ሰበር ዜና / Shocking News by Getu Temesegen
#ETHIOPIA | Veteran journalist and author Negash Gebre-Mariam has died, aged 93.
(1917 – 2009)
• ሥርዓተ ቀብራቸው ነገ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2009ዓ.ም በጉርድ ሾላ ሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን በ 9፡00 ሰዓት ይፈጸማል
***
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት ታሪክ ከፋና ወጊዎቹ አንዱ ነበሩ፡፡ ከባህላዊው የጋዜጣ አዘገጃጀትና የገጽ ቅንብር እንደ ሥነ ጋዜጠኝነት ደርዝ ባለው አገባብ እነ አዲስ ዘመን ጋዜጣ መልክ እንዲይዙ በማድረግ ከሚጠቀሱት አንዱ ነበሩ፡፡
አቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም ጋዜጠኛ ብቻም አልነበሩም፤ ባሕር ማዶ ተሻግረው እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የቀሰሙትን ለጋዜጠኞች የሥራ ላይ ትምህርት በመስጠትም አትርፈውበታል፡፡
ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት በአሜሪካ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ በኢትዮጵያን ሔራልድና በአዲስ ዘመን ጋዜጦች በአዘጋጅነት በተከታታይ መሥራታቸው፣ በተለይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሳቸው መምጣት በፊት ለሁለት አሠርታት የቆየውን ልማዳዊ ቅርፅና አፃፃፍ እንዲለወጥ ማድረጋቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
የጋዜጣውን ገጽ ቅንብር (ሌይአውት) የዜናና መጣጥፍ አቀማመጥ፣ ርዕሶች ሁሉ ሳይቀሩ ከዘመናዊው አሠራር ጋር እንዳስተዋወቁ ይነገራቸዋል፡፡
የጋዜጣው አቋም የሚንፀባረቅበትና ‹‹ኤዲቶሪያል›› ተብሎ ለዘመናት የቆየው ቃል ‹‹አማርኛ የለውም እንዴ?›› በማለት ጠይቀው በወቅቱ የጋዜጣው ባልደረባና በቤተክሀነት ትምህርት ሊቅ የነበሩት አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ ‹‹ርእሰ አንቀጽ›› የሚለውን ስያሜ እንዲያመጡ በማደረጋቸው ይወሳሉ፡፡
አቶ ነጋሽ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ከለቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን መምሪያ ረዳት ሥራ አስኪያጅ፣ በመቀጠልም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከጋዜጠኝነት ሙያው በተጓዳኝም እንደ ወንድማቸው አሰፋ ገብረ ማርያም (እንደወጣች ቀረች ደራሲ) ደራሲ የነበሩት አቶ ነጋሽ፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933) ላይ ጭብጡን ያደረገ ‹‹የድል አጥቢያ አርበኞች›› የተሰኘ ተውኔትም አቅርበዋል፡፡ ዕውቅናና ዝና ያተረፉበት ሁለተኛ የተውኔት ሥራቸው ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩልም ስለሴተኛ አዳሪነት ምክንያትና መፍትሔ የተንፀባረቀበት ‹‹ሴተኛ አዳሪ›› ልቦለድ እናኑ አጎናፍር በሚል የብዕር ስም አሳትመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ለሚሌኒየሙ ባሳተመው አጀንዳ ላይ እንደተመለከተው አቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም፣ በ1917 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ በጨርጨር አውራጃ በሀብሮ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ መቻራ በምትባል አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡
በቄስ ትምህርተ ቤት የጀመሩት ትምህርት አስበ ተፈሪ ከተማ በመሄድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ቀጥለውበታል፡፡ ወደ አዲስ አበባ በመሻገርም በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትና በመምህራን ማሠልጠኛ ተከታትለዋል በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በአሜሪካ ኢንፎርሜሽን ሰርቪስ ተቀጣሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡
የሥራው አጋጣሚም በአሜሪካ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመት ጋዜጠኝነት እንዲማሩ አስችሏቸዋል፡፡ ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ጡረታ ከወጡ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትርፍ ጊዜ መምህርነት የጋዜጠኝነት ኮርስን ሰጥተዋል፡፡
ከመንግሥት ለውጥ በኋላ የፕሬስ ነፃነት መታወጁን ተከትሎ በመጣ የግሉ ሚዲያ ዘርፍ የአቶ ነጋሽ አስተዋጽኦ የሚጠቀሰው፣ የአዕምሮ ጋዜጣ አሳታሚ የነበረው ማህደር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባቋቋመው የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ዋነኛ አስተማሪ ነበሩ፡፡
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ነጋሽ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም በሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡
***
እባክዎን፣ ይህንን ዜና እረፍት ሼር በማድረግ ለአገርና ለሕዝብ አድርሱልን፡፡
Average Rating