በነጻነት ቡልቶ
ክፍል አንድ
ጄነራል ጻድቃን፣ “የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፓሊሲ” እና “የፓለቲካ ችግሮች”
በግሪክ አቴናና በስፓርታ መካከል የተካሄደውን የጦርነት ታሪክና ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ስትራቴጃካዊ ጽንሰ ሃሳቦች በማፍለቅ ከሚደነቀው ጥንታዊው የታሪክ ጸሃፊ የቱስዳይስ The Peloponnesian war ጀምሮ እስከ የጀርመኑ ካርል ቮን ክልሽዊትዝ On War ፣ የባህር ሃይል ስትራቲጂ አባት አልፌሬድ ማሃን The influence of Sea Power Upon History፡ ከዘመን ተሻጋሪ የስትራቴጂ አስተምሮዎች ፈላስፋ ቻይናዊው ከሰን ዡ The Art of War አንስቶ እሰከ ሉትዋርክ፣ ኮሊንስ የመሳሰሉ የዘመናችን የስትራቴጂና የደህንነት ጥናቶች ታላላቅ ተመራማሪዎችና ምሁራን የጻፏቸውንና ያፈለቁዋቸውን የስትራቴጂ ጽንሰ ሃስቦችና ቀመሮች በጥልቀት ማጥናትና ማወቅ አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው፡፡ የሴኪዩሪቲና የስትራቴጂ እውቀቶችን ባካበቱ ምሁራንና ተመራማሪዎች የሚጻፉ የአብይ ስትራቴጂ (Grand strategy) ንድፈ ሃሳቦችና ጽንሰ ሃሳቦች፣ ከነዚህ የሚመነጩ የብሄራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ቀመሮችን ተመርኩዞ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፓሊሲዎችን መንደፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለተጋረጡባት ድርብርብ የፖለቲካ ችግሮችና ከችግሮቹም የሚመነጩትን ዘርፈ ብዙ የደህንነት አደጋዎችን ለመከላከል የማይናቅ ድርሻ አላቸው። በእነዚህም ዙሪያ ጥልቀት ያላቸው ጥናቶችን ማድረጉ አስፈላጊ ነው። እነዚህንም የሚያስፈጽሙ አካላት መኖርና መጠናከር ለኢትዮጵያም ሆነ ለማንም ሀገር አስፈላጊ ከሆኑ ተቋማት ውስጥ በቀዳሚነት የሚቀመጡ መሆናቸው አይካድም። ከዚህ አኳያ ጄነራል ጻድቃን በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎችና ተቋማት ለአንድ ሃገር የሚበጁ እንደሆኑ ወደ አደባባይ ጉዳዩን ማቅረባቸው ያስመሰግናቸዋል።
ነገር ግን በዋነኝነት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ስርአት መሪዎች ባህሪ ፣ የፖለቲካ ታሪካቸው (track record)፣ የሚከተሉት ኣካሄድና የፓለቲካ ፍላጎት በሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ቀዳሚና ወሳኝ (Decisive) ድርሻ እንዳላቸው ክርክር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ይህንን ቀላል ዕውነት መረዳት የችግሮቻችንን መሰረት ለማወቅ ፣ አውቆም በቀዳሚነት የሚያስፈልገው ያለፈው 26 አመት ህወሃት የዘረጋውን የፓለቲካ ስርአትና ተከትሎት የመጣውን ግዙፍ የደህንነት አደጋዎች ለመገንዘብ ይረዳናል። ይህን አደጋ ለመቀልበስ ደግሞ ቁርጠኝነትና የፓለቲካ ወኔ (Political will) መኖር ዋናው ቁልፍ ነው። ይህም በመሆኑ ነው “የፓሊሲዎች ቈንጮ የሆነውን የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ” በባለቤትነት፣ በአስፈጻሚነትና በኣስተግባሪነት አሁን ላለው የሀገሪቱ የደህንነት ስጋት ዋና ቀፍቃፊ ምንጭ ለሆነው የሕወሃት አመራር መስጠት ውሻን ሉካንዳ ቤት እንዲጠብቅ ከማድረግ ይቆጠራል ብዬ የምከራከረው። የብሄራዊ ደህንነት አደጋዎች አመንጪና አሽከርካሪ (driver) የሆነውን አካል የዚህ ፖሊሲ ባለቤትና አስፈጻሚ ማድረጉ ስርአቱን ትንሽ ጠጋግኖ ለማስቀጠል ይረዳ እንደሆን እንጂ በዘለቄታው የኢትዮጵያን የደህንነትና ተያያዥነት ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ችግሮች ማስወገድ አይቻልም። እንዳውም በተቃራኒው እነዚህ ዘርፈ ብዙ የሀገሪቱ የፓለቲካ ችግሮች ተወሳስበው መቀጠላቸውና ሀገሪቱንም ሆነ የአፍሪካ ቀንድን ለከፋ ትርምስና የደህንነት ኣደጋ ማጋለጣቸው አይቀሬ ነው።
ህወሃት የስልጣን ዕድሜውን ማስቀጠያ መርህ ወይም ከልቡ የሚያምንበት ገዢ ሃሳብ ከጠፋበት ሰንበትበት ብሏል። ህወሃቶችንና ኢህአዴጎችን አጣብቆ የሚያቆያቸው መርህ ፍርክርክ ባለበት፤ በተለይ ከቀድሞ መሪያቸው ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በእውር ድንብር በሚሄዱበት፤ በውስጣቸው የሚገኘው ቅራኔና ክፍፍል በጦዘበት፤ ሆኖም ላንሰራፉት የአንድ ብሄር የበላይነትና የዘረፋ ስርአት መሳሪያ የሆነን የመንግስት ስልጣን እንዳያጡ ተጣብቀው የሚገኙበት ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያማልሉበት፣ የሚያሳምኑበትና ከጎናቸው የሚያሰልፉበት ሃሳብ እንደሌላቸውም ግልጽ ከሆነ ቆይቷል። ባጠቃላይም በህወሃት የበላይነት ስር የሚገኘው የፖለቲካ ስርኣት የቅቡልነት፣ የህጋዊነት፣ ብሎም የራስ መተማመንና የውህድ አመራር እጦት ድርብርብ ቀውሶች ታማሚ ሆኖ በሚማቅቅበት በአሁኑ ቀውጢ ሰዓት ላይ ጄ/ል ጻድቃን አንድ መላ ይዞላቸው የመጣ ይመስላል። ምናልባትም “የሕዝብ የአስተሳስብ አንድነት” ሊያመጣ የሚችል ሁሉን አሰባሳቢ ገዢ ሃሳብ ነው ብለው ገምግመው ሊሆን እንደሚችል ከግምት ውስጥም ማስገባት ያስፈልጋል።
“ከህገ መንግስቱ በታች የፓሊሲዎች ቁንጮ” የሆነው የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፓሊሲ በአግባቡ ተቀርጾ፣ ይህንን በቋሚነት የሚሰራ ኣስፈጻሚ አካል ማደራጀት ዋነኛ የኢትዮጵያ የፓለቲካ ችግሮች መፍቻ ምትሃታዊ አቅም (ማጂክ ዋንድ) ወይም የብር ጥይት (ሲልቨር ቡሌት) እንዳለው ተደርጎ በጄነራሉ ሰፊ ትንታኔ የተሰጠበት አይነተኛ ምክንያትም ከላይ የተዘረዘሩትን ግቦች ለማስፈጽም እንዲረዳ ታስቦ ሊሆን ይችላል። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር ራሱ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነው። አገዛዙ የሚያራምዳቸው ዘርፈ ብዙ ጸረ-ህዝብና ጸረ -ዲሞክራሲያዊ ተግባሮቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ችግሮች ዋነኛ ምንጭና ተዋናይ መሆኑን በገሃድ የሚያሳዩ ምስክሮች ናቸው። ለዚህም ነው ጄ/ል ጻድቃን በሰፊው ትንታኔ የሰጠበት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፓሊሲ መኖር አለመኖር ወይም ይህን ፓሊሲ የሚከታተልና አማራጭ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ቋሚ አካል መኖር አለመኖር ሕወሃትን ቀስፎ ከያዘውና ከሚያሰቃየው የውስጥ ደዌው ጋር እምብዛም ተያያዥነት የለውም ብሎ መከራከር የሚቻለው። ጄ/ል ጻድቃን “የፓለቲካ ችግሮች” በሚል ጥቅል ሀረግ አደባብስው ያለፉዋቸውን ሕወሃት ሰራሽ የሆኑ ችግሮችን እንደሚከተለው ማቅረብ ይቻላል።
ዋናው የኢትዮጵያ የደህንነት ኣደጋ የሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት አለመኖር ነው። ትልቁ የደህንነት አደጋ የኢትዮጵያን የብሄር ችግሮች ፈትቷል ተብሎ ከጅምሩ ሕወሃት እንደ ትልቅ ስኬት ሲመጻደቅበት የቆየው ፌዴሬላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ዴሞክራሲያዊም ፌዴራላዊም አለመሆኑ ነው! የህወሃትን ፍላጎት፣ የበላይነት፣ የዘረፋ፣ የኣድሎአዊነትና የዘረኝነትን ስርዓት ማስጠበቂያና ማስቀጠያ መሳሪያና ጭንብል ከመሆን በዘለለ የተባለውን ሐቀኛ ዴሞክራሲንም ሆነ ፌዴራሊዝምን እውን አለማድረጋቸው ነው።
ህወሃት መራሹ የኢትዮጵ እገዛዝ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ በባርነት ቀንበር ውስጥ ጠፍንጎ ይዞ፣ ስልጣን ከላይ እስከ ታች ድረስ በአንድ ብሔር ቁጥጥር ስር አስገብቶ አይን ያወጣ ዘረፋ፣ ግድያና አፈና መፈጸሙና ማስፈጸሙ የህዝብና የዜጎች የዕለት ተዕለት ትእይንት የሆነባት አገር ናት ኢትዮጲያ! ህዝቦቿ ባዶ እጃቸውን አደባባይ ወጥተው የመብትና የዴሞክራሲን ጥያቄ ባቀረቡ ቁጥር መልሳቸው በአጋዚ ቅልብ ጦርና በፌዴራል ፖሊስ እንደ ጠላት በጥይት የሚቆሉባት፣ ዜጎቿ በጅምላ የሚታሰሩባት፣ የሚፈናቀሉባት፣ በየአመቱ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆቿ የሚራቡባት፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለተሻለ ሕይወት ወደ ስደት ሲሄዱ በባሕር ላይ የዓሳ ነባሪ ቀለብ ሆነው የቀሩባት፣ እህቶቻችን የአረብ ገረዶች ሆነው ለወሲብ ጥቃት የተጋለጡባት፣ ከፎቅ ላይ እየተወረወሩና በፈላ ውሃ እየተቀቀሉ በየቀኑ ሬሳቸው ወደ አገር ቤት የሚጫንባት፣ ነዋሪዎቿ በቆሻሻ ክምር ናዳ የሚያልቁባት አገር ሆናለች ኢትዮጲያ! ከዚህም በተጨማሪ ዜጎች የመኖር ዋስትና ተነፍጓቸው በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በሰላም መግባት የሚችሉበት ሕይወት የሩቅ ዘመን ትዝታ ከሆነ ሰነባብቷል። እንደ አሸን የፈሉ የስርዓቱ ሰላዮች እስከ ቤተክርስቲያንና መስጊድ ድረስ ሳይቀር ለመሰለልና አለመተማመንን ለመፍጠር የተሰማሩባት፣ ዘረፋ፣ ውሸት፣ ሌብነትና ማጭበርበር ባህል የሆነበትና ሰዎችን እንደሸቀጥ የማዘዋወር ንግድ እየተንሰራፋ የመጣበት አስደንጋጭ ሁኔታም ተፈጥሯል። እነዚህና ሌሎች እዚህ ላይ ያልተዘረዘሩ ተወራራሽ ችግሮች ህወሃት በሚመራው አገዛዝ የተፈጠሩ ናቸው።
ጄነራል ጻድቃን በእድገትም፣ በዲፕሎማሲም ሆነ በሰላም ማስከበር ወዘተ በአለም ማህበረሰብ ዘንድ የሃገራችን ተቀባይነት ጨምሯል በማለት የህወሃትን አገዛዝ “ስኬቶች” እውቅና በመስጠት ችግሩ በዋነኛነት የውጪና የደህንነት ፖሊሲ ችግር ነው በሚል አገላለጽ ለማድበስበስ ሞክረዋል። እንዲሁም ብጥብጥና ትርምስ የፈጠሩት የጸረ ሰላም ሃይሎች በቀጥታ ከሻዕቢያ ወይም በሻዕቢያ መንግስት አቀነባባሪነት የተፈጠረ ነው የሚል አንደምታ ያለውም ሃሳብ አስቀምጠዋል። በተለይም ደግሞ ጄነራሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያነሳውን ተደጋጋሚ የመብትና የነጻነት ጥያቄ በሻዕቢያ ተላላኪነት የፈረጇቸው ሽብርተኞችና የጸረ ህዝብ ሃይሎች ሴራ አድርገው ለማቅረብ የሞከሩበት ሂደት በጣም አስገራሚ ነው።
የህወሃት ትግራዮች የበላይነት በሌሎች ህዝቦች ኪሳራ በኢኮኖሚ፣ በፓለቲካ፣ በወታደራዊ፣ በደህንነት ተቋማት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉና ይህም ኢፍትሃዊ አሰራር በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የፈጠረው የበይ ተመልካችነት፣ የባይተዋርነትና የሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ስሜት በህዝቦች አብሮ የመኖር እድል ላይ አሉታዊ ጥላውን አሳርፏል። ይህም ጤናማና የተረጋጋ ማህበረሰብ ለዘለቄታው ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ላይ የራሱን ሳንካ ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን ህዝብ ለህዝብ፣ ብሄር ለብሄር በጎሪጥ ኣንዲተያይ፣ በተቃርኖ እንዲቆምና ወደ ግጭት ምናልባትም ፍጅት ወደሚያስከትል ደረጃ ያደርሰው እንደሁ እንጂ የብሄራዊ ደህንነትን ወደሚያረጋግጥ፣ የሰላምና መረጋጋትን ዋስትና ወደሚያስቀጥል መንገድ ፈፅሞ ሊመራው አይችልም።
እጅግ ጥልቀት ያለው የደህንነት ፖሊሲ ተቀመረ አልተቀመረ ፋይዳ ቢስ ነው። መሰረታዊ ምክንያቱም ይህ ፓሊሲ ሊከላከላቸው የሚችሉ የደህንነት አደጋዎች መሰረታዊ ምንጫቸው የደህንነት ፖሊሲ አወጣለሁ የሚለው ራሱ ህወሃት የዘረጋው አምባገነናዊ፣ ዘራፊ፣ ዘረኛ፣ አድሎአዊ የአፓርታይድ መሰል ስርአት በመሆኑ ነው! ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንዲሉ ህወሃት ራሱ የሃገሪቱ ዋነኛ የደህንነት ስጋት ሆኖ ሳለ “በጥልቀት የተጠናና ምልእኡ የሆነ የሃገሪቷን የደህንነት ፖሊሲ አስፈጻሚ/አስተግባሪ ምሆኑ በጣም አስቂኝ ያደርገዋል። ጄነራሉም ቢሆኑ ህወሃትን የሃገሪቷ የደህንነት ስጋቶችና አደጋዎች የሚያመንጭ ኃይል ሆኖ ሳለ ራሱ መፍትሄ ብሎ የሚያስቀምጠውን የደህንነት ፖሊሲ ባለቤትና አስፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል መረዳት የገባዋል። በህወሃት የበላይነት የሚዘወረው አገዛዝ የሃገሪቷ ትልቁ የደህንነት ስጋትንና አደጋ ስለመሆኑ መካካድ አያስፈልግም። ጄነራል ጻድቃን ይህንን ሐቅ ጠንቅቀው የሚረዱት ይመስለኛል።
ከላይ እንደተጠቀሰው እጅግ ከባዱ የኢትዮጵያ የደህንነት አደጋ ህወሃት በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያንሰራፈው የትግራይ የበላይነት ወይንም የገዢ መደብነት ስርአት ነው። ይህም ስርዓት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በመንግስታዊ ተቋማት፣ በመከላከያ፡ በደህንነት “እንወክለዋለን የሚሉትን” የትግራይ የህዝብ ቁጥር ፈጽሞ የማይመጣጠን የአናሳ ብሔር አባላትን የተጠቃሚነት፣ የፈላጭ ቆራጭነት፣ ኢፍትሀዊ በሆኑ መንገዶች ለዘመድ አዝማዶቻቸው ሁሉ ሳይሰሩ በአንድ ጀንበር ባለሃብት የሚሆኑበትንና የሚከብሩበትን መንገድ በግልጽና በስውር ያመቻቸ እኩይ ስርዓት ነው። በሌላ በኩልም በየእስር ቤቶቹ የሌሎች ብሄር ተወላጆች “አንተ አማራ፣ አንተ ኦሮሞ፣ አንተ ጉራጌ. ሽንታም ” በማለት እያዋረዱ ትግሪኛ ተናጋሪ በሆኑ የሰርዓቱ ሰዎች የሚፈጸሙ እጅግ ዘግናኝ ግፎችና ሰቆቃዎችን እዚህ መዘርዘሩ ለቀባሪው ማርዳት ነው። የዚህ መጥፎ ስርዓት ሰላባ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃያ ስድስት ዓመታት ያየው፣ የሰማው፣ የደረሰበትና ያንገፈገፈው የግፍ ዋንጫ ነውና! በብዙ መገለጫዎች የሕወሃትን የበላይነት፣ መሰሪነት፣ ስግብግብነት፣ ጭካኔ ማሳየት ይቻላል። ለዚህም ነው ህወሃት የሚዘውረው አገዛዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የደህንነት ስጋትና አደጋ ተደርጎ የሚቆጠረው። ጄነራል ጻድቃን ይህን ራሱ ስጋት የሆነውን ሃይል ነው እንግዲህ ሃገሪቷን የሚያረጋጋና ከተደቀኑባት የደህንነት አደጋዎችም መጠበቅ የሚያስችል የደህንነት ፖሊሲ እንደሚያወጣና የፖሊሲው ይዘትም ምን መሆን እንዳለበት የተናገሩት!
የኢትዮጵያ ህዝብ በፍትህ ህይወቱን የሚመራበትን፣ የህግ የበላይነት በሰፈነበት ስርአት የሚዳኝበትን፣ ፍትሃዊ የሆነ የስልጣንና የሐብት ክፍፍል፣ ማህበራዊ ፍትህ የሚሰፍንበትን ስርዓት ከምንም ጊዜውም በላይ ይናፍቃል። ዜጎች በነጻነት አብረው የሚኖሩባት ፣ የዘላቂ ሰላምና ደህንነት ዋስትና የተረጋገጠባት፣ ብዙሃኑ እየተራበ ጥቂቶች በጥጋብ የማያገሱባት፣ ማሕበራዊ ፍትህና ብልጽግና ለሁሉም አካባቢዎች በተግባር የሚተረጎምባትን ኢትዮጲያን ማየት ይመኛል። ሆኖም ከምኞት ባሻገር ለነኚህ የተቀደሱ ዓላማዎች መሳካት ዜጎች ሁሉ ከልብ ሊጨነቁባቸው፣ ብሎም በጽናት ሊታገሉላቸው የሚገቡ ግቦች መሆን አለባቸው። አሁንም እደግመዋለሁ! ዛሬ በኢትዮጳያ ውስጥ የተንሰራፋው የሕወሃት ገዢ መደብ ሁሉንም በባለቤትነትንና በበላይነት ይዞ በሚገኝበት እጅግ አስፈሪና አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን።
ይህ ዐይን ያወጣ አድሎአዊና ኢፍትሀዊ የስልጣን፣ የሀብትና የጥቅም ክፍፍል ብሎም ይህ ክፍፍል የፈጠረው አስከፊ የሆነ ብሄሮች የጎሪጥ የሚተያዩበት ሁኔታ ሊካድ አይገባውም። እንደውም የብልህና አርቆ አሳቢ፣ ዘመን ተሻጋሪ፣ ባለራይና የፓለቲካ መፍትሄ አመንጪነት መነሻ መሆን ያለበት ይህን መራር ሐቅ ከምንም በፊት አስቀድሞ በመቀበልና በመጋፈጥ መሆን ይኖርበታል።፡ ምክንያቱም ይህ ነባራዊ ሁኔታ ለዘለቄታው የሕዝብ አብሮ መኖር፣ ሰላም፣ መረጋጋትና ባጠቃላይ ለሀገሪቱ ህልውና የሚያሰጋ ትልቁ የደህንነት ፈተና በመሆኑ ነው። እናም ይህንን አደገኛ አካሄድ በትዕግስት፣ በጥበብና በቁርጠኝነት በመቀልበስ የአገሪቱን ህልውና፣ የሕዝቦችን በእኩልነትና በሰላም መኖር ለማረጋገጥ መጨነቅና መታገል ሲገባ ነው እንጂ ጄነራሉ እንዳነሱት ሃሳብ የችግሮቹን ዋና ምንጭ ትተው ጉዳዩን ከውጪና ደህንነት ፖሊሲ ጋር በዋነኘት በማያያዝ አይደለም።አለባበሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ እንዳይሆን።
በኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ የነበረው የጸጥታ ችግር አስቀድሞ ሊታይ ይችል ነበር። በሰው ህይወት፣ በንብረት ላይ ጉዳት ሳያስከፍል፣ የጊዜአዊ ኣስቸኳይ ኣዋጅ ሳያስፈልግ ለመከላከል ይቻል ነበር። ሀገር ተናውጦ “በጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጅ ነው የቆመው” ይላሉ ጄ/ል ጻድቃን! እውን የመጣው የህዝብ ቁጣና አልገዛም ባይነት የፖሊሲ አለመኖር ወይንስ የሕወሃት/ኢህአዴግ ፖሊሲዎች ጸረ-ህዝብነት ያመጡት ነው ብሎ ለጠየቀ ሰው መልሱ ግልጽና ግልጽ ሆኖ ይታየዋል። በተለያዩ ጊዜያት የተተገበሩ የህወሃት ፓሊሲዎች ያመጡት ድርብርብ ችግሮች መሰረቱ የስርዓቱ ጸረ- ዲሞክራሲያዊና ጸረ- ህዝብነት መሆኑ ላይ ነው። ሌላ ምንም ሚስጥር የለውም! ይህን መሰረታዊ ችግር በደህንነት ፖሊሲ ምሉዕነትና አፈጻጸም ያለመኖር የመጣ ችግር ነው ብሎ ለማቅረብ መሞከር ሃገሪቱ አሁን የገባችበትን ቅርቃር በሚገባ ባለመገንዘብ ወይንም ኃላፊነት በጎደለው መንፈስ ሆነ ተብሎ ለራስ በሚሰላ ጥቅም አማካኝነት ችላ የማለት ጉዳይ እንደሆነ ተደርጎ ነው የሚወሰደው።
ጄ/ል ጻድቃን የስርዓቱን ዝቅጠት “የውስጥ የፓለቲካ ችግር” ሲሉ በደምሳሳው ቢገልጹትም የሀገሪቱን የፓለቲካ ችግሮች ዋና ዋና ገጽታዎች ከዚህ በፊት በጻፉት ጽሁፍ በስሱም ቢሆን እንደገለጹት በዚህኛው ቃለ ምልልሳቸው ሊገልጹና ሊዘረዝሩ አልደፈሩም። መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችና ከላይ የተዘረዘሩት እውነታዎች የሚቀየሩበት መሰረታዊ ለውጦች እስካልመጡ ድረስ “የህዝብ የአስተሳሰብ አንድነት” ሊመጣ ከቶም አይችልም። በሀገሪቱ የሚገኙ ችግሮች ስርአቱ የወለዳቸውና ያሳደጋቸው እንደመሆናቸው መጠን በዚህ ስርአት የህዝብ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ እንደማይችሉ ያለፉት ሃያ ስድስት አመታት ስለ ስርአቱ ማንነትና ምንነት ብዙ አሳይቶናል፤ ብዙም አስተምሮናል። በዚህ ረዥም ሂደት ውስጥ ህወሃት ይበልጥ ከህዝቡ እየተነጠለ ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የስርአቱን መውደቅ የሚናፍቅበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ህወሃት የህዝቡን የአስተሳሰብ አድማስ ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ ለመምራት ቀርቶ የራሱንም ህልውና ለማቆየት ከማይችልበት አዘቅት ውስጥ መግባቱን ለማሳየት ብዙ መድከም የሚያስፈልግ አይመስለኝም። እንዳውም ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ““ሕወሃት የወደቀበት አዘቅት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ በሕይወት ይቆይ ይሆን?” የሚለው ይመስለኛል።
በመቀጠልም አሁንም ትልቅ የደህንነት አደጋ “እያረገዘ ያለ ሊኖር ይችላል” ይላሉ ጄ/ል ጻድቃን። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እነዚህ የተረገዙ ችግሮች የፖለቲካ ስርዓቱ መሰረታዊ ለውጥ እስካላመጣ ድረስ መፈንዳታቸው አይቀሬ ነው። ለማርቀቅና ለማጸደቅ ውይንም ለማሻሻል እያሰቡት ያለው የደህንነት ፓሊሲ ይህን የለውጥ ሱናሜ ሊያቆመው ከቶም አይቻለውም። ሌሎች የስርአቱ ፓሊሲዎች ሁሉ የሚመነጩት ከዚህ የህወሃት መለያ ከሆኑት ስግብግብነቱ፣ ጸረ ዲሞክራሲያዊና ጸረ ህዝብ ባህሪያቶቹ በመሆኑ ነው።”መከለስ ያለበት” የውጪና የደህንነት ፖሊሲም ከህወሃት ጸረ ህዝባዊነትና ጸረ ዲሞክራሲያዊነት የሚመነጭና የስርአቱን እድሜ ለማራዘም ተብሎ የሚቀመር በመሆኑ ከመነሻው ጄነራል ጻድቃን እንደተመኙት የችግሮቹ መፍትሄ ሆኖ ሊመጣ አይችልም።
መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በመሰረታዊ ለውጦች እስካልተመለሱ ድረስም “የህዝብ የአስተሳሰብ አንድነት” ሊመጣ አይችልም። የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ የፓለቲካ ችግሮች ለመፍታት የማይፈልግ፣ ይህን ካደረግኩ ስልጣኔን አጣለሁ በሚል ስሌት ዘረኛና አምባገነን የሆነውን የህወሃት የፓለቲካና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ለማስቀጠል የሚተጋ፣ በተንኮልና በመሰሪነት እንዲሁም በጭካኔው የተካነ መሆኑ የተረጋገጠለት ስርዓት የአገሪቱን የጸጥታና የደህንነት ችግሮች ለዘለቄታው ሊፈታ የሚችል ሃይል ሊሆን አይችልም።ከገለማ እንቁላል ጤናማ ጫጩት አይፈለፈልም እንዲሉ! ራሱ የሃገሪቷ የደህንነት ስጋት ስለሆነ ከማንም በላይ የችግሮቹ ምንጭና መንስኤ ነው!
አርበኞች ግንቦት 7ም ሆነ ኦነግ እንዲሁም ሌሎች ጄ/ሉ ያልጠቀሷቸው ሃይሎች ህልውና መሰረት በሃገር ውስጥ ህወሃት የፈጠራቸው ሁኔታዎች፣ ጸረ ህዝብነቱና ጸረ ዴሞክራሲያዊነቱ፣ ራሱ ያወጣውን ህገ-መንግስታዊ መብቶች በተደጋጋሚ በመርገጥ ስላማዊ ህጋዊ ትግልን ለማድረግ ፈጽሞ በማይቻልበት ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥፋቱ እንጂ እነዚህን የፓለቲካ ሃይሎች ሚረዱ ሁሉ፡ ኤርትራን ጨምሮ ስለፈለጉ ሊሆን አይችልም። ጭቆና ባለበት ጭቆናን የሚታገሉ ሃይሎች መኖራቸው ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። የነዚህን ሃይሎች ተጽዕኖ ለመቀነስና ጨርሶውኑ ለማጥፋት የደህንነት ፖሊሲ አይነቶች ቢደረደሩ ምንም የሚፈጥረው ፋይዳ የለም። የነዚህ ሃይሎች የህልውና መሰረት ስርዓቱ የፈጠራቸው ዘርፈ ብዙ “የፖለቲካ ችግሮች“ ናቸው። የስርዓቱ ጸረ ህዝብነትና ጸረ ዲሞክራሲያዊነት እስካለ ድረስ በየፊናው የሚደረገው ትግል እያደገና እየሰፋ እንደሚሄድና ህዝቡ ከዚህ አስከፊ ቀንበር ነጻ ለመውጣት ምንም አይነት መስዋዕትነትን ከመክፈል ወደኋላ እንደማይል ጄኔራሉ የሚጠፋቸው አይመስለኝም።
(ይቀጥላል)
ነጻነት ቡልቶን ቀጥሎ ባለው የኢሜልና ፌስቡክ አድራሻ ማግኘት ትችላላችሁ
https://www.facebook.com/netsanet.bulto.58
Average Rating