ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በህዝባችን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የኢኮኖሚ ዘረፋና የፖለቲካ ጭቆና የተፈፀመ ሲሆን በተለይም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ትዕግስቱ በመሟጠጡ በአገዛዙ ላይ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ የሚገኝ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እኛ ይህን ኢፍትሀዊነት የተቃወምን ዜጎች ከተወረወረንበት እስር ቤት ሆነን አሁንም ያገራችን ጉዳይ እንደሚመለከተንና እንደሚያሳስበን በመግለጽ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ለመንግስት ጠቋሚ ነው ብለን ያልነውን ምክረ-ሀሳብ መለገሳችን ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ሁኔታዎችን ከመለወጥ ወይም ከማሻሻል ይልቅ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በመጨፍጨፍና በማቃጠል ሺህዎችን በፌዴራልና በክልል እስር ቤቶች በመወርወር፣ አስር ሺህዎችን በፌዴራል ወታደራዊ ካምፖች በማጎር፣ ሺህዎችን ካገር በማሰደድ አገሪቱ በመበታተና በርስ በርስ ጦርነት መንታ መንገድ ላይ እንድትቆም አድርጓታል፡፡ በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ደግሞ ህዝባችን በቀደመት ሥርዓቶች ይቅርና ከጠላት ወረራ ጊዜ እንኳን በባሰ የነፃነት እጦት ውስጥ ለመኖር ተገዷል፡፡ ያን ሁሉ ግፍ በህዝብ ላይ እያደረሰ መልሶ ደግሞ “እንዲህና እንዲያ አደርግላችኋለው” ተብሎ በየማዕዘኑ መሠረት ድንጋይ እየተጣለ፣ የቁርጥ ቀን አርቲስቶችና አድርባይ ምሁራን ከየአፎታቶው እየተመዘዙ የማስመሰልና የማታለል ተግባራቸውን ለማከናወን እንደጥንግ በመወርወር ላይ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በቴሌቪዝን ብቅ ብለው በፓርቲያቸው የሚመራው መንግስት በጥልቀት መታደስ ስለመጀመሩ ሰፊ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ መታደስ ለመጀመሩ ማሳያ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦችም ዘርዝረዋል፡፡ ዋና ዋና ማሳያዎች ናቸው ብለው ያነሱት አዲስ የአመራር ምደባ መደረጉ፣ አስፈፃሚ አካላትን የሚቆጣጠሩ ተቋማትን ማጠናከር መጀመሩ፣ ዴሞክራሲን የማስፋትና የማጥለቅ ተግባርን ማጎልበት መጀመሩና ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ አዲስ ስትራቴጂ ተቀይሶ ሥራ ላይ መዋል መጀመሩ ናቸው፡፡ እነዚህ እርምጃዎች ካሁኑ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡ እኛም እሳቸው በሰጡት መግለጫና ከዚያ በኋላ በሁሉም አዳራሾች እየተስተጋባ ስላለው የጥልቅ ተሀድሶ ማደንዘዣ መርፌ ስህተተኝነት በማብራራት ሊሆን የሚገባውን ለመጠቆም እንፈልጋለን፡፡
አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲና መንግስት የኋላ ታሪክ ጥቂት መለስ ብለን ብንቃኝ አገር ለመምራት ሞራላዊ ብቃት የሌለው መሆኑን የሚያሳዩና ጥልቅ ተሀድሶ ተብዬውን ማደናገሪያ እንዳንቀበል የሚያደርጉ በርካታ ድርጊቶቹን እንመለከታለን፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት ይኼው ፓርቲ “የመበሰበስ አደጋ አጋጥሞኛልና የመታደስ ዕድል ስጡኝ” በማለት የተወሰኑ አባላቱን በማሰርና ከፓርቲው በማባረር ሁኔታው እንደማይደገም ቃል ገብቶ በአገዛዙ ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ንቅዘቱና መበስበሱ ቃል በተገባው መሠረት ባለመታከሙና ባለመቀረፉ ህዝቡ ቁጣውንና ቅሬታውን በ1997ቱ ምርጫ ድምፁን ለተቃዋሚዎች በመሰጠት ገለፀ፡፡ ዳግም ምርጫና ማሟያ ምርጫ በማለት የህዝቡን ድምፅ ያለአግባብ መልሶ ከወሰደ በኃላ አብዛኛውን ተቃዋሚ እስር ቤት አስገባ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ መሸነፉን በማመን “ህዝብ ድምፅ የነፈገኝ በገጠሩ ላይ አትኩሬ ከተማውን በመዘንጋቴ ነው” በማለት ከተሞችን በማልማት ስም የከተሞችን መሬት ለአባሎቹና ደጋፊዎቹ በማከፋፈል ዘርፎ አዘረፈ፡፡ በየአደረጃጀቱና በሲቪል ሰርቪስ አመራር ላይ የተመደበው የፓርቲ አባላም በዘርፉ ለይ በመሠማራቱ ህዝብን ማገልገል ተዘነጋ፡፡ ህዝቡ በመልካም አስተዳደርና ነፃነት እጦት በያለበት መነሳሳት ሲጀምር ቢፒአር የተባለ ዘመናዊ የአሠራር ጥበብ ሥራ ላይ በማዋል “ዳግም እንድታደስ ይፈቀድልኝ” በማለት ወትውቶ ከላይ እስከታች አዲስ መዋቅር መዘርጋቱን አስተወቀ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግድግዳቸው ፈራርሶ በመስተዋት ተተካ፡፡ በማንኛውም የሥራ መስክ ፀንቶ የኖረው ለህሊናና ለሙያ ሥነምግባር የመገዛት እሴት በይፋ ተቀበረና በመስተዋት ውስጥ መጠባበቅ ተጀመረ፡፡ አመራሮች ያለችሎታቸው መመደባቸውም እውቅና በማግኘቱ በተሃድሶው መሠረት በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰዎች በተገቢው ቦታ ይመደባሉ ተባለ፡፡ የሙሰኝነትና የመልካም አስተዳደር ችግርም እስከወዲያኛው ያከትምለታል በማለት ህዝቡ የተሰፋ እንጀራ በመመገብ እንዲረጋጋ ተደረገ፡፡ ነገር ግን የተባለው ቀርቶ ተቃራኒው ሥራ ላይ ይውል ጀመር፡፡ የአመለካከት ችግር አለባቸው የተባሉ ሰዎች ተጠራርገው እንዲወጡ በተደረገው ዘመቻ እንኳንና የኃላፊነት ቦታዎች በተራው የሥራ መደብ ላይ ያለፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ማንም እንዳይቀጠር ተደርጎ ሲቪል ሰርቪሱ በካድሬ ተጥለቀለቀ፡፡ ሌላው ዜጋ ለሥራ አጥነት ተዳረገ፡፡ በድብቅ ሲቀናቀን የነበረው አመለካከትም ይፋ ሆነ፡፡ ይህ አመለካከት ማንኛውም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ አገልግሎትና የፖለቲካ ዘርፍ በፓርቲው ቁጥጥር ሥር መዋል አለበት የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ተሞክረው ውጤት ያስገኙት ዘመናዊ የአሠራር ሪፎርሞች ለህዝብ ሳይሆን ለፓርቲ ወገንተኛ በሆኑ አመራሮችና ሠራተኞች ምክንያት መክነው የተዘመረለት መልካም አስተዳደርም የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ የተፈጠሩት አደራጃጀቶችና ቅጥሮች ሁሉ የሚከናወኑት ይህን አስተሳሰብ ከግብ ለማድረስ ነው፡፡
ታዲያ አሁን ወደ አመራር መጡ የተባሉት አዳዲስ ባለሥልጣኖች ከየት የመጡ ናቸው? በዚሁ አመለካከትና የታማኝነት መስፈርት ውስጥ አልፈው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲሠሩ የነበሩ አይደሉምን? ብዙዎች ኢህአዴግ “መቶ በመቶ አሸንፌ ይዣለሁ” ባለው ፓርላማ ውስጥ ታድመው እያየናቸው “ቴክኖክራቶች እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም” ብሎ ከመናገር የበለጠ ህዝብን መናቅ ከየት ሊመጣ ይችላል? የህዝቡን ድምፅ ዘርፈው ተፎካካሪዎቻቸውንና ታዛቢዎችን አስደብድበውና እስር ቤት አስወርውረው ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ወንጀለኞችን የጥልቅ ተሀድሶ ማሳያ ናቸው ማለት ሊታገሱት የሚከብድ ስድብ ነው፡፡ እነዚህ “ቴክኖክራቶች” የተባሉት አዳዲስ አመራሮች ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሚናገሩትንና የሚሠሩትን የተከታተለ ሰው ከኢህአዴግ በላይ ነባር ኢህአዴጋውያን መሆናቸውን ሊገነዘብ ይችላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥልቅ ተሀድሶው እንደሁለተኛ ማሳያነት ያነሱት አስፈፃሚ አካላትን የሚቆጣጠሩ ተቋማት በመጠናከር ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ አስፈፃሚውን አካል በዋናነት የሚቆጣጠረው የተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን የዋና ኦዲተርን፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን፣ ፀረ ሙስናና የእንባ ጠባቂ ተቋማትን በማጠናከር እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ገለፀዋል፡፡ የተጠቀሱት ተቋማት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን በመጠቆም ተስፋ ሰጭ ጅምር ነው ብለውታል፡፡ ለመሆኑ ተቆጣጣሪ ነው የተባለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምን ዓይነት ሁኔታ የመጣና እንዴት ያለ ስብሰብ ነው? እውን እነዚህ ሰዎች ህዝቡ ድምጹን የሰጣቸው እውነተኛ ተወካዮቹ ናቸው? እያንዳንዳችን ከየምንኖርበት አካባቢ እንዴት እንደመጡና ስንት ግፍ በእጃቸው እንደለ ስለምናውቅ ስለማንነታቸው ብዙ በማተት ጊዜ ማጥፈት አንፈልግም፡፡ አብዛኛዎቹ ህዝብ ይሁንታውን ሰጥቶ የላካቸው ባለመሆናቸው በራስ መተማመን የሌላቸው፣ ለፓርቲያቸው እንጂ ለህዝብ ወገንተኛ ያልሆኑ፣ ተጽፎ የተሰጣቸውን ጥያቄ የሚጠይቁ፣ አስቀድሞ ለሚሰጣቸው ጥያቄ “ስጡ” የተባሉትን መልስ ብቻ የሚሰጡ ‘ተቃወሙ’ ወይም ‘ደግፉ’ የተባሉትን ያለአንዳች ጥያቄ የሚቃወሙና የሚደግፉ፣ ተመርጠናል የሚሉበትን ክልል ህዝብ የማይወክሉ መሆናቸውን ብቻ መግለጽ በቂ ይሆናል፡፡ በምክር ቤት ውስጥ ያሉት ቋሚ ኮሚቴዎችም በአብዛኛው ላሉበት ቦታ የሚመጥን ብቃት እንደሌላቸው በሰፊው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል የውጪ ግንኙነት፣ የመከላከያና ደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባላት አገሪቱ ከየትኞቹ አገሮች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳላት፣ ምን ያህል የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት በስንት አገሮች ተሰማርተው እንዳሉ፣ ስንቶች ተሰውተው ላገራቸው አፈር ሳይበቁ እንደቀሩና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ያውቁ ይሆን? ለመሆኑ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ አካላት በየጊዜው መጥቶ ባለሥልጣኖች ኪስ ሲገባ የኖረውና በአገሪቱ ደም በአናታችን ላይ የሚያናጥረው የብድር ዕዳ ስንት እንደሆነ የሚያውቁ አባላት ምን ያህል ይሆኑ? ባገራችን ፓርላማ ውስጥ በቴሌቪዥን እንደምንመለከተው አስፈፃሚ አካላት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበው ሪፖርት ሲያቀርቡ አባላት ጥያቄ ሲጠይቁ እንኳን እንደዚያ የሚሸቆጠቆጡት ተቆጣጣሪ መሆናቸውን በትክክል ስለሚያውቁ ነው ማለት ይችላል? ህገ መንግስቱ ላይ የተፃፈውን ለጊዜ እንርሳውና የፓርላማውን ገሀዳዊ እውነት ብንመለከት ተቆጣጣሪ የሚመስለው ምክር ቤቱ ነው ወይስ አስፈፃሚው ነው? ታዲያ “እኔ ተቆጣጣሪ ነኝ” ብሎ የሚያስብ ወይም መሆኑን የማያውቅ ወይም አቅም የሌላው አካል እንዴት አድርጎ ሥራውን ሊያከናውን ይችላል? በመንግስት ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው የቋሚ ኮሚቴ አባላት አንዳንድ አስፈፃሚ መ/ቤቶችን በመጎብኘት ኃላፊዎችን አነጋግረው ገለፃዎችን አዳምጠው ይመለሳሉ፡፡ ቁጥጥር ማለት ይህ ነው? ተወካዮች ምክር ቤት ተጠናክሮ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ተብሎ የሚነገረን ይኼ ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እውን ተቆጣጣሪ ቢሆንና አባላቱም በህዝብ የተመረጡ፣ ለህዝብ የሚቆረቆሩ፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ነፃነት ያላቸው ቢሆኑ ኖሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሶስት ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶ በአስፈፃሚው ትዕዛዝ የዜጎች ህይወት ሲረግፍ አጀንዳ ለማሳያዝ የሚሞክር ሰው ባልጠፋ ነበር፡፡ ስለዚህ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይህን ኃላፊነት ሊወጣ አይችልም፤ ሊጠናከር የሚችልም አይደለም፡፡ አስፈፃሚ መ/ቤቶችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ይሰማል፡፡ ነገር ግን ከተጣለበት ኃላፊነት አንፃር አቅሙ ደካማ ነው፡፡ በአገሪቱ ከ250 በላይ ግዙፍ የፌደራል መንግስት መ/ቤቶች ሲኖሩ ተቋሙ በዓመት የፋይናንስ ኦዲት ሊያደርግባቸው የሚችለው ከስድሳ አይበልጡም፡፡ እያንዳንዱን መ/ቤት ለማዳረስና አንዴ ኦዲት ተደርጎ ጉድለት የተገኘበት መ/ቤት ተሻሽሎ እንደሆነ በዳግም ኦዲት ለማረጋገጥ ስንት ዓመት እንደሚፈጅበት መገመት ቀላል ነው፡፡ ተቋሙን በጥቂት ሚሊዮኖች አቅሙን አጎልብቶ የቁጥጥር ሥራ በማካሄድ ብዙ ሚሊዮኖችን ከምዝበራ መታደግ ሲቻል ከፓለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ የተነሳ የአገር ሀብት ለዘራፊ ተጋልጦ ጉዟችን የኋሊት ሆኗል፡፡ ይህንን ለማለት ያስቻለን ተቋሙ ካመጣቸው ሪፖርቶቸ ቀንጨብ ተደርጎ በሚዲያ ከተላለፈው በመስማት ካደረብን መጠነኛ እምነት ነው፡፡ ተቋሙ ከሙሉ ልቡ ሳይሆን ለይስሙላ ብቻ እንዲንቀሳቀስ መደረጉን ሌላው አመላካች ጉዳይ በኦዲት ጉድለት የተገኘባቸው መ/ቤቶችና እስከነአካቴው “ኦዲት አንደረግም” ባሉ መከላከያ ሚኒስቴርን በመሳሰሉ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቀሱ መ/ቤቶች ላይ እርምጃ አለመወሰዱ ነው፡፡ መንግስት ጉዳዩን አጥብቆ የሚሻው ሳይሆን የግብር ይውጣ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ መፈለጉን ሌላኛው ማሳያ የተቋሙ ሪፖርት ለሚዲያ ተቋማት የማይሰጥ መሆኑና በዝርዝር ይፋ የማይደረግ መሆኑ ነው፡፡ ኦዲት የሚደረጉ መ/ቤት ንጽህናና ሌብነት ከህዝብ እንዲሰውር የሚፈለገው ለምን ይሆን? አስፈፃሚውን አካል ይቆጣጠራል ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት ሁለተኛው ተቋም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነው፡፡ ይህ ተቋም የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ሳይሆን ሥርዓቱ ለሚፈጽማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የህጋዊነት ሽፋን ለመስጠት የተቋቋመ ነው፡፡ ከተመሠረተ ጀምሮ በአገሪቱ ከተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል የትኞቹን አጣርቶ እርምጃ እንዳሰወሰደ ከሠነዱ ማግኘት አይቻልም፡፡ ሌሎች የውጪ ተመሳሳይ ድርጅቶች ስለህዝባችን በርካታ ሪፖርቶችን ሲያወጡ ተቋሙ ግን ግፍን በዝምታ በማለፍ ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተቋም ቢኖረንማ ኖሮ በያመቱ ሺሀዎች ሲታሠሩ፣ ሲገደሉ፣ ካገር ሲሰደዱ፣ ዜጎች በጥይት ተቆልተው ወደ እሳት ሲጣሉ፣ በዓል ለማክበር ቀጤማ ይዘው ወጥተው ከሰማይና ከምድር በተርከፈከፈባቸው ጥይት ሲረግፉ “አሁንስ በዛ” በማለት ጥፋተኛን ያጋልጥ ነበር፡፡ አሁን ግፉ በዝቶ የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ የዓለም ሁሉ ዓይንና ጆሮ ወዳገራችን ሲዞር ሥርዓቱን ከውድቀት ለማዳን ሲውተረተር እንመለከታለን፡፡ የተቋሙ መሪ ኢህአዴግ “ሙሉ በሙሉ ቀናኝ” ባለበት 2007ንም ምርጫ ድምፅ ለእውነተኛ ባለቤቱ እንዳይሰጥ ወይም እንዳይቆጠር በማድረግ የመራጮችን ተስፋ በማጨለሙ ረገድ ዋናኛውን ሚና የተጨወቱ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በወቅቱ የፈፀሙት ድርጊት ትክክል አለመሆኑና ህዝቡም በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት አለመምረጡን “ተመራጩ መንግሥት” ሥራ በጀመረ በሁለተኛው ወር የህዝብ ተቃውሞ፡፡ መፈንዳቱ ያረጋግጥልናል፡፡ ስለዚህ የተቋሙ መሪ ከወራት በፊት በተጭበረበረ መንገድ ወደ ስልጣን ያመጡት መንግስት ግፍ ቢፈጽም በገልተኝነት አጣርተው ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለዚህ ነው በምርጫው ጊዜ በነበራቸው ኃላፊነት ቁም ስቅላቸውን ያሳዩአቸውን ለዴሞክራሲያዊ እየታገሉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ባላቸው ኃላፊነት ተጠቅመው ዛሬም ተጠያቂ አድርገው ያቀረቡት፡፡ በኮሚሽነሩ አማካኝነት በተዘረፈ ድምፅ በምክር ቤት የታደመው ፓርላማም ኮሚሽኑ “ከተቃውሞው ጀርባ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ” ሲል ያቀረበውን ሃሳብ ማጣራት ሳያስፈልገው ተቀብሎ አጽድቆ ቀደም ሲል ከተካሄደው የእስራት ዘመቻ የተረፉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ካሉ ታድነው እንዲታሠሩ የወሰነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰብአዊ መብት ኮሚሽናቸውን አስመልክተው በተናገሩት ንግግር ውስጥ አስገራሚ ነገሮችን አሰምተውናል፡፡ “አቅሙን ማጎልበት ይኖርብናል” ያሉትን ተቋም መልሰው ደግሞ “ለዚች ለተፈጠረችው ጉዳይ ግን በቂ አቅም አለው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ “ይቺ” ተብሎ ተንኳሶ የቀረበው ጉዳት በአንድ ቀን ጀንበር ስድስት መቶ ያህል ሰዎች የሞቱበትና የብሔራዊ ሀዘን የታወጀበት የእሬቻ እልቂት፣ በባህር ዳርና በጎንደር መቶዎች የተገደሉበት፣ በቂሊንጦ እስር ቤት ቁጥሩ ያልታወቀ እስረኛ ከነ ነፍሱ የተቃጠለበት፣ በጌዴኦ በርካታ ሰው የሞተበትና የተፈናቀለበት፣ በኮንሶ መጠነ ሰፊ ፍጅት የተካሄደበት ኢሰብአዊ ድርጊት ነው፡፡ እነዚህ ወደፊት ታሪክ ይፋ የሚያደርጋቸውን አሃዞች እንኳን ብንተው የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ “ቆጥሬ ደርሼባቸዋለሁ” ያለው የ495 ሰዎች ሞትና የ464 ሰዎች አካል ጉዳት እንዴት እንደአልባሌ ሊቆጠር ቻለ? ስንት ሰው ቢሞት ይሆን መንግስታችንን የሚያሳስበው? የዓለም ህዝብ ከጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ጎን እንዲቆም ካደረጉትና ለአፓርታይድ ስርዓት መውደቅ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ 69 ሰዎች የተገደሉበት የሻርፕል እልቂት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትራችን አያውቁም ማለት አንችልም፡፡ በህዝብ የተመረጡ መንግስሥታት ባሉባቸው አገሮች እንዲህ ያለው ጉዳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሥልጣን የሚያስወርድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”በብዙ የበለፀጉ አገሮች ግፍ እየተፈፀመ ማንም አይጠይቃቸውም” በማለት “እኛን ለምን ትጠይቁናላችሁ?” የሚል ምሬት ያለው ንግግርም ተናግረዋል፡፡ እንደኮሚሽነራቸው የሆነውን “አልሆነም” የተበደለውን “ተጠያቂ”፣ መቶውን “እስር” ነው ከሚሉ አንደኛውን “አትጠይቁን” ማለት ይሻላል፡፡
ለመሆኑ የሰብአዊ መብት ኮሚሽናችን ዓላማው የህዝብ መብት እንዳይጣስ ማድረግ፣ ተጥሶም ከተገኘ አጣርቶ እርምጃ ማስወሰድ ከሆነ ተመሳሳይ ዓለማቀፍ ድርጅቶች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉትና በማጣራቱ ተግባር እንዲያግዙት የከለከለው ምንን ለመደበቅ ብሎ ነውን ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ለመሥራት እርዳታና ብድር ሲያጎርፉልን “ሉአላዊነታችንን ደፍራችኋል ንቃችሁናል” ያላልናቸውን አካላት ዛሬ “በማጣራቱ ሂደት እንተባበራችሁ” ቢሉ ሉአላዊነትን መድፈር የሚሆነው በምን ስሌት ነው? እንዳይገለጥ የምንፈልገው እውነት ይኖር ይሆን? በአጠቃላይ “ተጠናከሯል፣ አስፈፃሚውን እየተቆጣጠረ ነው፣ ተአማኒነው፤” ተብሎ የሚሞካሸውና እየታደስን ለመሆናችን እንደማሳያ የተወሰደው ተቋሞ እንዲህ ያለው ነው፡፡ አስፈፃሚውን ይቆጣጠራሉ የተባሉት ሌሎች ተቋማት የእንባ ጠባቂ ተቋሞና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ናቸው፡፡ የነዚህ ተቋማት መኖር የሚታወቀው በዓመት የተወሰነ ቀናት ፓርላማ ላይ ሲቀርቡ ወይም መንግስት ባስፈለገው ቀን መዝዞ ለሰው ሲያሳያቸው ነው፡፡ ፋይዳ ያለው ሥራ ሲፈጽሙ አይሰማም ከሶስት ዓመታት በፊት የመንግስት አስተዳደር ኮሚሽን “ከፍተኛ ባለሥልጣኖች የመንግስት ቤቶችን አለአግባብ ይዘው አንለቅም ብለውኛልና አንድ በሏቸው” በማለት ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ቢያመለክት “በቅድሚያ ለኛ ቤት ስጡን” እንደተባለ ከመንግስት ሚዲያ ለመረዳት ችለናል፡፡ ህዝቡ የሙስና ኮሚሽን ብሎ ሲጠራው ስህተት መስሎን የነበረው ለካ ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ ራሱ ሌላ ተቆጣጣሪ የሚያሻው ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን ብር የተሠራ ህንፃ ጠፋ በሚባልበት አገር፣ ተማሪዎች መሬት እየተኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርስቲ አልጋዎች በሚከራዩበት ምድር አስተዳደራዊ በደል ደርሶባቸው ፍትህ የተነፈጉ መንገድ ላይ በሚንሰላወዱበት ስርዓት ውስጥ ፀረ ሙስና/እንባ ጠባቂ ተቋማት አሉ ማት ፌዝ ነው፡፡ የውጭ ለጋሾችን ለማታለል ካልሆነ ከህዝብ ጆሮ የሚገባ አይደለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥልቅ ተሀድሶው ሌላኛው መገለጫ ዴሞክራሲን የማስፋትና የማጥለቅ እንቅስቃሴ መጀመር መሆኑ ገልፀዋል፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፋት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን መገንባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም የሚገነባው ነፃ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲኖሩ፣ ድምፁ ዋጋ ያለው መሆኑን የሚያምን ህዝብ ሲኖር፣ የህግ የበላይነት ሲኖር፣ በነፃ የመደራጀት መብት ሲኖርና ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ህዝቡ ከመረጠው ብቻ ሥልጣን መቆየት የሚፈልግ መንግስት ባለበት አገር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስንመለከት የኢሀአዴግ መንግስት ለዚህ ዝግጁ አይደለም፣ ፍላጎትም የላቸውም፡፡ ከመድረክ ውጪ ከሚታወቅባቸው አባባሎች አንዱ “ደም ከፍለን የመጣነው በካርድ ለመውረድ አይደለም” የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ባህሪይ አስተዋጽኦ ያደረገው ሥልጣንንና በሱ አማካኝነት የሚገኘውን ጥቅም አብዝቶ በመሻቱ ብቻ ሳይሆን ገና ሲመሠረት የተጠናወተውና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን የማይፈቅደው የሶሻሊስ ርዕዮተ ዓለም አባዜ ነው፡፡ ድጋፋቸውን ለማግኘት ሲል በኃላ ላይ የምዕራቡን ዓለም አስተሳሰብ ተቀብያለሁ ቢልም በራሱ ውስጥ አስርጾ ሊጠቀምበት ባለመቻሉ አስተሳሰቡን እንደያዘ የማስመሰያ ሰልቶችን ለመቀየስ ተገደደ፡፡ ለማደናገሪያነት አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግሥት እና አውራ ፓርቲ የሚሉ ባዶ ቃላትን መሰበክ ጀመረ፡፡ በተግባርም ዴሞክራሲ ብሎም መድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚመሠረትበትን መሠረት መናድ ተያያዘ፡፡ ነፃ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳይመሠረቱ አደረገ፡፡ በትግል የተመሠረቱትን በራሱ ሠርጎ ገቦች አማካኝነት አፈራርሶ ጥገኛ ፓርቲዎች እንደአሻን እንዲፈሉ አደረገ፡፡ በተለይ በ1997 ህዝቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ከመረጠ በኃላ በብዙ ቦታዎች ምርጫ እንዲደገም አድርጎ አብዛኛውን መልሶ ወሰደ፤ በቀጣይ ምርጫ አንድ ተቃዋሚ ብቻ ፓርላማ መግባት ሲችል፤ በ2007 ደግሞ ሁሉንም ጨርሶ በመጨፍለቅ በአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ መንግስት አቋቋመ፡፡ አምባገነንነቱንና አይምሬነቱን ከወራት በኃላ በግድያ አስመረቀ በዚህም ድመፅ ዋጋ አለው ብሎ የሚያስብ ህዝብ እንዳይኖር የመጀመሪያውን መስፈርት አፈረሰ፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሰርዓት ያለ ገለልተኛ የፍትህ ተቋማት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ፍ/ቤቶች፣ ፓሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ማረሚያ ቤቶች በራሱ ሰው ብቻ እንዲያዝ እንዳረገ የህግ የበላይነትን ገደለ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በራሱ ፓሊሶች ተይዘውና ተመርምረው፣ በራሱ አቃቤ ህጎች ተከሰውና ተመስክሮባቸው፣ በራሱ ዳኞች ተፈርዶባቸው፣ በራሱ ጠባቂዎች የእስር ቤት ህይወት እንዲገፉ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ እንዴት ነው መድብለ ፓርቲ ሰርዓት በቅሎ ሊያድግ በሚችለው? በአገሪቱ ውስጥ በሽብርተኝነት ተከሰው እስር ቤቶችን ያጣበቡት እነዚህ የዴሞክራሲ ተሟጋች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በአገሪቱ ህግ መሠረት በነፃነት የመደራጀት መብት ተጽፎ ያለ ሲሆን ይህን መብቱን ለመጠቀም የቆረጠ ሰው ይዋል ይደር እንጂ መጨረሻው ቢያንስ እስር ቤት ነው፡፡ ከእስር በመለስ ያለው ፈተናም ቀላል አይደለም፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን በሰበብ አስባቡ ሁሉንም የዜግነት መብቶች ያስገፍፋል፡፡ ከሥራ ያስባርራል፣ ዕድገትና ሹመት ያስከለክላል፣ መኖሪያ ቤት በአንድንድ ቦታ ደግሞ ቀባሪም ያሳጣል፤ ቤተሰብ ለአደጋ ያጋልጣል፣ በአጠቃላይ ይህ ነው የማይባል ዋጋ ያስከፍላል ኢህአዴግ እንደፓርቲ የመንግስትን ሀብትና ንብረት ያለምንም ከልካይ ሲጠቀምበት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ንብረት ማፍራት አይችሉም፣ ቤት የሚያከራያቸው የለም፣ ድጋፍ ማሰባሰብ አይችሉም፣ ጽ/ቤት መክፈት አይችሉም፣ አዳራሽ ማግኘት ሚዲያ መጠቀም አይችሉም፡፡ በማንኛውም መንገድ ሲተባበራቸው የተገኘ ሰው ማረፊያውን ያውቀዋል፡፡ እንዲህ እያደረገ ነው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በመድብለ ፓርቲ ስርዓት አማካኝነት ዴሞክራሲን ለማስፋትና ለማጥለቅ እንቅስቃሴ እያደረግሁ ነው የሚለው፡፡ አሁንም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እስር ቤት አጉሮ፣ ጽ/ቤታቸውን ዘጋግቶ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁሉንም መብታቸውን ገፎ እየታደስኩ ነው ማለት የቀልዶች ሁሉ ቀልድ ነው፡፡
ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖር የግድ መሟላት ከሚገባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው የገለልተኛ ምርጫ አስፈፃሚ ተቋም መኖር ነው፡፡ በአገራችን ያለው የምርጫ አስፈፃሚ ከማዕከል ጀምሮ እስከ ምርጫ ጣቢያ ድረስ ያሉት በሙሉ የፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ አምስት አስፈፃሚዎችና አምስት የህዝብ ታዛቢዎች ገለልተኛ በሚል ስም የሚመድባቸው ኢህአዴግ ሲሆን በፓርቲው ስም አንድ ታዛቢ በመጨመር ተቃዋሚ ፓርቲ ከሚመድበው አንድ ሰው ጋር አደራ አንድ ለአንድ ይቀመጣሉ፡፡ በሁሉም ደረጃ ያለ የምርጫ አስፈፃሚ መዋቅር በዚሁ ዓይነት የተተበተበ በመሆኑ አንድ ቦታ የተዛነፈን ፍትህ የትም ማቃናት አይቻልም፡፡ ታዲያ የትኛውን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ምሰሶዎችን አስተካክሎ ነው መንግስት ዴሞክራሲን እያሳደኩ እያጠለቅሁነው የሚለው? ከላይ የጠቀስናቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ሊቀናቀኑ የሚችሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማዳከምና በማጥፋት ጥገኛ ፓርቲዎች ከጎኑ አሰልፎ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ያለ በማስመሰል ድራማ ይሠራል፡፡ “ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ንግግር ጀምሬያለሁ” እያለ ቀለብተኞቹን በሰፊው ያስተዋውቃል፤ ተቃዋሚ እንዲመስሉ አንድንድ ጥያቄዎችንም አፋቸው ላይ አድርጎ ህዝቡ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የግል ፕሬሶችንም አዳክሞ ከማጥፋት አልፎ ባህር ማዶ የሚገኙ አንድንድ የሚዲያ ተቋማት ላይም በቻይናውያን ቴክኖሎጂ እየተገዘ እንዳይደመጡ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ በ1997 ምርጫ ዋዜማ ጥቂት የዲሞክራሲ ጭላንጭል የታየ በመሰለበት ወቅት ልዩ ልዩ ውይይቶችን በማዘጋጀት መንግስትና ተቃዋሚዎችን ለማከራከር ወሳኝ ሚና የተጫወቱ የሲቪክ ማህበራትም በአፋኝ አዋጅ ደብዛቸው እንዲጠፉ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ያለ ዴሞክራሲ ነው የሚገነባው? ባለፉት ሁለት ዓመታት ለተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ቀዳሚ መንስኤ ነው ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለፀው የሥራ አጥነት ችግር ነው፡፡ በእኛ እምነት ግን አብይ መንስኤው ህዝቡ አሮጌውን አስተሳሰብና ሥርዓት መሸከም የማይችልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ነው፡፡ አሮጌው አስተሳሰብ ልማታዊ መንግስት ከሚለው አንፀባራቂ ስም በስተጀርባ ያለው ሁሉን ነገር በኢህአዴግ ቁጥጥር ሥራ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከኢሀአዴግ ወይም የሱ ተለጣፊዎች ውጪ ሌላ ፓርቲ እንዳይኖር፣ ከአባላቱ ውጭ ሌላ ሰው ባገሩ ሠርቶ እንዳይኖር፣ ሀብት እንዳያፈራ፣ ይህ እንዲሆን፣ በራሱ የማይተማመን፣ የኢህአዴግን ፈቃድ ጠብቆ የሚያድር ጥገኛ ሆኖ እንዲኖር የማድረግ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ለረጅም ጊዜ ሠርቷል፡፡ የትምህርት ሰርዓቱ ጥገኛና በራሱ የማይተማመን ዜጋ እንዲያፈራ አድርጓል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገሪቱ ሀብት በሙሉ በጥቂት የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እጅ አስገብቷል፡፡ ጥገኛ ባለሀብቶችም ብዙ የሰው ኃይል ሊያሳትፉ በሚችሉ የማኑፋክቼሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሳይሆን በጥቂት የቤተሰብ አባላት አማካኝነት ሀብት በሚዛቅባቸው የአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ለሥራ አጥነት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ወጣቱ በተገኙት ጥቃቅን ዕድሎች እንኳን እንዳይጠቀም “የወጣት ሊግ አባላት፣ የነዋሪዎች ፎረም ድጋፍ ያስፈልጋል” በማለት በፖለቲካዊ አመለካከት አግልሎአቶዋል፡፡ ስለዚህ አብዛኛው ወጣት ጊዜያዊ ሥራ አጥነቱ ብቻ ሳይሆን ነፃነቱንም ተገፍፎ የመኖር ዘላቂ ተስፋውን ያጨለመውን ስርአት ሊታገለው ተነሳ፡፡ ሥራ አጥነቱንም ቢሆን አሁን መንግስት ሊፈታ እየሄደበት ያለው አካሄድ ጥገኛ ህብረተሰብ በመፍጠር አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሥራ አጥ የሚመዘግበው፣ በማህበር የሚያደራጀው፣ ገንዘብ የሚያበድረውና ገበያ ትስስር የሚፈጥረው አሁንም መንግስት ስለሆነ ከጥገኝነት መላቀቅ አይችልም፣ ዓላማውም ይኼው ነው፡፡
በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነው መላው የኢህአዴግ ካድሬና ሚዲያ እየሰበከ ያለው በጥልቀት የመታደስ ጉዳይ በፍጹም ሊሆን የማይችልና ጊዜ ማባከኛ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ማሳያ ናቸው የተባሉ ድርጊቶችም ተሀድሶ ማምጣት የሚችሉ አይደሉም አዲስ የተባሉትም አዲስ አይደሉም፣ ቴክኖክራቶች አይደሉም፣ ለውጥ ለማምጣት የሚችሉም የሚፈልጉም አይደሉም፡፡ የሚመሩት በኢህአዴግ አስተሳሰብ ስለሆነ የሚታደስ ነገር የለም፡፡ አመራር አካሉን ለመቆጣጠር እየተጠናከሩ ናቸው የተባሉት የተወካዮች ም/ቤት፣ የዋና ኦዲተር፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የፀረ ሙስናና የእንባ ጠባቂ ተቋማት አፈጣጠራቸውና አደረጃጀታቸው በኢህአዴግ አሮጌ አስተሳሰብ የተቃኘ በመሆኑ ለጥልቅ ተሀድሶው አጋዥ ሳይሆኑ ስርዓቱን ከነአስተሳሰቡ ለማቆየት እየተፍጨረጨሩ ናቸው፡፡ ለማስፋት እየተሞከረ ነው የተባለው የዴሞክራሲ ምህዳርም ተቃዋሚዎችን በገፍ በማሰርና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት ሁሉንም እንቅስቃሴ በማገድ እስከነአካቴው በመጥፋት ላይ ያለ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ለወጣቶች እየተፈጠረ ነው የሚባለው የሥራ ዕድል አሁንም ወገንተኛና አድልኦአዊ ከመሆን አልፎ ለተማረ ወጣት ሳቢ አይደለም፡፡ ሰርዓቱ አሁን በተያዘው መንገድ ሊታደስ የሚችልም የሚገባውም አይደለም፡፡ አንድ ነገር እንዲታደስ የሚፈለገው 1ኛ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለው አካሉ አገልግሎት ሊሰጥ ከማይችለው አካሉ በልጦ ሲገኝ 2ኛ የሚያስወጣው ወጪ አነስተኛ ሲሆን 3ኛ አዲሱን ማግኘት ያልተቻለ ከሆነ ነው፡፡ የዚህን መንግስት አካላት ብንፈትሽ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል አንድም አካል የለውም፡፡ ሁሉም የሚኒስቴር መ/ቤቶችና አደረጃጀቶቹ ከላይ እስከታች ያረጁ በመሆናቸው ለማደስ የሚፈጀው ጊዜና ሀብት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አንድ ነገር ዘላለም ስታደስ አይኖርም፤ አገልግሎቱን ፈጽሞ ጨርሶ መታደስ የማይችልበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ከመወለድ፣ ከመጎልመስና ከመሞት ዲያሌክቲካዊ ህግ ውጪ መሆን የሚቻለው የለም፡፡ አገሪቷ ዘራፊ፣ ጉበኛ፣ ሙሰኛን በጥልቅ ተሀድሶ ስም ሥልጣን ላይ ትታ እሱን በዓይነቁራኛ ስትጠብቅ፣ ስትገመግም ዘመናት ልትቆጥር አትችልም፡፡ አሮጌ በአዲስ መተካት ግድ ነው፤ አገሪቱ አዲስ ሰርዓት አስፈልጓታል፡፡ መብት፣ ነፃነት፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት፣ ዴሞክራሲ የሚሉ አስተሳሰቦች እንደ አዲስ ሀሳብ ሳይሆን አዲስ ህልውና ሊያገኙ ገፍተው እየመጡ ነው፡፡ እነዚህን አስተሳሰቦች ሲጋፉና ሲያቀጭጫቸው የኖረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የልማታዊ መንግስትና የአውራ ፓርቲ አስተሳሰቦች ቦታ መልቀቅ አለባቸው፣ ምክንያቱም በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አይጨመር፡፡
ግንቦት 2009
Average Rating