————
ማክሰኞ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ዝዋይ ከተማ ደረስኩ። ዓላማዬም ዝዋይ እስር ቤት በግፍ እስር ላይ የሚገኙ የቀድሞ የስራ ባልደረቦቼን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬንና ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ ነበር።
በዝዋይ አቧራ በጥልቀት እየታደስኩም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ዝዋይ እስር ቤት ደረስኩ። ከእስር ቤቱ ጎን ዘመናዊ የሚመስል ሰፊ እስር ቤት ተገብንቶ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ማን ይገባበት ይሆን?! የዛሬ አሳሪ ወይስ ታሳሪ? …
ጥበቃው በር ላይ መታወቂያዬን ሰጥቼ መጠየቅ የፈልኩትን እስረኛ ስም አስመዘገብኩ፤ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬንና ተመስገን ደሳለኝን።
መዝጋቢው ፖሊስም መዝግቦ ጨረሰ። አንድ መሳሪያ የታጠቀ ፖሊስ መጣና የሚጠሩትን እስረኞች (በእነሱ አጠራር ታራሚ) ስሞች ከሰማ በኋላ ቀና ብሎ አፍጥጦ ተመልከተኝ።
“ምንህ ናቸው? በምንድን ነው የምተዋወቁት?”
“በስራ” አልኩት በአጭሩ።
ለመዝጋቢው ፖሊስ “የተመስገንን ስም ሰርዝ!” አለው ቆጣ ብሎ።
“ለምን?” አልኩት።
“ሰለማይቻል!”
“ለምንድን ነው የማይቻለው?!”
“ከቤተሰቡ ውጪ እንዳይጠየቅ ተከልክሏል”
“መቼ?”
“ቆየ”
በመገረም “ከሶስት ቀናት በፊት ቅዳሜ ወዳጆቹ መጥተው ጠይቀውት ተመልሰዋል። ስማቸውን ልነግርህ እችላለሁ። መዝገቡን ገልጠን እንየው?” ስል ጠየሁት።
ነደድ ብሎ ዝም አለና “አሁን መጠየቅ የምትችለው ውብሸትን ብቻ ነው።”
“ተመስገንንስ መቼ ነው መጠየቅ የምችለው?”
ፖሊሱ መልስ አልነበረውም። “ጥመት (መጥመም) 101” አልኩ በውስጤ።
ተበርብሬ ተፈተሽኩና ለጥየቃ የያዝኩትንም አስፈትሼና ቀምሼ አቧራማውን መንገድ ከንዳድ ጸሃይ ጋር እያጣጣምኩ ወደ ውስጥ ገባሁ።
ሁለተኛውን ፍተሻም አልፌ ውብሸትን አስጠራሁት። ከ15 ደቂቃ በኋላ ውብሸት መጣ። በእንጨት አጥር ላይ አልፈን ተቃቅፈን ሰላም ተባባልን። አንድ ፖሊስ ከእሱ ጀርባ ሁለት ፖሊሶች ከእኔ ጎን ቆመው ጆሯቸውን ቀስረው የምንነጋገረውን በጥልቅ ተሃድሷዊ ዝምታ ያዳምጣሉ። ሁነቱ ምቾት አይሰጥም፤ ትከሻን ይከብዳል። እኔና ውቤ ተነቃቅተን ፈገግ አልን።
በ30 ደቂቃ ውስጥ ያወጋነውም ሰለእሱ ጤንነት፣ ሰለእስሩ ርዝማኔ፣ ስለባለቤቱና ልጁ ሁኔታ፣ አብረን ስለሰራናቸው ባልደረቦች፣ ሰለበፍቃዱ ሃይሉ ዳግም እስር፣ ስለጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ክስ፣ ስለጌታቸው ወርቁ ፍርድ …ስለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኞች ያላባራ ፈተና፣ ስለተመስገን ጤንነት፣ ሰለራሱና ስለተመስገን መጽሃፎች፣ ስለእኔና አምሳሉ ገ/ኪዳን ክስና የክስ ሂደት …ወዘተ ነበር። በዝርዘር የልብ የልብን፣ የናፍቆትን ለመጨዋወት ጊዜውና ቦታውም አይፈቅድ ነገር። ….
አንደኛው ፖሊስም “በቃችሁ” አለን። የቀድሞ የስራ ባልደረባዬንና ስለጋዜጠኝነት ተግባራዊ ትምህርት እውቀት ካስቀሰሙኝ የሀገሬ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነውን ውብሸት ታዬን አቅፌ “አይዞን በርታ። ቀን ያልፋል። …ተሜንም በጣም ሰላም በልልኝ። እንደናፈቀኝም ንገርልኝ።” ብየው በተደበላለቀ ስሜት ተለየሁት። ተመስገንና ውብሸት አሁን አንድ ክፍል ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።
የእስር ቤቱ መውጫ በር ላይ ያስቀመጥኩትን እቃ ስወስድ “ተመስገንን መጠየቅ አትችልም” ያለኝ ፖሊስ መሳሪያውን እንደያዘ አገኘሁት። ውስጤን ሲከነክነኝ ነበረና “ተመስገንን መጠየቅ የምችለው መቼ ነው?” ስል ጠየሁት። በድርጊቱ የተረበሸ ይመስላል።
“ነገም ትችላለህ” አለኝ።
ተገርሜ “እርግጠኛ ናችሁ? ዛሬ እዚሁ ዝዋይ አድሬ ነገ ልጠይቀው እችላለሁ?” ብዬ የተሰበሰቡትን ፖሊሶች ጠየኳቸው። “አዎን። ከጥዋቱ 2፡30 በኋላ ና” ሲሉ መለሱልኝ።
በዝዋይ አቧራ በጥልቀት እየታደስኩ ከቀኑ 10፡15 ስዓት ላይ ወደዝዋይ ሃይቅ በማምራት በጉዞ ሳቢያ ከነጋ ምግብ አልበላሁምና የሃይቁን አሳዎች በንዴት ፈጀኋቸው…lol
በነጋታውም ካረፍኩበት የአልጋ ክፍል በጥዋት ወጥቼ፣ ለሁለቱም ቁርስ ይሆናል በሚል የጾምና የፍስክ ምግቦችን ከሆቴል አሰርቼ በጋሪ ወደእስር ቤቱ አመራሁ። በተባልኩት መሰረት ተመስገንን አስመዝቤ ተፈትሼና የያዝኩትንም አስትፈሼ ገባሁ።
እስረኞችን የሚጠራው ልጅ ወደእእኔ መጣ። “ተመስገን ደሳለኝ” የሚለውን ቁራጭ ወረቀት አቀበልኩት።
“ተመስገንን መጠየቅ አትችልም።”
“ለምን?!”
“እኔ ታራሚ ነኝ። እንደማይጥሩልህ አውቃለሁ” ብሎኝ ወደ ፖሊሶቹ ሄደ። ከዚያም አንድ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ባለማዕረግ ሽማግሌ ፖሊስ እኔ ጋር መጡ።
“ሰላም። ማንን ነው የምትጠይቀው?”
“ተመስገን ደሳለኝን”
“አይቻልም”
“ለምን?!”
“ትናንት የጠየከው ማንን ነው?”
“ውብሸት ታዬን”
“ትንናት ተናጋግራችሁ ነው ዛሬ ተመስገን ይጠራልኝ ያልከው”
“አይደለም። ሁለቱንም ልጠይቅ ነው የመጣሁት። ሄደን የትናንቱን መዝገብ ማየት እንችላለን!”
“ትናንት የጠየከው ውብሸትን ስለሆነ ዛሬም መጠየቅ የምትችለው እሱን ነው”
“እሱንማ ትናንት ጠይቄው ሄድኩ”
“አንተ አንድ ሰው ብቻ ነው መጠየቅ የምትችለው”
ማን ነው ያለው? ውብትሸና ተመስገን እኮ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ናቸው”
ፖሊሱ በስጨት አሉና “በቃ ውብሸትን የምትጠይቅ ከሆነ ድጋሚ በር ላይ ሄደህ ወረቀት አስቀይር።”
“ትንናት እዚህ ያደርኩት ዛሬ ተመስገንን መጠየቅ እንደምችል የራሳችሁ ፖሊሶች ነግረው እኮ ነው!”
“ዋ’አይ …”
“ዋ’አይን ምን አመጣው …”
“በል ተነስ …”
“ጥመት 102” – አልኩ በውስጤ።
በንዴት መውጣት ጀመርኩ። ሌሎች ፈታሽ ፖሊሶች “ምነው? ለምን አልጠየክም?” ሲሉ ጠየቁኝ። “ስራችሁ!” አልኳቸው ዞሬ ሳላያቸው።
በር ላይ ስደርስ “ለምን ተመለስክ?” አሉኝ ፖሊሶች። “ውብትሸን እንጂ ተመስገንን መጠየቅ አትችልም ተብያለሁ” አልኳቸው።
አንዱ መጣና ” አዎ ተመስገንን መጠየቅ አትችልም። እሱ በቤተሰቦቹ ብቻ ነው የሚጠየቀው። ውብሸትም አጥፍቶ ከተቀጣ በኋላ ነው አሁን መጠየቅ የጀመረው። አሁን እያጠፋ ያለው ተመስገን ነው። ቅጣት አለበት።”
“መቼ? ስንት ጊዜ?!”
ውሸቱን ስለነበረ ተደነጋገረና “ስድስት ወር …ምንናም”
“ከመቼ ጀምሮ?”
…”ላልተወሰነ ጊዜ”
በውስጤ ለፖሊሱ አፍሬለት “ከቀናት በፊት …ቅዳሜ ዕለት የጠየቁት ወዳጆች አሉ። እነ እገሌ ይባላሉ። መዝገቡን ማየት እንችላለን”
ተበሳጨና “በቃ ውብሸትን ብቻ ነው መጠየቅ የምትችለው!” አለኝ።
“ጥመት 103” አልኩ በውስጤ
ወረቀት ቀየሩልኝ። ከግቢ ሳልወጣም በድጋሚ ተፈትሼ እና ምግብ ቀምሼ ገባሁ። ይህ የፖሊሶች ድርጊት አስቆኛል። ትንሽ እንኳን አይምሯቸውን አይጠቀሙበትም።
ወረቀቷን ሰጥቼ ውብሸትን ሊጠራልኝ አንዱ ሄደ።
በድርጊታቸው አዝኜና ተናድጄ ስለነበረ በዝምታ ተውጩ ፊት ለፊቴ ያለውን የእስር ቤት ቅጥር ግቢ አይ ጀመር። ውብሸት የውሃ ሽታ ሆነ። 30 ደቂቃ አለፈ፤ አልመጣም።
አንድ ፖሊስ ከፊቴ ሶስቱ ደግሞ ከጀርባዬ ነበሩ። አንዱ ወደእኔ ቀርቦ “ሰላም ነህ” አለኝ። “ሰላም” ብዬ ፊት ለፊቴን ማየት ጀመርኩ። ከጀርባዬ ሆነው በለሆሳሳ ይነጋገራሉ።
አንድ ፖሊስ ከውስጥ መጣና ሰላም አለኝ።
“ኤልያስ ገብሩ ነህ አይደለ?”
“አዎን”
“ውብሸትንም መጠየቅ አይችልም”
የግርምት ሳቅ ሳኩኝና “ለምን ደግሞ?!” አልኩት።
“አይቻልም” ተብሏል።
“ማነው ያለው?”
“ከውስጥ ነው”
“ተመስገንን መጠየቅ አትችልም ውብሸትን እንጂ” ብለው ሲያደርቁኝ ወደነበሩት ሽማግል ፖሊስ በዝምታ ፊቴን አዞርኩ። አንገታቸውን አቀርቅረዋል። ለሁሉም (በተለይ) ለሽማግሌው ፖሊስ መናገር ያለብኝን ተናግሬ በቆሙበት በመካከላቸው አልፌ ትቻቸው ወጣሁ። ግን አይገባቸውም። ለአይኔም አስጠሉኝ፣ አነሱብኝ። የህጻን ልጅ ጨዋታ የሚጫወቱ መሰለኝ። ድራማቸውም አሳፋሪ ሆነ! ሰው ከመሆን ክቡር ደረጃም ወረዱብኝ!
ህወሃት/ኢህአዴግ፣ አስሮም አይረካም! አስሮም ያሰቃያል! ከእሱ ሃሳብ የተለዩ ግለሰቦችን በግፍ አስሯቸውም ስጋቶቹ ናቸው።
ሌሎች ፖሊሶችም በመንገዴ ላይ አግኝተውኝ “ምን ሆነህ ነው?!” ጥያቄያቸው ነበር። መልስ ሳልመልስላቸው ሄድኩ።
በዝዋይ እስር ላይ ከሚገኙ የህሊና እስረኞች በላይ በአካልና በመንፈስ የታሰሩ ፖሊሶች ቁጥር ቀላል አለመሆኑ ገባኝና “የቁም እስረኞች” አልኳቸው በውስጤ።
“አድርጉ!” የሚባሉትን ብቻ የሚያደርጉ የሰው ሮቦቶችም መሰሉኝ ብዙዎቹ። “The walking Dead” የተሰኘው ተከታታይ ፊልም አስታወሱኝ እነኚህ ህሊናቸውን ለአገዛዙ ቀመር የሰጡ ፖሊሶች። እንደሰውም አንዘኩላቸው። የተሻለ ህይወትን ኖረው ቢሆን እንኳ አንድ ነገር ነበር።
…በር ላይ ሞባይሌንና ቦርሳዬን ተቀብዬ የእስር ቤቱን ቅጥር ግቢ ለቀኩኝ። ሶስቱ ፖሊሶች በቅርብ ርቀት ወደእኔ አቅጣጫ እየመጡ ነበር። ዳግም ዞር ብዬ ሳላያቸው ጋሪ ተሳፈርኩ። የያዝኩትንም ምግብ ለአንዷ ተሳፋሪ ሰጠኋት። ለካስ ዩኒፎርሟን ቀይራ ከስራ የምትወጣ ሴት ፖሊስ ነበረች። ልብስ ቀይራ ነበረና የእስር ቤቱን አሰራር ብልሹነት ነገረችኝ። ስትወርድም “ለህሊናችሁ ኑሩ፣ ከፍርሃትም ውጡ!” አልኳት።
ሞጆ ከተማን አለፍ እንዳልን ስንሄድም ሆነ ስንመለስ በፖሊሶች ጥብቅ ፍተሻ አለ። ተበርብረን ተፈትሸናል። ኪሴ ስገባ ግን መታወቂያዬን ጣትሁት። ትዝ ሲለኝ፣ ፖሊሶቹ ጋር ቀርቷል።
…ዞሮ ዞሮ ብዙ ነገር ሳስብ ኢትዮጵያኖች በብዙ ነገር ወደኋላ ቀርተናል፤ እየቀረንም ነውና የምንሻቸው ነገሮች እውን እንዲሆኑ ዘወትር ተስፋ ሳንቆርጥ መታገል እንደሚገባን እምነቴ ነው! አሊያ መከራችን ይረዝማል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!
Average Rating