(በፍቃዱ ኃይሉ -ውይይት ቁ.13)
ኢትዮጵያን ለሥራ ጉዳይ የሚጎበኙ የውጭ ጋዜጠኞች ከባለሀብቶች ጋር ሲነጋገሩ ስለዴሞክራሲ የሚሰሙት ሁሌም ተመሳሳይ መልስ አለ፤ “ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ዝግጁ አይደለችም”።
ለባለሀብቱ ቀላል ቢመስልም እዚህ ዓይነቱ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ። ከነዚህ መሐል ምናልባትም ለአገሪቱ ዴሞክራሲ ሰጥቶ መሞከር አንዱ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ባለሀብቱ የሚያነሱትን ጥያቄ በትዝብት ከማለፍ በላይ ብዙ ጥያቄዎችን እያነሱ መፈተሽ ያስፈልጋል።
ባለሀብቱ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ብትሸጋገር የሚያሰጋቸው ነገር ይሆን? ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን ሲንጣት የነበረው ሕዝባዊ ቁጣ ምንጩ በባለሀብቱና ብዙኃኑ መሐከል ያለው የጥቅም ግጭት ይኖር ይሆን?
ዕውቆቹ የምጣኔ ሀብት ጠበብት፣ ዳሮን አቼሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰን እ.ኤ.አ. በ2005 ባሳተሙት “Economic Origins of Dictatorship and Democracy” የተሰኘ መጽሐፋቸው በፖለቲካ ልኂቃኑ እና ብዙኃኑ መካከል ዴሞክራሲን በተመለከተ የተለያዩ ፍላጎቶች እንደሚንፀባረቁ አሳይተዋል። በተለይ እንደኛ አገር በፖለቲካ ልኂቃኑ እና በባለሀብቱ መካከል መቀላቀል ሲኖር የጥቅም ግጭት ሊኖር እንደሚችል እና ብዙኃኑ ዴሞክራሲ ሲፈልግ፣ ልኂቁ ደግሞ እንደሚፈራ አመላክተዋል።
የመጽሐፉ ደራሲዎች “ዴሞክራሲ እንዴት ተፈጥሮ፣ እንዴት ይፀናል?” የሚለውን ነጥብ ለማስጨበጥ ያደረጉትን ምርምር ለመደገፍ የአራት አገራትን ተሞክሮ ሞዴል አድርገው ያቀርባሉ – እንግሊዝ፣ አርጀንቲና፣ ሲንጋፖርና ደቡብ አፍሪካ። በእንግሊዝ የሕዝብ ቁጣ ባንዣበበ ቁጥር፣ የፖለቲካ ልኂቃኑ ምኅዳሩን እያሰፉ እና ለሀብት ክፍፍል በር እየከፈቱ መምጣታቸውን ጥናቱ ያትታል። በአርጀንቲና (በተደጋጋሚ) በሕዝባዊ ቁጣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይጀመርና ወዲያው የፖለቲካ ልኂቃኑ መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ጅምሩን ያደናቅፉታል። በአርጀንቲና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የለም፤ ብዙውን ሀብት የፖለቲካ ልኂቃኑ ይዘውታል።
ሲንጋፖር የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ የሚባል ዓይነት ነው፣ በዚህም ምክንያት መጀመሪያውኑም የሕዝባዊ ቁጣ ስጋት የፖለቲካ ልኂቃኑ ላይ ተከስቶባቸው አያውቅም። የፖለቲካ ልኂቃኑም ቢሆኑ ሥልጣን ላይ ለመሰንበት ሕዝባቸውን አልጨቆኑም። በደቡብ አፍሪካ (አፓርታይድ ጊዜ) ሀብት በፖለቲካ ልኂቃኑ እጅ ተከማችቶ ከብዙኃኑ ጋር የሰፋ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር። ስለዚህ፣ የፖለቲካ ልኂቃኑ ሥልጣናቸውን (እንዲሁም ሀብታቸውን) ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጭቆናን መጠቀም ነበረባቸው።
እነዚህ የኢኮኖሚ ጠበብት የሚደርሱበት ድምዳሜ እንደሚያሳየው ‹ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሌለበት አገር ዴሞክራሲ ቢፈጠርም መፅናት እንደማይችል፤ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ካለ ግን ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ባይሆንም እንኳን የፖለቲካ ልኂቃኑ ሥልጣን ላይ ለመሰንበት ኃይል መጠቀም እንደማያስፈልጋቸው› ነው።
በተጨማሪም፣ ‹የፈለገውን ያህል ጭቆና ቢኖርም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሌለበት አገር ብዙኃን የማመፅ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑ› ጥናቱ ያስረዳል። ሌላኛው የጥናቱ ድምዳሜ የፖለቲካ ልኂቃን የሕዝባዊ ቁጣ አደጋ ሲያንዣብብባቸው እንደማስታገሻ ለሕዝቡ የሀብት ክፍፍል የሚያደርጉበትን የተስፋ ቃል ይለግሳሉ።
ባለሥልጣን እና ባለሀብት በኢትዮጵያ
……………………………….
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሥልጣን ማለት ባለሀብት ከማለት ዕኩል ነው። ብዙዎቹ ባለሥልጣኖች የመንግሥት ተቀጣሪዎች ቢሆኑም የንግድ ድርጅቶችም ባለቤቶች ናቸው። የመንግሥት ሥልጣን ያልያዙት ባለሀብቶችም ቢሆኑ ጉዳይ ለማስፈፀም የሚያስችል የቀረበ ግንኙነት ከባለሥልጣናቶቹ ጋር አላቸው። ለዚህም ይመስላል የገዢ ልኂቃኑ በሥልጣናቸው መባቻ ሰሞን ቃል የገቡትን ያክል ዴሞክራሲ አሁን መገንባት ያልቻሉት። የአገራችን የወቅቱ የፖለቲካ ልኂቃን በሥልጣናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በብዙኃኑ የተፈተኑት በምርጫ 1997 ነው። ከዚያ በኋላ የተከተሉት የፖለቲካ ስትራቴጂ (“ልማታዊ-መንግሥትነት” እወጃ) የሚያረጋግጠው የሀብት ክፍፍል ተስፋ ለብዙኃኑ እየሰጡ፣ የሕዝባዊ ቁጣን አደጋ በማስወገድ፣ የፖለቲካ እና የሀብት ልኂቃኑን ቁጣ ማስወገድ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የገዢው ፓርቲ ብያኔ መሠረት የኢትዮጵያ ችግር የሠላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ (እንደ ቅደም ተከተላቸው) ነው። ሦስተኛው ለሁለተኛው፣ ወይም ሁለተኛው ለአንደኛው ሲባል ሊጨፈለቁ ይችላሉ። ሦስቱ አብረው እንደሚገኙ ሳይሆን፣ በተራ በተራ እንደሚረጋገጡ ይደሰኮራል። ሠላም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መኖር አለበት የሚለው የኢሕአዴግ መደምደሚያ ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣን ለማብረድ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደውን በኃይል የማፈን ርምጃ ለማስተባበል (to justify) ውሏል። አንጻራዊ ሠላም ባለበት ጊዜ ደግሞ ዴሞክራሲ ለልማት በሚል እንዲደማ ይደረጋል።
በሌላ በኩል የዚሁ ብያኔ ባለቤት ኢሕአዴግ ለይስሙላ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ አይደለም፣ ግዴታ ነው” ይላል። ስለዚህ ‹ልማትና ዴሞክራሲን አብረን እያስኬድን ነው› የሚል ነቢብ እየደሰኮረ፣ በሌላ አጀንዳ ደግሞ መልሶ አንዳንዴ ‹አፍሪካ የራሷ ዓይነት ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል› የሚል ማደናገሪያ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹ለልማት ሲባል ዴሞክራሲ ይቆይ፤ የድኃ ሕዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ዳቦ ነው› በሚል ዴሞክራሲን ጥያቄ እንደቅንጦት እቃ ጥያቄ ቸል ይለዋል። የሁሉም ነገር ታዛቢዎች ‹አለ የሚባለው ልማትስ ቢሆን የታለ?› ብለው መጠየቃቸው አልቀረም።
እውን ልማትና ዴሞክራሲ ይጋጫሉ?
…………………………………..
ቻይናና ሕንድ፣ ሁለቱም፣ ልማታዊ አገረ-መንግሥት (developmental state) የሚል ማዕረግ አግኝተዋል። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ሕንድ ዴሞክራሲያዊ መሆኗ ላይ ነው። ዕውቁ ጋዜጠኛ ፋሪድ ዘካርያ “The Post-American World” ባሰኘው መጽሐፍ ሕንዶችን “በየዓመቱ በአማካይ 9 በመቶ የሚያድግ ኢኮኖሚ ይዘው በመሪዎቻቸው የማይደሰቱ ሕዝቦች ናቸው” ይላቸዋል። በየምርጫው መሪ ይቀያይራሉ። ቻይኖች ግን ለዚህ አልታደሉም። ነገር ግን እነሱ በኢኮኖሚ ግስጋሴው ተሳክቶላቸዋል።
ፋሪድን አንድ የሕንድ ባለሥልጣን እንዲህ ብለውታል፡- “በፖለቲካው ረገድ ሕዝባዊነትን የሚያስገኙ ብዙ ቂላቂል ተግባሮችን መፈፀም አለብን።… እነዚህ ነገሮች የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕቅዶቻችንን ያደናቅፋሉ። ነገር ግን ደግሞ ፖለቲከኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ድምፅ ያስፈልጋቸዋል።…” አርክቴክት ኖርማን ፎስተርየተባለ ሰውም ይህንኑ የሚያጠናክር የሚመስል ነገር ለፋሪድ ነግሮታል። “በሕንድ፣ የኸርትሮው 5ተኛ ተርሚናልን ለመገንባት፣ የአካባቢ ተስማሚነት ቅኝት (environmental review) ለማድረግ የወሰደበት ግዜ፣ በቻይና ቢሆን የቤጂንግ አየር ማረፊያን (የኸርትሮው 5ቱንም ተርሚናሎች ቢደመሩ የሚበልጠውን) ጨምሮ ለመፈፀም የሚበቃ ጊዜ ነው።” ቻይናዎች የዴሞክራሲ “ጣጣ” የለባቸውም፤ ኮሚኒስቶቹ ይህንን እንደመታደል ይቆጥሩታል።
የሁለቱን ልዩነት ፋሪድ ዘካሪያ ሲደመድም “ዴሞክራሲ ለረዥም ጊዜ ልማት የራሱ የሆነ ተመራጭነት ሊኖረው ይችላል፤” ይላል። ሆኖም አውቶክራሲያዊ (ሕዝባዊ ተጠያቂነት የሌለባቸው) መንግሥታት “ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማይቀናቀኑት አቅም ዐቅደው፣ በፍጥነት ማስፈፀም ይችልሉ፤” ይላል።
ግብፆች (እ.ኤ.አ. በ2011) ለአብዮት አደባባይ ሲወጡ አንድ ወጣት የተናገረውን በማስታወስ ንፅፅራችንን እንደምድም። “እኛ ቻይናውያን አደለንም፤ ልማት ያለዴሞክራሲ አንፈልግም። እኛ ሕንዳውያን አይደለንም፤ ዴሞክራሲ ያለልማት አንፈልግም።” ይህ የሚያመላክተን ለፖለቲካ ልኂቃን ከሁለት አንዱን መምረጥ ቀላል መሆኑን ነው፤ ለብዙኃን ግን ፈፅሞ አይቻልም። በዚህ መሠረት ዴሞክራሲም፣ ልማትም ተነጣጥለው መታየት የለባቸውም የሚሉ አክቲቪስቶች ‹ዴሞልማት› የሚል ጥምር ቃል ፈጥረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አሰፋ ፍሰሐ “Development with or without freedom?” በሚል ርዕስ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ (FSS) ያሳተመላቸው ጥናት ላይ ለኢትዮጵያ “ልማታዊ አገረ-መንግሥትነት” ተግባራዊ ትምህርት ሊሰጥ የሚችለው ከቻይና ይልቅ የሕንድ ተሞክሮ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹ሕንድ ብዙ ዘውግን (multiethnic) እና ብዙ ሃይማኖትን በተግባር ከተፈተሸ የፌደራል ሥርዓት ጋር አጣምራ የያዘች አገር በመሆኗ ለኢትዮጵያ ከቻይና የተሻለ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች። ሕንድ ዴሞክራሲና ልማት (ዴሞልማት) ተመጋግበው እንደሚኖሩ በኮንግረስ ፓርቲ የበላይነት ካስቻለች በኋላ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ተወልዶላታል።›
ዴሞልማትና የአንድ ፓርቲ የበላይነት
……………………………
የልማታዊ አገረ-መንግሥት ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱት ምሥራቃውያን ናቸው። በ20ኛው ክ/ዘመን መባቻ ኢትዮጵያውያን ልሒቃን (‹ጃፓናይዘርስ›) ሥልጣኔዋን ሊኮርጇት ይመኟት የነበረችው ጃፓን ቀዳማዊ እና ምናልባትም ልማታዊነትን ከዴሞክራሲያዊነት ጋር በተሳካ ሁኔታ በማጣመር ብቸኛዋ ናት። ሆኖም፣ ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ለአብዛኛው የ20ኛው ክ/ዘመን ጊዜ በጃፓን የበላይ (dominant) ነበር። ደቡብ ኮርያና ሜክሲኮ ወደ ዴሞክራሲ ከመሸጋገራቸው በፊት በአንድ ፓርቲ ፍፁማዊ እና አውቶክራሲያዊ የበላይነት ልማታዊ ኢኮኖሚን አራምደዋል። ቻይና እስካሁን ድረስ ከኮሙኒስት ፓርቲ በስተቀር በምድሯ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይንቀሳቀስ በሕግ አግዳለች፤ ሆኖም በልማቱ ስኬታማ ነች።
የአገራችን የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ልኂቃን ይህንን የምሥራቃውያን ሞዴል ወስደው ‹ለልማት ሲባል የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት የግድ ያስፈልገናል› ሲሉ እየሰበኩ ነው። ኢሕዴግአውያኑን ከጃፓን እና ከሕንድ የሚለያቸው የፖለቲካ የበላይነቱን እያገኙ ያሉት በሕዝባዊ ይሁንታ ሳይሆን በኃይል ወይም በማጭበርበር መሆኑ ላይ ነው። ይህ በራሱ ከልማታዊነት ጋር የሚጻረር ነው። ወይም መግቢያችን ላይ እንዳየነው የሕዝባዊ ቁጣን፣ በልማታዊነት ተስፋ ለማስወገድ እና ሥልጣናቸው ላይ ለመሰንበት እየሞከሩ ነው።
ኢትዮጵያ የተቀበለችው እና ልማትን እንደ ሰብኣዊ መብት የሚመለከተው የተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ (Declaration on the Right to Development) የልማትን ምንነት ሲበይነው፣ “የጠቅላላ ሕዝቡ እና ሁሉም ግለሰቦች ንቁ፣ ነጻ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ብሎም ተገቢ (Fair) የጥቅም ክፍፍልን መሠረት በማድረግ፣ ለቋሚ የደኅንነት (well being) መሻሻል ዓላማ የሚሠራ ጥቅል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ፖለቲካዊ ሒደት ነው”
ይለዋል። ከዚህ ብያኔ ውስጥ ቢያንስ ‹የሁሉም… ንቁ፣ ነጻ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ› የሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ፈፅሞ አይስተዋልም። ማይክል ቶዴሮ እና ስቴፈን ስሚዝ ባሳተሙት “Economic development (2012)” የተባለ መጽሐፍ ላይ በልማታዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የሕዝባዊ ተሳትፎን አስፈላጊነት “chief end of development” (‹የልማት መጨረሻ ግብ›) ሲሉ ገልጸውታል። የሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰሎሞን ንጉሤ ለልማት የሰብአዊ መብት አካታች አካሔድን ስለመከተል አስፈላጊነት በተነተኑበት (FSS ያሳተመላቸው) ጥናት ላይ ‹በኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን ሕዝብን በማሳተፍ የመቅረፅ ፖለቲካዊ ባሕል እንደሌለ ገልጸው፤ ‹በየቀበሌው እና በየወረዳው የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ውሳኔዎችንና ፕሮግራሞችን በግድ ለማስፈፀም ከላይ ወደታች
የሚወርዱበት (የሚጫኑበት) እንጂ አሳታፊነትን የሚያበረታቱበት አይደሉም› ይላሉ።
ለዚህ ርቀን ሳንጓዝ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ያገኘዋል የተባለው የሕገ መንግሥት አንቀፅ ተንተርሶ በቅርቡ የተረቀቀውን አዋጅ መጥቀስ ይቻላል። አዋጁ ምንም እንኳን ሕዝቡ ሳይማክር በፀደቀ ‹ማስተር ፕላን› የተነሳን ሕዝባዊ አመፅ ተከትሎ ቁጣ ለማብረድ የተረቀቀ ቢሆንም፣ ተመሳሳይ ስህተት ተሠርቷል። የከተማዋ ነዋሪ እና ሌሎችም አዋጁ ከመረቀቁ በፊት እንዲማከሩ የተሳትፎ ዕድል አልተሰጣቸውም። የተረቀቁ አዋጆች ያለምንም ችግር መፅደቃቸው ደግሞ የተለመደ ነገር ነው።
የፖለቲካ ልኂቃኑ ሕዝቡ በተሳትፎ ‹እፈልጋለሁ› ያለውን ሳይሆን፣ የገዢው ፓርቲ ‹ይበጅሃል› የሚሉትን ለመጫን እንዲመቻቸው የአንድ ፓርቲ የበላይነትን እንደብቸኛ አማራጭ ይወስዱታል። የአንድ ፓርቲ የበላይነት በይሁንታ መገኘት ስላልቻለ ደግሞ የፈጠሩት ይፋዊ ያልሆነ አሀዳዊ ፓርቲ ነው። ሆኖም ፓርቲው በአወዛጋቢ (contested) ሁኔታም ቢሆን አስመዘገብኳቸው የሚላቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ቁጥሮች አሉ። ቁጥሮቹን እንመናቸው ቢባል እንኳን ዕድገቱ ያፈራው የሀብት ክፍፍል ምን ይመስላል የሚለው በአግባቡ አልተመለሰም። ኢኮኖሚስቱ ሎሬት አማርትያ ሴን “የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻውን እንደመጨረሻ ውጤት ሊታይ አይገባውም፤ ልማት የምንመራውን ሕይወት ማሻሻል እና የነጻነታችንን ልክ ማስፋት ላይ ማተኮር አለበት” የሚሉት የኢኮኖሚ ዕድገት ልማትን እንደማያረጋግጥ ለማመልከት ነው። ልማትን በአጭሩ “የምርጫ ነጻነት” ነው ይሉታል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የኢሕአዴግ የበላይነት የሚሰበከው “ልማቱ እንዳይደናቀፍ” በሚል ሰበብ ነው። ልማቱ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ምክንያት እንደማይደናቀፍ ቢያንስ ሕንድ ማሳያ ትሆናለች። ይሁንና አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ተጋብዘው “ዴሞክራሲያዊ አለመሆን የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያደናቅፍ የሚያረጋግጥ ‹ኢምፔሪካል ሪሰርች› የለም” ማለታቸው ይታወሳል። ዴሞክራሲ አገሪቱ ውስጥ አለመኖሩ ልማቱን ያጓድለዋል መባሉ ለእርሳቸው ‹የመኝታ ሰዐት ተረት› (“bed time story”) ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ‹የመኝታ ሰዐት ተረት› ሊባል የሚገባው የአቶ መለስ የራሳቸው አባባል።
ለብዙኃን የኢኮኖሚ ዕድገትን ስለማያደናቅፍ ብቻ አውቶክራሲነት ከዴሞክራሲያዊነት የበለጠ የማይመረጥ ቢሆንም፣ የአቶ መለስ ድምዳሜም ስህተት እንዳለበት ማሳየትም ያስፈልጋል። እነ ማይክል ቶዴሮ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፋቸው ላይ ዴሞክራሲ ልማት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ‹ኢምፔሪካል› ጥናቶች የተለያየ ውጤት እንደሚያሳዩ ቢናገሩም፤ ከነዚህ ጥናቶች ውስጥ ሲሦዎቹ ብቻ ‹ዴሞክራሲ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ› መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።ሲሦዎቹ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው ሲሉ፣ ቀሪዎቹ ሲሦዎች ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የለውም ብለዋል። ይህም ማለት 2/3ኛ ያክሉ ጥናቶች ዴሞክራሲ መኖሩ ልማቱን ባይጠቅመውም እንደማይጎዳው የሚያረጋግጡ ናቸው ማለት ነው። በተቃራኒው ካየነው 2/3ኛው ድምፅ የአቶ መለስን ድምዳሜ የሚደግፍ ቢመስልም፣
የብዙኃኑ ምርጫ የሚሆንበት ምክንያት የለም።
“Why Africa is Poor” የሚል መጽሐፍ የጻፉት ግሬጅ ሚልስ የእነማይክል ቶዴሮን ሐሳብ የሚያጠናክር ነገር ጽፈዋል። “ዴሞክራሲ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትአስፈላጊ የሚሆነው ለሰብኣዊ መብት ሲባል ብቻ ‹ቢኖር ጥሩ የሆነ› ነገር ስለሆነ አይደለም። ከምሥራቅ እስያ ውጭ ባሉ ታዳጊ አገራት እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አገሮች ከአውቶክራሲዎች 50 በመቶ የፈጠነ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል።”
ኢትዮጵያ ልማታዊ አገረ-መንግሥት አላት?
………………………
ኢሕአዴግ አሁን-አሁን “ልማታዊ ዴሞክራሲ” እያለ የሚጠራው (የአብዮታዊ ዴሞክራሲ) ርዕዮተዓለሙ አማካኝነት ካፒታሊዝምን በኢትዮጵያ ካዋለደ በኋላ ‹እከስማለሁ፤ ሊበራል ወይም ሶሻል ዴሞክራት ሆኜ በሌላ ቅርፅ እመለሳለሁ› ይላል። (አቶ ስብሐት ነጋ ለቪኦኤ ተናግረውታል በሚል አሰፋ ፍስሐ ቀደም ብለን የጠቀስነው ጥናታቸው ላይ እንዳጣቀሱት!) እንመነው ቢባል እንኳ በፖለቲካ የበላይነት ዘመኑ የልማታዊ አገረ-መንግሥት ባሕሪ አዳብሯልን? አሰፋ ፍስሐ ልማታዊ አገረ-መንግሥት “ጠንካራ፣ የተረጋጋ እና ማዕከላዊ፣ እርስ በርሱ የሚግባባ ቢሮክራሲ” ሊኖረው ይገባል ይላሉ።
ጥንካሬን መለኪያው አንዱ የሲቪል ሰርቪሱ አቅም ሲሆን፣ የእኛው ከሙያ ብቃተኞች ይልቅ በፖለቲካ ታማኞች የተሞላ በመሆኑ ጠንካራ ሊባል አይችልም።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ‹ያሉትንም መያዝ ሆነ አዳዲስ ብቁ ሰዎችን ማፍራት አልቻለም›። “የተረጋጋ” (stable) የሚለውም ቢሆን በፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ሳቢያ የትጥቅ ትግልን መርጠው ያመፁ ኃይሎች በሁሉም አቅጣጫ አሉ። በምሥራቅ ኦ.ብ.ነ.ግ.፣ በሰሜን (ኤርትራ በኩል) ኦ.ነ.ግ.፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ዴ.ም.ሕ.ት.፣ አ.ዴ.ኃ.ን… በጥቅሉ ሁሉንም ክልሎች እንወክላለን የሚሉ የታጠቁ ኃይሎች በመኖራቸው ‹የተረጋጋች› የሚለው እንዲበዛባት ሆኗል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ማዕከላዊ (centralized) የሆነ አስተዳደር አትከተልም፤ ፌደራላዊት ናት። ፌደራሊዝም እና ልማታዊነት አብረው እንደማይሔዱ የኢትዮጵያን ምሳሌ
በማጣቀስ ፕሮፌሰር ክላፋምን ጨምሮ ብዙ ምሁራን ገልጸውታል። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ቢያንስ በተጻፈ ሕግ ደረጃ “ማዕከላዊ” አስተዳደር የሚሻውን የልማታዊ አገረ-መንግሥት ባሕሪም አያሟላም ማለት ነው።
አሰፋ ፍስሐ “ልማታዊ አገረ-መንግሥት የገዛ መቃብሩን ቆፋሪ ነው ይባላል” ሲሉ ጽፈዋል። ልማታዊ አገረ-መንግሥታት ልማት ሲመጣ ሕዝቡ ዴሞክራሲን እንዲጠይቅ መገፋፋቱ አይቀርም ማለታቸው ነው። ፋሪድ ዘካርያም የምዕራባውያንን ዓይነት የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ደርሳ የነሱን ያክል ዴሞክራሲ ላይ ያልደረሰች ብቸኛዋ አገር ሲንጋፖር ነች ይላል። የሲንጋፖርን የተለየችነት (exceptionality) መግቢያችን ላይ የጠቀስነው ጥናት በቅጡ አስረድቶታል። የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊነት በፖለቲካ ልኂቃኑ ላይ የጠነከረ ተቃውሞ አላስነሳባቸውም፤ እነርሱም ሥልጣን ላይ ለመክረም ጭቆናን አልተጠቀሙም። ‹ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ፖለቲካዊ መሻሻልን በግድ ያስከትላል› የሚለውን አባባል የሻረች የምትመስለው ቻይና እንኳን የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከ5,000-10,000 የአሜሪካ ዶላር ሲደርስ የዴሞክራሲ ጥያቄ ዓይኑን አፍጥጦ ይመጣባታል ባይ ነው ፋሪድ። ለዚህም ከወዲሁ ወጣት ፖለቲከኞቹን ወደ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር ልካ ‹ፖለቲካዊ ሪፎረም›
እያስተማረች ነው።
በተቃራኒው ደግሞ፣ Foreign policy የተባለ የበይነመበረብ መጽሔት ተንታኝ የሆኑት Bruce Bueno de Mesquita እና George W. Downs በቻይና እና ራሽያ ምሳሌ የሚመሩት የአሁኖቹ አውቶክራሲያዊ መንግሥታት የኢኮኖሚ ዕድገት በውጤቱ ዴሞክራሲ አምጥቶ እነርሱን ጠርጎ እንዳያስወጣቸው ኢኮኖሚስቶች “coordination goods” እያሉ የሚጠሩትን እንደመገናኛ ብዙኃን እና ሲቪል ማኅበረሰቦች (በእኛ አገር እስከቴሌኮም አገልግሎት ይዘልቃል) የማገድ ሥራ እንደሚሠሩ ተከራክረዋል። ተንታኞቹ ከ150 በላይ አገራት ላይ ለ30 ዓመታት ያክል በተደረገ ጥናት መሠረት “በአንድ አገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃንና ሲቪል ማኅበረሰባት መኖር የአውቶክራሲያዊ መንግሥት ዕድሜን ከ15 እስከ 20 በመቶ ይቀንሰዋል”፤ የአውቶክራቶቹ ሥራ በተገላቢጦሽ ማቀድ ነው።
የኢሕአዴግ ፍጻሜ (የዴሞልማት ጅማሬ)?
……………………………
የመጀመሪያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ (ዕትዕ) መባቻ ላይ ለ15 ዓመታት እንደሚቆይ እና ሦስት ደረጃ (phase) እንዳለው አልተነገረንም ነበር።
‹ተጋኗል› የሚል ትችት ከዓለም ባንክ ጀምሮ እስከ ተቃዋሚዎች ድረስ ሲቀርብ በአቶ መለስ የተሰጠው መልስ ‹ሳስበው ደከመኝ› ብለን አንቀመጥም የሚል ስላቅ ነበር። አሁን ግን ዕቅዱ የተጋነነ እንደነበሩ መንግሥት ብዙ ሀብት ከባከነ በኋላ አምኗል። የሚገርመው ተከታዮቹ ሁለት ዕትዕዎች ከአንደኛው ዕትዕ የጎላ ግብ የሌላቸው መሆኑ ነው። ምናልባትም ዕትዕ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚሻ ዕቅድ በመሆኑ እስከ 2017 ድረስ የኢሕአዴግ ፍፁማዊ የበላይነት እንደሚዘልቅ በገደምዳሜ እየተነገረን ይሆናል። ምናልባትም ደግሞ አቶ ስብሐት ነጋ እንዳሉት ፓርቲው ካፒታሊዝምን አዋልዶ የሚያከስምበትን ዓመት እየነገሩን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን (ከነሙሉ ክብሩ) የምናገኘው በኢሕአዴግ ፍፃሜ እንደሆነ ኢሕአዴግ (በዚህ ንግግሩ) ይገምታል።
ልማታዊ አገረ-መንግሥት በኢትዮጵያ ቢኖር የማይጠላበት ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንድ፡- በእስያ እና በላቲን አሜሪካ እንደታየው ስር ነቀል የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እና ድኅነትን ለማሸነፍ ሁነኛው መንገድ መሆኑ በመረጋገጡ፤ ሁለት፡- የዘውግ ብሔርተኝነት መክረር የመበታተን አደጋ ያጠላባትን ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትስስሮሽ ሊፈጥርላት የሚችል በመሆኑ። በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ግን ፈታኞቹ ጥያቄዎች፤ ‹እውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ልማታዊ ነው? የመሆን አቅሙ እና ፍላጎቱስ አለው? ዴሞክራሲን ሳይጨፈልቅ ተፈላጊው ግብ ላይ ያደርሰናል?› የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው።
በኢትዮጵያ ግን የፖለቲካዊ ልኂቃኑ እና የባለሀብቱ አስተያየት የተለየ ነው – ‹አገሪቱ ለዴሞክራሲ ዝግጁ አይደለችም› ብለው ያስባሉ። ለዚህም የልማታዊ መንግሥት ፅንሰ ሐሳብ በመደስኮር፣ በነሱ አነጋገር ‹ኢትዮጵያን ለዴሞክራሲ ለማዘጋጀት› የወሰዱት አውቶክራሲያዊ አካሔድ ላይ ሕዝቡ ቁጣውን ገልጧል። ይህም ባለሀብቱ እና ባለሥልጣናቱ ሕዝቡን አሳንሰው በማየት ለዴሞክራሲ እንዳልተዘጋጀ የሚናገሩት ፍሬቢስ መሆኑን ያረጋገጠ ነው። አሁን ያለው ሁኔታ በፖለቲካ ልኂቃኑ (ወይም ባለሥልጣናቱ) እና ብዙኃኑ መካከል የጥቅም ግጭት መቀስቀሱን የሚያስረዳ ነው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀጥ ያለ የሚመስለውም ሕዝባዊ ቁጣ የጥቅም ግጭቱ እስካልተቀረፈ ድረስ ቆይቶ ማገርሸቱ አይቀሬ ነው። መጪው ምርጫ ከዴሞክራሲ እና ከሕዝባዊ ቁጣ አንዱን የመምረጥ ይመስላል።
Average Rating