በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመንግሥት የተሰጡ ከቀረጥ ነፃ መብቶች ማስፈጸሚያ መምርያ ኃላፊ፣ በተጠረጠሩበት ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል በድጋሚ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡
የመምሪያ ኃላፊዋ ዓለምፀሐይ ግርማይ (ዶ/ር) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው፣ ወደ ውጭ አገር ሊወጡ ሲሉ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዋ የተለያዩ ድርጅቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ከተፈቀደላቸው በላይ እንዲያስገቡ በመፍቀድ፣ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን 10,697,468 ብር በማሳጣት ጉዳት አድርሰዋል፡፡
መኖርያ ቤታቸው ተበርብሮ የተለያዩ ማስረጃዎች መሰብሰቡን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፣ ለኦዲተር በማቅረብ ሙያዊ ትንተና እያሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የተለያዩ ድርጅቶች የጠየቁባቸውን ደብዳቤዎች መሰብሰቡንና የውስን ኦዲት ምርመራ ቃል መቀበሉንም አስረድቷል፡፡
ከውጭ አገር የሚያስመጣቸው ዲክላራሲዮኖች እንዳሉ፣ የተለያዩ ሰነዶችን መሰብሰብ እንደሚቀረው፣ የምስክሮችና የባለሙያዎች ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ ከባለሥልጣኑ ማብራሪያ እንደሚጠይቅ፣ ውስን የኦዲት ምርመራ እንደሚቀረውና የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት እንደሚቀረው በማስረዳት፣ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዋ በጠበቃቸው አቶ አበበ አሳመረ አማካይነት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ እፈልጋቸዋለሁ የሚላቸው ሰነዶች በሙሉ በተቋሙ የሚገኙ ናቸው፡፡ ደንበኛቸው የተያዙት ከቀረጥ ነፃ የተፈቀዱ ዕቃዎችን ከተፈቀደላቸው በላይ እንዲያስገቡ ፈቅደዋል ተብለው መሆኑን አቶ አበበ አስታውሰው፣ ዕቃዎቹ ሲገቡ ዲክላራሲዮን የሚያዘጋጀው ባለሥልጣኑ መሆኑ እየታወቀ፣ መርማሪው ዲክላራሲዮን ሳይይዝ ደንበኛቸውን ማሰሩ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡፡
ተጠርጣሪዋ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል ጠርጥሯቸው ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ምርመራ ተደርጎባቸው ምንም ነገር ስላልተገኘባቸው በነፃ መሰናበታቸውንና ማረጋገጫ ሠርተፊኬት እንደተሰጣቸውም ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ተቋሙን ከለቀቁ አራት ዓመታት፣ ከኃላፊነት ከተነሱ ደግሞ ስድስት ዓመታት እንዳለፋቸውም አክለዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ፣ ተጠርጣሪዋ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና በምርመራ ነፃ የተባሉት በአሁኑ አሠራር ሳይሆን ቀድሞ በነበረው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆኑን አስረድቷል፡፡ አሁን ግን 10,697,648 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን አክሏል፡፡ የተያዙትም በወንጀል እንደሚፈለጉ አውቀው ከአገር ሊሸሹ ሲሉ መሆኑንም መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡ ምርመራ እየተጣራባቸው በመሆኑም የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዋ ፍርድ ቤቱ እንዲናገሩ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንደተናገሩት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታገዱት በ2005 ዓ.ም. ነው፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለአንድ ዓመት አጥንተው ከአሜሪካ ሲመለሱ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ አካሂዶባቸው ነፃ ሆነው በመገኘታቸው ሠርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የታገዱ ካርታ፣ የባንክ ደብተሮችና ሌሎች ንብረቶችም እንደተመለሱላቸው አስረድተዋል፡፡ አሁን የሚሠሩት ኢንቨስትመንት ላይ ከሚሠራ የአሜሪካ ድርጅት ጋር መሆኑንና የውጭ ባለሀብቶችን እያግባቡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመትም ለኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘታቸውንም አክለዋል፡፡
ተጠርጣሪዋ እንዴት እንደተያዙ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፣ አለቃቸውን ለአምስት ቀናት አስፈቅደው ዱባይ ደርሰው ለመመለስ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ሠራተኞች መያዛቸውንና ለፌዴራል ፖሊስ ተላልፈው መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ ትዳርም ሆነ ልጅ እንደሌላቸው በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ሳይሆን ሰባት ቀናት ለመጨረሻ ጊዜ መፍቀዱን አስታውቆ፣ ተጠርጣሪዋ የጠየቁትን ዋስትና እንዳልተቀበለው ነግሯቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡
Average Rating