(*በ2004 ዓ.ም ደራስያን ማኅበር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በብሔራዊ ቲያትር ያዘጋጁት መድረክ ላይ የቀረበ። ሳሙኤል ተመስገን)
ጓደኛዬ አቡዬ ስለ ጉቦ አውርቶ አይጠግብም “ያለጉቦ አይሞላም የኑሮ ገንቦ፤ያለጉቦ ሕይዎት ባዶ ናት…” ይላል።
የአቡዬ ነገር ይቆየኝና ስለ ጉቦ ጥቂት ልበል፦
የጉቦን ቃላዊ ፍቺ ጋሽ አስፋው ዳምጤ እስከነገሩኝ ቀን ድረስ ጉቦ “ጉቦ” የተባለው ስልጣን ላይ ጉብ ባሉ ሰዎች ስለሚፈፀም ይመስለኝ ነበር።
ዛሬ በሀገራችን የመገናኛ ብዙሐን ጉቦ ሳይሆን ሙስና እየተባለ ይጠራል።
ይህም ጉቦን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ አዘግይቶታል ብዬ አስባለሁ።
ለምን የሚል ባይኖርም ቅሉ ለምን እንደሆነ ግን መናገር ተገቢ ይመስለኛል።
ሙስና ለጆሮ እንግዳ ብዙም ያልተለመደ ከመሆኑም ሌላ ሀገሬው ሙስናን የሚያውቀው ኮሶ የሚያሽር ዛፍ እንደሆነ እንጂ ከስልጣን የሚያሽር ወንጀል እንደሆነ አይደለም።
እናም ጉቦን ለመከላከል ያስችል የነበረው ጊዜ ሙስናን በማስተዋወቅ ባከነ።
በነገራችን ላይ ሙስና ባይኖር ኑሮ ኢቲቪ እና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ምን ይሠሩ እንደነበር አላቅም።
ለነገሩ እነሱም እንዲናፈቅ እንጂ እንዲጠፋ አይደለም የሚተጉት፤
እውነቴን ነው! የሙስና ማስታወቂያዎች ተከታታይ ድራማ እንጂ የፀረ ሙስና ዘመቻ አይመስሉም።
የዚህችን ሀገር ችግር ለመፍታት እና የሕዝቡን ስነ ልቦና ለማጥናት መንገደኛ ምዕራባዊያን የጠረዙትን ሰነድ ከማገላበጥ ይልቅ ወንዛፈራሽ ሥነ ቃሎችን መፈተሽና መመርመር እጅግ የላቀ ፍንጭ ይሰጣል።
በፓርላማ ቁጭ ብሎ “የፀረ ሙስና ህጋችን ከእንግሊዝና ከአሜሪካ ተጨምቆ ነው የተዘጋጀው!” ብሎ ደረት ከመንፋት ይልቅ ሀገረሰቡ ስለ ጉቦ ያለውን እይታ በዕለት ከዕለት እንጉርጉሮው አጮልቆ ማየት በተገባ ነበር።
“የኃጢአት ክፉ ጉቦ፣
የበሽታ ክፉ ተስቦ!”
ለሚል ማህበረሰብ የእንግሊዝን ረቂቅ ህግ በኮንቴነር ጭኖ ማምጣት ምን ይሉታል?
“የአህያ ባል ከጅብ ጉቦ በላ” እንደሚባለው ካልሆነ በቀር።
ጉቦ በተለያዬ መንገድ ሊፈፀም ይችላል ለምሳሌ በሰላምታ በቁሳቁስ በጥሬ እና በጥሬ ሥጋ (በሩካቤ) ሊከወን ይችላል።
በግዕዝ ቋንቋ ሙስና ሁለት ትርጉም አለው አንደኛው ጥፋት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ደም-ግባት።
“የከንፈሯ ለዛ የጉንጯ ሙስና፣
አርብ ሮብ ያስታል እንኳን ሐሙስና!”
የሚለው የቆዬ ሥነ ቃልም ሙስና ለውበት መገለጫ እንደሆነ ይገልፃል።
ስለዚህ “ልዩነታችን ውበት ነው!” ከሚለው የኢፌዲሪ መፈክር ጎን ለጎን “ሙስናም ውበት ነው!” የሚል ጥቅስ ቢጨመርበት የመጭውን ትውልድ የቋንቋ ክህሎት ያሳድጋል የሚል እምነት አለኝ።
ባለፈው ከአቡዬ ጋር ‘እጅ መንሻ ሙስና ነው ወይስ ማህበራዊ ትውፊት?’ የሚል ርዕሰ ጉዳይ አንስተን ነበር።
አቡዬ የእጅ መንሻ ቀጥተኛ ትርጉም ገፀ በረከት ነው ብሎ ያምናል።
“ገፀ በረከት ደግሞ ለፍቅረኛህ ወይንም ለንስሀ አባትህ ልታበረክት ትችላለህ እርግጥ ነው ፍቅረኛህ ከወትሮው በተለየ መልኩና ስጦታህን የሚመጥን እቅፈት ልታበረክትልህ ትችላለች፤ ንስሀ አባትህም ቢሆኑ ተግተው ሊፀልዩልህ ይችላሉ ይሁን እንጂ ያንተ ፍቅረኛ ግለት ና የንስሀ አባትህ ትጋት በዚህች ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚጋርጡት አደጋ ስሌለለ እጅ መንሻ ሙስና ሊሆን አይችልም” ብሎ ሀሳቤን ሳይጠይቅ ፋይሉን ዘጋው።
አቡዬ ህልም አለው!! ህልሙ ደግሞ ጉቦ መብላት ነው።
ገና ስለ ጉቦ ማሰብ ሲጀምር ከመጎምዠቱ የተነሳ አፉ በምራቅ ይሞላል፤ ምራቁን ሲውጥ ጉሮሮ አካባቢ ግጉግቦግ የሚል ድምፅ ይሰማል።
ሥራ ሲቀጠር ራሱ ለህልሙ መሳካት ምቹ ይሆናል ብሎ ከሚያስበው መስሪያ ቤት ነው የገባው።
አቡዬ ይህን ሀሳቡን እንዲቀይር ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፤
ለለውጥ እቁብን መሰረት ያደረገ ዕቅድ ይኖረው ዘንድ ለማሳመን
‘ስማ አቡዬ ሰውን ሰው ያረገው ምን ይመስልሃል?’ ስለው ፈጠን ብሎ “ጉቦ ነዋ!” አለኝ እቁብን ከቁብ ሳይቆጥር
“ስማኝማ…” ቀጠለ አቡዬ “ጉቦ ካልበላህ እቁብስ ቢሆን ከምን አምጥተህ ትጥላለህ?”
እንዴ ሠርተህ የምታገኘው የሀቅ ገንዘብህስ? ጥያቂዬ ነበር
“ኦዎዎዎይ ምን የዛሬ ጊዜ ገንዘብ ጉቦ ጣል ካላደረክበትኮ አይጠራቀምልህም
ለምን እንደዚህ ትላለህ ኦሾ?(አንዳንዴ ልፈላሰፍ ይላልና) እስኪ እነ ጋሽ ዲንቃ ዶሪን እነ ወይዘሪት ዘበናይ ሀይሌን … አትመለከትም? እዚህ ደረጃ የደረሱት እንኮ በእቁብ ነው! አልኩት ቆጣ ብዬ ዳሩ ምን ያደርጋል እሱ የበለጠ ተቆጣ
“በሳንቲም ስናዎራ ቆይተን የፎቅ እቁብ ስለሚጥሉ ሰዎች ታዎራኛለህ? ማንን ልታነካካ ነው ያለምሳሌ ማውራት አትችልም?”
ከዚህች ደቂቃ ጀምሮ አቡዬን ስለጉቦ እና እቁብ ላላወራው ወስኘ ነበር አንድ ቀን ከሦስተኛ ፓሊስ ጣቢያ ተደውሎ አቡዬ ቁርስ እና ልብስ አቀብለው ዘንድ እንደሚፈልግ ተነገረኝ…
…አቡዬ ጋር ዓይን ለዓይን ተፋጠጥን ታስሯል እስከምችለው ድረስ ተጠጋሁት በጉቦ ነው አይድል? አልኩት በለሆሳስ አልመለሰልኝም እኔ ግን ቀጠልኩ ‘እሽ አሁን ገባህ አይድል? የጉቦን መዘዝ ተማርክ አይድል?’ ስለው
እጁን እያወናጨፈ “እባክህ የተማርኩት አንድ ነገር ብቻ ነው” አለኝ ‘ምን?’ “ሙስና እና ወሲብ አንድ እንደሆኑ…አየህ ሳሚ ሙስና እንደ ወሲብ በሁለት ሰው ብቻ መፈፀም አለበት ሦስተኛ ወገን ከገባበት አለቀልህ! አንድ ደላላ ሸወከብኝ…” ገረመኝ እና አቋርጨ ሌላ ጥያቄ ጠየቅኩት ግን እንዴው አቡዬ ሙስና ከሀገራችን መቼ የሚጠፋ ይመስልሃል?”
አቡዬ ከተለመደው ውጪ ፂሙን ሳያሻሽ ፈጥኖ መለሰልኝ “ሀምሳ ብር ከች አ’ርግና ልንገርህ!”
ቸር ይግጠመን
Average Rating