—
በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ መሄዱን በተመለከተ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እና ታዛቢዎች የሚያቀርቦቸው ትችቶች እና አሰተያየቶች እንደሚያመለክተው የጉዳዩ አሳሳቢነት ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ነው። በፍትሕ ሥርዓቱ በዋነኝነት ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ “የሐሰተኛ ምስክርነት” ነው። በተለይ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን አስመልክቶ በከሳሽ የዐቃቤ ሕግ የሚቀርቦት ምስክሮች፤ ምስክርነታቸው “ሐሰት” እንደሆነ በተከሳሾች በተደጋጋሚ እየተገለፀ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቂሊንጦ እስር ቤትን በማቃጠል፣ ንብረት ማውደምና የሰው ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ስር በተከሰሱ 38 ግለሰቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን፤ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሐሰተኛ መሆናቸውን አስመልክቶ “በመንግሥት እና በተቋም ደረጃ የሐሰት ምስክርነት” እየተሰጠብን ነው በማለት እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ አቤቱታ አቅርበው እንደነበር የሚታወስ ነው።በተከታታይ ቀናት ቀጥሎ የነበረው ምስክርነት በዛሬው እለት ተቋርጦ ለታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል ።ዐቃቤ ሕግ እስከዛሬ ያቀረባቸው ምስክሮች በቂሊንጦ እስር ቤት የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ቀሪ 33 ምስክሮች በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል ። ዐቃቤ ሕግ 85 ምስክሮች እንዳሉት ከዚህ በፊት ገልፆ እንደነበር የሚታወቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች እነ ጉርሜሳ አያኖ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው እለት አሰምተዋል ። በዚሁ ችሎት ወ/ሪት ንግስት ይርጋ በቤተሰቦቿ፣ በጠበቃ፣ በጓደኞች የሰዓት ገደብ ሳይደረግባት ማንኛዉም እስረኛ እንደሚጠየቀው እሷም እንድትጠየቅ በማለት ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ትእዛዘ ተፈፃሚ እንዳልሆነ አቤቱታ ብታቀርብም ፍ/ቤቱ አቤቱታ በጽሑፍ እንዲሆን ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ በዚሁ መዝገብ (በእነ ንግሥት ይርጋ) ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥቅምት 21 ቀን 2010 ተሰጥቷል ።
—
(ይድነቃቸው ከበደ)
Average Rating