Read Time:3 Minute, 53 Second
==================================
* ክምሩን የሀገር ሀብት ስርቆት ፣ ብክነት ሳስበው
* የግፍ መንገድ ፣ በጉድ ሀገር …
* እንኳንም ተፈታህ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ !
ክምሩን የሀገር ሀብት ስርቆት ፣ ብክነት ሳስበው …
================================
ክምር በቢሊዮን የሚቆጠር የሀገር መዋዕለ ንዋይ ከመቶ ባልበለጡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የመዘረፉን ወንጀል እየሰ ማን ነው ። ጥሎብኝ ገንዘቡን ወደ አባይ ግድብ አስጠጋውና የሳውዲ ነዋሪ ለአመታት ካጠራቀመው ጋር አወዳድረዋለሁ ። አልገናኝህ ይለኛል … ገንዘቡ ከፍ ሲል ሌላ ማወዳደሪያ እፈልጋለሁ ። .. ውጭ ያለው በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ ወደ ሀገር ከሚልከው ገንዘብ የተገኘውን ገቢ አስበውና እንደገና የተሰረቀው ከባድ የመሆኑን ክብደት ያስደነግጠኛል ፣ እደነግጣለሁ ። ” ጠፋ ፣ ተሰረቀ ” የተባለው የዚህች ድሃ ሀገር ገንዘብ ስንት አውሮፕላን እንደሚገዛ ሳሰላ ውዬም አውቃለሁ ፣ የሞኝ ነገር ትሉኝ ይሆናል ። ግን አይደለም ። የገንዘቡን ክብደት ለማወቅ እንጅ … እንዲህ ሲቆጨኝ ስዳክር ነው የሰነበትኩት 🙁
ክምሩ የሀገር ሀብት መሰረቅ መረጃ እንደዋዛ አጋርቸ ” ወደ ገበያ ሲረጭ ጣራ የነካውን ኑሮ ሽቅብ ስለሚያጉነው እውነት ምን ትላለህ ? ” ያልኩት አንድ የምጣኔ ሀብት ተንታኔ ያጫወተኝ ቀልቤን ጨምድዶታል ። ብሩን ወደ ኢንዲስትሪ ቀይሮ ለሳውዲ ተመላሽ አስተማማኝ ገቢ እንሚፈጥርም ሲያሰላው ሀገሬ የገባችበትን የዝርፊያ መቀመቅ በቁጭት አሰደመመኝ ። … ግን ክምሩን የሀገር ሀብት ስርቆትና ብክነትና ጫፍ የነካ ሙስና ሳስበው ባልበቃቃ ምክንያት የሚሰቃዩት ጎልማሳ ወጣት ትንታጎች ስቃይ አመመኝ 🙁 እነሱ ትልልቅ አሳዎች ናቸው … የሚታሰሩት በክብር ፣ ፍርድ ቤት የሚቀርቡት በክብር ፣ ወህኒም የሚወርዱበት ሁኔታ አይታወቅም ..
የክምሩ ዘርፊያ ተዋናኞችን ትላልቅ አሳዎችን አስቤ
ሀሳባቸውን በነጻ በገለጹ ፣ ለሀገራቸው መጻኤ ህይዎት ህልም ባለሙ ፣ የሚሳደዱት ፣ የሚታሩት ፣ እድሜያቸውን በወህኒ የሚያሳልፉት ግፉአን ታወሱኝ ፣ ምክንያቴ የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ከእስር መፈታት ሆኖ ድምጽ ጠራኝና የግፍ መንገድ ፣ በጉድ ሀገር ብዬ ቀጠልኩ …
የግፍ መንገድ ፣ በጉድ ሀገር …
==================== በዚህ ሁሉ መካከል ያን ሰሞን ወጣቷ ንግስት ይርጋ በማዕከላዊ የደራባትን መራራ ስቃይ ሰምተን ባይገርመንም ፣ ተበሳጨን 🙁 ሀዘናችን ሳይበርድ ሌላ ሌላ ሰማን …ከቀናት በፊት ደግሞ ጉምቱው ፖለቲከኛ ፕሮፊሰር መራራ ጉዲና ” ፍርድ ቤት የፍጥኝ ታስሮ ቀረበ ” የሚል መረጃ ተሰራጨ …የብዙው ሀገር ወዳድ ቅስም ተሰብሮ ተመለከትኩ … እኔን ግን አልደንቅህ አለኝ ፣ አላመመኝም 🙁 አበሳጨኝ እንጅ … 🙁 በዚህም መካከል የታሳሪው ጋዜጠኛ የኤልያስ ገብሩና የጎልማሳው ፖለቲከኛ የዳንኤል ሽበሽ በዋስ የመፈታት መረጃ ሰምተናል …የዋስ ብር ጠፋ ተብሎ ስንታመስ ያ የተገፋው ትንታግ ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው መዠረጥ አድርጎ የዋስ ብሩን መክፈሉን ስሰማ ደስታዬ ወሰን አጣ … በዚህ መካከል ነው እንግዲህ ግፍ ያተገታው የወጣት ጎልማሳው ፣ ግፍ ያልተንበረከከው መንፈስ የታየኝ …
ግፍ ያልገታው ፣ ያልተንበረከከው መንፈስ …
============================ ከባለ ብሩህ አእምሮው የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከምናውቀው መሳደድ ፣ መታሰር ፣ መገለል ፣ መገፋት … መክሳት መጥቆር አልፎ ብዙ አይተን ሰምተናል…ትንታጎቹ ሀገር ወዳድ የሀገሬ ልጆች ግን አልሸሹም… በእስክንድር እግር ሳተናውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሞጋች ብዕሩን ሲያነሳ በእርግጥም ነበልባል ብዕሩ በእውነት የተሞላ ነበርና ትንታኔው ይለበልባል ፣ አሸብሯል … እናም በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መንፈስ ልቡ የተንቀለቀለው ጋዜጠኛ እስክንድር ስቃይ ተሜ አላሸሸውም … ብርቱው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተራው ተሳዶ ፣ ታስሮ ፣ ተፈረደበት …በእስር ላይ እስር ይሆንበት ፣ ይጨልምበት ዘንድ በጨለማ ቤትም ተወረወረ 🙁 ጨለማ አልገታውም !!! … ተመስገን የህግ አሳሪ ህገ መንግስታዊ መብቱ ሲገፈፍ በእናቱ እንዳይጎበኝ ከመደረግ ጀምሮ ፣ ህክምና የማግኘትና በጠበቃና በሀይማኖት አባቶች የመጎብኘት መብቱን ሳይቀር ተገፎ ከርሟል … ይህ ሁሉ ስቃይ ግን ጋዜጠኛ ተመስገንን ቀርቶ ሊጠይቀው አሳር መከራውን እያየ ያለውን ወንድሙን ታሪኩን Tariku Desalegn መንፈስ አላንበረከከውም… !
ግፍ ሲበዛ ፣ ታሪክ ራሱን ደገመ ፣ ምሬት ሌላ ትንታግ ይወለድ ዘንድ ምክንያት እንጅ የወጣቱንና የጎልማሳውን ሀገር ወዳድ ልብ አላንበረከከውም… መንፈሰ ጠናካራው ታሪኩ ደሳለኝ ፖለቲለኛ አይደለም ፣ የላቀ እውቀትን ያዳበረ የፊልም ጥበበኛ ነው … የመገፋት መረጃ ትረክቱን ደጋግሞ አጋርቶናል …ከቀናት በፊት በጠራራው ጸሐይ በመሃል አዲስ አበባ መሀል ፒያሳ ገጀራ የያዙ ወሮበሎች ሞባይሉን ነጥቀው የፈጸሙበትን ደብደባና ዝርፊያ ላነበበ ታሪኩ ደሳለኝ በሙያው ከጋዜጠኞቹ ከእኛ በላይ መጻፍ መቻሉን ምስክር እንሰጥ ዘንድ ቀልባችን ደጋግሞ ወስዶ አሳዝኖናል… ወንድሙን ብሎ በሄደበት መንገድ ግን ሲገፉት ፣ሲጨቁኑት የነጻነት መንፈሱን ፈትነው የወንድሙን የደም ውርስ አወረሱት … እየጎነተሉ እያማረሩ ፣ እያስከፉ የሆነውን ቀሽሮ የሚጽፍ ጎበዝ ጋዜጠኛ አደረጉት !
የጋዜጠኛ እስክንድር መገፋት ጋዜጠኛ ተመስገንና ወንድሙን ብቻ አላሳየንም…መግለጽ ለሚቸግረኝ ትንታግ ሀገር ወዳዶች ተመልክተናል … ፖለቲለኛው ፣ አክቲቪስቱ ፣ ጋዜጠኛውና ተራው ዜጋ ሲገፋ መብት ይከበር ዘንድ የሚጽፉ ትን የቀደመው ሆነ አሁን የምንሰማው የማዕከላዊ ማሰቀያ እስር ቤት አሰቃቂ ድብደባና ምርመራን እየሰማን የፈራ የለም ። ግፍ በበዛ ፣ በተሰማና በታየ ቁጥር ጭራሹኑ ወጣቱ ጎልማሳው አምርሯል ። የትንታግ ወጣት ታዳጊዎችንና ጎልማሳ ሀገር ወዳዶችን ወኔ የንግስት ይርጋ የመረረ መብት ገፈፋ ፣ ሰሞነኛው የዶር መራራ ጉዲና ልብ ሰባሪ አያያዝም ሆነ በፍርድ ቤት ሞቱ በተነገረው ታሳሪ ጎልማሳ አየነ በየነ ነጋሳ ህልፈት ማንንም ሊያስፈራና ሊያሸሽ አልተቻለውም ። ጭራሽ ወጣት ጎልማሳው ለነጻነት መብቱ በሰላማዊ መንገድ ይታገል ዘንድ ያበረታው እንጅ የሚያምበረክክ የሚያሸሽው አይመስልም ። አጠንክሮት አየን እንጅ … ሲገፉ ስለ መጠንከር ፣ ሲቀጠቀጡ ስለ በመበርታት ስናወሳ የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩና የፖለቲከኛው የዳንኤል ሽበሽ የወራት ስቅየት እንግልት ይዘከራል …
እንኳንም ተፈታህ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ …
============================= መገፋት የወለደው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ከወራት እንግልት በኋላ በመፈታቱ ደስ ብሎኛል ፣ ጎልማሳው ፖለቲከኛው ዳንኤል ሽበሽም ነገ ከእስር ይፈታል ተብሏል ሁሉም ግፍ ያበረያቸው ፣ ግፍ የወለዳቸው ሀገር ወዳዶች ናቸው ። ያሳለፉት ስቃይ አይገድባቸውም ፣ መታሰር መገፋታቸው ነገም እንደ ትናንቱ ለነጻነት መብታቸው ከመናገር ፣ ከመመስከር የሚገታቸው አልሆነም ። የወጣት ጎልማሳው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊነት ወኔ አልተቻለም !
ከመታበይ ወጥቶ በሰከነ አዕመሮ እየሆነ ያለውን መንገዱን ለማይገመግመው ፖለቲከኛ የማያየው እውነት ይታየናል …በእርግጥ የወደፊት የሀገር ተስፋ ሀገር ወዳዶችን ጊዜ በእስር ማባከን የሀገርን ተስፋ ማጨለም ጭምር ነው …በእርግጥ የወደፊት የሀገር ተስፋ ሀገር ወዳዶችን ገላ በምርመራ ዱላ እየመተሩ ማኮላሸት የታሪክ ጠባሳን ከትውል ድ ትውልድ ያወርሳል እንጅ ትውልዱን አይጠቅምም። በአደባባይ የቀሪውን ሞራል ለመስበር የአዕምሮ ጦርነት በአደባባይ መክፈት ፣ የሀገርን ተስፋ ማኮላሸት ፣ የማደግን ህልም ማጨለም ጭምር መሆኑ ሊገባቸው ይገባል !
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እንኳን በሰላም ከቤተሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ ከአድናቂ አፍቃሪዎችህና ከሚወድህ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጋር ተገናኘህ !
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓም
Average Rating