www.maledatimes.com ወርሃዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁነቶች አጭር ማጠቃለያ | ሰኔ 2009 ዓ.ም - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ወርሃዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁነቶች አጭር ማጠቃለያ | ሰኔ 2009 ዓ.ም

By   /   July 13, 2017  /   Comments Off on ወርሃዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁነቶች አጭር ማጠቃለያ | ሰኔ 2009 ዓ.ም

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 15 Second

 

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የተዘጋጀ
1. የመሬት መብት ተሟጋቹ ኦሞት አግዋ ቀሪ መከላከያ ምስክራቸውን ያሰሙት ባሳለፍነው ሰኔ ወር ነበር፡፡
የመሬትና አካባቢ ጥበቃ አክቲቪስት ኦሞት አግዋ ሰኔ 05/2009 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ቀሪ ሁለት የመከላከያ ምስክሮችን አስደምጠዋል፡፡ ምስክሮቹ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋመቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ እና አቶ ሳምሶን አባተ የተባሉ ምስክር ናቸው፡፡
ምስክሮቹ በዋናነት ኦሞት አግዋን የሚያቋቸው በ1996 ዓ.ም ጋምቤላ ክልል በተነሳ ግጭት በክልሉ መንግስት በተቋቋመ የሰላም ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ግጭቱን ለማብረድና ግጭቱን በመሸሽ የተሰደዱ ዜጎችን ለማስመለስ መልካም ስራ መስራታቸውንና ተከሳሹ “የጋምቤላ ሰለምና ልማት ጉባኤ” የሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅትም መስርተው ሲሰሩ እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀሪ ሦስት የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮችን ከዝዋይ እና ሸዋ ሮቢት የፌደራል እስር ቤቶች ሲቀርቡ ለመስማት በሚል ለሀምሌ 20/2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
2. የኦፌኮ አባላትና አመራሮች እነ ጉርሜሳ አያና ላይ ይሰጣል የተባለው ብይን አሁንም በቀጠሮ መጓተቱ ቀጥሏል
የሽብር ክስ በቀረበባቸው የኦፌኮ አመራሮችና አባላት እነ ጉርሜሳ አያኖ (በቀለ ገርባ) መዝገብ ላይ ሰኔ 9/2009 ዓ.ም ብይን ለማሰማት የመጨረሻ ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበር ቢሆንም ብይኑ ‹‹ተሰርቶ አላለቀም›› በሚል ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ለብይን በሚል ቀጠሮ እየተሰጠባቸው አራት ወራት ያህል ያስቆጠሩት እነ ጉርሜሳ አያኖ (22 ሰዎች)፣ ብይኑን ትሰማላችሁ ተብለው ለሰኔ 15/2009 ቀጠሮ ቢሰጣቸውም በዕለቱ ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ተከሳሾቹን ፍርድ ቤት ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ በዚህም ፍ/ቤቱ እንደገና ተከሳሾች ባልቀረቡበት ሁኔታ ለሐምሌ 06/2009 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
3. በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ባለመቅረባቸው ተከሳሾች በቀጠሮ እየተጉላሉ ነው
በአክቲቪስት ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ በሽብር የተከሰሱት ተከሳች ላይ አቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች ባለማቅረቡ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ተከሳሾች መጉላላት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰኔ 20/2009 ዓ.ም ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ችሎት ቀርበው የነበሩት ተከሳሾች ምስክር ሳይሰማባቸው እንደገና ምስክር ለመጠባበቅ ለሐምሌ 11/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች በተደጋጋሚ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ መሰጠቱን በመቃወም አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ በዚህም 5ኛ ተከሳሽ የሆነው በላይነህ አለምነህ “እኛ የታሰርነው እና ድርጊቱ ተፈፀመ የተባልነው ባህርዳርና ጎንደር ቢሆንም ምስክር እየተጠበቀ ያለው ግን ከአዲስ አበባ ነው፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል? በባለፈው ቀጠሮ ምስክር ረጅም ቀጠሮ እየተሰጠን ያለው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እስኪያሰለጥን ድረስ ነው ወይ ብለን አስተያየት ሰጥተን ነበር፡፡ ፍ/ቤት አቃቤህ ግን ማዘዝ ከቻለ ለምንድነው ሃይ የማይለው?” ሲል ተናግሯል፡፡
4. ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል
*የምስክሮች ማንነት ይገለጽ በሚለው መቃወሚያ ላይ ብቻ ብይኑ አልተሰራም፤ ጉዳዩ ለህገ-መንገስታዊ ትርጉም ለፌደሬሽን ም/ቤት ተልኳል ተብሏል፡፡
በፌደራል አቃቤ ህግ ሦስት የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው የኦፌኮ ፕሬዚደንት ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀረቡባቸው ክሶች ላይ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያዎች አብዛኞቹ ውድቅ ሲደረጉ አንዱ ብቻ ለህገ-መንግስታዊ ትርጉም ለፌደሬሽን ም/ቤት መላኩን ሰኔ 30/2009 ዓ.ም ጉዳዩን ለማየት የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አስታውቋል፡፡
ዶ/ር መረራ መቃወሚያቸው ውድቅ መደረጉን ከችሎቱ ከሰሙ በኋል፣ ‹‹የተከሰስሁት ፖለቲካዊ ክስ ነው፡፡ እኔ የተከሰስሁት ለኦሮሞ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በመከራከሬ ነው፡፡ ይህንን እናንተ ዳኞችም፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ያውቃል፡፡ እኔ የተከሰስሁት በሀገራችን ሀቀኛ ፌደራላዊ ስርዓትና ፍትህ እንዲሰፍን በመከራከሬ ነው›› ሲሉ አስተያየታቸውን አሰምተዋል፡፡
ችሎቱ የፌደሬሽን ም/ቤት የተላከለትን የትርጉም ስራ ሰርቶ መላኩን ለመጠባበቅ በሚል ለሐምሌ 25/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
5. ጋዜጠኞችና አርቲስቶች ሙዚቃና ግጥሞችን ዩ ቲ ዩብ ላይ ጭነዋል በሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል
ሁከትና አመጽ የሚያስነሱ ዜና፣ ግጥምና ሙዚቃ በማዘጋጀት ዩ ቲ ዩብ ላይ እንዲጫን አድርገዋል በሚል ሰባት ሰዎች የሽብር ክስ የቀረበባቸው ባሳለፍነው ሰኔ ወር ነበር፡፡
በፌደራል አቃቤ ህግ ክሱ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ኦሊያድ በቀለ፣ ኢፋ ገመቹ፣ ሞይቡሊ ምስጋኑ፣ ቀነኒ ታምሩ፣ ሃይሉ ነጮ፣ ሴና ሰለሞን እና ኤልያስ ክፍሉ ናቸው፡፡ አቃቤ ህግ ተከሳሾችን የጸረ-ሽብር አዋጁን አንቀጽ 4 መተላለፍ ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ሰኔ 23/2009 በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19 ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ ተነቦላቸዋል፡፡
6. ሁለት ጋዜጠኞች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ባሳለፍነው ሰኔ ወር ከእስር ተፈተዋል
የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እና የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ አዘጋጅና ባለቤት ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የተበየነባቸውን የእስር ቅጣት አጠናቀው ከእስር ተፈተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው አመጽ በማነሳሳት ጥፋተኛ ተብሎ የተበየነበትን የአንድ አመት ከስድስት ወር እስሩን ጨርሶ ከቃሊቲ እስር ቤት የተፈታው ሰኔ 16/2009 ዓ.ም ሲሆን፣ በስም ማጥፋት ክስ የአንድ አመት እስር ተበይኖበት የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ደግሞ በአመክሮ ከሸዋሮቢት እስር ቤት የተፈታው ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on July 13, 2017
  • By:
  • Last Modified: July 13, 2017 @ 12:14 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar