==================================
* የምህረት አዋጁ የመራዘሙ መረጃ
* ሪያድ ጅዳ ላይ ስላለው እውነታ …
* ጉድ ያደረገን አንጋፋው አየር መንገዳችን …
* “… ፈተናው ውስጥ ሳንገባ ነው የወድቀናል ! “
* ወደ ፈተናው ሳንገባ የመውደቃችን አበሳ !
* እያለፈ ካለው እንግልት ምን ተምረናል
ከ90 ቀኑ የምህረት አዋጅ በኋላ …የመራዘሙ መረጃ
==================================
90 ቀኑ የሳውዲ የምህረት አዋጅ ተጠናቋል ። ቀኑ ደርሶ “ይደረጋል” የተባለው የከበደ እርምጃ ቢያንስ እስካሁን የለም። የፍተሻ አሰሳው ስጋት ቀዝቀዝ ብሏል። በአንጻሩ “የምህረት አዋዱ ለወራት ይራዘማል ” የሚለው መላ ምት በተጨናነቀው የውጭ ዜጋ መካከል በሰፊው እየተሰራጨ ነው ። ማምሻውን ደግሞ መረጃውን ከየት እንዳገኙት ያልጠቀሱ የማህበራዊ መገናኛ ገጾች ” አስደሳችና መልካም ዜና ” እየተባለ መሰራጭት ጀምሯል ። መረጃው ” የሳውዲ ወገኖቻችን የምህረት አዋጅ ማራዘሚያ ተደርጎበታል !” ተብሎ የምስራች እየተጎሰመ አምሽቷል ። ይህን መረጃ በተደጋጋሚ እንዳስታወቅኩይ በግል የምጠብቀው ቢሆንም ከትክክለኛ ምንጭ ለማረጋገጥ አልቻልኩም ! የሚሆነው የሚጠበቀው ቢሆንም ትክክለኛነት እስኪረጋገጥ ትንፋሽን ዋጥ አድረጎ መጠበቅ የግድ ነው !
ሪያድ ስላለው እውነታ …
================
በሪያድ ሰነድ ይዘው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቲኬት የቆረጡ ተጓዦች እስካሁን ድረስ በእንግልት ላይ ናቸው ። አየር መንገዱ ባለፉት ቀናት ጉዟቸውን አስተጓጉሎ ሜዳ ላይ ጥሏቸው የነበሩትን ዜጎችን ወደ ሆቴል አስገብቷቸ ዋል። ጉዟቸውን ለማመቻቸትም ሙከራ እያደረገ ስለ መሆኑን መረጃ ደርሶኛል ።
ሪያድ ስላለው እውነታ …
================
ጅዳ ላይ በእንግልት ላይ ከሰነበቱት መካከል ማምሻውን ወደ 300 ተመላሾች ጉዞ አድርገዋል። በሂደቱ ከጊዜው መጠናቀቅ በፊት ቲኬት ይዘው የተስተጓጎሉትን መላክ ቢቻልም ጥቂት ተመላሾች አዋጁ ተጠናቋል ተብለው በፖስፒርት ፖሊሶች ስለመመለሳቸው የተረጋገጠ መረጃ አግኝቻለሁ። ስለዚህ አዳዲስ ቲኬት ቆራጮች የገዛችሁት ቲኬት እንዳይቃጠል መረጃውን ሳታጣሩ ቲኬት ባትቆርጡ የወዳጅ ምክር እለግሳችኋለሁ!
ጉድ ያደረገን አንጋፋው አየር መንገዳችን …
============================
በመጨረሻው የ90 ቀን ምህረት ሳምንታት በአንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገዳችን በኩል ቲኬት የቆረጡት በአየር መንገዱ ችግር በሽዎች የሚቆጠሩት ቲኬት ተሰረዘ ። ከአንጋፋው የማይጠበቅ መስተጓጎል በዜጎች ላይ ደርሶ ሰው አለቀሰ አዘነ …በደል ዝቅ ሲል በደንበኞች ከፍ ሲል በዜጎች ላይ ተፈጸመብን ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎቱን ፈልገው ገንዘብ የከፈሉትን ተመላሾች ለማስተናገድ አለመቻሉን ማየት አይደለም መስማት ያንገበግባል ። ይህ ብቻ አይደለም ፣ የራስን ዜጋ እያንገላቱ የሌላን ዜጋ ማስቀደምን ምን ይሉታል? ብለንም በሸቅን አገልግሎት ፈላጊ ዜጋን ከአለም አቀፍ የአቭየሽን ህግ በማይፈቅደው ደረጃ አውላላ ሜዳ ላይ መጣል በእርግጥ ም አየር መንገዳችን ያልተጠበቀ ግን ሳንወድ በግድ ያከናነበን የማይረሳ በደል ሆኖብናል። በአንጋፋው አየር መንገዳችን አፍረናል !!! አዘነናል
ወደ ፈተናው ሳንገባ የመውደቃችን አበሳ !
===========================
እሰከ 400 ሽህ ኢትዮጵያዊ ህገ ወጥ አለ ብለን ከርመናል ። ለመስተናግዶውም በመርህ ደረጃ ታጠቅን ብለን መባጀታችን እውነት ነው። ከዚህ ትልቅ ቁጥር ውስጥ የሰራተኛ ስምምነቱ ገፋኤ ሆኖ 83 ሽህ ሰው ወደ ሀገር ለመግባት ተመዝግቧል ። ከተመዘገቡት መካከልም 45 ሽህ አካባቢ የሀገራቸውን አፈር ረግጠዋል። ይህ ትልቅ ነገር ነው!
የኢንባሲና የቆንስላ ተወካዮች ፣ ተመላሾችን ለመደገፍ የተደራጀው ኮማንድ ፖስት ትልቅ ስራ ሊሰራ ተልሞ ለጥቂቶች ሳይሆን ቀረና አዘንን በእርግጥም በመንግስት ደረጃ ተደራጅቶ እና ብዙ አቅዶ በጣም ትንሽ ተመላሾችን ለማስተናገድ ፣ ብሎም በችግራቸው ወቅት አለመድረስና ለመደገፍ ሳይችሉ ቀርቶ መሽመድመድ ለሰሚው ግራ ያጋባል ። ወደ ውስጥ ዘልቆ ጆሮውን ጣል ላደረገ በጅዳ ብቻ ከ18 አባላት ያላነሱ የኮማንድ ፖስት አባላት ተደራጅተው በስራ ላይ የተገኙት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ የመሆናቸው ያልነገሩን እውነት ብዙ ተመላሽ ቢመዘገብ ኑሮ ሊደርስ የሚችለውን ቀውስ ላሰበው ” ሁሉም ለበጎ ነው! ” ብለን በመቆዘም አሁን በደረሰው የዜጎች መስተጓጎልና መንገላታት እጽናናለሁ ፣ አንጽናናለን !
ይህ ክፍተት እያለ ሳይስተካከል ጊዜ ባክኗል ። እየሆነ ባለው የዜጎች እንግልትና የባለድርሻ አካላት መካከል በታየው የአሰራር ክፍተት የተገረሙት የሪያድ ኮሚኒቲ ሊቀ መንበር አቶ ሻዎል ጌታሁን ለጀርመን ራዲዮ በሰጡት አስተያየት ወጌን ልቋጭ ፣
አቶ ሻዎል የሆነውንና ከላይ እኔ በግርድፍ የጠቃቀስኩትን በቅርብ ያውቁታልና እውነቱን ቦርቀቅ አድርገው በአጭር አማርኛ ገልጸውታል ። እንዲህ ነበር ያሉት
” መጀመሪያ ላይ እኛ የነበረን ስጋት የምህረት አዋጁ ተጠናቆ ቀኑ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ እኛ ያልመጡ ሰዎች በምን መልኩ የዚህ አገር መንግስት ትሪት ያደርጋቸዋል ? ምን ችግርስ ይከሰታል ? የሚል ስጋት ነው የነበረን ። አሁን ግን ያ ቀን ሳይመጣ ፣ የጉዞ ሰነዳቸውን ወስደው ወደ ሀገር ለመሄድ የተዘጋጁ ሰዎች እነሱን ማንሳት አልተቻለም ። እንደ እኔ አስተሳሰብ ፣ ፈተና ውስጥ ሳንገባ ነው የወደቅነው ! ” ግሩም ምስክርነት ነው !
አሁንም ወደ ሀገር ከመመለስ የሸሸና ፣ ወደ ሀገር ለመግባት የሚፈልግ በመቶ ሽዎች የሚቆጠር ዜጋ በሳውዲ ምድር ከጫፍ እስከ ጫፍ ፈሷል ። እናም ምናልባት የምህረት አዋጁ ቢራዘምም ሆነ ባይራዘም ለዜጎች ድጋፍ ለመስጠት ምን ለመስራት ተዘጋጅተናል ? የሚለውን ለማጠየቅ እወዳለሁ ። አባቶች ” ሰርገኛ መጣ ፣ በርበሬ ቀንጥሱ ” እንድሚሉት እንዳይሆን የከበደ ፈተና ይጠብቀናና መዘጋጀቱ ግድ ይለናል ። የእኔ ጥቃቄና የወጌ ማጠንጠኛ የሚሆነው ከላይ ከዳሰስነው ተምረን ለቀጣዩስ ድጋፍ ምን ታስቧል ? እላለሁ ! አንጋፋው አየር መንገድ ያስከፋ ያሰሰዘነውን ዜጋ ለመካስ ምን ያህል መዘጋጀት አለበት ብዬም አጠይቃለሁ! የሚሰማ ተገኘም አልተገኘ የዜጎች ጉዳይ የሚያገባን እየተገፋንም እንናገራለን !
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓም
Average Rating