የ2008ቱን ሕዝባዊ ተቃውሞ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ኦነግ ትዕዛዝ በመቀበል፣ በሕጋዊ ፓርቲ (ኦፌኮ) አባልነት ሽፋን “የሽብርተኝነት ድርጊት” ፈፅማችኋል በሚል ክስ የተመሠረተባቸው 22 ፖለቲከኞች፣ ዛሬ – ሐምሌ 6፣ 2009 ልደታ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው 4ኛ ወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ብይን ተሰጥቷል። በዚሁ መሠረት 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብዲሳ፣ 9ኛ ተከሳሽ ፍራኦል ቶላ፣ 10ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ደረጄ፣ 13ኛ ተከዳሽ አሸብር ደሳለኝና 22ኛ ተከሳሽ ሔልካኖ ኮንጤራ የቀረበባቸውን ክስ “የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ማስረዳት ስላልቻሉ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ” ፍርድ ቤቱ ወስኗል። የተቀሩት ተከሳሾች ከ4ተኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ በስተቀር በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 7/1 መሠረት የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ተበይኗል። 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ 8ኛ፣ 11ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ቀድሞ የተመሠረተባቸው “የሽብርተኝነት ድርጊት መፈፀም” ወንጀል በዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ሊረጋገጥ ባለመቻሉ ነገር ግን ማስረጃዎቹ “በሽብር ድርጅት ውስጥ የአባልነት ተሳትፎ እንዳላቸው ያረጋገጠ በመሆኑ” ክሳቸው ወደ አንቀፅ 7/1 ዝቅ እንዲል ተደርጎ፣ እንዲከላከሉ ተወስኗል። 14ኛ፣ 15ኛ፣ 16ኛ፣ 17ኛ፣ 18ኛ፣ 19ኛ፣ 20ኛ እና 21ኛ ተከሳሾች ቀድሞ የተከፈተባቸውን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 7/1ን እንዲከላከሉ ተበይኗል።
የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የተመሠረተባቸው ክስ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 257/ሀ መሠረት “ግዙፍ ያልሆነ በንግግር አመፅ ማስናዳት” ወደሚል ዝቅ ተደርጎላቸው እንዲከላከሉ ተወስኗል። የአቶ በቀለ ጠበቃ ላነሱት የዋስትና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ “በጽሑፍ አቅርቡ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ የተመሠረተውን ክስ ጥቅል ይዘት የሚከተለው ሊንክ ውስጥ ይመልከቱ፣ – PDF
Average Rating