ብዙውን ግዜ “ሙስና” ሲባል ፖለቲካዊ ችግር እንደሆነና በመንግስት ባለስልጣናት ብቻ እንደሚፈፀም እናስባለን። በእርግጥ የመንግስት አሰራርና አመራር ለሙስና መስፋፋት አስተዋፅዖ አለው፡፡ ይህን በተመለከተ “ኢህአዴግ እና ሙስና ስጋና ነፍስ ናቸው” የሚለውን ፅሁፍመመልከት ይቻላል። ነገር ግን፣ ሙስና ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም። ከዚያ በተጨማሪ ሙስና የከፋ ማህበራዊ ችግር መገለጫ ነው። በመሰረቱ የሙስና ወንጀል የሚስፋፋው እንደ ሕዝብና ሀገር ያሉንን ማህበራዊ ሃብቶች (social capital) ስናጣ ወይም ማህበራዊ ኪሳራ (social deficit) እንዳለ በግልፅ ይጠቁማል። በዚህ ፅሁፍ በዓለም-ገና የሚገኘውንና በተለምዶ “ሰርቆ-ማሳያ” የሚባለውን ሕንፃ እንደ ማሳያ በመውስድ ሃሳቡን በዝርዝር እንመለከታለን።
ከሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የሙስና ችግር ከሚስተዋልባቸው አከባቢዎች አንዱ በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነው። በተለይ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ የሆነ መሬት ወረራና ሙስና እንደነበር ይታወቃል። ከፍተኛ የሆነ የሙስና ችግር ከታየባቸው ከተሞች ውስጥ የዓለምገና ከተማ አንዷ ናት። ለዚህ ፅሁፍ በማሳያነት የወሰድነው የሰርቆ-ማሣያ ሕንፃም የሚገኘው በዚህች ከተማ ነው። በእርግጥ “ሰርቆ-ማሣያ” የሚለው የሕንፃው ትክክለኛ መጠሪያ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የዓለምገና ነዋሪዎች ሕንፃው “የሙስና ቅርስ” መሆኑን ለመጠቆም በተለምዶ የሰጡት ስያሜ ነው።
እኔ የሕንፃውን ባለቤት በግል አላውቃቸውም። ስለ ሕንፃው ያወቅኩት ራሱ ከአዲስ አበባ ወደ ወሊሶ እየሄድኩ ሳለ ከጎኔ የነበረ አንድ ተሳፋሪ “ይህ ህንፃ ሰርቆ-ማሣያ ይባላል” ብሎ ካሳየኝ በኋላ ነው። ስለዚህ ግለሰቡን በሙስና ወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ ተጨባጭ መረጃ የለኝም። ነገር ግን፣ የዓለምገና ነዋሪዎች ስለ ግለሰቡና ስለተጠቀሰው ሕንፃ ምን ይላሉ? ይህን ለማወቅ ዛሬ ጠዋት በፌስቡክ ገፄ ላይ ስለ ሕንፃውና ግለሰቡ መረጃ ያላቸው ሰዎች እንዲጠባበሩኝ ጠያቄ ነበር።
በዚህ መሰረት ብዙ ሰዎች የተለያዩ መረጃዎችን በፌስቡክና በስልክ አድርሰውኛል። ከደረሱኝ መረጃዎች ውስጥ “የሕንፃው ባለቤት አቶ መርጋ ይባላሉ፣ በመጀመሪያ በቱሉ-ቦሎ ማዘጋጃ መዝገብ ቤት ውስጥ ይሰሩ ነበር፣ ቀጥሎ ደግሞ በዓለምገና ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሬት አስተዳደር ክፍል ሰርተዋል፣ በአንድ ወቅት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ነበረ፣ እንዲሁም በዓለምገና ከሚገኘው የሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ በተጨማሪ ፉሪ (Furii) በሚባል አከባቢ ሌላ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ አላቸው” የሚሉት ይጠቀሳሉ።
አሁንም ቢሆን ግለሰቡ የሙስና ወንጀል ሰርተዋል እያልኩ አይደለም። በእርግጥ ግለሰቡን በአካል አግኝቼ ብጠይቃቸው “በስርቆት ሳይሆን በራሴ ጥረት ያፈራሁት ሃብት ነው” እንደሚሉኝ አልጠራጠርም። ነገር ግን፣ በሙስና የተገኘ ሃብት ባይሆን ኖሮ የዓለምገና ነዋሪ ለሕንፃው “ሰርቆ-ማሳያ” ሣይሆን “ሰርቶ-ማሳያ” የሚል ስያሜ ያወጣለት ነበር። ግለሰቡ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል፥ አልፈፀሙም የሚለውን ለሚመለከተው አካል መተው ይሻላል። ነገር ግን፣ ግለሰቡ ሰርቶ ሆነ ሰርቆ በሕንፃው ስያሜ ላይ ብቻ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ “ሰርቆ.ማሳያ” የሚለው ሕንፃ በዓለምገና መሃል ከተማ መገኘቱ ምን ያሳያል? እና በማህብረሰቡ ስነ-ልቦና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመለከታለን።
በመጀመሪያ ደረጃ የሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ ባለቤት በራሳቸው ጥረት የተገነባ ቢሆንም እንኳን አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ በሙስና የተገኘ ሃብት እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል። በመሆኑም፣ “የሰርቆ-ማሳያ ህንፃ በከተማዋ መሃል መኖሩ ምን ያሳያል?” ለሚለው፦ አንደኛ፡- ለማህብረሰቡ የሞራል ሕግ መገዛት፣ የፀረ-ሙስና ግዴታን መወጣት፣ ሥነ-ምግባር ከጎደለው ተግባር መታቀብ፣ …ወዘተ የሚሉት ማህበራዊ እሴቶች ሙሉ በሙሉ መጣሳቸውን ያሳያል። ሁለተኛ፡- ሙስና በመንግስትና የንግድ ተቋማት ዘንድ የተለመደ ሥራና አሰራር እንደሆነ ያሳያል። ሦስተኛ፡- በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ቅጣትና እገዳ የሚጥሉ ማህበራዊ ደንቦች ትርጉም አልባ መሆናቸውን ያሳያል። በዚህ ምክንያት፣ ለሙስና ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴት፣ ልማድና ደንብ መፈጠሩን፣ ይህም ትልቅ ማህበራዊ ኪሳራ (social deficit) እንዳስከተለ በግልፅ ይጠቁማል። በአጠቃላይ፣ ሙስና የማህበራዊ ሕይወታችን አካል ሆኗል ማለት ይቻላል።
በመጨረሻም፣ ሙስና በገሃድ የሚስተዋል ችግር መሆኑ ምን ዓይነት ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል? ይህን ለመረዳት የአንድ ከተማ ማዘጋጃ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ወይም የመሬት አስተዳደር ኃላፊ ከልጁ ጋር በሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ በኩል ሲያልፍ የሚያደርጉትን ምናባዊ ቃለ-ምልልስ እንመልከት፡-
ልጅ፡- “አባዬ…ይሄ ሕንፃ ለምን “ሰርቆ ማሳያ” ተባለ?”
አባት፡- “ባለቤቱ በሙስና የሰራው ሕንፃ ስለሆነ ነው”
ልጅ፡- “የት መስሪያ ቤት ነበር የሚሰራው?”
አባት፡- “እኔ የምሰራበት ቢሮ ነበር የሚሰራው?”
ልጅ፡- “ታዲያ ስንት አመት ተፈረደበት?”
አባት፡- “ሦስት አመት ብቻ ታስሮ ተፈታ”
ከዛ ልጅ በአግራሞት በውስጡ እንዲህ ይላል “ምነው አንተም ሦስት አመት ታስረህ ሚሊዬነር ብትሆን?” አሃ… ሃቀኝነት ለአንተና ለቤተሰብህ ምን አተረፈ? ሃቀኛ ሰራተኛ ድህነት ሲሸምት፣ ሙሰኛ ሃብትና ንብረት እያፈራ፤ አንተ በቤት ኪራይ ስትኖር ሙሰኛ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ያከራያል፤ አንደ እኔ መምህር ከሆንክ ደግሞ፣ አንተ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጥህ ስትለምን እንደ አቶ መርጋ ያለው ደግሞ በሪል-ስቴት ቪላ ቤቶች እየሰራ በውድ ዋጋ ይሸጣል። የዓለምገና ልጆች ወደፊት መሆን የሚፈልጉት እንደ እኔ ዓይነት ደሃ የዩንቨርሲቲ መምህር ሳይሆን እንደ አቶ መርጋ ያለ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ነው።
በመንግስት ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ ቅጣትና ተጠያቂነት ከሌለ አብዛኛው ሰው ከመስራት ይልቅ መስረቅ ይመርጣል። እንደ ዓለምገና ባሉ ከተሞች ሙስና በአረዓያነት የሚያስጠቅስ ተግባር ሆኗል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ፣ የመሃምድ ሰልማን “ፒያሳ፡ መሃሙድ’ጋ ጠብቂኝ” በሚለውን መፅሃፍ፣ በተለይ የፒያሳን ማራኪ ገፅታና ትዝታዎች ያስታውሳል። በዚህም፣ የአዲስ አበባ ከተማን ማራኪ ገፅታና ትዝታዎች በአንባቢዎቹ አዕምሮ ውስጥ እንዲቀረፅ ያደርጋል። ነገር ግን፣ “ዓለምገና፡ ሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ’ጋ ጠብቂኝ” ሲባል ግን፤ መስረቅ የሃጢያት ሳይሆን የሃብት ምንጭ እንደሆነ፤ ሙስና በሕግ ሆነ በሥነ-ምግባር እንደማያስጠይቅ፤…ሙስኛ ቢታሰር ምን ይሆናል – እስር ቤት ሆኖ የዘረፈውን ሃብቱን ያስተዳድራል፣ ከእስር ሲፈታ ኢንቨስተር ይሆናል። በአጠቃላይ፣ በተለምዶ “ሰርቆ-ማሳያ” የሚለው ስያሜ “መስራት ምን ሊረባኝ – መስረቅ ይሻለኛል” የሚል ዓይነት አመለካከት በማህብረሰቡ ዘንድ እንደሰረፀ ያሳያል፡፡ ሙሰኝነት፥ ስርቆት እንደ መልካም ገፅታና ተግባር ስያሜ ሆኖ ሲያገለግል ከማየት የበለጠ ማሀ ኪሣራ ያለ አይመስለኝም፡፡
Average Rating