የብአዴን ፅህፈት ቤት ሀላፊ እና የብአዴን/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አቶ አለምነው መኮንን ከጋዜጠኛ ተስፋይ ሃይሉ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ከወይን መፅሄት የካቲት 2009 እትም።
ወይን፡- በትግራይ እና በአማራ ህዝቦች የነበረውና ያለው ግንኙነት እንዴት ይገልፁታል?
ኣቶ አለምነው፡- አገራችን የብዙ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ነች። የትግራይና የአማራ ክልል ህዝቦች ደግሞ በኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ የየራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ እና ልማድ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። በዚህ መልካም ግብረ ገብነትና ትስስር ያሉ ጥንታዊ ህዝቦች መሆናቸው ነው የምገነዘበው። ይህ ብቻ ሳይሆን የትግራይና የአማራ ህዝቦች የዘመናት የአብሮነት ታሪካቸው በጣም ሰፊ መሰረት ያለው ነው። ለምሳሌ የክርስትና እና የእስልምና እምነትን በጋራ ተቀብለው በጋራ ተሳስሮ የመሄድ፣ ይህ ብቻ ሳይሆን የጋራ የሆነ ኣለባበስ፣ ወግ ልማድ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። በዚህ የተወሰነም ኣይደለም፤ የጋራ ጠላታቸው የሆኑትን የባዕድ ወራሪዎች በተከታታይ በጋራ እየተፋለሙ አገራችንን ጠብቀው ያቆዩ ህዝቦች ናቸው።
በቋንቋ አንፃራዊ ልዩነት ቢኖርም በባህል፣ ስነ-ልቦና፣ ሀይማኖት፣ ኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ መሰረት እጅግ ትስስር ያላቸው ናቸው። ድህነትንና ኋላቀርነትን በጋራ በመፋለም ባካሄዱት ጥረት የድህነትና የኋላቀርነት ጠበቃ የነበረው አምባገነኑን የደርግ ስርአት በማስወገድ ሂደት እጅግ ብርቱ ተባባሪነት፣ የአብሮነት ኣስተሳሰብና መንፈስ ይዘው የታገሉ ህዝቦች ናቸው። በ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሂደት ውስጥ ሰፊው የትግራይ እና የአማራ ህዝብ ልጆች እጅና ጓንት ሆነው፣ “እኔ ቀድሜ መስዋእት ልክፈል” በሚል ፅኑ እምነት በአንድ ምሽግ እየወደቁ፣ በአንድ ጉድጓድ እየተቀበሩ መላ የኢትዮጵያ ህዝብን ነፃ በማውጣት ሂደት ታሪክ ሊዘነጋው የማይችል አኩሪ ገድልና አንፀባራቂ የተጋድሎ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። የደርግ ስርአት በማስወገድ ብቻም ተወስነው ኣልቀሩም። ስርአቱን ለማስወገድ ያደረጉት የጋራ ትግል ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ በጣምራ ዘርፈ ብዙ ተጋድሎ ኣካሂዷል፤ እያካሄዱም ይገኛሉ።
በዚህ መሰረት የጋራ የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ፖሊሲዎችን ነድፈው ከገጠር እስከ ከተማ በጋራ እና በአብሮነት መንፈስ ለመበልፀግ ላለፉት 25 ዓመታት ከፍተኛ ትግል ያካሄዱበት ነው። ይህ በመሆኑ ምክንያት የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች እንዲሁም መሪ ድርጅቶቹ ህወሐትና የቀድሞው ኢህዴን የአሁኑ ብአዴን በጣምራ ትልልቅ የለውጥ አብዮቶችን አካሂደዋል። እነዚህ ድርጅቶች የለውጥ አብዮቶች አካሂደው ዘላቂ የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ በሮችን ከፍተዋል። በዚህ ደግሞ ለዴሞክራስያዊ ብሄርተኝነት መሰረት የሆነ የጋራ ህገ መንግስት እንዲኖር በአገር አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በዚህ ሳይወሰኑ ለአብሮነታቸው እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በቀጣይነት እየፈቱ ከጥንት ጀምሮ ኣብሮ ያደገውና የመጣው ብዙ ገፅታ ያለው መልካም ነገር ተጠናክሮና ዳብሮ በልማታዊና ዴሞክራስያዊ መልክ ጎልብቶና ፋፍቶ እንዲሄድ ብዙ ትግል እያካሄዱ ያሉ ህዝቦች ናቸው።
ወይን፡- ከጥቂት ወራት በፊት በአማራ ክልል አንድ አንድ ኣካባቢዎች በተለይም በሰሜን ጎንደር በትምክህተኞች የተፈፀመውን የጥፋት ድርጊት መነሻው እና ምንጩ ምንድ ነው?
አቶ ኣለምነው፡- በቅርቡ በአማራ ክልል አንድ አንድ ኣከባቢዎች የተፈጠሩ ኣለመግባባቶች የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች የማይወክሉ የተዛቡ የዘረኝነት ገፅታ ያላቸው መጥፎ ተግባራት ተስተውሏል። እነዚህ ችግሮች ስረ መሰረታቸው ምንድ ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። እነዚህ ችግሮች ሰፊውን ህዝብ እንደማይወክሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መገንዘብ አለበት። እነዚህ የትምክህት ሀይሎች ሰፊውን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ይሄ ደግሞ መላ የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች ሊገነዘቡት ይገባል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በጥቂት ሀይሎች አቀነባባሪነት የዘረኝነት መልክ ያለው ኣስነዋሪ ተግባር መከናወኑ ከህፃን እስከ ኣዋቂ አንገት የደፉበት፣ ሊወገዝ የሚገባው መጥፎ ተግባር እንደተከናወነ የቅርብ ትዝታ ነው። ታድያ እውነታው ይህ ከሆነ መነሻው እና የነገሩ ስረ መሰረት ምንድን ነው? ይሄ ነገር እንዴት ነው የጀመረው? የሚሉትን ነገሮች አሟልቶ መረዳት በጣም ጠቃሚ ነው።
እንደሚታወቀው በአገራችን ሰፊ የልማት በር ተከፍቶ ሁሉም በጥረቱና በድካሙ ጥሮግሮ የሚያድግበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ድባብ ተፈጥሯል። የተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድባብ ላይ ተመስርቶ የተፈጠረ መነሳሳትም አለ። ለምሳሌ ህዝብ በጥረቱ ልክ ተጠቃሚ መሆን የጀመረበት ሁኔታ አለ። ይሄ ደግሞ የሚበረታታ እና የሚያኮራ ለውጥ ነው። በእነዚህ የተፈጠሩ የለውጥ ተስፋዎች እና ተጨባጭ የዕለት ተዕለት ተጠቃሚነቶች የበለጠ ህብረተሰቡ እንዲነሳሳ፣ በለውጥ ማእበል እንዲበረታታ፣ የለውጥ ሀሳቦች ይዞ እንዲነሳ የሚያደርግ፣ ባገኘው ጥቅም ረክቶ የማይቀመጥ ህብረተሰብ ተበራክቷል። ከዚህ በመነሳት ብአዴን እና ያዋቀረው መንግስት በሚሰሯቸው ስራዎች የመደሰቱን ያክል በአንፃሩ ደግሞ የሚያስከፉት ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ ለመጥቀስ ያክል፤ አንደኛ ስራ አጥነት እየተበራከተ፣ በአንፃሩ የሚፈጠረው የስራ ዕድል ደግሞ አነስተኛ እየሆነ የመሄድ ጉዳይ ነው።
ሁለተኛ የግብርና ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አላደገም። እድገት መጥቷል፤ ግን በሚፈለገው ደረጃ አላደገም። በተጨማሪ የኢንዳስትሪ ልማት እና የአምራች ኢንዳስትሪ መስኮች ልማት ህብረተሰቡ ብዙ እንዲስፋፉ ይጠብቃል። ይሁን እንጂ የኢንዳስትሪ ምርታማነትም ሆነ ራሳቸው የኢንዳስትሪ ቁጥሮች አልተበራከቱም። ይህ ብቻ ሳይሆን የልማት፣ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እየተነሱ ግን በወቅቱ ያልተመለሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ነበሩ። ሌላው የዕለት ተዕለት የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል የፈጠረው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው። እነዚህ ጥያቄዎች በቂ መልስ ባለማግኘታቸው ቅሬታና አለመግባባት እየፈጠሩ የመጡበት ሁኔታ ነበር። በተመሳሳይ የወሰንና የቅማንት የማንነት ጥያቄም ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረና በወቅቱ ያልተመለሰ ጉዳይ ነው የነበረው። እነዚህ ተደምሮ ህብረተሰቡ ቅር ያሰኙት ጉዳዮች ነበሩ። እነዚህን ቅሬታዎች የተገነዘቡ የተቃዋሚ ሀይሎች ቅሬታዎቹ በቅሬታነታቸው ብቻ እንዲፈቱ ሳይሆን ያዩዋቸው ይሄን ኣጋጣሚ ወደ ከፍታ ጎትተው “ይሄ የሆነው እኮ የህወሐት የበላይነት ስላለ ነው። የህወሐት አመራሮች እና በዛ ዙርያ ያሉ ሰዎች የላቀ ተጠቃሚ ይሆናሉ። በአንፃሩ ብአዴን ይህንን የመሟገት አቅም የለዉም፤ አቅመ ደካማ ነው። ስለዚህ የልማት አድሎ እየደረሰብህ ነው” ብለው ህብረተሰቡ ያነሳቸው የዕለት ተዕለት ጥያቄዎች አዛብተውና ከትክክለኛ መንፈሱ ውጭ አድርገው የመግለፅና የተዛባ ኣካሄድ የመሄድ ሁኔታ ነው የነበረው።
ስለዚህ የችግሩ መንስኤ የህብረተሰቡ ቅሬታዎች ሁነው ሲያበቁ እነዚህን ቅሬታዎች ግን ወደአልተገባ አቅጣጫ፣ ህዝብን ከህዝብ ወደ የሚያጋጭ አቅጣጫ ጎትተው በመውሰድ “የህወሐት የበላይነት አለ፤ ስለዚህ እነሱ ላይ እርምጃ በመውሰድ ከአካባቢያችን ብናስወጣቸው የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን” ወደሚል መጥፎ አስተሳሰብ እንዲጎተት አደረጉት። በዚህ ምክንያት የጥፋት ሀይሎች እና የጥፋት ሀይሎቹ ያደናገሯቸው ጥቂት ግለሰቦች ተረዳድተው በአማራ ክልል አንድ አንድ አከባቢዎች ለምሳሌ በመተማ ዮሃንስ፣ በጎንደር አንድ አንድ ኣከባቢዎች፣ በአርማጮሆና በመሳሰሉት የተለያዩ ጥፋቶች ፈፅመዋል። ግርግሩ እና ሁከቱ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው በሰፊው የአማራ ህዝብና በክልሉ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ነው። ስለዚህ የትምክህት አስተሳሰብና ተግባር በጥፋት ሀይሎቹ ተጎትቶ ወደ ከፍታ ሲወጣ ከሁሉም በላይ ቀድሞ የሚጎዳው የራሱን ብሄር ነው የሚለው ፅንሰ ሀሳብ መሬት ላይ የታየበት ክስተት ነው ያጋጠመው። ከዚህ ባልተናነሰ ደግሞ በትግርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ጉዳት ደርሷል።
በዚህ ጉዳት ብአዴን እና የክልሉ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ሀዘን እና ቁጭት የፈጠረበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ ብቻ ሳይሆን ሰፊው ህዝብ ያዘነበት ነው። ምክንያቱም ሰፊው የአማራ ህዝብ በጠቅላላ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመልካም ግብረ ገብነት የመኖር ታሪክ ያለው ህዝብ ነው። በተለይም ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ጋር በብዙ ገፅታ ክፉ ሲገጥመው በጋራ እየመከተ፣ ደግ ነገር ሲገጥመው ደግሞ በጋራ ደስታውን እያጣጣመ የኖረ ህዝብ ነው። በተጨማሪ በጋብቻና ቤተሰብነት የተሳሰረ ህዝብ ነው። ስለዚህ ይህን የመሰለ ህዝብ የመለያየት የጥፋት ሴራ ነው የተቀነባበረው። ዋናው መሰረቱ ግን መሪዎች ያልፈታናቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መኖራቸው እነዚህን ብሶቶች የጠላት ሀይሎች ጎትተው ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ መውሰዳቸው ነው። ከዚህ ተከትሎ ደግሞ የዘር ገፅታ አስይዘው የዘመናት ድንቅ የመግባባትና የአብሮነት ታሪክ ያለው ህዝብ የመለያየት ክፉ ተግባር የጥፋት ሀይሎች በማከናወናቸው የተፈፀመ ነው።
ወይን፡- ብአዴን በሚመራው ክልል የተፈጠረው ሁከት ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር ውጪ የሆነበት ምክንያት ምንድ ነው? ሁኔታው ሲከሰት ብአዴን አስቸኳይ መፍትሄ ለማስቀመጥ እና እርምጃ ለመውሰድ ያስቸገረው ምክንያትስ ምንድ ነው?
አቶ አለምነው፡-እንደተገለፀው ህብረተሰቡ ቅሬታ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው በግምገማ ላይ እንደተለየው የብአዴን አመራርና የመንግስት መዋቅር ህብረተሰቡ የሚያረኩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ካለማከናወን የተነሳ ነው። በዚህ ቅሬታ ውስጥ ያለ ህብረተሰብ ቅሬታው እስካልተፈታለት ድረስ መሪዎቹን በቀላሉ ሊሰማ አይችልም። መሪ እና ህዝብን የሚያገናኘው ድልድይ፣ የህዝብን ችግር የመፍታት ጥረትና ከዚህ ጥረት የሚመነጭ መተማመን ነው። ስለዚህ ህብረተሰቡ በአመራር አፈፃፀም ላይ ቅሬታ ፈጥሯል። በሌላ አገላለፅ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የጥፋት ሀይሎቹን አስተሳሰብ የመስማትና እንደ ትክክለኛ የመውሰድ በምትኩ ቦታ ይዘዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በአመራሩ ሆነ በአባል ድርጅት መዋቅር ውስጥ እነዚህን የተዛቡ አስተሳሰቦች፣ የትምክህት እና ተጓዳኝ አስተሳሰቦች ተዛምተው ታይቷል። ስለሆነም በተፈጠረው የተዛባ አስተሳሰብና ህብረተሰቡ በሚያነሳቸው ጥያቄዎች እንደአመራር እነዚህ ጉዳዮች ለመፍታት ቁርጠኝነት ባለማሳየታችን የፈጠረው ቅሬታ ተደምሮ የማስተካከያ እርምጃ እንዳንወስድ እና የአቅም ማጣት እንዲያጋጥም ምክንያት ሁኗል።
ስለዚህ ችግሩን ያልተስተካከለበት ዋናው ምክንያት በአስተሳሰቡ የመበከል ሁኔታ በአመራር አካላት ውስጥ ታይቷል። ከዚህ አልፎም ችግሩን ለማስተካከል የመደማመጥ ጉድለት በየእርከኑ ነበር። ከዚህ በመነሳት በአንፃራዊነት የጥፋት ተግባር የተሻለ ተቀባይነት ነበረው ማለት ነው። ከዚህ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው ሁኔታውን ወደዚህ ደረጃ ያደረሰው።
ወይን፡- ብአዴን እንደ ፖለቲካዊ ድርጅት ለዚህ ድርጊት ዘላቂ መፍትሄዎች ብሎ ያስቀመጣቸው ምንድን ናቸው?
አቶ አለምነው፡-እንደ መፍትሄ የተቀመጠው ከመስመር ለአብሮነታችንም ሆነ በአብሮነት ለመበልፀግ፣ በአብሮነት ለማደግ እና በጋራ ትልቅ አገር፣ የበለፀገ ህብረተሰብ፣ የህዝቦች ሁሉም አቀፍ መብት የተከበረባት አገር መገንባት የሚያስችል ምርጥ ህገ መንግስት አለ። ህገ መንግስቱ ብቻ ሳይሆን ከህገ መንግስቱ የተቀዱ እና የተስፋፉ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የተካሄደባቸው የፖሊሲና የስትራቴጂ ሀሳቦች፣ የልማታዊ እና ዴሞክራስያዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አሉ።
ከዚህ ወደ ፊት ያለው ጉዳይ ልማት፣ ዴሞክራስያዊ አስተሳሰብና ተግባር በማፋጠን የሚወሰን ነው። ህብረተሰቡን ቅር ያሰኙት የአፈፃፀም ችግሮች ናቸው። የመስመር ችግሮች አይደሉም። እንዲሁም ህብረተሰቡ ቅሬታ ውስጥ የከተቱት የሀሳብ ጉድለቶች አይደሉም፤ የአፈፃፀም ጉድለቶች ናቸው። ስለዚህ እኛ መፍትሄ ያልነው ህብረተሰቡን ቅር ያሰኙ ችግሮች በሙሉ ፈልፍለን እና ለቅመን በመፍታት በህብረተሰቡና በድርጅታችን ብአዴን/ኢህአዴግ መካከል ያለው ድልድይ መጠገንና ማደስ የሚል ነው።
ከዚህ በመነሳት በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ቀይሰን እየሰራን ነን። በብአዴን ደረጃ “በጥልቀት በመታደስ ክልላዊ እና አገራዊ ህዳሴያችን እናፋጥናለን” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የንቅናቄ መድረክ ከፍተን ድርጅቱ በተዋረድ ህብረተሰቡን እያሳተፈ እያደሰ ያለው። ምክንያቱም መፍትሄ ያልነው ይህ ስለሆነ። ከዚህ አኳያ እንደ ችግር የለየናቸው አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። እነዚህ እስከ አምስቱ ተላላፊ እና ገዳይ ፖለቲካዊ በሽታዎች ብለን ነው የምንጠራቸው። ከእነዚህ ፖለቲካዊ በሽታዎች የአስተሳሰብ መዛነፍ አንዱ ነው። ልማታዊ እና ዴሞክራስያዊ መስመር ኣለ። ያንን የተሰመረ የልማት እና የዴሞክራሲ መስመር በትክክል ተግባራዊ አለማድረግ የሚለው አንደኛው ያስቀመጥነው ነው። ሁለተኛው ችግር ብለን የለየነው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነው። በዚህ ዙርያ ብዙ የተለዩ ሁኔታዎች አሉ። የምንኖርበት ሁኔታ በጥረቱና ልፋቱ ጥሮ ግሮ ከማደግ በአቋራጭ የመክበር፣ ከባለ ስልጣን ጋር ተጠግቶ የማደግ፣ በትስስር የመበልፀግ፣ በትስስር የመጠቃቀም ሁኔታ ስለሆነ ይሄን የሚቀይር ትክክለኛ አማራጭ መፍጠር አለብን ብለናል።
በመሆኑም እስካሁንም የሰራነው ስራ አለ፤ ግን የበለጠ እዚህ ላይ ለውጥ ማምጣት አለብን የሚል ነው። ሶስተኛው እንደችግር የለየነው እና መረባረብ አለብን ያልነው የህዝብን አንገብጋቢ ችግሮች ነቅሶ የመፍታት ነው። ቅድም የተዘረዘሩትን የግብርና እና የኢንዳስትሪ ምርታማነት፣ የመሰረተ ልማት፣ የማህበራዊ ልማት ጥራትና ተደራሽነት፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች የዴሞክራሲ ጉዳዮች የመሳሰሉት በአግባቡ ለይተን መፍታት ብለን ያስቀመጥነው አለ። ስለዚህ እነዚህን ድርቅ በሚያጠቃቸው አከባቢዎች፣ ዝናብ በተሻለ የሚያገኙ አከባቢዎች ብለን ምርታማነትን የማሻሻል፣ የስራ አጥነት ችግርን የመፍታት፣ የመልካም አስተዳደር ማስፈን ማተኮር አለብን ብለን ይዘናል። አራተኛው ዴሞክራስን የማስፋት እና የማጥለቅ ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲ ወደ ህብረተሰቡ እንዲሰፋና እንዲጠናከር ማድረግ ነው። ዴሞክራሲ በውስጠ ድርጅት ደረጃ የተመለከትነው እንደሆነ ከህብረተሰቡ የጠቅላላ የዴሞክራሲ ፍላጎት ሲታይ እንደ ሰርቶ ማሳያ የሚወሰድ ነው። የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እንደ ሰርቶ ማሳያ ሁኖ ሲያበቃ ግን በውስጠ ድርጅት ብቻ ታጥሮ ዴሞክራሲው ከቀረ ዋጋ የለውም። መላ ህብረተሰቡ ደርሶ ሊያሰፋውና ሊያበለፅገው ሲችል ነው ዘላቂነት የሚኖረው።
ስለዚህ በዚህ ዙርያ የሚታዩ የፀረ- ዴሞክራሲ እና በተፅእኖ የማሰራት የመሳሰሉት ህዝቡን የሚያስቀይሙ መጥፎ ተግባራት መወገድ አለባቸው ብለን በዛ ዙርያ እየሰራን ነው። ሌላው አፅንኦት ሰጥተን መወገድ አለበትና ትግል ማካሄድ አለበት ብለን እየሰራነው ያለነው ለአብሮነታችን፣ ለዴሞክራስያዊ አንድነታችን እንቅፋት የሆኑ የትምክህትና የጠባብነት በተወሰነ ደረጃ በአንድ አንድ አካባቢዎች የጎጠኝነት እና የአክራሪነት ሀይማኖት ሽፋን እያደረጉ አክራሪነት እና መሰል ኋላቀር አስተሳሰቦች ለአብሮነታችን እና ለአንድነታችን እንቅፋት ናቸው። ሲጀመር ቀድመው የሚጎዱት ሰፊው የአማራ ህዝብ ነው። በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ብሄር፣ ብሄረሰቦች ነው የሚጎዱት። ቀጥለው ደግሞ ወደ ሌሎች ህዝቦች የመሸጋገር ችግር አለባቸው። እዚህ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አለብን። ይህም ሁሉም ለማድረግ የጠቀስኳቸውን አምስት ዋና ዋና ችግሮች በዘለቄታው ለመፍታት የአስተሳሰብ ችግርን፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ከህዝብ ችግር አፈታት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከፀረ-ዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ የተለዩ መፍታት ያለባቸው ጉዳዮች እንዲሁም አብሮነታችን የሚፈታተኑ የትምክህትና ኋላቀር አስተሳሰቦች በድምሩ ከአመራር አኳያ ሲታይ የስልጣን አያያዝና አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው።
ሀላፊነትን ለህዝብ ኑሮ መለወጫ አድርጎ ከማየት ይልቅ የኑሮ መሰረት አድርጎ በዛ ዙርያ የመሄድ ጋር የተያያዙ መንስኤዎች እንደሆኑ ተለይተዋል። እነዚህን በቋሚነትና በቀጣይነት በመዋጋት ዴሞክራስያዊ አንድነታችንን የሚያጠናክር ሁሉን አቀፍ ርብርብ እናደርጋለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው። በዚህ ረገድ ባለፉት አራት ወራት በተካሄደው ሰፊ ንቅናቄ ብዙ የመጡ ማሻሻሎች አሉት። ይህንን አጠናክረን ወደ ፊት እንራመዳለን ብለን ነው እየሄድን ያለነው።
ወይን፡- በኢህአዴግ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የ15 አመት ግምገማ (ተሃድሶ) ተከትሎ ብአዴን እንደ አንድ የኢህአዴግ አባል ድርጅት እንዴት ራሱ ገመገመ? በተፈለገው አቅጣጫ ውስጡን አይቷል ብለው ያምናሉ?
አቶ አለምነው፡- ቅድም እንደጠቀስኩት በብአዴን ሁኔታ የኢህአዴግን የግምገማ ሀሳብ መሰረት በማድረግ “በጥልቀት በመታደስ ክልላዊ እና ሃገራዊ ህዳሴያችን እናፋጥን” በሚል መሪ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ ሰፋፊ የአስተሳሰብ ትግሎች ኣካሂዷል። በመጀመሪያ ያደረገው በኢህአዴግ የተዘጋጀውን በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ ሰነድ መሰረት በማድረግ በብአዴንና በአማራ ክልል ሁኔታ ሰነዱን በአግባቡ የማዘጋጀት ሁኔታና ገምግሞ ስምምነት ላይ የመድረስ ጉዳይ ነው።
በዚሁ ሰነድ እንደየአግባብነቱ እየተስተካከለ እስከ መላ ህዝቡ እንዲደርስ ተደርጓል። ይህ ማለት ለክልል አመራሩ፣ ለማእከላዊ ኮሚቴው እና ከፍተኛ አመራር፣ ለመካከለኛ አመራር፣ ለታችኛው አመራር እና ለጀማሪ አመራር፣ ለመላ አባላት፣ ብሎም ለገጠርና ለከተማ ህዝብ፣ ለመንግስት ሰራተኛው እና ለመሳሰሉት በዚህ የንቅናቄና በጥልቀት የመታደስ ሰነድ ላይ ተመስርቶ ሰፊ የውይይት መድረኮች አከሂደዋል። የሰነዱ ጭብጥ አንደኛ ባለፉት 25 አመታት በተለይም ደግሞ ላለፉት 15 ኣመታት የመጡ ለውጦች ይገመግማል። ይሄ ጉድለቶቹ ለማየት እንደ መስፈንጠርያ አቅም ሁኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተደራጀ ነው።
ሁለተኛው ድክመቶቹና የድክመቶቹን መንስኤዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ቅድም መንስኤውን ይዳስሳል። ሶስተኛው ከዚህ በመነሳት ወደ ፊት ምን ይፈልጋል? የሚለውን የሚመለከትና በዛ ላይ በየደረጃው ያሉ ተሳታፊዎች ተጨማሪ ሀሳብ የሚሰጡበትና በቀረበው ጭብጥ ላይ የላቀ መግባባት በሚደርሱበት ሁኔታ የተደራጀ ነው የነበረው። በዚህ ላይ ብዙ ርቀት ሂደናል። ሆኖም ግን ሙሉ በሙሉ ችግሮች፣ አስተሳሰቦቹ ተፈቷል ብለን አላየንም። ግን ብዙ ርቀት ተጉዘናል ብለን አይተናል።
የመጀመሪያው ይሄ ነው የነበረው። ከዚህ ቀጥሎ በየደረጃው እንደገና የአካል ግምገማ ለምሳሌ የማእከላዊ ኮሚቴ የአካል ግምገማ፣ የከፍተኛ አመራር የአካል ግምገማ ወዘተ እያለ ከጠቅላላ ሰነዱ ተነስቶ በድክመትና ጥንካሬ በተለይም ደግሞ ድክመቶች ላይ በማተኮር ድክመቶችና የድክመቶቹ ምንጮች ላይ በማተኮር የአካል ግምገማ ሂስና ግለ ሂስ በማካሄድ በዛ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ የመስጠት ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህ መሰረት የተሰጡት ውሳኔዎች በሂስ ከማለፍ ጀምሮ የማስጠንቀቂያ፣ ከደረጃ የማውረድ፣ ከሀላፊነት የማንሳት፣ በሙስና እና በተለያዩ ጥፋቶች የሚጠረጠሩ ካሉ ደግሞ ወደዛ የመውሰድ ጭምር በሚያካልል ነው እየተካሄደ ያለው።
በዚህ ሂደት እስካሁን ባለፍንበት ጉዞ በአጠቃላይ ሲወሰድ በክልል ደረጃ 55 በመቶ የሚሆኑ የካቢኔ አባላት በአዲስ ካቢኔ አባላት እንዲተኩ ተደርጓል። በዞን ደረጃ እስከ 44 በመቶ የሚሆኑ የካቢኔ አባላት በአዲስ አመራር እንዲተኩ ተደርጓል። በወረዳ ደረጃ ደግሞ እስከ 47 በመቶ የሚደርሱ አመራሮች በአዳዲስ አመራሮች የተተኩበት ሁኔታ ነው የታየው። በዚህ ደረጃ ችግሮችን በመፈተሽ የማስተካከል፣ ለውጥ የማምጣት፣ በአዲስ መልክ፣ በአዲስ መንፈስ አሻሽሎ የመሄድ ሁኔታዎች ናቸው የተሰሩት ማለት ነው። ይሄም ሁኖ የተደረጉ ማሻሻዎች በዚህ ሳይወሰኑ ህዝብን አስተያየት እንዲሰጥባቸው መሪዎች አንዱን አንስቶ ሌላው በመቀየር ሳይሆን በሂደቱ ህብረተሰቡ እንዲሳተፍበት አስተያየት እንዲሰጥበት፣ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እየተከራከሩ መቀጠል የሌለባቸው እንዳይቀጥሉ መቀጠል ያለባቸው እንዲቀጥሉ የማድረግ ስራ ነው የተሰራው። በሂደቱ እኛ ትኩረት የሰጠነው በጥልቀት መታደስ ሲባል ድርጅቱን በድምር ተጠናክሮ እንዲወጣ የማድረግ አቅጣጫ ነው እንጂ በልዩነትና የድርጅቱን አቅም በመከፋፈልም ሊፈታ ይችላል።
ይሄኛው መንገድ እኛው አልመረጥነውም። ምክንያቱም ሰው ድክመቱን እስካየ ድረስ፣ በወሳኝነት በጥፋቱ እስከ ተፀፀተ ድረስ፣ የጎላ ወንጀል ካልፈፀመ፣ አሻሽሎ ወይም ዝቅ ባለ ደረጃ ወይም ባለበት የሚቀጥልበት ሁኔታ ነው ያየነው። በአጠቃላይ ሂደቱ ድርጅቱን አጠናክሮ እንዲወጣ ነው እንጂ ሌላ ቁርሾ እና ሌላ ንትርክ በሚፈጥር እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ተደርጓል።
ስለዚህ በእኛ አተያይ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው በሂደት ላይ ቢሆንም እስካሁን ባለፍንበት ሂደት እንደኛ በችግሮቹና በመፍትሄ ቀመሮቹ ላይ ጥሩ መግባባት ፈጥሯል። ይሄ ደግሞ አንድ ጥቅም ነው። በዚህ መሰረት ድርጅቱን አንዣብቦበት ከነበረው የመናጋት አደጋ አትርፎ አጠናክሮ በተሻለ ቁመና አመራር ሊሰጥ በሚችልበት ሁኔታ ላይ አደራጅቶታል። ስለሆነም የችግሮቹ አደጋዎች በብቃት መፍትሄ ካልሰጠናቸው በስተቀር ችግሮቹ ተመልሰው ሊወጡ እንደሚችሉና ከዚህ አደጋ ለመውጣት ጠንክረን መስራት እንዳለብን መነሻ መግባባት ተፈጥሯል። ይሄ በሂደት የሚዳብር መሆን አለበት። ይሄ ብቻ ሳይሆን፤ በኪራይ ሰብሳቢነት በአስተሳሰብና በተግባር በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው የሚለውን ለመረዳትና የመፍትሄ እርምጃዎች ለመውሰድም የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። ስለዚህ በብዙ መገለጫዎች ወደ ፊት የሚያራምድ ሁኔታ ፈጥሯል። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጠንክረን ካልሰራን የማይቀለበስ አይደለም። ምክንያቱም የተጀመረው ንቅናቄ ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል። ስለዚህ እንዳይመለስ አሁን በተግባርና በልማት፣ በዴሞክራስያዊ ተግባራት፣ በመልካም አስተዳደር መሰረት አድርገን ችግሮቹን እየፈታን የበለጠ እያጠናከርን እንሄዳለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው።
ወይን፡- ከተሃድሶ በፊት እና በኋላ ብአዴን ያለው ሁኔታ እንዴት ተገመገመ? ውጤቱስ ምን ይመስላል? የተካሄደውን የተሃድሶ መድረክ ተከትሎ በጠቅላላ ህዝቡ፣ አባሉና አመራሩ የተፈጠረውን ስሜት እንዴት ይገልፁታል?
አቶ አለምነው፡- እስካሁን በቆየንበት ሂደት ስናይ ከሞላ ጎደል በውስጠ ድርጅቱ ታጥሮ የቆየ ነው። ህብረተሰቡ ሙሉ ይዘቱን እስከ ቅርብ ጊዜ ሰነዱ አልቀረበበትም ነበር። ግን በተለያዩ መገናኛ ብዙኋን እና በተለያዩ መድረኮች በሚያዳምጠው፣ ድርጅቱ የጠፋውን ጥፋት ለማስተካከል ራሱ ወደ ውስጥ እያየ እንደሆነ ግንዛቤ ነበረው። ያልተሟላ መረጃም ቢሆን የሚገነዘባቸው ጉዳዮች ነበሩ። በዚህ ጉዳይ የበለጠ ግልፅ የሆነለት አሁን ነው። አሁን ወደ ህብረተሰብ እየቀረበ ነው። ወደታች እየቀረበ ለአስተያየት ክፍት እየሆነ ነው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ሲታይም “ድርጅቱ ወደ ቀድሞው ይዞታው እየመጣ ነው” የሚል አዝማሚያዎች እየመጡ ናቸው። ሆኖም ግን ሙሉ በሙሉ ወደዛ ደርሷል ማለት አይቻልም። በአጠቃላይ ሲታይ ብአዴን ወደ ድሮ ይዞታው እየመጣ ነው። ምክንያቱም መሪዎችን ቀርበውልን ከገመገምን፣ የማንስማማባቸው መሪዎች ከተቀየሩ፣ ጥሩ መሪዎች ካገኘን ይሄ አንዱን የሚያስማማን መሰረታዊ ጉዳይ መጣ የሚል ተስፋ የማሳደር ሁኔታዎች አሉ፡፡
ይሄ ግን የበለጠ ሊጠናከር የሚችለው በተጨባጭ ተግባር ሲደገፍ ነው። ዞሮ ዞሮ ህብረተሰብ የሚለካው ተጨባጭ ወደ ግል ሂወቱና ወደ አከባቢው ልማት ባመጣው ነገር ነው። ስለዚህ ለውጡን የሚለካው በግል ሂወቴ ምን ለውጥ መጣ? በአከባቢው ልማት ምን ለውጥ መጣ? ብሎ ነው የሚለካው። በዚህ መለኪያ ሲታይ ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል። ገና ወደ ስራ እንገባለን ያለነው አሁን ነው። የበለጠ መተማመኑ ከዚህ በኋላ ባለው ሂደት ሊመጣ የሚችል ነው። እስካሁን በመጣንበት ርቀት ግን ይሄ ድርጅት ታድሶ ወደ ተሻለ ቁመናው ይመጣል የሚል ተስፋ ማሳደር እየጀመረ እንዳለ ነው።
ወይን፡- በክልሉ በትምክህተኞች የተከሰተውን ህገ ወጥ ድርጊት ለማስቆምና ህዝቡ በተረጋጋ ሁኔታ ልማቱን እንዲያካሂድ ታስቦ የወጣው አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ እንዴት እየተተገበረ ነው? በተለይም በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት የተሳተፉ እና የመሩ ሰዎች በህግ ስር ለመዋል ምን ተሰርቷል? ውጤቱስ?
አቶ አለምነው፡- በእኛ እምነት እንደ ብአዴን ትልቁ ማረጋጋት አስተዋፅኦ አደረገ የምንለው የተጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ ነው። ዋናው ይሄ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ የሚለው ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሁኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ የማይተካ ሚና ተጫውቷል ብለን እናምናለን። እነዚህን ተደጋግፈው ያመጡት መረጋጋት ነው ብለን እናምናለን። ይህንን ታሳቢ አድርገን እስካሁን ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚልዮን ህዝብ ኣከባቢ በገጠር በከተማ በአስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል። በአጠቃላይ ድምዳሜው ሲታይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፣ ሰላም አረጋግቷል፣ የልማት እንቅስቃሴ እንዲጀመር አድርጓል፣ ሰዎች በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ የዕለት ተዕለት ሂወታቸው እንዲመሩ ዕድል ፈጥሯል። ስለዚህ ይሄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል አስተሳሰብ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የሚያሳስቡት ነገሮች አሉ። በዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አድርጎ የቂም በቀል መወጣጫ እና መጠቃቅያ እንዳይሆን፣ ሰዎች በድብቁ እየጠቆሙ የግል ቅሬታቸውን የሚገልፁበት እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ የሚል የጥንቃቄ ሀሳብ አምጥቷል።
ይሄ ሁሉ ሁኖ ግን በድምሩ ሲታይ በክልሉ በፊትም የተረጋጋ አካባቢ የበለጠ መረጋጋትና ጥንካሬ እንዲኖራቸው አስችለዋል። ከዚህ ባለፈ አንድ አንድ ሁከት እና ግርግር የነበረባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሁከት እና ግርግር አቁሞ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖር ህገ ወጦችን ህብረተሰቡ ባደረገው ትግል ወደ ህግ እየቀረቡ እንዲታረሙ እና መደበኛ የልማት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅም የፈጠረ ነው። ከዚህ በበለጠ ለማጠናከር ደግሞ በጥልቀት ከመታደስ ንቅናቄው ጋር አስተሳስረን በላቀ ደረጃ ወደ ፊት እንወስዳለን ብለን እየሰራን ነው።
ወይን፡- በህገ ወጥ ስራዎች የተሳተፉ ሰዎች እና አመራሮች በቁጥጥር ስር ለማዋል የህዝቡ ተሳትፎ እንዴት ይገልፃል?
አቶ አለምነው፡- በመጀመሪያ አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር ይዞታና ሀሳብ እስኪረዳ ድረስ ጉዳዩን ለመረዳት ጊዜ የመውሰድ ሁኔታ ነበረ። እኛም በጥልቀት መታደስ ላይ አተኩረን ስለነበረ ፈጥነን አላወያየነውም። እዛ ላይ የተወሰነ ግር የማለት ወይም ግራ የመጋባት ነገር ነበረ። ከዚህ የተነሳ የህብረተሰቡ የራሱ ሚና ምን መሆን እንዳለበት በብቃት አልተሰራም ነበር። በኋላ ወደ ህዝቡ እየወረድን የሚጠበቅብንን እየሰራን ስንሄድ መጀመሪያ ራሱን የበለጠ የሰላም ፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ ሀይል አድርጎ አጠናክሮ የመሰለፍ ሲጀምር ራሱን አሻሽሎ የመሰለፍ ሁኔታ ነው የነበረው። በዚህ ሳይወሰን ግን ከዛ ቀጥሎ ያደረገው ጥፋትን የመጠቆም እና ጥፋተኞች እንዲጠየቁም ድጋፍ እንደሚሰጥ የመግለፅ ሁኔታ አለ። እዚህ ላይ ሲገለፅ ግን ከጥንቃቄ ጋር ነው። ያለ ስራቸውና ያለ ጥፋታቸው የሚጠየቁ ሰዎች እንዳይኖሩ ጥንቃቄ ይደረግ የሚለውንም በደንብ ያሰምርበታል። ስለዚህ ህብረተሰቡ ውስጥ በድምሩ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ሁኔታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይፈልጋል። እንዲሁም ህገ ወጦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ይፈልጋል። ይሄ እንደተጠበቀ ሁኖ ሂደቱ በመጠቃቃትና ቂመኝነት ያለው እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ ደግሞ ያሳስባል።
ወይን፡- ሌላው የወልቃይት ጉዳይ ነው “ወልቃይት የአማራ ነው” የሚሉ የተወሰኑ ግለሶቦች አሉ። ደጋግመው ጥያቄዎች ሲያነሱም ይሰማሉ። ጥያቄው ማንሳት ያለበት ግን የወልቃይት ህዝብ ኣይደለም? ይሄ እንደ ብአዴን አመራርና የብአዴን /ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንዴት ያዩቷል? እንደ ድርጅት ስንመለከትስ ለምን ዘላቂ መፍትሄ አላስቀመጠም?
አቶ አለምነው፡- በዚህ ጉዳይ ብአዴን ከምስረታው ጀምሮ ግልፅ አቋም ኣለው። በወልቃይት ወይም የሆነ አካባቢ ብሎ ሳይሆን አጠቃላይ የብአዴን አቋም ምንድ ነው? ህዝቦችን ማንነታቸው የብሄር፣ ቋንቋ፣ የባህል፣ የስነ-ልቦና ማንነታቸው ተከብሮ፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራስያዊ አንድነት መኖር አለበት የሚል ከምስረታው ጀምሮ ፅኑ አቋም ይዞ የታገለበት ነው። ድርጅቱ አሁን 36ኛ አመቱ አክብሯል፤ ባለፈባቸው ጉዞዎች ውስጥ የድርጅቱ አቋም ይሄ ነው። በቅርቡ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ተነሳ በተባለበት ወቅት የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ የካቲት 2008 ዓ/ም ተሰብስቦ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ ላይ ምንድ ነው ያለን ሀሳብ? ይሄ ጥያቄ እየተነሳ ነው የሚለው ከማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ሲነሳ ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ አድርጎ አቋም ወስዷል። አቋሙ የባለፉት 36 አመታት አቋሙን የሚያጠናክር ነው የነበረው። የወሰደው አቋም የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ካነሳ በሚተዳደርበት ክልል ከአካባቢው ጀምሮ በተዋረድ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሚፈቅደው አኳኃን ጥያቄ ማንሳት ይችላል። በዚህ መሰረት ህገ መንግስቱ መፍትሄ ይሰጧል። ብአዴን ክልላዊ ድርጅት ነው። የአማራ ክልል ህዝቦችን የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ነው። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ቀጥታ ተሳትፎ የለውም። በወልቃይት ውስጥ ገብቶ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርግ አይችልም። በአገር ደረጃ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሳሰሉት ጉዳዩ ከተነሳ እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ከመርሁ ተነስቶ አቋም ሊይዝ ይችላል።
ከዛ ውጭ ግን ይሄ ጉዳይ በህወሓትና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ነው የሚፈታው ብሎ ያለ ልዩነት በሙሉ ድምፅ ነው ማእከላዊ ኮሚቴው የወሰነው። ይህ ማለት የባለፉት 36 ኣመታት አቋሙ በ2008 ዓ/ም የካቲት ላይም ተደግሟል ማለት ነው። ይሄን አቋም ይዞ ነው ሲሰራ የቆየው። ይህ እንደተጠበቀ ሁኖ ግን ጉዳዩን በአጠቃላይ ቅድም እንደጠቀስኩት በእኛ አካባቢ ህብረተሰቡ ቅር የተሰኘባቸው የስራ አጥነት ችግሮች የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመበራከታቸው የተነሳ የተለያዩ ሰበቦች ይፈለጉ ስለነበር የወልቃይት የማንነት ጥያቄም በእኛ አካባቢ አንድ የሁከትና ግርግር መነሻ ምክንያት ሁኖ አገልግሏል። ይሄም ሁኖ ግን የጥፋት ሀይሎቹ ሁሉንም ጉዳዮች ወደ ላቀ ከፍታ ወስደው የማጋጨትና ህዝብን ከህዝብ የማነታረክ አላማ ስለነበራቸው ያንን አላማ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ማሳካት ችለዋል። አሁን አሁን ጉዳዩ ግልፅ እየሆነ ነው ያለው።
አሁን በጥልቀት መታደስ ንቅናቄው ላይ የበለጠ ፍንትው ያለው ነገር ምንድ ነው? በ2008 ዓ.ም የካቲት ላይ ብአዴን የወሰነው ውሳኔ በኋላም በተሃድሶ መድረክ በግልፅ የተቀመጠ ጉዳይ ነው። ያ ማለት የወልቃይት አካባቢ ህዝብ ጥያቄ ካለው ጥያቄዎችን በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሊያቀርብ ይችላል። የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይህንን የመመለስ አቅምም ችሎታውም አለዉ። ብአዴን በዚህ በኩል ቀጥተኛ ተሳትፎና ሚና የለውም። በአማራ ክልል ሁኔታም ቢሆን ቀጥተኛ የሆነ ሚና የለውም። ይሄ ህገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ መሰረት ያደረገ ጉዳይ ነው ብለን ነው ለህብረተሰቡ እያስረዳን ያለነው። አሁን ሁኔታውን የመረዳት ሁኔታ አለ። ይሄ ጉዳይ የበለጠ ወደ ጥፋት የሚጎትቱ ሀይሎች የሉም እያልኩ አይደለም፤ አሉ። ግን በአብዛኛው ጉዳዩን ህብረተሰቡ እየተገነዘበው ያለ ጉዳይ ነው። የብአዴን አቋም ደግሞ በዝርዝር የገለፅኩት አቋም ነው።
ወይን፡- የግጨው ሁኔታስ እንዴት ነው? ለምን እስካሁን ሁለቱም ድርጅቶች ተወያይተው ዘላቂ መፍትሄ አላስቀመጡለትም?
አቶ አለምነው፡- የአማራ ጠገዴ እና የትግራይ ፀገዴ ኩታ ገጠም ያሉ አካባቢዎች ጉዳይ ከመጀመሪያው ጉዳዩ መዘግየት አልነበረበትም። ጉዳዩን የሚነሳ መሆን አልነበረበትም ኣይባልም። ሊነሳ የሚችል ነው የነበረው። በየቦታው የወሰን የመሳሰሉት ጥያቄዎች በብዛት አሉ። ዋናው እዚህ ላይ እኛ እንደ ጉድለት የምናየው ጊዜ መውሰድ አልነበረበትም። አፈታቱ ጊዜ መውሰድ አልነበረበትም። ለምንድነው ጊዜ የወሰደው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ይሄ ችግር ጊዜ የወሰደበት ዋነኛ ምክንያት በሁለታችን እህት ድርጅቶች ውስጥ የአስተሳሰብ መዛነፍ አጋጥመዋል። ከዚህ በመነሳት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ እና ተግባር ውስጥ የመግባት ሁኔታ ታይቷል። እዚህ ላይ የህዝብን አንገብጋቢ ችግሮችን ሳይፈቱ በትንንሽ አጀንዳዎች ችግር ፈች መስለው መታየት አመለካከት ነበረ። ከዚህ አልፎም የትምክህት አስተሳሰብና ተግባር በየደረጃው ያለው አመራር ተስተውሏል። ስለዚህ ይሄ ችግር ከመኖሩ ተያይዞ የወሰኑ ጉዳይ በአማራ ጠገዴ እና በትግራይ ፀገዴ መካከል ያለውን የወሰን ጉዳይ አንደኛው ከአቅሙና ከደረጃው በላይ አጋኖ የመረዳት ጉዳይ ነው።
ይሄ በሁለት ጠባብ አካባቢዎች ያለው የወሰን ጉዳይ ነው። ስለሆነ ጤናማ አስተሳሰብ ቢኖር ኑሮ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ነው። ነገር ግን የአስተሳሰብ መዛነፍ ስላለ ከአቅሙና ከደረጃው በላይ ተጋኖ እንዲታይ አድርጓል። ሁለተኛው ሌላ ትልልቅ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራ ሞልቶ ይሄ ጉዳይ ከሚገባው ጊዜና ቦታ የወሰደ አስተሳሰብ መዛነፍ ስላለ በዚህ ጉዳይ አልባሌ ጊዜ ማሳለፍ ታይቷል። ስለዚህ አሁን ጉዳዩ በአጭር ጊዜ መፈታት አለበት።
ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ መሬቱ ያለው ከሁለቱም ህዝቦች የሚያልፍ አይደለም። እዛ ኩታ ገጠም ብቻ ያሉት ህዝቦች የሚጠቀሙበት ነው። እና ይሄ ሁሉ በአስተሳሰብ እና በአተገባበር ብልሽት የተፈጠረ ነው። በዚህ ምክንያት ከልክ በላይ ተጓትቷል። ህብረተሰቡም አመራሩ የተዛባ አስተሳሰብ በያዘ ቁጥር ትልቅ ነገር ያለ መስሎት በዛው ልክ ቀላል ያልሆነ ቁጥር ያለው ሰው የተደናገረበት ሁኔታ ታይቷል። አሁን እየሰራነው ያለነው ምንድ ነው? መጀመሪያ በአስተሳሰብ የተበላሸን ነገር እናስተካክል ብለን ለአስተሳሰብ ጊዜ ሰጥተን እየፈታን ነን። ጥሩ ስራ የጥሩ አስተሳሰብ ውጤት ነው። መጥፎ ስራ የመጥፎ አስተሳሰብ ውጤት ነው። ስለዚህ በትግራይ ፀገዴ እና በአማራ ጠገዴ መካከል ያለውን የወሰን ጉዳይ በአስተማማኝነት መፍታት የሚቻለው የተስተካከለ አስተሳሰብ ስያዝ ነው። ይሄን አስተሳሰብ ለመፍጠር የሰውን ትክክለኛ የስነ-ልቦና የማስተካከል ስራ እየሰራን ነን፤ በተሃድሶ መንፈስ። ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ከያዝን በኋላ በቀጥታ የወሰን ጉዳይ ይፈታል። የወሰን ጉዳይ የሚፈቱት ራሳቸው የሚያርሱት ሰዎች ናቸው። ማሳው ላይ የሚያርሱት ሰዎች ነው የሚፈቱት። ምክንያቱም መሬቱም ጋ ያሉ እነሱ ናቸው፤ አለመግባባትም የተፈጠረው በሁለቱ መሪዎች ነው። ስለዚህ መሪዎቹ በትክክለኛ አስተሳሰብ ውስጥ ከገቡ ችግሩን እየፈቱት ይሄዳሉ ብለን ነው የምናምነው።
ወይን፡- በመጨረሻ ለሁለቱም ህዝቦች እና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያስተላለፉት መልእክት ካለ
አቶ አለምነው፡- መጀመሪያ ለመላው የትግራይ ህዝብና ለህወሓት ታጋዮች እንኳን ለ42ኛው አመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ! እንኳን አብሮ አደረሰን እላለሁ። አሁን በምንገኝበት ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በዋናነት በውስጣዊ ምክንያቶች በተደራቢ ደግሞ በውጭ ወይም በጥፋት ሀይሎች አቀነባባሪነት ጣምራ እንቅስቃሴ ለዘመናት በአብሮነት የሚታወቁ ህዝቦች እጅግ የሚያስቀና የጋራ ትግል፣ የጋራ መስዋእትነትና የጋራ ድል ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ልያለያይ የሚችል የዘረኝነት አስተሳሰብና ተግባር በጥፋት ሀይሎች ተሰንዝሮ ዕድል አግኝቷል። ነገር ግን ይሄ ጊዚያዊ ችግር ነው እንጂ የማናልፈው ችግር አይደለም። ምክንያቱም ሰፊው የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች እጅግ ዘርፈ ብዙ የአብሮነት ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። መሰረታዊ ጥቅሞቹ በአብሮነት የሚያስቀጥሉ እንጂ የሚያለያዩ አይደሉም። የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ አጀንዳዎቹ የአብሮነት ጉዞ የሚጠይቁ ናቸው።
ስለዚህ የማስተላልፈው መልእክት የጋራ እሴቶቻችንን ጠብቀን የጋራ ጠላቶቻችንን እና ዕንቅፋቶቻችን በመመከት እና በመጥረግ ተባብረን የህዳሴ ጉዟችንን የጋራ ቤታችንን ለማሳካትና ጠላትን ድል ለማንሳት ተባብረን መነቃነቅ አለብን። ስለዚህ ለሁለቱም ህዝቦች በጋራ መስራት አለብን የሚለውን መልእክትን ነው የማስተላልፈው። በመጨረሻ ለአገራችን ህዝቦች ከዘመናት የማሽቆልቆል ጉዞ በኋላ አገራችን የለውጥ ጎዳና ይዛለች። ትልቅ የህዳሴ ፕሮጀክት አለን። ጠቅላላ የለውጥ ጉዟችን የህዳሴ ፕሮጀክት ነው። ይሄ ፕሮጀክት ከተሳካ አገራችን ድሮ ትልቅ ነበረች፤ አንድ ወቅት አሽቆልቁላ ነበረች፤ ትልቅ ትሆናለች። በዚህ ደግሞ ህዝባችን ከድህነትና ኋላቀርነት ወጥቶ፣ ከጉስቁልና ወጥቶ እድገትና ብልፅግና ውስጥ የገባ ህብረተሰብ ይሆናል። ይሄ ሊሆን የሚችለው ሰላም ሲጠበቅ ነው። ይሄ ሊሆን የሚችለው የልማት ጥረታችን ተጠናክሮ ሲቀጥል ነው። ይሄ ሊሆን የሚችለው የዴሞክራሲ ጉዟችን ሲጠልቅና ሲስፋፋ ነው። ይሄ ሊሆን የሚችለው ህዝብና መሪዎች እጅና ጓንት ሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈቱ ነው። ስለሆነም የመጀመርነው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ እንቅፋት እንዳይገጥመው እጅ ለእጅ ተያይዘን መልካም ሁኔታዎችን እንድናጠናክር፣ እንቅፋቶችን ደግሞ ተባብረን እንድናስወግድና የህዳሴው ጉዞ እንድናፋጥን ነው ጥሪየን ማስተላለፍ የምፈልገው።
ወይን፦ ዘርዘር ያለ እና ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ማብራሪያ ስለሰጡን እናመሰግናለን።
አቶ አለምነው፦ እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!
*******
Source: HornAffairs.com
Average Rating