ይድረስ ለዳንኤል ብርሃኔ /ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ/
ልብ ብለህ አንብባት ባለቤት አልባ አገር
“እናንተ ዛሬ የአየር ኃይላችንን የጥራት መመዘኛ አሟልታችሁ በውጪ አገር ትምህርታችሁን ለመከታተል የምትሄዱ ወጣቶች፤ በቅድሚያ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ። በቆይታችሁ ወቅትም ትምህርታችሁን በሚገባ ቀስማችሁ አገራችን ኢትዮጵያን ለማገልገልና ለህዝባችን ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት እንደሚኖርባችሁ ለአፍታም መዘንጋት የለባችሁም። ትልቅ አደራም ተሸክማችኋል።
ምንም እንኳ የከፋ ድህነት ያለባት አገር ዜጐች ብንሆንም በአያት፣ ቅድመ አያቶቻችን ተጋድሎና መስዋዕትነት የቀደምት ነፃነት ባለቤት አገር ዜጐች በመሆናችን እራሳችንን በኩራት ቀና አድርገን እንድንሄድ አስችሎናል። በርከት ያሉ አገሮች ዜጐቻቸውን የሚያስተምሩበት ት/ቤት ውስጥ ከመጨረሻዎቹ ደሃ አገሮች መካከል ብንገኝም ጊዚያዊ የሆነውን ቁሳዊ ድህነትን ተቋቁሞ የአገር አደራን መወጣትን የመሰለ ታላቅ ክብር እንደ ሌለ ለኛ ለኢትዮጵያውያኖች ማንም ሊያስተምረን አይችልም። በዕውቀት በልፅጋችሁ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመማር ከጊዜው ጋር አብሮ ለመጓዝ የምትችል ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስተላለፍ ክቡር የዜግነት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳችሁ።
ከሚገጥሟችሁ የብዙ አገር ተማሪዎች መካከልም ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በዚሁ ት/ቤት ውስጥ ዜጐቻቸውን ያስተምራሉ። ንቀት፣ ጥላቻና ትንኰሳ ሊደረግባችሁ ይችላል። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎችን በተቻለ መጠን በትዕግስትና በአስተዋይነት ማሳለፍ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አገራችሁ ከሰጠቻችሁ አደራና ከሄዳችሁበት ዓላማ በምንም መንገድ ዝንፍ ማለት አይገባችሁም። እንዲህ ስላችሁ ግን የዜግነት ክብርን የሚነካ፣ ህሊናን የሚያቆስል ትንኰሳ ከሆነ ግን በምንም ዓይነት ዝም ብሎ ማለፍ አይገባም፤ አፀፋውን መመለስ ይኖርባችኋል። በዚህ ጉዳይ ለሚመጣ ማናቸውም ነገር ከጐናችሁ ነን። መልካም የትምህርት ዘመን”።
ሜ/ጄ አምሃ ደስታ
ታህሳስ 1976 ዓም
ደብረ ዘይት – ሃረር ሜዳ
ጊዜው እንዴት ይሮጣል? ይህ ከላይ ያነበባችሁትን ተወዳጁ የአየር ሰው ሜ/ጄኔራል አመሃ ደስታ ከ32 ዓመታት በፊት እኔ አባል ለሆንኩበት ታዳሚ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ለበረራ ስልጠና ስንሄድ ያስተላለፉት መልዕክት ነበር። ጊዜ በማይሽረውና በማይለውጠው መልኩ ዛሬ ድረስ በልቤ ውስጥ ታትሞ ተቀምጧል። እኚህ ጀነራል መኰንን በመጨረሻም ቃላቸውን በመጠበቅ እኛን ስለአስተማሩን የዜግነት ክብር ጉዳይ ነፍሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። መቼም ቢሆን የማይረሳ፣ የማይዘነጋ፣ ድንቅና ህያው ታሪክ ነው።
ጄኔራል አምሃ ካለፉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያችን ውስጥ መንግስት ተለወጠ። እንዳለመታደል ሆኖ የመንግስት ለውጡ በኃይልና መሳሪያ ባነገቱ ታጣቂዎች በመሆኑ ሁሉም ነገር በመሳሪያና በኃይል ቁጥጥር ስር ዋለ። ለዚህም ይመስላል አዲስ የተለወጠው ስርዓት በቀድሞው መንግስት ዘመን የነበረውን በጐ ነገር ሁሉ ከመጥፎው ጋር ቀላቅሎ እኩል ኰነነ። በቀደመው ርዓት የተገነቡ የመንግስት መዋቅሮች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች … ሁሉም በኃይል ተለወጡ። ለአገር ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ጥናት፣ ብዙ ሃብት የፈሰሰባቸው ተቋሞች እንደቀልድ ለዘላለም ተበታተኑ… ጠፉ። የሚያሳዝነው ጉዳይ ታድያ እነዚህን ተቋማት መልሶ ለመገንባት ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድቶ የአገርን ሃብት ከጥፋት የታደገ ያለመኖሩ ነበር። በኋላ ግን ከምር ዋጋ አስከፈለ። በአልባሌ ግጭት እልፍ አእላፍ ህይወት ተገበረ።
ይኼ ሁሉም ሆኖ ዛሬም ድረስ አገሪቷን ዋጋ እያስከፈለ ስለአለው ጉዳይ ለአብዛኞቻችን ቁብ የሰጠን አይመስልም። በመንግስት ለውጡ ሳቢያ በገሃድ ተጠቂ ከሆኑት ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነው። የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በጅምላ እንዲፈርስ የጭካኔ ፍርድ መፍረድ እብደት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊባል አይችልም። ያም ሆኖ አይኔ እያየ እነ ፎጊ፣ ቬኖምና ድራጐንን የመሳሰሉ ኢትዮጵያችን መልሳ ልታገኛቸው በማትችላቸው የአቭዬሽን ባለሙያዎች አማካኝነት ከፍርስራሽ ስር አንስቶ መልሶ ለማቋቋም ቢሞከርም እንዲህ ቀላል ሆኖ አልተገኘም። እጅግ ከፍተኛ ዋጋን አስከፈለ።
የአቬዬሽን ህግ ሁሉ የደርግ ህግ የመሰላቸው የፖለቲካ ካድሬዎች ሁሉንም ነገር በጅምላ ደርግ ከሚለው ቃል ጋር የሚመዘን አድርገው ያለ ዕውቀት አየር ኃይሉን ያለርህራሄ ወደገደል ወረወሩት።
“ The more you sweat in peace , the less you bleed in war” የሚለውን “ላብ ከደም ያድናል” የስልጠና ህግ ፤ “ war ’’(ጦርነት) የሚል ቃል ስለአለበት ብቻ የጦረኛነት መፈክር ነው በሚል ትርጉሙን አንሻፈፉት። ደርግ የፈጠረው ቋንቋ መሆን አለበት በሚል አላዋቂነትም መወንጀያ ሆነ።
በ1969 ዓም ከሶማሊያ ተስፋፊ ጦር ጋር የተፈጠረውን ፍትሃዊ የመከላከል ጦርነት የደርግ የጦረኝነት ባህሪይ ሆኖ እንጂ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የተገባበት እራስን የመከላከል ተጋድሎ አይደለም ብለው ያለፈውን ስርዓት ሲወነጅሉበት ተደመጡ። በግዙፍ የሜካናይዝድ ጦር ድሬ ዳዋ ድረስ ለጥፋት የመጣን የሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት ለመከላከል የተደረገውን እልህ አስጨራሽ መስዋዕትነት የደርግ የጦረኝነት ባህርይ ሲያደርጉት፤ በተቃራኒው ደግሞ ባድመ የተባለች አነስተኛ መንደር ተወረረች በሚል ኃላፊነት የጐደለውን የእርስ በእርስ ፍጅት ሉዓላዊነት የማስከበር ፍትሃዊ ጦርነት ነው በማለት ለራስ ሲቆርሱ… የራስ ወዳድነት አባዜ በገሃድ ተስተዋለ።
“ Through this portal passes all African finest pilots ” የሚለው ጥቅስ በኢትዮጵያ አየር ኃይል በረራ ት/ቤት መግቢያ በር ላይ በትልቁ ተፅፎ ይነበባል። “ምርጦቹ የአፍሪካ በራሪዎች የዚህ ት/ቤት ውጤት ናቸው” ማለት ነው በግርድፉ ሲተረጐም። ይህ ደግሞ እውነት ነው። ከዚህ ት/ቤት ስልጠናቸውን ጨርሰው የወጡ በራሪዎችና አጠቃላይ የአየር ኃይሉ ባለሙያዎች ምርጦች እንደነበሩ በግዳጅ አፈፃፀሟቸው ብቃታቸውን በግልፅ ለዓለም አሳይተዋል። ለአገራችንም ሆነ ለህዝባችን የዜግነት ኩራት ነበሩ። ስርዓቱ ተለወጠም አልተለወጠም፣ መረረም ጣፈጠም የሙያው ባለቤቶች የሃገርና የህዝብ ሃብት ናቸው።
ለምሳሌ የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚውና በሶማልያ ጦርነት ወደር የሌለው ጀግንነት የፈፀመው ጄ/ል ለገሰ ተፈራ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት የበራራ ትምህርታቸውን አጠናቀው፣ በወታደራዊው የአስተዳደር ዘመን ደግሞ ከሶማልያ ተስፋፊ ሰራዊት ጋር በተደረገው ተጋድሎ መስዋዕትነት የከፈሉት የዜግነት ግዴታቸው ሆኖ እንጂ ለንጉሱ ወይም ለደርግ ብለው አልነበረም። ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስም ቢሆን በንጉሱ ዘመን በፈረንጆቹ 1969 ዓም ጀምሮ አየር ኃይሉን ተቀላቅሎ በወታደራዊው ስርዓት ዘመን ከሶማልያ ለተሰነዘረብን የእብሪት ወረራ የሶማልያን አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች በአየር ላይ በመልቀም የሚታወቅ ዕውቅ ጀግና መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው።
በተጨማሪም ይኼው እራሱ ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስ እንደገና በህውሃት/ኢህአዴግ ዘመንም ከኤርትራ ጋር ለተገባው ግጭት በግምባር ተሰልፎ ታላቅ መስዋዕትነት የመክፈሉ ተምሳሌነት የአገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ግዳጅ ለስርዓት ሲባል ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ መሆኑን ያሳየ ህያው ምስክር ነበር። እኛ ግን አገርና ህዝብ ከስርዓት በላይ መሆናቸውን መገንዘብ ተስኖን ብሄራዊ ጀግኖቻችን እየተዋረዱ ወደ ወህኒ ሲወረወሩ ቁጭ ብለን ታዘብን። ይህም ሆኖ አዲሱ ስርዓት ይህንን ብሄራዊ ተጋድሎ በዜግነት ዕይታ ማየት ቢሳነው መላው የአየር ኃይል ሰራዊትና ቤተሰብ ግን የእነ ጀ/ል ለገሰንና የመሳሰሉትን ብሄራዊ ጀግንነት ለአፍታም የሚዘነጉት አልሆነም።
በዚህ አጋጣሚ ሶቭዬት ህብረት የበረራ ትምህርት ልከታተል ሄጄ በትምህርት ቤቱ ካሉት የተለያዩ ዜጐች መካከል በአንደኝነት ተመርጦ ፎቶ ግራፉ በትልቁ ከፍ ብሎ የተሰቀለውን የአገሬን ልጅ ጂልቻን ስመለከት የተሰማኝ ወደር የሌለው ደስታ በዜግነት ስላጐናፀፈኝ ክብር እንጂ የጅማ ልጅ ስለሆንኩ አልነበረም። አፈወርቅ ኪዳኑም ሆነ መንግስቱ ካሳ እንዲሁም ባጫ ሁንዴ የዚሁ የዜግነት ክብር ተምሳሌቶች ናቸው። ሌላው ቀርቶ እጅግ ከመሸ በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ህይወታቸውን ለአገር አንድነትና ሉዓላዊነት አሳልፈው የሰጡትን እነ መ/አ መርዕድ ዳጨው፣ መ/አ አማኑኤል አምደ ብርሃንና መ/አ ጥላሁን ኃይሉን የመሳሰሉ አድገው ያልጨረሱ ለጋ ወጣቶች ስናስብ ለኢትዮጵያ አንድነት የተከፈለው መስዋዕትነትና የፈሰሰው የእነዚህ ወጣቶች ትኩስ ደም ከአለት በላይ ከብዶ ይሰማናል። በኰ/ል መንግስቱም ሆነ በአቶ መለስ ስርወ ስርዓት አየር ኃይልን ያሳተፈ ከጐረቤት አገር ጋር ደም ያፋሰሰ ጦርነት ተካሂዷል።
በደርግ ዘመን ከሶማልያ ጋር የነበረውን የአየር ኃይል ተሳትፎ፣ ስለ ግዳጅ አፈፃፀሙና የጦርነት ውሎው ብዙ ብዙ ተብሎለታል። በዚያ ዘመን ኢትዮጵያ ከንጉሱ ስርዓት ወደ ወታደራዊው አገዛዝ የምታደርገውን ሽግግር ምክንያት አድርጐ በአየርም ሆነ በየብስ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የኢትዮጵያን ግዛት የወረረውን የሶማልያ ተስፋፊ ሰራዊት በሰባት የኤፍ-5 አውሮፕላን ብቻ ጠላቱን የገጠመው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አለምን ጉድ ባሰኘ መልኩ በርካታ የሶማልያን የጦር አውሮፕላኖች በአየር ለአየር ውጊያ ብቻ ሲያራግፍ መታዘባችን የዘመኑን የአየር ኃይልን ስልጠናና የውጊያ ብቃት ቁልጭ አድርጐ ያሳየ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ በአቶ መለስ ዘመን ህውሃት ከአዲሲቷና ትንሽዬ ኤርትራ ጋር ባደረገው ፋይዳ ቢስ ግጭት ቁጥሩ ምን ያክል የህይወትና የንብረት ኪሳራ እንደደረሰ ማሰብ ሁለቱም ጦርነቶች የአንድ አገር የጦርነት ታሪክ መሆናቸውን ለማመን ያስቸግራል።
በአምስት አመት ታዳጊ አየር ኃይል የምትመሰለዋ ትንሽዬዋ ኤርትራ በሃምሳ አመት ጐልማሳነት ከፈረጠመችው ኢትዮጵያ ጋር ነፃ ትግል ሲገጥሙ ማየት የሚያሳፍረውን ያክል፤ በግጭቱ ሳቢያ የደረሰውን ኪሳራ ስናሰላ ኢትዮጵያ በሶማልያ ላይ እንዳስመዘገበችው ድል አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት የምንጓዝበት ታሪክ እንዳላስመዘገብን ማሰብ በእጅጉ ያሸማቅቃል። አሳዛኝ ዋጋ መክፈል ይሏል ይኼ ነው።
በእርግጥ ለዚህ ሁሉ ጥፋት፣ ኪሳራና ብሄራዊ ውርደት የተዳረግነው ስርዓት ስለተለወጠ ብቻ በብዙ ድካም የተገነቡትን ተቋሞቻችንን አፍርሰን ከዜሮ በመጀመራችን ነበር። የመንግስት ለውጡ ከመጣ ከጥቂት ቀናት ጀምሮ ለቁጥር የሚታክትና ለሂሳብ የሚያስቸግር ውድቀትና ውድመት ተመዝግቧል። ህውሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረና እስከ ፈረንጆቹ 2000 ዓም ማለትም ከኤርትራ ጋር የነበረው ዕልቂት ጋብ እስከአለበት ድረስ ብቻ የነበረውን የአየር ኃይልን ኪሳራ ብናሰላ፤ ሃላፊነት በጐደለው መልኩ የአየር ኃይልን ወታደራዊ ተቋም ማፍረሳችን ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈለን ለመረዳት ግሩም ማስረጃ ይሆናል። ለዚህ ታላቅ ኪሳራና ብሄራዊ ውርደት ዋናው ምክንያት ደግሞ የሙያውን ባለቤቶች ወደ ጐን ገፍትሮ ሙያ አልባ ካድሬዎችና የአየር ኃይሉን ማልያ የለበሱ እንጂ ዕውን አየር ኃይል ያልነበሩ ታጣቂዎች በመረከባቸው መሆኑን ማሰብ በራሱ ክፉኛ ያስቆጫል።
በእርግጥ አደጋን መቀነስ እንጂ ፍፁም ማስቀረት እንደማይቻል ግልፅ ነው። የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሲዊድኖች ዕርዳታ ሲቋቋም በየጊዜው አደጋ ሲያጋጥም እንደነበረና እንዲያውም ሲዊድኖቹ በሻጥር ሲጠረጠሩበትና ሲታሙበት እንደነበር አንድ አዛውንት የአቭዬሽን ሰው አጫውተውኛል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የበረራ ስልጠናም ሆነ የአየር ኃይል ግንባታ ጉዞ ተደጋጋሚ አደጋዎች (accidents and incidents) ተመዝግበዋል። ከዚህ ሁሉ በከፋ መልኩ ግን እንደ ህውሃት ዘመኑ አየር ኃይል እጅግ የከፋ አልተመዘገበም። ዘግናኝ አደጋዎችን በማስመዝገብ ህውሃትን የሚወዳደረው ገና አልተፈጠረም። ይህ ደግሞ የአየር ኃይሉን ዝና ዝቅ የሚያደርግና ብሄራዊ ውርደትን የጨመረ ነበር። ተጠያቂነት የሌለበት ስርዓት በመፈጠሩ እንጂ ህግና ፍትህ ቢኖር ኖሮ ብዙ የሚያጠያይቁ፣ ብሄራዊ ደህንነታችንን ለአደጋ ያጋለጡ፣ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስም መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች ከፊታችን ተደቅነዋል። ይህንን አባባል በቅርብ ጊዜ የተካሄደውን የህውሃት/ኤርትራ ግጭትን ለአብነት በማስረጃ ብንፈትሽ ….
•ሱፐር ሶኒክ አውሮፕላንን ከታጠቀች ዘመናትን ያስቆጠረችውና በአየር ኃይል ብቃቷ አለም የመሰከረላት ገናናዋ አገራችን ገና ዳዴ በማለት ላይ በነበረችው ኤርትራ ያውም በመለማመጃ አውሮፕላን የአየር ክልላችን ተጥሶ እስከ መቀሌና አዲግራት ድረስ ዘልቆ በመግባት ለደረሰው ከፍተኛ ኪሳራና ብሄራዊ ውርደት ቀጥተኛ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አካላት እስከ አሁኗ ደቂቃ ባለመኖራቸው።
•በዚሁ ከላይ በጠቀስነው ግጭት ሳቢያ በዓለም ታይቶም ሆነ ተሰምቶም በማይታወቅበት ሁኔታ በሚገባ እየሰራ ያለ ተዋጊ ሄሊኰፕተርን በውጊያ መስመር ውስጥ ለጠላት አሳልፎ ሰጥቶ የተመለሰና፣ የተለየ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር እንኳ ቢባል ተዋጊ አውሮፕላኑ ለጠላት ጠቀሜታ እንዳይውል ባለበት ቦታ ላይ ማውደም ሳይቻል ቀርቶ በአጭር ደቂቃዎች ውስጥ ጥለን የሄድንላቸውን አውሮፕላን ጠላት አንስቶ መጠቀሙና ጉዳት ማድረስ መቻሉ ፤ ለዚህም ዛሬ ድረስ ተጠያቂ የተደረገ ክፍል ያለመኖሩ።
•የራስን ተዋጊ አውሮፕላን ግዳጅ ፈፅሞ ወደ ቤዙ በመመለስ ላይ እያለ በተደጋጋሚ ዓልሞ በአየር መቃወሚያ መትቶ የጣለና የአየር ኃይሉን መልካም ዝና ወደ ውርደት ዝቅ የደረገ ተግባር የፈፀሙ ተጠያቂ ሲሆኑ ያለመስተዋሉ።
•እንኳንስ ለኢትዮጵያ ይቅርና ለመላዋ አፍሪካ የሚተርፉ ምርጥ የአቬሽን ባለሙያዎች ባለቤት የሆነችው አገራችን በስርዓት ለውጥ አስባብ ብቻ እንደ ኰብራ፣ ነብሮና ጓደኞቻቸውን የመሳሰሉ ምርጥ የአቭዬሽን ሰዎች በእስር ቤት አጉሮ ከዓለም ላይ ለተለቀሙ ቅጥረኞች (Mercenaries) በሚሊዮን ዶላር ሃብት ማፍሰሳቸውን አስመልክቶ እስከዛሬ ተጠያቂ የሆነ አካል ያለመገኘቱ።
•የጦርነት ውሎዎችንም ብንዳስስ በቡሬ ግንባር እነ ተጋዳላይ ሃመዴን የመሳሰሉትን ተራ ካድሬዎች በአየር ኃይሉ ዕዝ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ በማድረግ የአቬዬሽን ስርዓትና ህግ በጣሰ መልኩ እንደነ በልሁ ዋሲሁን የመሳሰሉትን የህዝብ ሃብት ለአላስፈላጊ መስዋዕትነት ጭዳ ማድረጋቸውና ለዚህ የአቭዬሽን ህግ ጥሰት ተጠያቂ ሆኖ የቀረበ አካል ያለመታየቱ።
•በባድሜ ግንባር ደግሞ የወጣቱ የአበራ ገዳይ እየተባለ በሰፊው የሚታወቀው ተጋዳልይ በሪሁ እንዲሁ የአቬሽንን ህግ በመጣስ ሚ- 35 ተዋጊ አውሮፕላንን እበራለሁ በሚል ስሌት በሙያው እጅግ የሚበልጠውን በራሪ ቦታ በጉልበት ወስዶ ምንም ካልተፈጠረበት ሰላማዊ ሰማይ ላይ ወድቆ በመከስከስ በራሱና በሌሎች ባለሙያዎች ላይ አላስፈላጊ መስዋዕትነት መዳረጉ
•እነ ተጋዳላይ ዮሃንስ ዓይናለም በሌላ ሚ-35 ተዋጊ ሄሊኰፕተር እንደዚሁ ያለብቃት በፈቃዳቸው መብረር ሲሞክሩ የደረሰ አደጋ… ወዘተ
በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 5 ሚ-35 ተዋጊ ሄሊኰፕተሮችን ስናጣ በጥቅሉ ህውሃት አየር ኃይሉን ከተቆጣጠረ ጀምሮና እስከ ህውሃት ኤርትራ ግጭት ፍፃሜ ባሉት 8 ዓመታት ብቻ ….
•ከ10 በላይ ሚግ ተዋጊ አውሮፕላኖች
•ከ10 በላይ ተዋጊና ትራንስፖርት ሄሊኰፕተሮች
•8 ኤል-39 የተዋጊ መለማመጃ አውሮፕላኖች
•በተጨማሪም 1 አንቶኖቭ – 32 የጭነት አውሮፕላን ፣
•1 አልዌቲ – 3 የነፍስ አድን ሄሊኰፕተርና የመሳሰሉት በሙያ መዛባት ብቻ ኪሳራ ደርሷል። ………
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ከላይ የተዘረዘሩት ውድቀቶችና ምንጮቻቸው ፈጠው ወጥተው ሳለ አየር ኃይላችን ልዩ ነው… ከመቼውም በላይ ተጠናክሯል የሚሉ ቋንቋዎች መሰማታቸው እየተለመደ ሲመጣ በእጅጉ ያስተዛዝባል። በአየር ኃይሉ የደረሰውንም ሁለ ገብ ኪሳራ ለመሸፈንና የገፅታ ግንባታ ላይ ያተኰረ በመገናኛ ብዙሃን የታገዘ ሰፊ ዘመቻ እየሰማን አለን። በእውቅ አርቲስቶች የታጀበው የአየር ኃይል ጉብኝትና ፕሮፖጋንዳ ከመስመር ሁሉ ዘሎ በብቃትና በጥንካሬ እንደ ህውሃት ዘመኑ አየር ኃይል በኢትዮጵያችን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም እያሉ ከሙያው ጋር ዝምድና የሌላቸውን ታዋቂ ሰዎች ሲጠቀሙባቸው ማየትም ያስፀይፋል።
በእርግጥ እነዚህ አርቲስቶች ሃቁ ይጠፋቸዋል የሚል የዋህነት አይኖረንም። ቢያንስ ቢያንስ እንደ እነ ሙላቱ አስታጥቄን የመሳሰሉ አዛውንት የአገሪቱ ዜጐች እነ ጄኔራል ፋንታ በላይን በቅርበት አያውቋቸውም ብሎ ማሰብ ጅልነት እንጂ ሌላ ሊባል እንደማይችል እናስባለን። ሃቁ ግን ይህንን ሁሉ ኪሳራ መሸፈን የሚቻል አይደለም። እንኳን አርቲስቶች ቀርቶ በአቭዬሽን ሙያ አንቱ የተባሉ ምሁራንም ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ዕውነት በደረቅ ፕሮፖጋንዳ ለማዳከም መሞከር ህዝብን መናቅ ይባላል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ገሃድና አደባባይ መውጣቱ የማይቀር ነው። ለአሁን እዚህ ላይ እናብቃ ፤ ወደፊት ግን ዝርዝር ጉዳዩን እንመለስበታለን። በመጨረሻ እስኪ ባህር ኪነ ጥበብ ባለሞያ በሰሟኋት ስንኝ ልለያችሁ …..
ካቻምና በበቅሎ አምና በፈረስ
ዘንድሮ በአህያ ያውም በውርንጫ
አወይ የኛስ ነገር አዘቅዝቆ ሩጫ።
Average Rating