስክር/ሮች የሚያገኙ ተከሳሾች በማስረጃነት የተያያዘባቸውን ቃል ዳኞች ውድቅ የሚያደርጉባቸው አጋጣሚዎች ውስን ቢሆንም አልፎ አልፎ ይከሰታል። ልክ እንደ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን። ዳኞች በመቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ጉዳይ የቀረበላቸውን ማስረጃ መዝነው፤ በግዳጅ በተለይም ደግሞ አካሉን አጥቶ (ሰብዓዊ መብቱ ተጥሶ)፤የሰጠው የእምነት ቃል መሆኑንን አረጋግጠውማስረጃውን (በግዳጅ የተሰጠውን ቃል) ውድቅ አድርገው ከክሱ “ነፃ” ነህ ብለው ውሳኔ ሰጥተዋል። ነገር ግን ዳኞቹ ማስረጃውን ውድቅ ከማድረግ ባሻገር መስጠት የሚገባቸው ተጨማሪ ውሳኔ ወይም ትእዛዝ መኖር አልነበረበትም ወይ? መቶ አለቃ ጌታቸው አንድ አመት ከስምንትወራት አላግባብ መታሰሩእንዲሁምበ “ምርመራ” ወቅት የደረሰበት የአካል ጉዳት በምንድነው የሚካሰው?ወንጀሉን የፈፀመው አካል ዝም መባል አለበት ወይ? ከክሱ ነፃ መባሉ ብቻ ፍትህ አግኝቷል ያስብላል ወይ?
“መርማሪዎች” ተከሳሾች እና ተጠርጣሪዎች ላይ በሚፈፅሙት ወንጀል መጠየቅ ያለባቸው ፍ/ቤት ድርጊቱን ባረጋገጠበት ጊዜ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ቢያንስ ፍርድ ቤት ድርጊቱን ባመነበት አምኖም ተከሳሹን ከክሱ ነፃ ባወጣበት አጋጣሚ ግን ተከሳሹ የሚካስበትን እና ወንጀሉን ያደረሰው አካል/ግለሰብ ደግሞ በሕግ የሚጠየቅበትን አግባብ ፍርድ ቤቱ ራሱ ሐላፊነቱን ወስዶ ተበዳይ ወገን ፍትህ እንዲያገኝ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ።
Average Rating