‹‹ቀበርናቸው!!!››
#ETHIOPIA :
• በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ቤተሰቦቻቸው፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ አርቲስቶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል
• ደቡብ ኮሪያውያን የሀዘን የክብር ልብስ ለብሰው ተገኝተዋል
• ከመኖሪያ ሠፈራቸው ጀምሮ በቄራ ልጆች ሞተረኞች ታጅበዋል
• መልካምነት ማስታዎቂያ አይፈልግም፤ ቀኝህ የሚሰጠውን ግራህ አያይም፡፡ እናም ሰይፉ ፋንታሁንን አመስግኑልኝ
***
አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሃገር ልዩ ስሙ ከዱ በተሰኘ ስፍራ አባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ሰኔ 20 ቀን 1916 ዓ.ም ተወለዱ።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ጎባ ከተማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ፡፡ ቤተሰባቸው በስራ ምክንያት ወደ ጊንር በመቀየራቸው ትምህርታቸውን በጊንር ቀጠሉ፡፡ በመቀጠል ወደ ሐረር ሄዱ፡፡ ሐረርም የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው ተማሩ፣ ለተወሰኑ ዓመታት ሐረር ከኖሩ በኋላ በ14 ዓመታቸውም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
ፋሽስት የጣልያን መንግስት አገራችንን በወረረበት ወቅት በርካታ ሰዎችን ረሽናል፡፡ ከረሸናቸው ሰዎች መካከል የእሳቸው እናትና አባት ይገኙበታል፡፡
ተስፋዬ ሳህሉ በጣልያን ወረራ ወቅት በልጅነታቸው ከቤተሰቦቻቸውና ከአካባቢያቸው በቀሰሙት የሽለላ፣ ቀረርቶና መሰል ትውፊታዊ ክዋኔዎች እና በውስጣቸው በነበረው የኪነ ጥበብ ፍቅር እንዲሁም ፍላጎት አማካኝነት ወደ ሙያው ተቀላቀሉ።
ገና በልጅነታቸው እናትና አባታቸውን ያጡት አባባ ተስፋዬ ለከፍተኛ የሕይወት ፈተና የተጋለጡ ቢሆንም ያጋጠማቸውን የሕይወት ፈተና ተቋቁመው በአገራችን አንቱ ለመባል በቅተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር ቤት የትያትር ፍላጎት ያላቸውን ሲያሰባስብ ተስፋዬ ሳህሉ በወር 11 ብር ተከፋይ ተዋናይ ሆኑ፡፡
ከአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በኋላም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አገልግለዋል፤ አባባ ተስፋዬ በትወናው ዓለም ከሰባ (70) በላይ ትያትሮችን ተጫውተዋል።
ሀ ሁ በስድስት ወር፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ ኤዲፐስ ንጉስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ዳዊትና ኦርዮን፣ ኦቴሎ፣ አስቀያሚዋ ልጃገረድ ፣ ስነ ስቅለት እና የአዛውንቶች አባት አባባ ተስፋዬ ከተወኑባቸው ተውኔቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
ብጥልህሳ፣ ነው ለካ እና ጠላ ሻጯ የተሰኙ ተውኔቶችን ደግሞ በድርሰት አቅርበዋል።
ሁለገብ የሙያ ሰው ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) በሙያ ዲስፕሊን ሠርተው አገር እና ሕዝብን በታማኝነት እና በቅንነት አገልግለዋል፡፡ ስለ ሙያቸው እንዲህ ይሉ ነበር ፤ ‹‹ኪነ ጥበብ አባቴ ነው፤ ንጉሤና አሳዳርዬ ነው። እፈራዋለሁ፡፡ አከብረዋለሁ፡፡ የኪነ ጥበብ ባሪያ ነኝ፡፡ ከኪነ ጥበብ የምለየው ስሞት ብቻ ነው››
ከ10 በላይ ሙያዎች የተካኑ ናቸው፡፡ ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ የልጆች ተረት ደራሲ፣ ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የምትሃት ባለሙያ ይጠቀሣሉ።
አባባ ተስፋዬ ብዙዎቻችን በምናውቃቸው የልጆች ክፍለ ጊዜ ፕሮግራማቸው ቢሆንም የተለያዩ ሙያ ባለቤትም ናቸው።
ይጫወቷቸው ከነበሩት የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከልም በገና፣ ዋሽንት፣ ክራር፣ መሰንቆ እንዲሁም ፒያኖ፣ አኮርዲዮን፣ ትራምፔት ይጫወቱ የነበሩት አባባ ተስፋዬ አንቺ ዓለም፣ አንድ ጊዜ ሳሚኝ፣ ሰው ሆይ ስማን አዚመዋል።
በብዙዎች ዘንድ አባባ ተስፋዬ በመባል ይታወቃሉ፡፡ በተረት መልክ በርካታ ኢትዮጵያንን ባህል እና ቁም ነገርን አስተምረዋል ።
ለህጻናት የሚያገለግሉ ተረቶችን በማዘጋጀትም በቁጥር አምስት የሆኑ የተረት መጻሕፍትን ለኅብረተሰቡ አበርክተዋል።
ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሃሳቡን አቅርቦ በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለ42 ዓመታት በአባትነት፤ ፕሮግራማቸውን ሲጀምሩ’’ጤና ይስጥልኝ ! … የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምናችሁ ልጆች !’’ እያሉ አቅርበዋል። በበርካቶች ዘንድ የሚታወስና የማይረሳ ነው።
የቀድሞ ኃ/ስላሴ ቴአትር ቤት ወይንም በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በ1948 ዓ.ም በይፋ ስራ ሲጀምር በማዘጋጃ ቤት አብረዋቸው ይሰሩ ከነበሩ ተዋናይ ጋር ተሸጋግረዋል፡፡
ለ42 ዓመታት ልጆችን ተረትና ምሳሌ በማስተማር፤ የሚታወቁት አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰው በ1998 ዓ.ም. በኋላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መቀጠል አልቻሉም።
አባባ ተስፋዬ የተለያዩ ቋንቋዎችንም አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና እና ፈረንሳይኛ ይናገሩ ነበር ።
በኢትዮጵያ የትወና ታሪክ ውስጥ ከራሳቸው ተፈጥሯዊ ትወና በተጨማሪ ሴቶች ወደመድረክ መምጣት ባልደፈሩበትና የሴት ተዋናይት ባልነበሩበት ወቅት በጎንደሬው ገ/ማሪያም፣ ቴዎድሮስ፣ አፋጀሽኝ፣ መቀነቷን ትፍታ፣ ጠላ ሻጯ እና የጠጅ ቤት አሳላፊ ቴአትሮች ላይ የሴት ገፀ ባህሪያትን ለአራት አመታት ተጭውተዋል፡፡ ከ4 አመታት በኋላ ሰላማዊት ገ/ስላሴ የተባለች አርቲስት በመምጣቷ ምክንያት ወንድ ገፀ ባህሪያትን ተላብሰው መጫወትን ቀጠሉ፡፡
አባባ ተስፋዬ ሴት ሆነው ሲጫወቱ ገፀ ቅባቸውን የሚሠሩት እራሣቸው ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ለ36 ዓመታት ያገለገሉት አባባ ተስፋዬ በ1973 ዓ.ም በጡረታ ተገለሉ። ሆኖም በቴአትሩ አይቀጥሉበት እንጂ በልጆች ክፍለ ጊዜ ለረጅም ዓመታት ለአገር እና ለሕዝብ ሠርተዋል።
ደቡብ ኮሪያ በተወረረችበት ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን (የአሁኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት) አባል በመሆኗ በቀረበላት ጥሪ ወቅት የክቡር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ አባል በመሆን
ከ1944 -45 በ2ኛ ቃኘው ሻለቃ
ለ2ኛ ጊዜ ከሄደው ሠራዊትጋር ደግሞ
ከ1946-47 በ4ኛ ቃኘው ሻለቃ ለሁለት ጊዜ የወታደራዊ ሳይንስ ተዋናይ በመሆን ሠራዊቱን አገልግለው ለዚሁም የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
በክብር ከተሰጣቸው ሜዳልያዎች መካከል ጥቂቶቹ
1. የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ ሜዳሊያ ባለ 1 /ዘንባባ/ ከኢትዮጵያ መንግስት
2. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ የወርቅ ሜዳልያ ከኢትዮጵያ መንግስት
3. ዩኒየን ሣይቴሽን ከአሜሪካ መንግስት ተሸልመዋል፡፡
አባባ ተስፋዬ ስራቸው ያስገኘላቸው የህዝብ ፍቅር እንጂ የገንዘብ ሃብት አልነበረም፡፡ በስራቸው ገሪያ፣ ግብፅ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ሱዳንና ሌሎች ሀገራት /እኔ የሰው ሀገር እንግዳ እንጂ ነዋሪ አይደለሁም ብለው ተመልሰዋል/
አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ እጅ ሦስት ጊዜ የወርቅ ሰዓት ተሸላሚ ናቸው፡፡ እንደዚሁም በ1991 ዓ ም በኪነ ጥበብ ለአገር እና ለሕዝብ በአበረከቱት ሥራ የኢትዮጵያ የኪነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በቴአትር ዘርፍ ‹‹የሕይወት ዘመን›› ተሸላሚ ናቸው፡፡
አባባ ተስፋዬ ሐምሌ 22 ቀን 2ዐዐ9 ዓ. ም ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለ34ተኛ ጊዜ ተማሪዎችን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም ባስመረቀበት ስነ ስርአት ላይ ረዥም ዘመን የላቀ አገልግሎት የሚሰጠውን የክብር ዶክትሬት ከሸኸ መሐመድ ሁሱን ዓሊ አላሙዲን ሥም የተሰየመውን ሜዳልያ የልጃቸው ሚስት ወ/ሮ ወይንሸት ተሾመ ተቀብለዋል፡፡
ወ/ሮ ወይንሸትም ሽልማቱን ይዘው ፈጥነው ቤት ደረሱ፡፡ የክብር ዶክትሬት ሜዳሊያውን ከአንገታቸው አውልቀው ለአባባ ተስፋዬ አጥልቀውላቸውል፡፡
በዚህን ጊዜ አባባ እንዲህ አሉ፤ ‹‹ልጆቼ! … ዛሬ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ … ይህ የመጨረሻ የክብር ሽልማቴ ይመስለኛል፡፡ ሰው የሚፈልገው ከፈፀመ በኋላ የሚጠብቀው ክቡር ሞቱን ነው በማለት በደስታ ውስጥ እያሉ ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም በመኖሪያ ቤታቸው በተወለዱ በ93 ዓመታቸው ደህና ሁሉ ልጆች ብለው ላይመለሱ አሸልበዋል።
በትዳር ሕይወታቸውም ለ48 አመታት አብረው ከኖሩት ከባለቤታቸው ደብሪቱ አይታገድ ጋር ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የበኩር ልጃቸው ከአባባ ቀድሞ አርፏል፡፡ ይሁንና አባበ አምስት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።
የአርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ፤ (አባባ ተስፋዬ) ሥርዓተ ቀበር ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2009ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በ 9፡00 ሰዓት ተፈጽሟል፡፡
***
ደህና ናችሁ ልጆች!
ደህና ናችሁ ልጆች!
ደህና ናችሁ ልጆች! …
Average Rating