የማለዳ ወግ …
======================================
* ውሃ የበላው ጎልማሳና እኔ …ያኔ 🙁
የማወጋችሁ ዛሬ ስለሌለ ፣ ትናንት ስለነበረ አንድ ጎልማሳ ወንድም ነው … ተንከራታች እግሬ የማያደርሰኝ ቦታ የለም ፣ ክፉው ስደት የማያሳይ የማያሰማኝ የለም። እኔና ከዚህ በታች የማወጋችሁ ጎልማሳ ወንድም ከሁለት ወር በፊት የሳውዲን የውጡ ምህረት አዋጅ ተከትሎ መልዕክት ልኮልኝ ግንኙነነት ተጀመረ … ብዙ ሳይቆይ ለአመታት ይሰራበት ወደ ነበረው የአሲር ግዛት ለኩባንያ ስራ ሳመራ በፊስቡክ የጻፍኩትን መረጃ ተመልክቶ በአካል ሊያገኘኝ እንደሚፈልግ ጠየቀኝ…ፍቃደኝነቴን ገለጽኩለት … ደስታው ገልጾልኝ በክልሉ ለስራ ጉዳይ ስተላለፍ ተገናኘን ። ለሰዓታት ባንደ ተቀምጠን የሆድ የሆዱን ዘርግፎ እንደ ትልቅ ወንድም አምኖ አጫወተኝ ።
ሲሰደድ …
========
ጎልማሳው ታታሪ ገበሬ ነበር ፣ እያረሰ እስከ 10 ክፍል ቢማርም ተምሮ ወገኖቹን የመደገፉ ነገር ራቀበትና ወደ አሳደገው እርሻ አደላ ። አባቱን በልጅነቱ ያጣው ጎልማሳ የተጫነበትን የቤተሰብ ኃላፊነት መቋቋም ግድ ሆነ ። አርሶ ለእሱ ለባለቤቱ ፣ ለልጁና ለቀረች እናቱ የእለት ጉርስ አያንስም ነበር ። በእርሻው አብረው የሚያግዙትን ወንድምና እህቱንም በማስረማሩ ይደግፋል ። ጉልበት እያለው የሚያርሰው በቂ ማሳ ባያገኝም ተመስገን ብሎ ኑሮን ይገፋል ። ቀለም መቁጠሩ ንቃተ ህሊናው ከፍ አድርጎታልና ሲበደልና ሲገፋ ” ለምን ?” ይላል ሹሞችን ይጠይቃል ። በመሬት ክፍፍሉና በአንድዳንድ ጉዳይ ከሹሞች ጋር አይስማማም ። በትውልድ ቀየው የደረሰን የአስተዳደር በደል ደጋግሞ በመቃዎሙና መገፋትን አሻፈረኝ ብሎ መጨቆን ለምን ? በሎ በጠየቀ በሹሞች ተጠምዷል … ሲላቸው ፖለቲከኛ አድርገው ዘብጥያ እንዳያወርዱት ስጋቱ ከእሱ አልፎ የመላ ቤተሰቡ ሆኗል። ብዙም ሳይቆይ ከወንድሙ ጋር የተሰጠችውን የበሬ ግንባር የምታክል መሬት አርሶ ኑሮን መግፋት ቢጀምርም ኑሮን መግፋት ተሳነው ። በላዩ ላይ የሹሞች የሚደርስበት እለታዊ ጫና አስከፍቶ አሰደደው …
ስደትና ፈተናው …
==============
ስደቱ በሶማሊያው ቦሳሳ በኩል በቀይ ባህር የሚደረግ ስደት ነበር ፣ ሲናገረው መስማቱ ይከብዳል። የመንን ከእገታ አምልጦ በሳውዲው ገጠር ያሳለፋቸው አራት የእረኝነት አመታት ለእሱ ከሀገር ቤቱ ኑሮ የባሱ ነበሩ ። በአራት አመት ቆይታው ሁለት አመት ደመወዙን በሰላም ተቀብሎ ቤተሰብ መርዳት ቢችልም ። ድፍን የሁለት አመቱን ደሞዝ በአሰሪዎቹ ተቀምቷል …
የሁለት አመት ደመወዙን ደግሞ አላጠፋውም ። ለራሱ እንደነገሩ እየኖረ ሀገር ቤት ሚስትና አንድ ልጁን ይረዳል ። መሬት ገዝቶ ፣ ቤትም ሰርቷል ። በሰራው ቤት ባንዱ መስኮት የተከፈተችው ሱቅ ደግሞ ልጁን ትንሿን ቤተሰብ ትደግፍለታለች ። … ሁለት ወንድሞቹ ወደ ከፍተኛ ትምህርት አስገብቶ እያሰተማረ ነው። አንድ አብሮ አደግ ” እሳት የበላ ” የሚባል ጎበዝ ተማሪ አብሮ አደግ ዘመዱን ደግሞ እየደገፈ በዲግሪ አስመርቋል። ወጣቱቹን ከስደት ለመታደግ ሲደግፍ አሳዳጊ እናቱን ቸል አላቸው። ከቀለብ ባለፈ ዘና አድርጎ በወጉ መርዳት አለመቻሉ ህመም ሆኖታል።
ያላሰለሰ ድካሙ ውጤት ግን ራቀው …የሚደግፋት ሚስቱ ለምን እኛን ብቻ አልደገፍክም ከሚል ሙግት ሰላም ነሳችው … በግብር ሱቄ ታሸገ ስትል እያማረረች በላቡ የሰራው ቤት ካደችው ፣ ቤቱ ቀርቶ ልጁን ነጠቀችው ” የማታውቀው ያልረዳህው ልጅ ልጄ ነው አትበል !” ብላ በፍጹም ጭካኔ ካደችው ። ከአንድ ልጁ ለያየችው …
የሚረዳቸው ተማሪ አንድ እህትና ወንድሙ ገና ትምህርታቸውን አላገባደዱም ። … ደግፎ ያስመረቀው አብሮ አደጉ ተማሪዎችን ይደግፋል ብሎ ቢያስብም እሱም ተምሮ ስራ አጣ … ጭራሽ ” ወደ ሳውዲ ውሰደኝ ” እያለ ወተወተው ። ተምሮና ለወግ ማዕረግ በቅቶ በሀገሩ ስራ ላጣ የደከመባቸው የሚያስተምራቸው ወንድምና እህቱ መጨረሻ አሳሰበው ። ጭራሽ ተምሮ መሰደድን የመምረጡን መርዶ ከነገረው በኋላ ተስፋ ቆረጠ … በሚስቱ ክህደት ፣ በተማረው ስራ ማጣት ፣ በተማሪዎች የጨለመ ተስፋ ተማርሮ ፊቱን ወደ እናቱ አዞረ …
እናቱን ለመደገፍ በወጠነበት ሰዓት ደግሞ የሳውዲውን ህገ ወጥ የእረኝነት ህይዎት የሚያናጋ ፈተና ተጫነው ። የሳውዲ ውጡ አዋጅ ደራሽ ጎርፍ ሆነበት ። ግራ ተጋባ … ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች እየኖረ ሁሉም ነገር አድርጎ አልሳካ ሲለው ፣ እናቱን ለመርዳት ወጥኖ ውጥኑ መና ሲቀር ወደ ሀገር የመግባቱን ነገር ሲያስበው ደግሞ ሌላ ስጋት ከፊቱ ተደቀነ ። ሀገር ቤት እያለ ከቀበሌ ሾሞች ጋር የነበረው አለመግባባት ቂም እንደተቋጠረበት ይነገረው ነበርና ይህም ወደ ሀገር እንዳይመለስ ስጋት ሆነው … ይህንና ልገልጸው የማይቻለኝን የቤተሰብ ወግ ዘክዝኮ አካፈለኝ ። ውስጤ ደማ ፣ አሳዘነኝ … 🙁 ስላመነኝ ደግሞ ውስጤን የደስታ ስሜት ተሰማኝ …
እኔና የጨነቀው ወንድም …
==================
በድቅድቁ በርሃ መካከል አሉ ተብሎ በማይታመኑት የአሲር ግዛት አረንጓዴ ሰንሰለታማ ተራሮች ባንዱ ጫፍ ላይ ቁጢጥ ብለን የገጠመውን ፈታኝ ህይዎት ሲያማክረኝ ወደ ሀገሩ እንዲገባ በያዘውን ውሳኔ እንዲጸና ደገፍኩት ። እሱ ሲወስን በአዲሱ የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት እመለሳለው ብሎ ነበር ። እኔ ስደግፈው በሰራተኛ ስምምነቱ ይመጣል ብየ አልነበረም ፣ ያም ሆነ እዚህ ያሳየውን ትጋት ትንሽ በቋጠራት ጥሪት ሀገር ገብቶ በመስራት ይለወጣል ፣ ይሻሻላል በሚል ነበር። … ከምንም በላይ ያ ጎልማሳ አምኖኛልና ሀገር ለመሄድ ቆረጠ ። ግን በአካል ከተለያየንም በኋላ የልጅ ናፍቆቱን ፣ ባዶ እጁን እናቱን ለማየት የከዳውን ሞራል ፣ ብዙ ከሚጠብቁት ቤተሰቦች የመቀላቀሉን ክብደት ብቻ ሳይሆን በፖለቲከኞች የመጠለፍ ስጋቱን ደጋግሞ አጫውተኝ … መረር ያለ ምላሽ ነበረኝ … ፖለቲከኞችን ተዋቸው እንዳሻቸው ያደርጉህ ዘንድ ፍቀድ … እውነትክን ለፈጣሪ ስጥ ስል አምርሬ መከርኩት … ቂም ቋጣሪዎች ቢያሳድዱ ቢያስሩህ ፣ በለየለት ማሰቃያ አሰቃይተው ቢገርፉህ ፣ ድምጽህን አጥፍተው ቢገሉህ እዳው የእነሱ ነው ። ወደ ፊት ትውልድ የሚከፍለው እዳ … አልኩትና በስሜት ተናገርኩት ፣ ወደ ሀገሩ ለመሄድ የማንም ፖለቲከኛ ዛቻ እንዳይገታው አበረታታሁት …ብዙም ሳይቆይ ሁለመናውን አገናዝቦ ፣ …ልክ ከሳምንታት በፊት ቢበዛ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የወንድም ምክሬንም ሰምቶ ጠቅልሎ ወደ ሀገር ገባ …
ግራ የገባቅ ተመላሹ በሀገር ቤት …
=======================
ሀገር በገባ በጥቂት ሳምንታት ያየው ኑሮ ሳይገባው አማረረው ። በስራ ስምሪቱ ስምምነት ለመመለስ ማህበራዊና ኢምግሬሽን ደጋግሞ ጎራ በማለት ቢጠይቅም ” በሀገርህ ሰርተህ ተለወጥ ” ምክራቸው አደከሙት ። ለአዲስ መጤው ላልተማረው ለእሱ ቀርቶ አብሮት የሚንጎራደድ የተማረ ዲግሪ የጫነ ባልንጀራው ስራ ፈት ሆኖ ምኑን ሰርቶ መለወጥ አለ ሲል ቢጠይቅም መልሱ ግን ሩቅ ነው …የማይጨበጥ … ሀገር ቤት ስገባ እታሰራለው ያለው ስጋት ብቻ ሆኗል ። ወደ ገጠር መንደሩ ዘልቆ ስጋቱ ለአደጋ እስኪዳርገው ወይም መናኛ ስጋት መሆኑን አልተረዳም ። ብቻ መሀል ከተማ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ደስ ብሎታል … ከሳውዲ ካርጎ የጫናት ትንሽ እቃ አልደረሰችም … ጉምሩክ ሄዶ የለም ሲባል ሳውዲ ደውሎ ልከነዋል ብለውት እየዋለለ ነው ። በዚህ መካከል የሳምንታት የአዲስ አበባ ቆይታው የቋጠራትን ገንዘብ አባከነበት … ወዲህ እናቱን ማየት ሲፈልግ ባዶ እጁን ሆነ ፣ ወዲያ ምን ይዥ ሲል ልቦናው ባዶነቱን እየነገረው በህይዎት አጣብቂኝ ፈተና ተፈተነ … አማራጩ አንድ ብቻ ሆነ ወደ ቀየው ወርዶ ከመዋረድ ፣ ገንዘቡ ሳይሟጠጥ ወደ ለመደው ስደት ወደ ሳውዲ በመከራው መንገድ መጓዝ ብቻ ሆነና ወሰነ … በገንዘብ የማትለወጥ ፣ አይኑን ብቻ ለማየት የሚንከራተት እናቱን ላለማየት የተደራረበው ፈተና አሸሸው …ዳግም ስደትን አማራጭ አደረገ …ጎልማሳው ወንድም ይህንኑ ያጫወተኝ ሳውዲ ሆኖ አይደለም ፣ ከሳምንታት በፊት መሀል አዲስ አበባ ላይ ሆኖ እንጅ …
የህይዎት ፈተናውና ደርሶ መልሱ ???
========================
… ግመልና ፍየል እየጠበቀ የገነባው ትዳሩ ፈርሷል ፣ የሚወዳት ሚስቱ በላቡ የሰራውን ቤት ፣ ያፈራውን ንብረት ብቻ ሳይሆን በልጆቹ ላይ ክህደት ተፈጽማበታለች …..የሚያስተምራቸው ወንድሞቹ ተስፋ ጨልሞ ተስፋውን አስቆርጦታል ..ያስመረቀው ወዳጁ ስራ አጥቶ እሱም እንዳልተማረ ልሰደድ ባይ መሆኑ ግራ አጋብቶታል ….ከሳውዲው ስደት ወደ ሀገር ተመልሶ … ኑሮው አልገባህ ብሎት ከፍቶት ፣ የሸሸውን ስደት ለመቀላቀል ወስኖ ጉዞ ወደ የመን ሳውዲ ጀምሮ በባህሩ ላይ ተሰናክሏል …
በመጨረሻው ሰዓት መርዶ ሰማሁ … 🙁
==========================
ከሳምንታት በፊት ያወራሁት ሰው ፣ ብርቱው ጎልማሳ ዛሬ የለም ። ስደት ክፉ ነው…ከወራት በፊት ከስደት ተመለሰ “ባዶ እጀን የምወዳት እናቴን አላይም ” ብሎ ለዳግም ስደት ተዳረገ … ከትናንት በስትያ ውሃ በላው ፣ እንኳንም እናት አልሰማች ! … ያማል 🙁
ነፍስ ይማር እንጅ ምን ይባላል … 🙁
ነቢዩ ሲራክ
ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓም
Average Rating