የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰፊ ውይይት ካካሄዱበት በኋላ በተወካዮቻቸው አማካይነት ያፀደቁት ህገ-መንግሥት የሁሉንም ሕዝቦች መብቶችና ጥቅምች የሚያስጠብቅ ነው፡፡
ህገ-መንግሥቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቃል-ኪዳን ሰነድ ሲሆን ዓላማውም በሕዝቦች መፈቃቀድና ፍላጎት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጎልበት እንዲቻል በጋራ ያፈሯቸው እሴቶችና ሃብቶች እንዲሁም ትስስሮች እንዳሏቸው በማመን በታሪካቸው ሂደት ውስጥ ያጎለበቷቸውን የጋራ ጉዳዮች ይበልጥ ለማበልፀግና የተዛቡ ግንኙነቶችንም በማረም አንድ ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እና የጋራ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባትና ለማጠናከር የታለመ ነው፡፡ ይህንን በማድረግም በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሠፍንና ፈጣንና ህዝቡ በየደረጀው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን በራሳቸው ፈቃድና በፍላጎታቸው የመረጡት መሆኑን በፅኑ የሚያምኑበት ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ልዩ ጥቅም በህገ-መንግሥቱ እንዲሰፍር ያደረጉት የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ መላው የሀገራችን ሕዝቦች ናቸው፡፡ የመረጡት የፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የፌደራል መንግሥትና የክልሎች መንግስታት እንደሚኖሩ የሚደነግግ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነች ከተማ መመረጥ ስለነበረበትም የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ መላው የሀገራችን ህዝባች በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ ያለችውን አዲስ አበባ ከተማን የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ አድርጎ መርጧታል፡፡ ይህም በህገ መንግሥቱ እንዲሰፍር አድርገዋል፡፡
ይህንን ውሣኔያቸውን መሠረት በማድረግም በህገ-መንግቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀስ 5 ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፡፡ “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” በማለት ደንግጓል፡፡
ይህንን የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ የቃል-ኪዳን ሠነዳቸው ያሰፈሩትን ጉዳይ በዝርዝር ሕግ መመለስ የሚያስፈልግ በመሆኑ የሕገ-መንግሥቱን መንፈስ ተከትሎ ዝርዝሩ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ ዝርዝሩን ለመሥራት ግብዓት እንዲሆን በክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድና በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በፌዴራል ደረጃ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተው በመጨረሻ በኢህአዴግ ሥራ-አስፈጻሚ ደረጃ በዝርዝር ታይቶ የመንግሥት ህጋዊ ተቋማት መክረውባቸው ህግ-ሆኖ እንዲወጣ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በዚህም መሠረት የኢፌዲሪ የሚንስትሮች ም/ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት የሚከተሉትን ጉዳዮች ተመልክቶ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መክሮበት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ አስተላልፉዋል፡፡
ህገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5 ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች
1ኛ/ ከአገልግሎት አቅርቦት ልዩ ጥቅም አኳያ፣
2ኛ/ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ልዩ ጥቅሞች አኳያ፣
3ኛ/ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ፤ የኦሮሚያ ክልል ያለው ልዩ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲቀረፁና እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
የህገ-መንግሥቱ ዋና ማነሻም አንድ ጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው ጥረት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ የምትገኝ ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሦስተኛ ማዕከል የሆነች፣ የአፍሪካውያን የፖለቲካና ዲፕለማሲ መዲና የሆነች መሆኗንም ታሣቢ በማድረግና እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሐሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው ፈቃድና በፍላጎታቸው የመሠረቱት የፌዴራል ስርዓት ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫና ሕገ-መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በሽግግር ወቅትም የክልል 4 ዋና መዲና እንዲሁም ህገ-መንግሥቱ ከፀደቀም በኋላ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ሆና እየገለገለች ያለች ናት፡፡
ከዚህም ተነስቶ አዲስ አበባ እነዚህን የዓለምአቀፍ፣ የአህጉራዊ እንዲሁም የሀገራዊ ከዚያም አልፎ በፌዴራል ሥርዓታችን መሠረት የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም አካቶ የያዙ ሃላፊነቶችን መወጣት ያለባት ከተማ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅ የሚወጣው ህግም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪያዎችን መብቶችና ጠቅሞች በምንም መልኩ የማይሸራርፍ ይልቁንም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በመጠበቁ ምክንያት የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕዝብና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ትስስርና መስተጋብር ይበልጥ ህጋዊ መሥመር ይዞ እንዲጠናከር የሚያደርግና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ይሆናል፡፡ የከተማዋና የክልሉ የመንግሥት አካላትና ነዋሪ ሕዝቦችም ዘላቂ ያለው ሰላም እንዲሰፍን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት እንዲሁም ፈጣንና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል፡፡
የአገልግሎት አቅርቦት ጉዳዮችን በተመለከተ
በማህበራዊ አገልግሎቶች ልዩ ጥቅም ማለትም ከትምህርት አኳያ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የአርሶ አደሩ ልጆችን እንዲሁም አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ ምክንያት ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ ዜጎች የከተማ አስተዳደሩ በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ማደራጀት እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ላይ ያለው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ አብዛኛውን አገልግሎቱን በተለይም የሆስፒታል አገልግሎቶችን ከከተማዋ የሚያገኝ በመሆኑ በኦሮሚያ እምብርት ላይ የተቆረቆረች ይህች ከተማ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በእቅዷ ውስጥ ማካተት ይኖርባታል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ከማህበራዊ አገልግሎቶች የሚመደበው ሌላው የባሕል፣ የቋንቋና የሥነጥበብ አገልግሎቶች ሲሆን ከዚህ አኳያም የማህበራዊም ሆነ የኢኮኖሚ አገልግሎቶች ለማቅረብ እንዲቻል ልዩ ጥቅሙን ለማስጠበቅ በዚህ አዋጅ መሠረት አገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በቋንቋቸው አገልግሎቱ እንዲቀርብ አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ የሚያገልግል ይሆናል፡፡
በመግቢያ ላይ ለማመላከት እንደተሞከረው የአዲስ አበባ ከተማ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ እንዲሁም ሀገራዊና የከተማ ነዋሪዎቹን ለማገልገል ከምታደርገው ጥረት ባሻገር የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት የሚያንፀባርቁ አሻራዎች በከተማዋ ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከክልሉ ሕዝብ ጋር በተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ስም መታሰቢያዎች አንዲኖሩ አመቺ የሆኑ እንደ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሰፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች አንደአስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የከተማዋ አስተዳደር የኦሮሞ ሕዝብ ባሕልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ የባሕልና ታሪክ ማዕከላት፣ ቲያትርና ኪነጥበባትና የመዝናኛ ማእከላት የሚነገቡበትንና የሚተዋወቁበትን ሁኔታዎች የሚያመቻች ይሆናል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተያያዘም የከተማዋ ስያሜ ፊንፊኔ ተብሎ ስትቆረቆር በነበረው ስያሜዋ የሚጠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዓለም አቀፍ፣ በአህጉራዊና በሀገር ደረጃ በፌዴራል መንግሥቱና በአዲስ አበባ አስተዳደር አዲስ አበባ ተብሎ የሚጠራ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ይህም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ በሁለቱም እርከኖች ያለው የከተማዋ መጠሪያ ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉ ተገቢና ይኼው እንደተጠበቀ ሆኖ የሁለቱም የከተማዋ መጠሪያዎች “ፊንፊኔ” እና “አዲስ አበባ” በሕግ ፊት እኩል እውቅና እንዳላቸው ማስቀመጡ ተገቢ ይሆናል፡፡ መሠረታዊ ነገሩን የሚቀይር ባይሆንም የስሞቹን አጠቃቀም ዝርዝር በደንብ መወሰን ያስፈልጋል በሚልም ተቀምጧል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ሲዘረዘር ከመሬት አቅርቦት፣ ከውሃ አገልግሎት አቅርቦት፣ ከፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች የማስወገድ አገለግሎት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የሥራ እድል አቅርቦት፣ በመንግሥት ወጪ ከሚገቡ የኮንደሚኒየም ቤቶች አቅርቦት እንዲሁም ከገበያ ማእከላት አቅርቦትና አርሶ አደሩ ለልማት ተነሺ ሲሆን በቂ ካሣ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም አገለግሎቶችን ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
እዚህ ላይ ብዥታ ሊኖር የማይገባው ነገር ቢኖር እነዚህ አገልግሎቶች በሚቀርቡበት ጊዜ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ሊጠበቅለት የሚገባው ልዩ ጥቅምን ለማመላከት እንጂ በአዲስ አበባ ነዋሪ ዜጎች ላይ በብሔር ልዩነት ምክንያት የተለየ ጥቅም ለማቅረብ እንዳይደለ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ በብሔር ልዩነት ምክንያት በግለሰብ ባለሀብቶች፣ መንግሥት ሠራተኞች ወይም በማናቸውም ዜጎች መካከል ልዩነት አይኖርም፡፡ የመሬት አቅርቦቱም ለክልሉ ለተለያዩ መንግሥታዊ ሥራዎች እና ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎች የሚሠሩበትን መሬት ከሊዝ ነጻ እንዲያገኙ ለተቋማቱ ብቻ የተፈቀደ መሆኑ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጠጥ ውሃ የሚያገኘው በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር መገኛዎች በመሆኑ ከዚህ አኳያ ጉድጓዱ የሚቆፈርበት፣ ግድብ የሚለማበት ወይም የውሃ መስመሩ አቋርጠው የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞችኛ አና ቀበሌዎች በአስተዳደር ወጪ የመጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግ በሕጉ ተቀምጧል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ የተቀናጀ የትራንስፖርት ስምሪት ኖሮ የሕዝቡን ትስስር ለማጠናከር የአውቶቡስ፣ የታክሲ እንዲሁም የባቡር አገልግሎት መሠረተ-ልማትና አገልግሎቶች ስምሪት የተቀናጀና በዙሪያው ያሉ ከተሞችንም ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ በዙሪያ ያሉ ወጣቶች በተቀናጀ ሁኔታ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሌሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉት አካባቢዎች አዲስ አበባ የሚሠራቸው ሥራዎች ለዙሪያ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲያመቻች በእውቀትና በእቅድ የተመሠረተ ሥራ መሠራት ያለበት ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ ያለች በመሆኑ በዙሪያዋ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ አ/አደሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ለአዲስ አበባ ከተማ የምግብ እህል በማቅረብ የከተማዋን ሕዝብ ኑሮ ደግፎ የያዙ ናቸው፡፡ አርሶ አደሮችም በቀጥታ ከምርቶቻቸው ተጠቂሚ እንዲሆን የመሐል ደለሎችን አስወግደው በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በግብይት ሰንሰለት እንዲተሳሰሩ የከተማ አስተዳደሩ ምርቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን የገበያ ቦታ በማዘጋጀት በራሱ ወጭ የግብይት ማእከላትን አቋቁሞ ለአርሶ አደሮቹና ማህበሮቻቸው እንዲያቀርብ እንዲደረግ በአዋጁ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከባንኮች ጋር በመተባበር የማህበራዊ ቤቶች የሆኑትን የኮንደሚኒየም ቤቶች አስገንብቶ ከነዚህ ውስጥ በከተማው ላሉ የመንግሥት ሠራተኞትና ሴቶች በኮታ በእጣ ወስጥ ገብተው እንደወዳደሩ የደርጋል፡፡ በተመሳሳይ መለኩ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኛ ሆነው በከተማው ውስጥ ለሚኖሩትም ተመሳሳይ እድል እንዲሰጥ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
በከተማው ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት የኖረው የኦሮሞ አርሶአደር ቁጥሩ ቀላለ ባልሆነ ሁኔታ በልማት ምክንያት ተነሺ ነበር፡፡ አሁንም ለልማቱ ተፈላጊ እስከሆነ ድረስ በማሳመን ይህንኑ መፈፀም የሚገባን ይሆናል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ይህ ተነሺ አርሶአደር ቢያንስ ቢያንስ ከቀድሞ ኑሮ የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ በልማቱ ማስፋፋት ምክንያት ተጎጂ ሊሆን በጭራሽ አይገባም፡፡ በዚህ መሠረት ለወደፊቱ በቂ ካሣና በዘላቂነት የሚቋቋምበት ሁኔታ እንዲመቻችለት፣ ከዚህ በፊት የተሠራውም ሥራ ተፈትሾ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ፣ እነዚህን ሥራዎች የሚያስተባብር የሚመራና የሚያስፈጽም ጽ/ቤት እንዲደራጅ በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
የኦሮሚያ ክልል በከተማው ስለሚኖረው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ጥቅም፣
ከከተማው መሠረተ-ልማት አቅርቦት፣ ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር የተያያዘ በተፈጥሮ ሃብት ላይና በአየርና ውሃ ላይ የሚደርስ ብክለት እንዳይኖር የሚያደርግና ይህንን መብት የማስጠበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ታመኖበታል፡፡
ከዚህ አኳያ
* በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ከከተማው ከሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የመጠበቅ መብት እንዳላቸው፣
* ከአዲስ አበባ ከተማ በሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የክልሉን ከተሞችና ቀበሌዎች ለመጠበቅ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ እንደሚደረግ፣ ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም ሥርዓት እንደሚዘረጋ፣
* በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ደህንነቱ ሳይጠበቅና ቁጥጥር ሳይደረግበት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በሕግ አግባብ ከአስተዳደሩ ካሳ የማግኘት መብት እንደሚኖራቸው፡
* ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የግንባታ ማእድናት ማግኛ ሥፈራዎች የአየር ብክለት እንዳያስከትሉ እና ለደን ልማት ወይም ለሌሎች ልማቶች መዋል እንዲችሉ እንዲያገግሙ አንደሚደረጉ፣
* ለአዲስ አበባ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፈራዎች አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸወ ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ አንደሚደረጉ፣
በአዋጁ በዝርዝር እንዲካተት ተደርጓል፡፡
ተቋም ስለማደራጀት
በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 14 በአስተዳደሩ ውስጥ በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔር አርሶ አደሮች ዘላቂ መቋቋሚያ የሚሆን ካሣ የማግኘት መብታቸውን ለማስከበር እና ከዚህ በፊት በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ እና በቂ ካሣ ያላገኙ የኦሮሞ ብሔር አርሶ አደሮች በጥናት ላይ የተመሠረት የማስተካከያ ሥራ ለመስራት ከሚቋቋመው ጽ/ቤት በተጨማሪ አዋጅ ውስጥ የተጠቀሱትንና ሌሎች የጋራ ጉዳዮችን ክልሉ አና አስተዳደሩ የሚወያዩበትና የሚወስኑበት ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት የሆነ ከአስተደደሩና ከክልሉ ምክር ቤት የተውጣጣ የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተመለክቷል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ዓላማውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ መሠረት የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦተ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ከልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በዚህ አዋጅ የተዘረዘሩትን ልዩ ጥቅሞች በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን መከታተል፣ መገምገምና ለአፈጻጸሙ ቅልጥፍና ድጋፍ ማድረግ ይሆናል፡፡
የምክር ቤቱን አባላት በተመለከተ ከአስተዳደሩ ምክር ቤትና ከክልሉ ምክር ቤት በእኩል ቁጥር የሚወከሉ እንደሚሆን፤ ዝርዝር የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተግባርና ሀላፊነት፣ የሥራ ዘመን፣ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት የአባላት ሥነ ምግባር እና በጀት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣ ደንብ እንደሚወሰን ተመልክቷል፡፡
ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ /5/ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል በማለት ይደነግጋል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በሥራ ላይ ለማዋል እና የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ ዝርዝር ሕግ ለማውጣት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተው ይህ ረቂቅ አዋጅ ሊዘጋጅ ተችሏል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ሂደት ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የመንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል፡፡ በአዋጁ የመጽደቅ ሂደትም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሣተፉበት ይሆናል፡፡
ዋናው ጉዳይ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መላው የአገራችን ብሔሮር፣ ብሔረሰባችና ሕዝቦች ተስማምተው ያፀደቁት ድንጋጌ ነው፡፡ በመሆኑም መላውን የሐገራችንን ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረውና ሕዝቦች በመከባበርና በመፈቃቀድ ለሐገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ፈጣንና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማረጋገጥ ይረዳናል፡፡ ይህን ልዩ ጥቅም በዝርዝር አዋጁ ማውጣቱ የማንንም ሕዝብ እንዲሁም የአዲስ አበባን ነዋሪዎች መብትና ጥቅም በማይጋፋ መንገድ በህገ መንግሥቱም የተቀመጠ በመሆኑ ይኸው በዝርዝሩ ሕጉም በጥንቃቄ የተሠራ ነው፡፡ ጉዳዩ ከሁሉም ሕዝቦች ጥቅም አኳያ ተዘርዝሮ የተዘጋጀ ነው፡፡
ሰኔ 2009
Average Rating