2. መረጃዎችን ከአካላዊ ጥፋት ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንችላለን?
የርዕስ ማውጫ
<p> ኮምፒውተራችንን ከጥቃት ለመጠበቅ በርካታ ዲጂታል መከላከያዎችን አዘጋጅተን ይሆናል፤ ነገር ግን አንድ ቀን በድንገት ኮምፒውተራችን ራሱ አለዚያም በውስጡ የያዘውን መረጃ ቅጂ (ኮፒ) የያዝነበት የመረጃ ቋት ሊጠፋ፣ ሊሰረቅ፣ ወይም ሊበላሽ ይችላል። ምክንያቱ አደጋ፣ አጋጣሚ ምናልባትም ሆን ተብሎ የተፈጸመ ተንኮል ሊሆን ይችላል። የኤሌክትሪክ ኅይል መጠን በከፍተኛ መጠን መለዋወጥ ወይም የምናጣጥመው ቡና ኮምፒውተራችን ላይ መደፋት የምንሳሳለትን መረጃ እስከወዲያኛው እንድናጣው ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የአደጋ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ አስቀድሞ መገምገም፣ ኮምፒውተር ለመጠቀም የሚመች ከባቢ መምረጥ እና በጽሑፍ የሰፈረ የደኅንነት ፖሊሲ (security policy) ይህን መሰሉ አደጋዎችን ለማስወገድ ይረዱናል።
አስረጅ አጋጣሚ
ትእግስት እና ዲባባ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ የሚሠራ ድርጅት ይመራሉ። ለዚህ ድርጅት አገልግሎት የሚሆኑ ኮምፒውተሮችን እና የቢሮ መረብ መሣሪያዎችን ለመግዛት ይፈልጋሉ። የሚገዙዋቸው ኮምፒውተሮችና ተያያዥ መሣሪያዎች በአገራቸው ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ደካማ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የመረጃ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያስችላቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ። ከዚህም በላይ መሣሪያዎቹ ከተለዋዋጭ የኤሌክትሪክ ኅይል ስርጭት፣ ከመብረቅ፣ ከስርቆት/መወረስ ከሚመጣ አደጋ የተጠበቀ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። የሚገዙዋቸው ኮምፒውተሮች እና በቢሮ የሚዘረጋው መረብ አካላዊ ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን የኮምፒውተር ቴክኒሺያን የሆነችውን ሔለንን ምክር ጠይቀዋል።
የምእራፉ ዋና ዋና ጭብጦች
- የኮምፒውተራችን እና በውስጡ ያጠራቀምነው መረጃ አካላዊ አደጋዎች (physical threats) የሚያጋጥሙት አደጋዎች
- ኮምፒውተራችንን ከእነዚህ አደጋዎች በተሻለ መንገድ መከላከል የምንችልባቸው ምርጥ ዘዴዎች
- ለኮምፒውተሮች እና ለግንኙነት መረብ መሣሪያዎች ምቹ የሆነ የሥራ ከባቢ (operating environment) እንዴት መፍጠር ይችላል?
- በቢሮዎች ውስጥ ለምንጠቀምባቸው ኮምፒውተሮች የደኅንነት እቅድ (security plan) ስናዘጋጅ ከግምት ልናስገባቸው የሚገቡ ጉዳዮች
አደጋን መመዘን
አንዳንድ ድርጅቶች (መሥሪያ ቤቶች) የሕንጻዎቻቸውን/ቢሮዎቻቸውን እና የመገልገያ መሣሪያዎቻቸውን አካላዊ ደኅንነት (physically secure) አስፈላጊነት ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። በዚህም ምክንያት ኮምፒውተሮቻቸውን እና የመረጃ መጠባበቂያ ቋቶችን (backup storage devices) ከስርቆት፣ ከጎጂ የአየር ሁኔታ እና ከሌሎችም አካላዊ አደጋዎች (physical threats) ለመከላከል ምን ምን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ግልጽ ፖሊሲ የላቸውም። እርግጥ ይህን መሰል ፖሊሲ የማዘጋጀት አስፈላጊነትን መረዳት ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህን ፖሊሲ ማዘጋጀትና መተግበር ቀላል ሥራ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ብዙ ድርጅቶች ለቢሮዎቻቸው ጥሩ የበር ቁልፍ ይገጥማሉ፤ አልፎም መስኮቶቻቸውንም ጭምር አጥብቀው ይቆልፋሉ። ነገር ግን ለኮምፒውተሮቻቸው የምሥጢር ቁልፍ ጥብቅነት እና የምሥጢር ቁልፉን የሚያውቁ ሰዎች ብዛትና ማንነት ወዘተ ተገቢ ትኩረት ካልሰጡ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መረጃዎች ለአደጋ መጋለጣቸው አይቀርም።
አስረጅ አጋጣሚ
ትእግስት፦ የደኅንነት ፖሊሲያችንን (security policy) በአጭሩ አዘጋጅተን ለሚመለከታቸው ሠራተኞቻችን እንድንሰጥ እፈልጋለሁ። በዚህ ፖሊሲ ውስጥ ማካተት ያለብን ነገሮች ምንድን ናቸው?
ሔለን፦ ለሁሉም አይነት አደጋዎች ለሁልጊዜም የሚሠራ አንድ ወጥ የመፍትሔ አማራጭ ማዘጋጀት በጣም አስቸጋሪ ነው። የጥሩ ፖሊሲዎች ዝርዝር እንደድርጅቶቹ ሁኔታ የተለያዩ ናቸው። አንድ መርሳት የሌለብሽን ነገር ግን ልነግርሽ እችላለሁ። ይህን ፖሊሲና ፕላን ስታዘጋጁ የቢሯችሁን የሥራ ከባቢ በጥንቃቄ አጥኑት፤ ክፍተቶቹ ምን እንደሆኑ ለመለየትም በጥንቃቄ መርምሩት፤ ከዚያ በመነሣትም መለወጥና መጠናከር ያለባቸውን ነገሮች መወሰን ትችላላችሁ።
የድርጅታችንን እና የግላችንን ተጋላጭነት መጠን እና ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ስንገመግም መረጃችን ለጉዳት ሊዳረግ የሚችልባቸውን በተለያየ ደረጃ የሚፈጠሩ ሁኔታዎች መመልከት አለብን።
- የግንኙነት መስመሮቻችን እና የአጠቃቀም ልምዳችን ምን ይመስላል? ለምሳሌ ደብዳቤዎች (የወረቀት)፣ ፋክሶች፣ የመስመር ስልኮች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች (ሞባይሎች)፣ ኢሜይል እና የስካይፕ የስካይፕ (glossary#Skype) መልእክቶች ማለታችን ነው።
- ጠቃሚ መረጃዎችን የምናጠራቅመው እንዴት ነው? የኮምፒውተር የመረጃ ቋቶች (hard drives)፣ ኢሜይል እና ዌብ ሰርቨር፣ የመረጃ ማህደር (USB memory sticks)፣ ሲዲዎች፣ ዲቪዲዎች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ የታተሙ ወረቀቶች እና በእጅ የተጻፉ ማስታወሻዎች ሁሉ እዚህ ውስጥ የሚያዩ ናቸው።
- መረጃዎችን የያዙት እነዚህ ቁሳቁስ የሚቀመጡት የት ነው? እነዚህ መረጃዎች ምናልባት ቢሯችን፣ አለዚያ በመኖሪያ ቤታችን፣ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን አሁን ደግሞ ብዙ መረጃዎችን ኢንተርኔት ላይ እናስቀምጣለን። እርግጥ ኢንተርኔት ላይ የሚቀመጡ መረጃዎች አካላዊ አድራሻ በቀላሉ ለመለየት የሚያስቸግር ነው።
ሆኖም እነዚህ ኢንተርኔት ላይ የተቀመጡ መረጃዎች በተለያዩ ደረጃዎች ለአደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም። ተንቀሳቃሽ የመረጃ ማህደራችንን (USB memory sticks) ማልዌር (malware) ለመከላከል ጸረ ቫይረስ ሶፍትዌሮች እንደምንተማመን ሁሉ መረጃዎቻችንን ከስርቆት፣ ከመጥፋትና ከመበላሸት ለመጠበቅ ዝርዝር የአካላዊ ደኅንነት እቅድ ማዘጋጀት ይኖርብናል። ከድረ ገጽ ውጭ መረጃ የማስቀመጥ ፖሊሲን ጨምሮ አንዳንድ የደኅንነት መጠበቂያ ዘዴዎች ከዲጂታልም ይሁን ከአካላዊ አደጋዎች ለማምለጥ የሚጠቅሙ ቢሆኑም ሌሎቹ የበለጠ ዝርዝር የአጠቃቀም ሂደት ያላቸው ይገኛሉ።
በጉዞ ላይ ያለ ሰው ተንቀሳቃሽ የመረጃ ማህደሩን (USB memory stick) በኪሱ ውስጥ አለዚያም በላስቲክ ጠቅልሎ በሻንጣው ስር ሲሸጉጥ የመረጃውን አካላዊ ደኅንነት የተመለከተ ውሳኔ እየሰጠ ነው። መረጃው የሚገኘው በዲጂታል ቅርጽ ቢሆንም ውሳኔው እጅግ አስፈላጊ የሆነውን አካላዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ የተደረገ ነው። ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛው ምርጫ እንደየሁኔታው ይለያያል። ሰውየው የሚንቀሳቀሰው በሚኖርበት ከተማ ውስጥ ነው ወይስ ድንበር ተሻግሮ ሊሄድ ነው? ቦርሳውን የሚይዘው ባለቤቱ ራሱ ነው ወይስ ሌላ ሰው? በጉዞው ላይ ዝናብ ይኖራል አይኖርም? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች የመረጃችንን አካላዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
መረጃዎችን ከአካላዊ ደፋሪዎች መከላከል
ጠቃሚና ስሱ የሆኑ መረጃዎቻችንን ከፈቃዳችን ውጭ ለማግኘት የሚሞክሩ ግለሰቦችን አንድ የአካላዊ አደጋዎች ክፍል አድርገን እንመለከታቸዋልን። ይህን አደጋ በመረጃችን ላይ ብቻ የተጋረጠ አድርጎ መመልከት ችግሩን አሳንሶ ማየት ነው። እንደሌለ መቁጠርም አርቆ አሳቢነት የጎደለው ምልከታ ይሆናል።
አካላዊ ጣልቃ ገብነቶችን ለመከላከል የሚረዱ ብዙ ዘዴዎች አሉ። በቀጣዩ ክፍል የቀረቡትን መሠረታዊ ዘዴዎችና ምክሮች በቢሮም ሆነ በቤት/በግል ልንጠቀምባቸው እንችላለን። በተናጠል እንዳለብን የአካላዊ ደኅንነት ስጋት ሁኔታም ተጨማሪ መከላከያዎችን ልንፈጥር እንችላልን።
በቢሮ አካባቢ
- አጎራባቾቻችንን እንወቅ! በአካባቢያችንን እና በአገራችን እንዳለው የደኅንነት ሁኔታ ከሁለት አንዱ ይገጥመናል፤ ባልደረቦቻችን የቢሯችንን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚረዱን የምንተማመንባቸው አጋሮቾቻችን ይሆናሉ አለዚያም የደኅንነት እቅዳችን እንደ አደጋ ምንጭ የሚመለከታቸው አካላት ይሆናሉ።
- ወደ ቢሯችን ሊያስገቡ የሚችሉ በሮች፣ መስኮቶችና ሌሎችም መሰል መተላለፊያዎችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል መመዘን
- የሚቻል ከሆነ የስለላ ካሜራ ወይም የእንቅስቃሴ መጠቆሚያ ደወል (motion-sensor alarm) መግጠም
- እንግዶች ወደቢሯችን ከመግባታቸው በፊት የሚጠብቁበት “የእንግዳ መቀበያ” አካባቢ እንዲኖር ለማድረግ መሞከር፤ የሚቻል ሲሆንም እንግዶች ሲኖሩን የምናነጋግርበት ከቢሯችን (ከመደበኛ የሥራ ቦታችን) የተለየ የመሰብሰቢያ ክፍል ቢኖረን እጅግ ይጠቅመናል።
በቢሮ ውስጥ
- የኔትወርክ መስመሮችን በተቻለ መጠን በቢሮ ውስጥ ብቻ እንዲዘረጉ ማድረግ
- የአካባቢ መረብ መሣሪያዎችን (network devices) ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በማይደርሱበት ክፍል ወይም ሳጥኖች ውስጥ ማስቀመጥ/መቆለፍ። (ለምሳሌ ሰርቨሮች (Server) ፣ ራውተሮች (Router) ፣ ማዞሪያዎች (switches) ፣ መገናኛዎች (hubs) እና ሞደሞች (modems) የመሳሰሉትን ማለት ነው።) ይህ ካልሆነ ግን መሣሪያዎቹን በአካል ማግኘት የሚችል ሰው መረጃችንን ለመስረቅ ወይም በቢሮ መረባችን ውስጥ ኮምፒውተሮችን ለማጥቃት የሚያስችለውን ማልዌር በነጻነት የመጫን (install) እድል ያገኛል።
- የምንጠቀመው በገመድ አልባ የግንኙነት መረብ ከሆነ የዋና ማስተላለፊያው/የመግቢያ ነጥባችን (access point) ደኅንነት የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፤ አለበለዚያ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ወደ መረባችን ሊገቡ ወይም የመረጃ ልውውጣችንን ትራፊክ ሊከታተሉ ይችላሉ። ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ገመድ አልባ መረብ የምንጠቀም ከሆነ በአካባቢያችን ላብቶፕ የሚጠቀም ማንኛውም ሰው በቀላሉ ወደ መረባችን ሊገባ የሚችል ተጠርጣሪ ይሆናል። የገመድ አልባ መረባችንን ትራፊክ ሳናውቀው የሚከታተል ማንኛውም ጣልቃ ገብ ግለሰብ የቢሯችንን በር ሰብሮ የኢንተርኔት መስመራችንን ከሚጠቀመው ሰባሪ ባላነሰ መረጃችንን ሊያገኝ ይችላል። የገመድ አልባ መረቦችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ልንከተላቸው የሚገቡት ደረጃዎች እንደምንጠቀምበት የዋና ማስተላለፊያ የመግቢያ ነጥባችን ፣ ሐርድዌር እና ሶፍትዌር ሊለያይ ቢችልም በአብዛኛው አስቸጋሪ አይደልም።
በሥራ ቦታ
- የኮምፒውተራችን የማንበቢያ ሰሌዳ (ስክሪን) አቀማመጥ ሌሎች የምናነበውን/የምንሠራውን ነገር እንዲያዩ የተመቸ መሆን የለበትም። ስለዚህም በተቻለ መጠን በቢሮ ውስጥ ኮምፒውተራችንን የምናስቀምጥበትን አቅጣጫ ስንመርጥ መስኮት፣ በር፣ የእንግዳ ማሪፊያ ወንበር እና የሌሎች ባልደረቦቻችን አቅጣጫ ከግምት ማስገባት ይኖርብናል።
- አብዛኞቹ የጠረጴዛ ኮምፒውተሮች መቆለፊያ አላቸው፤ የመክፈቻ ቁልፍ የሌለው ሰው ኮምፒውተሮቹን መክፈት አይችልም። ኮምፒውተራችን ይህ መቆለፊያ ካለው ወደሌላ ቦታ ስንሄድ ምንግዚም ዘግተን መሔድ እንችላለን፤ ይህም ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ውስጣዊ ሐርድዌሮችን እንዳያበላሹ ይከላከልልናል። አዲስ ኮምፒውተር ስንገዛ ይህን መቆለፊያ አብሮ መግዛትን ማስታወስ አይከፋም።
- ኮምፒውተራችንን ከነነፍሱ (በአካል) አንስተው ከሚወስዱ ሌቦች ለመጠበቅ ደግሞ የኮምፒውተር ማሰሪያ ገመድ ማሰሪያ ገመድ (security cable) እጅግ የተመረጠ ነው። ይህ ማሰሪያ በተለይ በቦርሳ ተደብቀው፣ በጉያ ተሸሽገው ሊወሰዱ የሚችሉትን ላፕቶፕ እና ለአነስተኛ የጠረጴዛ ኮምፒውተሮች ለመጠበቅ በጣም ጠቃሚ ነው።
ከአካላዊ ደኅንነት ጋራ የተዛመዱ ሶፍትዌሮች እና አሠራሮች (ሴቲንግ)
- ኮምፒውተራችን ጠፍቶ ሲበራ (ሲነሳ) ሶፍትዌሮችን ሥራ ለማስጀመር እና ፋይሎችን ለመክፈት የይለፍ ቃል (የምሥጢር ቁልፍ) የሚጠይቅ ማድረግ አለብን። ይህን ለማድረግ የዊንዶውስ ተጠቃሚዎች የሚከተለውን ደረጃ በቅደም ተከተል ሊፈጽሙት ይችላሉ። ስታርት ሜኑን መጫን፣ ኮንትሮል ፓናል (Control Panel) መምረጥ፣ ዩዘር አካውንት (User Accounts) ውስጥ ገብቶ፣ የራስን አካውንት መምረጥ፣ ክሪኤት ፓስወርድን (Create a Password) መርጦ የይለፍ ቃሉን መፍጠር። በቀላሉ የማይገመት አስተማማኝ የምሥጢር ቃል መፍጠር የግድ ነው። ስለምሥጢር ቃል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ምእራፍ 3 ፤ አስተማማኝ የይለፍ (የምሥጢር) ቃል መፍጠር እና መጠቀም መመልከት ይበጃል።
- በኮምፒውተራችን ባዮስ (BIOS) ውስጥ አካላዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚረዱን አሠራሮች (settings) ይገኛሉ። በመጀመሪያ ኮምፒውተራችን ከፍሎፒ፣ ሲዲ-ሮም ወይም ዲቪዲ (ድራይቭስ) መጠቀሚያ በቀጥታ እንዳይነሣ ማለትም ቡት (boot) እንዳያደርግ ማስተካከል አለብን። በሁለተኛ ደረጃ ባዮስ (BIOS) ውስጥ ጣልቃ ገቦች የኮምፒውተራችንን አሠራር እንዳይቀይሩ (ወደ በፊቱ እንዳይመልሱት) የሚከላከል የምሥጢር ቁልፍ መፍጠር ይኖርብናል።
- በምእራፍ 3 እንደተጠቀሰው የዊንዶውስ እና የባዮስ(BIOS) የምሥጢር ቁልፎችን የምንመዘግብበት/የምናጠራቅምበት ፋይል ካለን፣ የዚህ ፋይል ቅጂ በኮምፒውተራችን ላይ ብቻ ሳይሆን በሌላም አስተማማኝ ቦታ እንዲኖረን ማድረግ አለብን።
- ኮምፒውተራችንን ባለበት ትተን ወደ ሌላ ቦታ በምንንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ በምሥጢር የይለፍ ቃል ብቻ እንዲከፈት አድርጎ የመቆለፍን ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። የዊንዶውስ ተጠቃሚዎች በመተየቢያችን ላይ የሚገኘውን የዊንዶውስ ምልክት ያለበት ቁልፍ ከ “ኤል” (L) ጋራ በመጫን በቀጥታ ኮምፒውተሩን መቆለፍ እንችላለን። ይህ የሚሰራው ግን አስቀድመን ለራሳችን የተጠቃሚ መዝገብ (account) የይለፍ የምሥጢር ቃል/ቁልፍ ፈጥረን ከሆነ ብቻ ነው።
- ስሱና ከፍተኛ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን በኮምፒውተሮች እና በሌሎች የመረጃ ማከማቻ ቋቶች ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን ኢንክሪፕት ኢንክሪፕት (Encryption) ማድረግ ሌላው እርምጃ ነው። ነገሩን በበለጠ ለመረዳትና ዘዴውን በአግባቡ ለመጠቀም ምእራፍ 4፤ በኮምፒውተራችን ውስጥ የሚገኙ ስሱ መረጃዎችን እንዴት መጠበቅ ይቻላል? የሚለውን መመልከት ነው።
ዲባባ፦ ባዮስ ትንሽ ውስብስብ ይመስላል፤ ስሕተት እንዳልሰራም ፈርቻለሁ። አንድ ስሕተት ብፈጽም ኮምፒውተሬን መልሼ መክፈት እችላለሁ? ሔለን፦ በእርግጥ እስክትለምጂው አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል። በአጠቃላይ የኮምፒውተርሽን መጠባበቂያዎች አይነት የመለወጥ ሒደት ቀላል ነው። ነገር ግን የባዮስ ሰሌዳ/ስክሪን በመጠኑ የሚያስቸግር ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ሒደት ስሕተት ከፈጸምሽም ኮምፒውተርሽን ለተወሰነ ጊዜ መክፈት አትችዪ ይሆናል። ስለዚህ ይህን በራስሽ መፈጸም ካስፈራሽ የኮምፒውተር ልምድ ያለው ሰው እንዲረዳሽ መጠየቅ ይበጅሻል።
ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎች (PORTABLE DEVICES)
- ስሱ መረጃዎቸን የያዙ ላፕቶፕ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ሌሎች ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎቻችንን ፈጽሞ ከአጠገባችን መለየት የለብንም። በተለይም ራቅ ወዳለ ቦታ የምንጓዝ ወይም ሆቴል ውስጥ የምናርፍ ከሆነ ሁልጊዜም የላፕቶፕ ማሰሪያ ገመድ (security cable) ይዞ መጓዝ ጥሩ ሐሳብ ነው፤ ሆኖም ላፕቶፑን የምናያይዝበት ሌላ በቀላሉ የማይንቀሳቀስ ቁስ ማግኘት ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ተጓዦች የሚመገቡባቸው ጊዜዎች ለሌቦች የተመቹ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ለተለያየ ዓላማ ላፕቶፖችንን ለመስረቅ የሚሞክሩ ሰዎች በቸልታ የተተዉ መሣሪያዎችን ለማግኘት በመመገቢያ ሰዓታት የሆቴል ክፍሎችን ያስሳሉ።
- ላፕቶፕ ወይም በእጅ የሚያዙ ሌሎች መሰል መሣሪያዎች (ለምሳሌ Personal Digital Assistant (PDA)) ከያዝን በተቻለ መጠን ከሕዝብ እይታ ለመደበቅ መሞከር ጥሩ ሐሳብ ነው። ውድ ዋጋ የሚያወጣ፣ ውድ መረጃዎችን የያዘ መሣሪያ መያዛችንን ገላልጦ ማሳየት የማያስፈልግ ትኩረት ይስባል። እንዲያውም አካባቢው አስጊ በሚሆን ጊዜ ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎቻችንን ሕዝብ በተሰበሰበበት አለመጠቀም፣ ላፕቶፓችንንም ላፕቶፕ መያዛችንን በማያስታውቅ ቦርሳ መያዝ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
ለኮምፒውተር ሐርድዌሮች ጤናማ ከባቢ መፍጠር
እንደማንኛውም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ኮምፒውተሮች በጣም ስሱ ናቸው። ተለዋዋጭ የኀይል አቅርቦትን፣ ከፍተኛ ሙቀት/ቅዝቃዜን፣ እርጥበትን፣ አቧራን እና ሜካኒካል/አካላዊ መናወጥን በቀላሉ መለማመድና መቋቋም አይችሉም። ኮምፒውተሮቻችንን እና ሌሎች መሣሪያዎችን ከእነዚህ አደጋዎች ለመጠበቅ ልናደርጋቸው የሚቻለን ብዙ ነገሮች አሉ።
- የኤሌክትሪክ ኅይል መጠን መለዋወጥ፣ መቋረጥ እና መቃጠል የኮምፒውተራችንን አካሎች ሊጎዳ ይችላል። እንዲህ አይነት አለመረጋጋቶች የኮምፒውተሮች ሐርድዌር መስራት እንዲያቆም (‘crash’) ሊያደርጉ፣ በውስጡ የሚገኘውን መረጃ ሊያበላሹ/ሊያጠፉ፣ ወይም የኮምፒውተሩን ኤሌክትሮኒክ አካሎች ሊጎዱ ይችላሉ።
- የሚቻል ከሆነ በጣም ወሳኝ ሥራ ለሚያከናውኑ ኮምፒውተሮቻችን “የማይቋረጥ የኅይል አቅርቦት ማረጋገጫ” ዩፒኤስ (UPS)ብንገጥምላቸው ችግሩን ማስወገድ ይቻላል። ዩፒኤስ (UPS) የኤሌክትሪክ ኀይል መቋረጥ ሲያጋጥም ጊዜያዊ የኅይል ምንጭ ይሆናል።
- ዩፒኤስ (UPS) መግጠም የማያስፈልግ ወይም በጣም ውድ በሚሆንበት ወቅት የኀይል መጠን መቆጣጠሪያዎችን ወይም የኀይል ብዛት መከላከያዎችን (power filters or surge protectors) መጠቀም እንችላለን።
- በጣም አስፈላጊ መሣሪያዎችን ከማገናኘታችን በፊት የኤልክትሪክ መረባችንን መፈተሽ አስተዋይነት ነው። የሚቻል ከሆነ ሦስት ቀዳዳዎች ያሉትን ሶኬት መጠቀም ይመከራል፤ አንደኛው ቀዳዳ አደጋዎችን ለመከላከል የተሠራ (ግራውንድ ላይን) ስለሆነ። በተቻለ መጠን የምንጠቀምበት (ቢሮ/ቤት) የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተለያዩ መሣሪያዎችን (አምፖል/መብራቶች፣ ፋን፣…) ስንጠቀም ምን ለውጥ እንደሚያሳይ መከታተል ጠቃሚ ምልክት ሊሰጠን ይችላል። ይህንን ሙከራ ኮምፒውተሮችን ከመግጠማችን በፊት ብናደርግ ደግሞ አደጋ ላይ ከመውደቅ ይጠብቀናል።
- ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን መሣሪያዎች በቀላሉ ሊነካኩ በሚችሉበት በመተላለፊያ፣ በእንግዳ መቀበያ እና በመሳሰሉ ቦታዎች ማስቀመጥ የለብንም። ዩፒኤሶች፣ የኅይል መቆጣጠሪያዎች (power filters)፣ የከፍተኛ ኀይል መከላከያዎችን (surge protectors)፣ የኤሌክትሪክ ሶኬት ማርዘሚያ ገመዶች ባልታሰበ እንቅስቃሴ ተነክተው ሊጠፉና ሊነቀሉ በሚችሉበት ቦታና አቅጣጫ መቀመጥ የለባቸውም። በተለይም እነዚህ ገመዶች ከሰርቨር እና ከመረብ መሣሪያዎች ጋራ የተያያዙ ሲሆኑ የተለየ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል።
- በቂ ጥራት ያላቸውን የኮምፒውተር ገመዶች፣ የኀይል ማስተላለፊያ ገመዶችና ማገናኛዎችን መጠቀም፣ የሚቻል ሲሆን በበቂ ሁኔታ መግዛት እና መጨመር ይመከራል። በግድግዳ ሶኬት አካባቢ የሚገኙ ማገናኛዎች ብዙ ጊዜ ይላላሉ፣ በቀላሉ በመለያየትም የኀይል መቆራረጥ ያስከትላሉ። እንዲህ ያለው መቆራረጥ የኮምፒውተራችንን አካላዊ ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በዚህም የተሰላቹ ተጠቃሚዎች በፕላስተር በማጣበቅ ችግሩን ለማስወገድ በሚያደርጉት ሙከራ የተነሣ የእሳት አደጋ ሊቀሰቀስ ይችላል።
- ኮምፒውተራችንን በመሳቢያ ውስጥ የምንቆልፍ ከሆነ መሳቢያው በቂ የአየር ማስገቢያ እንዳለው ወይም ከፍተኛ ሙቀት እንደማይፈጠር መረጋገጥ ይኖርብናል።
- የኮምፒውተር መሣሪያዎች ከማሞቂያ/ማቀዝቀዣ ሞተሮች፣ ከሙቀት ማስወጫዎች፣ ከአየር ማቀዝቀዣዎች (air conditioners) እና ከሌሎችም ቱቦዎች (duct) ከሚተላለፉባቸው አካባቢዎች ርቀው መቀመጥ ይኖርባቸዋል።
ትእግስት፦ ከእነዚህ ችግሮች የተወሰኑትን ቀደም ከወር በፊት ፈተናቸዋል። ከኮምፒውተሮቻችን በቀላሉ የማይላቀቁ ገመዶችን/ኬብሎችን ማግኘት ረጅም ጊዜ ወስዶብናል።
ሔለን፦ የቢሮ ምንጣፉችንን በእሳት የሚያያይዙ የሚመስሉትን የኤሌክትሪክ ኅይል ማስተላለፊያ ገመዶች በአስተማማኞቹ መተካትስ ቀላል ነበር?
ትእግስት፦ እርሱም ቀላል አልነበረም። አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ገመዶችን የሚያቀርቡ ሱቆችን መፈለግ፣ የባለሞያ አስተያየት መጠየቅ ነበረብን። ዲባባ ይህን ለማሳካት ብዙ ደክሟል። የኤሌክትሪክ ኅይል አቅርቦቱ አሁንም ከፍተኛ መዋዠቅ የሚታይበት ቢሆንም መሣሪያዎቻችንን ስለተሟሉ በተሻለ ሁኔታ ሥራችንን ማከናወን ችለናል።
የአካላዊ ደኅንነት ፖሊሲ ማዘጋጀት
እንደሁኔታው በግለሰብ እና/ወይም በመሥሪያ ቤት ደረጃ ያሉብንን አደጋዎች እና ተጋላጭነቶች ከገመገምን በኋላ ምን ምን እርምጃዎችን በመውሰድ አካላዊ ደኅንነትን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ማሰብ ይኖርብናል። የምንወስደውን እያንዳንዱን ዝርዝር እርምጃ የሚያሳይ የደኅንነት ፖሊሲ (security policy) በጽሑፍ ማዘጋጀት ቀጣዩ ተግባራችን ነው። ይህ ሰነድ ለራሳችን፣ አብረናቸው ለምንሠራቸውም ሆነ ወደፊት ለሚቀላቀሉን ባልደረቦቻችን እንደ አጠቃላይ መመሪያ ያገለግለናል። ሰነዱ ከአካላዊ ደኅንነት ጋራ የተያያዙ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ምን አይነት እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለብን በዝርዝር ማመልከት ይኖርበታል። እያንዳንዱ ሰውም ይህን ሰነድ ማንበብ እና እያንዳንዱን መመሪያ መከተል ይኖርበታል። ሰነዱን በየጊዜው የበለጠ ለማዳበርም ውይይቶችን ማካሔድ ጠቃሚ ነው።
የአካላዊ የደኅንነት ፖሊሲ ሰነዳችን እንዳለንበት ሁኔታ የተለያዩ ክፍሎች ሊኖሩት ይችላሉ።
- የቢሮ መግቢያ/መውጫ ፖሊሲ፦ ምን አይነት መቆለፊያዎች እንጠቀማለን፣ የመክፈቻና መዝጊያ ቁልፍ የሚኖራቸው እነማን ናቸው? የቢሮው የአደጋ ጥሪ ደወል የሚሠራው እንዴት ነው? እንግዶች ወደ ቢሮ የሚገቡት በምን ሁኔታ ነው? የቢሮ ጽዳት የሚያከናውኑት ሰዎች እነማን ይሆናሉ ወዘተ.
- ለተፈቀደላቸው ጎብኚዎች ብቻ ክፍት የሚሆኑት ክፍሎች/አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
- የመሣሪያዎች ምዝገባ እና ቆጠራ፣ የመለያ ቁጥር እና የአካላዊ መግለጫ ምዝገባ
- ስሱ መረጃዎችን የያዙ ወረቀቶች እና ሌሎች መሣሪያዎች የሚወገዱት እንዴት ነው?
- የአደጋ ጊዜ እርምጃዎች
- ስሱ የሆነ ምሥጢራዊ መረጃ ድንገት ወጥቶ ወይም በሌሎች እጅ ገብቶ ቢገኝ ይህ ሊነገራቸው የሚገባቸው ሰዎች እነማን ናቸው?
- የእሳት፣ የጎርፍ እና የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ቢያጋጥሙ አስቀድመን የምናሳውቀው ለነማን ነው?
- አስቸኳይ ጥገናዎችን ሲያስፈልጉ እነዚህን የምናደርገው እንዴት ነው?
- የኤሌክትሪክ፣ የኢንተርኔት፣ የውሃ እና የመሳሰሉነትን አገልግሎቶች የሚያቀርቡ ድርጅቶችን ማግኘት ቢያስፈልገን የምናገኛቸው እንዴት ነው?
- ከድረ ገጽ ወይም ከኢንተርኔት ውጭ የተቀመጠ መረጃን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የመጠባበቂያ መረጃ አቀማመጥን በተመለከተ ምእራፍ 5 ፤ የጠፉ መረጃዎችን መልሶ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን መመልከት ይቻላል።
የደኅንነት ፖሊሲ በየጊዜው የሚከለስና የሚሻሻል መሆን አለበት። የደኅንነት ፖሊሲ እንደሌሎች አስፈላጊ መረጃዎቻችን ሁሉ በመጠባበቂያ ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል። የደኅንነት ፖሊሲ አዘገጃጀትን የበለጠ ለመረዳት የተጨማሪ ንባብ ክፍሉን ማንበብ ይጠቅማል።
Average Rating