ይልቅ ወሬ ልንገርህ በፕሬዚዳንት ሙላቱ እውቅና ስለሚሰጣቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን መቼም የሀገራችን የግል ፕሬስ ታሪክ ሩብ ምዕተ ዓመት ማስቆጠሩን ታውቃለህ አይደል? እንዴት አልክ? የኢትዮጵያ ሚዲያ ዘርፍ ከመንግሥት ሙሉ ይዞታና ባለቤትነት ወጥቶ በዜጎችም ተሳትፎ ጭምር መካሄድ ከጀመረ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኃሳብን በነፃ የመግለፅና የነፃ ሚዲያ ሥርዓት ከፍተኛ ማነቆ የሆነው የቅድሚያ ምርመራ አዋጅ በሕግ ከተሻረ 26 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በሚዲያው ዘርፍ ላይ በጉልህ የሚታዩት የግል ሕትመቶችና የብዙሃን መገናኛ ማሰራጫዎች (ሬዲዮና ቴሌቪዥን) የዚህ ታሪካዊ ውሳኔ ውጤቶች መሆናቸው ልብ አልክ? በሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. የወጣው የሽግግር ቃል ኪዳን (Charter) የቅድሚያ ምርመራ ስርዓትን ማገድ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም በህጋዊም ሆነ አስተዳደራዊ መንገድ እንዳይተገበር ከልክሏል፡፡ ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ ሲፈረምና እርሱን የተካው ሕገመንግስት ሲፀድቅ በሙያቸው፣ በልምዳቸውና በዕውቀታቸው ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ኢትዮጵያውያን ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አልክ? ለምሳሌ አቶ ክፍሌ ወዳጆ የኃሳብ መግለፅን፣ የመናገርና የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመቃወም፣ የማምለክ ነፃነቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች የሚገባቸውን ሥፍራ አንዲያገኙ በፅኑ እንደተሟገቱ ይታወሳል፡፡ ሌላስ? በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ድንጋጌዎች በመመርኮዝና በመተማመን የሚዲያ ዘርፍን ባለፋት ሩብ ምዕተ አመታት ከተቀላቀሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አቶ አማረ አረጋዊ አብይ ቦታ አላቸው፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ በነበሩት ጥቂት አመታት በመንግስት ይዞታ ሥር የሚገኙትን የሚዲያ ተቋማት በመምራት በጊዜው የተመሰገኑ ለውጦችን አሳይተዋል፡፡ ከዚያም ወዲህ ባሉት አመታት የሚዲያና ኮሚውኒኬሽን ሴንተር ኃ. የተ. የግ. ማህበርን በማቋቋም የሪፖርት ጋዜጦችንና መፅሔቶችን በማሳተም ለሚዲያው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ እያበረከቱም ነው፡፡ እናስ? እናማ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሚዲያ ምክር ቤት ከቆመላቸው መሠረታዊ አላማዎች መካከል አንዱ ለሚዲያ መጎልበትና ዕድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በመለየት እና በመሸለም ማበረታታት ነው፡፡ ሌሎችም የእነርሱን አርአያ እንዲከተሉ ማስተዋወቅ ነው፡፡ እናስ? የኢትዮጵያ ፕሬስ ካውንስል ከዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማኅበር ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ለእነዚህን ሁለት ኢትዮጵያውያን የምስጋና እና የሽልማት ቀን አዘጋጅቷል፡፡ መቼ አልክ? የፊታችን ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አባባ ሒልተን ሆቴል ነው የሚካሄደው፡፡ በዝግጅቱ ላይ ማን ይታደማል አልክ? የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚጋበዙ ሲሆኑ በሚዲያ ዘርፍ ላይ ያገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ 100 ባለሙያዎች ይታደማሉ፡፡ ከተሸላሚዎቹ መሀል አቶ ክፍሌ ወዳጆ የሉም አይደል? አዎ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ግን ቤተሰቦቻቸው ተገኝተው ሽልማቱንና እውቅናውን ከፕሬዚዳንቱ እጅ ይ ቀበላሉ፡፡ አቶ አማረስ? አቶ አማረ አረጋዊ ባለፉት በ26 ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ ሚዲያ እድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦና አገልግሎት መወደስ ይቀርብላቸዋል፤ ሽልማትም ይበረከትላቸዋል፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ የእራት ግብዣና በአዲስ አኩስቲክ ባንድ የሙዚቃ ዝግጅት ይቀጥላል፡፡ በዝግጅቱ ላይ እንዴት መታደም ይቻላል አልክ? ከተጠሩት 100 ሰዎች መሀከል 99ኙ ካርዳቸውን ወስደዋል፤ አንዱስ? አንዱማ እኔ ነኝ… በል ቻዎ….
ይህንን ከላይ ያለውን ሃሳብ ከቁምነገር መጽሄት አዘጋጁ ታምራት የወሰድነው ቢሆንም የእርሱን ሃሳብ በመጋራት ሌሎች በቁም እስራት ያሉ ብዙሃን ጋዜጠኞችን እና በስደት አለም ህይወታቸውን ያደረጉት ትንታግ ጋዜጠኞችን ለዛሬው ሩብ ምእተ አመት ያደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ ትልቁን ድርሻ አለው ።
ከእነ አቶ ክፍሌ ሙላት ጀምሮ ፣እስክንድር ነጋ ፣ውብሸት ታዬ እነ ደሳለኝ ፣ሆነ ኤልያስ አለበለዝያም በእስር ቤት ውስጥ በመደብደብ ብዛትም የሞቱትም ይሁን በአሁን ሰአት በችግር ምክንያት ድምጻቸው ደብዛው የጠፋው ብዙሃኑ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ወስደዋል።
አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ከ፺፯ በፊት በነበረው የመገናኛ ብዙሃን እርምጃ ምንም አይነት ትኩረት አይሰጣቸውም ነበር ሆኖም ግን የምርጫ ፺፯ን አስመልክቶ ያቀርቡት የነበረው ሚዛናዊ ሪፖርት እና የሃገሪቱ መንግስት በህዝብ እና በሃገር ላይ የሰራውን ወንጀል ፍጥርጥር አድርገው ለአለም ማቅረባቸው ዛሬም ድረስ በነጻ ጋዜጠኞች መድረክ ላይ ጥቁር ጥላ እንዲያጠላበት ተደርጓል ።
በአሁን ሰአት ንጹሃንን ጋዜጠኞችን እድሜ ልክ እየፈረዱ እና እንደፈለጋቸው የፍርድ ሂደትን እያዛቡ ለዘመናት ተሻጋሪ ብለው ተላላኪዎቻቸውን ለመሸለም መብቃት እና ዘመን ተሻጋሪ ብለው ማላገጥ በህዝብ እና በንጹሃን ደም ላይ እንደመጨማለቅ ይቆጠራል ።
Average Rating