(ዘ-ሐበሻ) ሕወሓት መራሹ መንግስት የጣለውን አግባብ ያልሆነ ግብር በመቃወም የተጀመረው የሥራ ማቆም አድማ በተለያዩ ቦታዎች እየተስፋፋ ነው:: በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሳሪስ እና ኮልፌ አካባቢ ንግድ ሱቆች መዘጋጋታቸው ታውቋል::
ሳሪስ ሙሉ በሙሉ ዝግ ስትሆን በኮልፌ አካባቢ ግን አንዳንድ ነጋዴዎች የመንግስትን ማስፈራሪያ ተቀብለው መክፈታቸው ተሰምቷል:: ለነዚህ ሱቃቸውን በመክፈት መንግስትን ለተባበሩት ነጋዴዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ እንደተላለፈላቸው ለማወቅ ተችሏል::
በደምቢዶሎ ከተማ ትንስፖርት ቆሞ ሱቆች ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት ቡራዩ ከተማም ዛሬ ጭር ብላ መዋሏን የአካባቢው የህቡዕ ታጋዮች በፎቶ ግራፍና ቭድዮ አስታከው ከላኩት መረጃ ሌረዳት ተችሏል::
ነጆ ከተማም እንዲሁ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ዘጋግተው ቤት ቁጭ ያለ ሲሆን የመንግስት ኃይሎች ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉባቸው እንደሆነ ከሥፍራው የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል::
በሌላ በኩል በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በሰነበተችው ነቀምቴ ከተማ መንግስት የባጃጅ ሹፌሮችን ስራ አስፈትቶ ሥብሰባ እንዲቀመጡ ማድረጉ ታውቋል::
በሕዝባዊ እምቢተኝነቱ የቀጠለችው ነቀምቴ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴዋ እጅጉን መዳከሙን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት የባጃጅ ሹፌሮችን በስብሰባ ላይ የማትገኙ ከሆነ ታርጋችሁን እቀማለሁ በሚል አስፈራርቶ እንደሰበሰባቸውና በታክስ ስም ፕሮፓጋንዳውን እያስተማራቸው መሆኑን ከስፍራው የተገኘው ዜና ይገልጻል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚጓጓዙ መኪኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ት ዕዛዝ ተላለፈ:: በሕቡዕ ጉዳዩን እያደራጁ የሚገኙት ወጣቶች (ቄሮዎች) ያሰራጩት ማስጠንቀቂያ እንደሚከተለው ቀርቧል::
“ማስጠንቀቂያ… ማስጠንቂያ… ዛሬ በሱልታ፣ በጫንጮ፣ በጎርፎ፣ በዱበር፣ በሙከ ጡሪ፣ በደብረ ፅጌ፣ በፊቼና በገርባ ጉራቸው ከተሞች ውስጥ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ለ3 ተከታታይ ቀናት የማቆም አድማ ይደረጋል። ሱቆች፣ሆቴሎችና የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች በሙሉ ተዘግተው ይውላሉ። በመሆኑም ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልልና ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ይቋረጣሉ። ይህን ህዝባዊ ጥሪ አልፎ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግ አካል ካለ ለሚወሰድበት እርምጃ ተጠያቂ ራሱ ይሆናል።”
ወጣቶች (ቄሮዎች) ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ
Average Rating