www.maledatimes.com የነጉርሜሳ አያና ምስክሮች ለአራተኛ ቀን መደመጥ ቀጥሏል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የነጉርሜሳ አያና ምስክሮች ለአራተኛ ቀን መደመጥ ቀጥሏል

By   /   August 19, 2017  /   Comments Off on የነጉርሜሳ አያና ምስክሮች ለአራተኛ ቀን መደመጥ ቀጥሏል

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 45 Second

 

የነጉርሜሳ አያና ምስክሮች ለአራተኛ ቀን መደመጥ ቀጥሏል።(11/12/2009) በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ በዛሬው ቀጠሮ የሚሰሙት ምስክሮች ለ2ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያና 4ት ምስክሮች እንዲሁም ለ3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ የምትመሰክር 1 ምስክር ባጠቃላይ 5ት ምስክሮች የቀረቡ መሆናቸውን ጠበቆች ተናግረዋል።

በቅድሚያ ለ3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ የምትመሰክረው ተመላላሽ ሰራተኛው የነበረችው ወ/ት ፈለቁ ሃይሌ ፓሊሶች ለፍተሻ በመጡ ሰአት እቤት የነበረች መሆኑን እና በወቅቱ ያየችውን ነገር በተጨማሪም ከአቶ አዲሱ ቡላላ ቤት ያልተገኘ ነገር ተገኝቷል ብላ እንድትመሰክር ሲያስገድዷት አልመሰክርም በማለቷ 3ወር ከ15 ቀን ራስራ መውጣቷን እንደምትመሰክር ጠበቆች በጭብጥነት አሲዘዋል።

ምስክሯ ስሟ ፈለቁ ሃይሌ እንደምትባል፣ አዲሱ ቡላላ ቤት በተመላላሽ ሰራተኝነት እንደምትሰራ፣ ታህሳስ 14/2009 ቀን 9 ሰአት አካባቢ ወደ አዲሱ ቤት በምትሄድበት ጊዜ በሩ አካባቢ ፓሊሶች እንደነበሩ፣ ከምሽቱ 12 ሰአት አካባቢም አዲሱ በፓሊሶች ታጅቦ እንደመጣ ከዛ በኋላም ፓሊሶቹ እና ፈታሾቹ እቤት ገብተው እሷን እንዳስወጧት ነገር ግን ለበሩ አቅራቢያ የሆነ ቦታ ላይ ሆና ከውስጥ የነበረውን ነገር ስትከታተል እንደነበር ተናግራለች። “ይሄ ወረቀት ያንተ ነው በግድ ትፈርማለህ ሲሉት ሰምቻለሁ። እነሱ ያንተ ነው እሱ ደግሞ የኔ አይደለም ይላል። በመጨረሻ ላይም ጠርተውኝ የሆነ ባንዲራ ነገር መኝታ ቤት ከሚገኝ የማይፈልጋቸው ልብሶች ከሚቀመጡበት ሻንጣ ውስጥ ተገኝቶ ነው ስለማየትሽ ምስክርነትሽን ትሰጪያለሽ ሲሉኝ፤ ሻንጣውን በየጊዜው ስለማራግፍ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ነገር እዚህ ቤት አላቅም በማለቴ ከአዲሱ ጋር አብረው ማእከላዊ ወስደውኝ መስክሪ እያሉ ሲጨቀጭቁኝ ነበር፤ 3ወር ከ15 ቀን ታስሬያለሁ።” በማለት ምስክርነቷን ሰጥታለች። ታህሳስ 12/2008 ቀን ለመጨረሻ ጊዜ ሻንጣው ማራገፏን የተናገረችው ምስክሯ “ታህሳስ 13 እና 14 ቀን አዲሱ ባንዲራውን ያስቀምጥ አያስቀምጥ በምን ታውቂያለሽ?” ብሎ አቃቢ ህግ ሱጠይቃት፤ አዋራ ምታራግፍበትን ጨርቅ ሻንጣ ውስጥ ስለምታስቀምጥ እሱን ስታስገባ እና ስታስወጣ አዲስ ነገር ቢኖር ማየት ትችል እንደነበር ገልፃ ምስክርነቷን ጨርሳለች።

በመቀጠል 2ኛ ተከሳሽ የሆነው የደጀኔ ጣፋ ምስክሮች እንደሚሰሙ ጠበቆች ለችሎት በማሳወቅ በመጀመሪያ የደጀኔ ጣፋ ባለቤት ወ/ሮ አሰለፈች ቀርባ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች። “ታህሳስ 14/2008 7ሰዐት ላይ ለደጀኔ ጋር ልንገናኝ ቀጠሮ ነበረን። ከ7ት ሰአት ጀምሮ ስደውልለት ስልኩ አይነሳም። በመሃል ስልኩ ኪሱ ውስጥ ሆኖ ሲነካካ መሰለኝ ተነሳና ሰዎች ሲጨቃጨቁ ሰማሁ። ሰፈሩ አሸዋ ሜዳ ነው ሲሉም ነበር። ከዛ ለዶ/ር መረራ ደውዬ ስልኩ እንደማይነሳ ስነግራቸው ከቢሮ አካባቢ ፌደራሎች ወስደውታል የሚባል ነገር መስማታቸውን እና ወደ ቤት እንድሄድ ነገሩኝ። እኔም ለመረጋጋት እየሞከርኩ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እና ሁኔታውን መከታተል ስላለብኝ ቶሎ ብዬ ወደ ቤት ሄድኩ። ለትልቋ ልጄ ደውዬ ፓሊሶች ለፍተሻ እየመጡ መሆኑን ነግሬያት ቀድመውኝ ከደረሱ ሳይፈተሹ እቤት እንዳይገቡ አስጠነቀቅኳት። ቤታችን ኮንዶሚኒየም ውስጥ ነው። ወደ ግቢ ስደርስ 7ት በላይ መኪናዎች ቆመዋል። ስደር ሁለት ልጆቼ ከቤት አስወጥተዋቸው ትልቋ ልጄ፣ አንድ ጎረቤታችን፣ ደጀኔ እና ፈታሾቹን መኝታ ቤት አገኘኋቸው። ሳሎን ቤቱን ፈትሸው ጨርሰው ነበር ስደርስ። ቤቱ ጥግ ጥግ መሳሪያ ይዘው የቆሙ ወታደሮች አሉ። ሳሎን አካባቢ ሲቪል ለብሶ ባይንደር ነገር የያዘ አብሯቸው የመጣ ቁጭ ብሏል። ከአንድ ጎረቤታችን ውጪ አመጣን ያሉት ታዛቢ ማንነታቸው የማይታወቅ የሰፈራችን ሰዎች ያልሆኑ ናቸው። እኔ እቤት ከመድረሴ በፊት በኮንዴሚኒየሙ ለሚገኙ የቀበሌ ሰዎች እና ጥበቃዎች ወደ ቤቴ ሄደው እንዲታዘቡ ልኬ ነበረ። ነገር ግን እነሱን ራሱ በር አካባቢ የነበሩ ወታደሮች ደብድበዋቸዋል። ጥርሳቸውን አውልቀዋቸዋል። መጨረሻ ላይ ጨርሰናል ብለው የሚፈልጉትን ወስደው ወደሳሎን ስንገባ ትልቋ ልጄ ‘ይሄን ወረቀት ኬት አመጣኸው? የኛ አይደለም! ለምን ከቦርሳህ አውጥተህ ትሰጠዋለህ?!’ እያለች ከፓሊሶቹ ጋር ስትተናነቅ ደረስኩ። ምንድነው ብዬ ሳይ ሲቪል ለብሶ ሳሎን በር ላይ ቁጭ ብሎ የነበረው ሰውዬ ከባይንደሩ ያወጣውን ወረቀት ሊሰጠው ከነበረው ፓሊስ እና ልጄ ጋር ይጨቃጨቃሉ። ወረቀቱን ልየው ስላቸው አላሳይም አሉኝ። ከላዩ ላይ ግን የኦሮሚያ ካርታ፣ የኦነግ ባንዲራ የሚመስል ነገር አለበት። ‘ይሄን ነገር መቼም ከቤቴ አታገኝም‘ አልኩት። ፓሊሱ ልጄን እና እኔን ገፈተረን። ልጄ ላይ እግሯ ላይ ቆመባት። ‘እንዳቃጠላችሁን ትቃጠላላችሁ’ በማለት እነሱንም መኪና ውስጥ ውሰዷቸው ብሎ አዘዘ። ደጀኔም ይህን ሲያይ ‘በቃ ዝም በያቸው አንቺ ይሄ የተበላበት እቁብ ነው’ አለኝ። እኔም ‘ቤቴ ውስጥ ወንጀል ሲሰራ ዝም ብዬ አላይም’ የሚል ምላሽ ሰጠሁት። ‘እነሱን ተዋቸው እኔን ነው ልትይዙ የመጣችሁት’ ሲላቸው ነበር። ሰራዊት ሰው ቤት ገብቶ እንዲህ ሲያደርግ ሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ‘ትንሽ ፈሪሃ እ/ር የለም እንዴ?!’ ስል ጭራሽ ባሰባቸው። የእ/ርን ስም ስጠራ አንገበገባቸው። ብዙ ጭቅጭቅ ተፈጠረ። ከቤታችን ያልተገኙት ወረቀቶች ላይ አልፈርምም አለ። መጨረሻ ላይ ከቤቴ ያልተገኘ ብለህ ፈርም ብዬው እንደዛ ብሎ ፈረመ። ጎረቤታችን የነበረችው ሴትዮም ‘ምን ብዬ ነው ምፈርመው የሄ ወረቀት ሲገኝ አላየሁም’ ስትል፤ እሷም ከቤት ያልተገኘ ብላ እንድትፈርም ተደርጓል። ”

አቃቤ ህግ ወ/ሮ አሰለፈች የምስክርነት ቃሏን ከሰጠች በኋላ አቃቤ ህግ ለምን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳስፈለጋት እና ለምን ፍርሃት እንዳደረባት ጠይቋት ነበር። ወ/ሮ አሰለፈችም ” ከ1996 ጀምሮ ቤቴ ሲፈተሽ ነበር። በየጊዜው ነው ፍተሻ የሚመጡብን። የለመድነው ነገር ነው። በተጨማሪም ድሮ ግቢያችን ውስጥ ተማሪዎች ይኖሩ ስለነበር እነሱን ለማሰር ፍተሻ ሲደረግ አቃለሁ። እንዲያውም አንዱን ተማሪ ለማሰር ግቢዬ ውስጥ ቦንብ እራሳቸው አስቀምጠው አገኘን ያሉበት አጋጣሚም ነበር። እንዲያውም እናንተ እ/ር ይስጣችሁ ወረቀት ነው ያመጣችሁት።”

በሁለተኝነት እንድትመሰክር የተደረገችው የደጀኔ ጣፋ ልጅ ሲንቦ ደጀኔ ናት። ታህሳስ 14/2008 በቤታቸው ስለነበረ ነገር የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች። ” ሲምቦ ደጀኔ ጣፋ ነው ስሜ። 21 አመቴ ነው። ታህሳስ 14/2008 ከቀኑ 10:30 አካባቢ ፓሊሶች አባቴን ይዘውት መጡ። የፍ/ቤት ማዘዣ አምጡ ስላቸው እሱ ያውቃል አሉኝ። ሳትፈተሹ አትገቡም ስላቸው ‘ፓሊስ ቤት ሃገር ነው ሲፈተሽ የምታውቂው’ አሉኝ። ‘ደሞ ምን ይዛችሁ እንደምትመጡ ምን አቃለሁ’ ስላቸው አባቴ ‘በጉልበት ከሆነ ተያቸው ይግቡ’ አለኝ። ባይንደር የያዘ እና የላፕቶፕ ባግ የያዙ ሲቪል ለባሾች ነበሩ። ብዙ ፓሊሶች ከነመሳሪያቸው ገቡ። መኝታ ቤቱን ፈትሸው ጨርሰው የሚፈልጉትን ይዘው ወጡ። እኔ ሳሎን ነበርኩ። አንዱ ፓሊስ ፊትሽን ወደዛ አዙረሽ ኮምፒውተሩን ክፈቺ አለኝ። እሱ እንዳለኝ ከፍቼ ዞር ስል አንድ ሲቪል የለበሰ ሰውዬ በእጁ ከያዘው ቦርሳ ወረቀት አውጥቶ ለፓሊሱ ሊሰጠው ሲል አየሁት። ‘ምንድነው የሰጠኸው? እሱ ከኛ ቤት የተገኘ አይደለም’ እያልኩ ስጨቃጨቅ እናቴ ደረሰች። ወረቀቱን አሳየን ስለው አላሳይም ኦሮምኛ ነው የተፃፈው አለን። ኦሮምኛ እንደምንችል ብንነግረውም ሊያሳየን አልፈቀደም። ጭራሽ እኔንም እናቴንም ገፈተረን። ፓሊሱ አንገቴን አንቆ እግሬን ረገጦኝ ቆመ። ‘እኛም እንዲህ ነው የተቃጠልነው’ አለ። እናቴንም ይዟቿት ሂዱ መኪና ውስጥ ክተቷቸው አለ። ከዛም አባቴ ‘እኔን ነው ምትፈልጉት እሷን ተዋት ልጆቻችንን ታሳድግበት’ አላቸው። ”

በሶስተኝነት የመሰከረችው ወ/ሮ ነፃነት ሞገስ ትባላለች። ወ/ሮ ነፃነት ቄራ አካባቢ ትኖር እንደነበር እና በቅርብ ወደ አሸዋ ሜዳ አቶ ደጀኔ የሚኖሩበት ኮንዶሚኒየም እንደገባች ተናግራ ታህሳስ 14/2008 ቀን አቶ ደጀኔ ቤት በነበረው ፍተሻ ታዛቢ እንደነበረች በመግለፅ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች። “ታህሳስ 14/2008 ከቀኑ 10:30 ሰአት ይሆናል። ልጆቼን ላይ ወደ በር ወጥቼ በነበረ ሰአት አቶ ደጀኔ ጣፋን በፓሊሶች ተይዞ መጣ። ብዙ ፌደራሎች ነበሩ። ልጆቹን ወደቤት እንዳስገባ አዘዙኝ። ልጆቹን አስገብቼ በር ላይ ቆምኩ። ትልቋ ልጃቸው ፌደራሎቹን ሳትፈተሹ አትገቡም ብላ ገትራ ይዛ ነበር። ደጀኔም እኔ እንድታዘብ ትግባ ብሎ ሲጠይቃቸው አስገቡኝ። በብዙ ፌደራል ታጅበን ነው ፍተሻው የተካሄደው። የሳሎኑ ፍተሻ ቶሎ ነበር ያለቀው። መኝታ ቤት መአት ወረቀቶች እና መፅሃፍቶች አሉ። ፈታሾቹ የሚፈልጉትን እየመረጡ ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን አቶ ደጀኔ እንዲተረጉም እየጠየቁ እየተረጎመላቸው እና ሁላችንም እየፈረምንባቸው መሬት ያስቀምጧቸው ነበር። አጠቃላይ ፍተሻ ጨርሰን ወደ ሳሎን ስንገባ ልጅቷ ከፓሊሶች ጋር ትጨቃጨቅ ነበር። ሚስትየው ወ/ሮ አሰለፈችም እዛ ነበረች። ‘ወረቀቱ ከኛ ቤት አልተገኘም እንየው’ ሲሉ ነበር። እስከዚች ሰአት በሰላማዊ መንገድ ነበር ፍተሻው ሲከናወን የነበረው። ቤቱ ውስጥ ግርግር ተፈጠረ። ሚስትየዋንም ውሰዷት መኪና ውስጥ አስገቧት ሲሉ ነበር። ከዛ አቶ ደጀኔ ‘እሷን ተዋት ልጆቹን ታሳድግበት’ ሲላቸው ነበር። እኔ ቄራ ክ/ከተማ ነበር እኖር የነበረው። እንዲህ አይነት ሁከት እና ግርግር አይቼ አላውቅም። ወረቀቱን በፍተሻ ወቅት ሲገኝ ስለእውነት አላየሁም። ኬት እንዳመጡትም አላቅም። ፈርሚበት ሲሉኝ፤ ‘እኔ ይሄ ወረቀት ሲገኝ አላያሁም ምን ብዬ ነው ምፈርመው? ግራ ገባኝ’ ስላቸው፣ ከቤት ያልተገኘ ብለሽ ፈርሚ አሉኝ። እንደዛ ብዬ ፈረምኩ። ሌሎቹ ከቤት የተገኙት ወረቀቶች እና መፅሃፍቶች ላይ ግን ከቤት የተገኘ ብዬ ነው የፈረምኩት።” በማለት የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች።

አራተኛው ምስክር ከሶስቱ ምስክሮች የተለየ እንደማይመሰክር በመግለፅ ሳይመሰክር እንዲሰናበት ተደርጎ የእለቱ ችሎት ተጠናቆ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት በአዳሪ ቀጠሮ ተይዟል። ከማረሚያ ቤት ጋር በተያያዘ ይሰጣል የተባለው ትእዛዝም ስላልደረሰ በአዳሪ በተያዘው ቀጠሮ ትእዛዙ እንደሚገለፅ ተነግሮ ከማረሚያ ቤት የቀረቡ ሃላፊዎችም እንዲቀርቡ ተነግሯቸዋል።

 

ምንጭ: የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 7 years ago on August 19, 2017
  • By:
  • Last Modified: August 19, 2017 @ 8:58 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar