የይድነቃቸው ተፅእኖ በአፍሪካ መድረክ
ትላንት በክፍል አንድ የታላቁን የእግርኳስ ሰው ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ህይወት ዳስሰን ነበር፡፡ በዛሬው ክፍል ደግሞ ይድነቃቸው በአፍሪካ መድረክ የሰሩትን ስራ እንዳስሳለን፡፡
ይድነቃቸው በእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወታቸው ለ23 ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ማሊያን አድርገው ተሰልፈዋል። ክለቡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም የውጪ ሃገር ክለብ ገጥሞ የአርመኑን አራራት ክለብ 2-0 ሲያሸንፍ አንዱን ግብ ከመረብ ያሳረፉትም ይድነቃቸው ነበሩ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1940 ዓ.ም. ከተቋቋመ በኋላም ለ15 ጨዋታዎች ሃገራቸውን ወክለው ተጫውተዋል።
የተጫዋችነት ህይወታቸው ከተፈፀመ በኋላም ይድነቃቸው ከእግርኳሱ አልራቁም ነበር። የተለያዩ የስፖርት መስሪያ ቤቶችን በሃላፊነት ደረጃ መምራት ከመቻላቸውም በላይ ሃገራችን ኢትዮጵያ በትልቅ ውድድር ላይ ያስመዘገበችውን ብቸኛ ዋንጫ በ1955ቱ የአፍሪካ ዋንጫ በዋና አሠልጣኝነት አሳክተዋል። ይድነቃቸው ተሰማ ለእግርኳሱ ያደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ግን በአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን አመራርነታቸው ሳይሆን አይቀርም።
ይድነቃቸው ከካፍ ፕሬዝዳንትነታቸው በፊት….
በ1936 ዓ.ም. ገና በ22 ዓመት እድሜያቸው የኢትዮጵያ ስፖርት ፅህፈት ቤትን በማቋቋም የተጀመረው የአመራር ጉዞዋቸው እስከ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንትነት እና እስከ የፊፋ ስራ አስፈፃሚ አባልነት ድረስ ዘልቋል።
የይድነቃቸው የአፍሪካ እግርኳስ ጉዞ ከቅኝ አገዛዝ፣ በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፓርታይድ ስርአት እንዲሁም አፍሪካ በአውሮፓውያን ቁጥጥር ስር በነበረው ፊፋ ተገቢው ቦታ እንዲሰጣት ከተደረገው ትግል ጋር ሰፊ ቁርኝት ያለው ነው።
በ1946 ዓ.ም. አራት የአፍሪካ ሃገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን እና ደቡብ አፍሪካ) ለመጀመሪያ ጊዜ በፊፋ ጠቅላላ ጉባዔ በታዛቢነት ተሳተፉ። አፍሪካውያኑም በፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተወካይ ለማግኘት እና የራሳቸውን ኮንፌዴሬሽን ለማቋቋም ጥያቄ አቀረቡ። ይህ ጥያቄያቸው በመጀመሪያ በአውሮፓውያኑ የፊፋ አመራሮች ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ደቡብ አፍሪካዊው ፀሃፊ ዴቪድ ጎልድብላት ‘The Ball is Round’ በሚለው መፅሃፉ “አፍሪካውያኑ ያቀረቡት ጥያቄ በአውሮፓውያን የበላይነት ሲመራ በነበረው ፊፋ ውድቅ ተደርጎ ነበር። ለዚህ አውሮፓውያኑ የሰጡት ምክንያትም ከግልፅ ዘረኝነት የመነጨ ነበር፤” በማለት አስፍሯል።
ነገር ግን አፍሪካ ከሶቭየት ህብረት እና ተከታዮቿ እንዲሁም ከደቡብ አሜሪካ ሃገራት ድጋፍ አገኘች። በፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ተወካይ ለማግኘት ቻለች። ግብፃዊው ኢንጂነር አብዱላዚዝ አብደላህ ሳሌም የአፍሪካ የመጀመሪያው ተወካይ ነበሩ። አፍሪካ የራሷን የእግርኳስ ኮንፌዴሬሽን እንድታቋቁምም ፊፋ ፈቃዱን ሰጠ።
የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በ1950 ዓ.ም. ሲቋቋም ገና የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወታቸው ያላበቃው ይድነቃቸው፣ ጄነራል አማን አንዶም እና ገበየሁ ደበሌ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ነበሩ። የካፋ መመሪያ ጥራዝ ሲዘጋጅም ዋነኛ ሃሳብ አቅራቢዎች ይድነቃቸው እና የሱዳኑ አብደልራሂም ሻዳድ ነበሩ። ኢንጂነር ሳሊም የካፍ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት ሆነው ሲመረጡ ይድነነቃቸውም የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመረጡ።
ከመስራች ሃገራቱ አንዷ ደቡብ አፍሪካ በወቅቱ 2 የእግርኳስ ፌዴሬሽኖች ነበሯት። አንዱ በነጮች የሚመራ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጥቁሮችን ጨምሮ ሌላ ዘር ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ ነበር። ይህ በግልፅ እየተሰራበት የነበረው ዘረኝነት ግን ለይድነቃቸው ተሰማ የሚዋጥ አልሆነም። ሱዳናዊው ዶ/ር አብደልሃሊም መሃመድ በ1979 ዓ.ም. ለካፍ መፅሄት በሰጡት ቃለምልልስ ይድነቃቸው በዚህ ጉዳይ የነበራቸውን አቋም እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፤
“ደቡብ አፍሪካውያን በዘር በተከፋፈለ አሠራራቸው ለ4 ዓመታት ሲጠቀሙ ማንም ተቃውሞውን ያሰማ አካል አልነበረም። ይድነቃቸው የካፍ ስራ አመራር ከሆነ በኋላ ግን ይህንን ፍፁም እንደማይቀበለው አስታወቀ። በስብሰባዎች ላይም ደቡብ አፍሪካ ነጮችንም ጥቁሮችንም ያካተተ ቡድን ካልመረጠች ከካፍ መታገድ እንደሚኖርባት አጥብቆ ተከራከረ።”
በ1954 ዓ.ም. ካፍ ደቡብ አፍሪካን ከአባል ሀገርነት በማገድ የመጀመሪያው ስፖርታዊ ተቋም ሆነ። በወቅቱ አፓርታይድ በፊፋም ሆነ በዓለም ዓቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቀባይነት ነበረው። እነዚህ ትልቅ የስፖርት ተቋማትም የካፍን ውሳኔ “ፖለቲካንና ስፖርትን የሚቀላቅል” በሚል አጣጥለውት ነበር። ፊፋም በአፋጣኝ ደቡብ አፍሪካ ወደ ካፍ አባልነቷ እንድትመለስ የሚል ቀጭን መመሪያ አስተላለፈ። ወጣቱ ኮንፌዴሬሽን ግን የፊፋን ሃሳብ እንደማይቀበለው አስታውቆ አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ አባልነቷም ጭምር እንድትታገድ መታገል ጀመረ።
ሶስቱ የካፍ መስራች አባላት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ አባልነቷ ካልታገደች ራሳቸውን ከማህበሩ እንደሚያገልሉ አስታወቁ። የፊፋ ፕሬዘዳንት የነበሩት እንግሊዛዊ አርተር ድሬውሪም የአፍሪካን አቋም ለመገምገም ተስማሙ። ነገር ግን አዲስ የተመረጡት የፊፋ ፕሬዘዳንት ስታንሊ ሮውስ የአፍሪካውያኑን ሃሳብ ውድቅ አደረጉት።
ይድነቃቸው የካፍ ዋና ፅህፈት ቤትን ወደ አዲስ አበባ ለማዞር ጥረት ያደርጉ ነበር። በተለይ ጋና እና ቱኒዚያ ኮንፌዴሬሽኑን ከተቀላቀሉ በኋላ ድጋፋቸውን አገኛለሁ በማለት ጉዳዩ ለጠቅላላ ጉባዔው እንዲቀርብ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ግብፃዊው የካፍ ፕሬዘዳንት አብደላዚዝ ሙስጣፋ በምርጫው ያሳደሩት ተፅዕኖ እና ግብፅ ለካፍ ታደርግ የነበረው የፋይናንስ ድጋፍ የይድነቃቸው ሃሳብ እንዳይሳካ ያደረጉ ዋና ምክኒያቶች ናቸው።
በ1956 ዓ.ም. ካይሮ ላይ በተደረገው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ 23 አባል ፌዴሬሽኖች ተሳታፊ ነበሩ፤ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ተቃርኖ ውስጥ ገብተው የነበሩት የፊፋ ፕሬዘዳንት ስታንሊ ሮውስም በተጋባዥነት ተገኝተዋል። በዚህ ስብሰባም ይድነቃቸው ተሰማ የካፍ ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነው ተሾሙ። ይድነቃቸው በዚህ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ካከናወኗቸው ነገሮች ግንባር ቀደሙ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና መጀመር ነው።
በ1957 ዓ.ም. በጃፓን ቶክዮ በተደረገው የፊፋ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ጋና በህብረት አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከአባልነት እንድትታገድ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄውም ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቶ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ ውጪ እንድትሆን ተደረገ። የወቅቱ የፊፋ ፕሬዘዳንት ስታንሊ ሮውስ ደቡብ አፍሪካን ወደ ፊፋ ለመመለስ ያደረጉት በርካታ ሙከራዎች ሳይሳኩላቸው ቀርተዋል። ስታንሊ ሮውስ በፊፋ ዕውቅና ያለው እና ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪሸስ፣ ቦትስዋና፣ ርሆዴሲያ፣ ማዳጋስካር እና ማላዊን በአባልነት የያዘ የደቡባዊ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ለመመስረት በሚስጥር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ መረጃ የደረሳቸው የካፍ አመራሮች የ1959ኙን የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ረግጠው እንደሚወጡ ማሳወቃቸው ዕቅዱ እንዳይሳካ አድርጎታል።
በተመሳሳይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ርሆዴሲያ (የአሁኗ ዚምባቡዌ) ከፊፋ እንድትወገድ ይድነቃቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በ1962 በሜክሲኮ የተደረገው የፊፋ ጉባዔ ላይም ከተፈሪ በንቲ ጋር በጋራ የህግ መዝገብ በማዘጋጀት እና መዝገቡ ለአባል ሃገራት እንዲቀርብ በማድረግ ርሆዴሲያ ከፊፋ እንድታገድ አድርገዋል።
በፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የካፍ ተወካይ የነበረው ጋናዊው ኦሄኔ ድጃን በሃገሩ በተከሰተው መፈንቅለ መንግስት ምክኒያት ከጋና እንዳይወጣ ማዕቀብ ተጣለበት። ድጃንን በመተካት የፊፋ ስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሆን ይድነቃቸው ተሰማ ተመረጠ። ይድነቃቸው ይህን ቁልፍ ሃላፊነት የተረከበው በወሳኝ ሰዓት ላይ ነበር። በፊፋ ጠቅላላ ጉባዔ የሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ እያንዳንዱ አባል ሀገር አንድ ድምፅ አለው። የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት እየተላቀቁ መምጣት እና የካፍ አባል ሃገራት ቁጥር መጨመርም ለአውሮፓውያኑ የፊፋ መሪዎች ራስ ምታት ነበር።
በ1950ዎቹ መጨረሻ 30 አባል ሃገራት የነበሩት ካፍ በዓለም ዋንጫው ግን ግማሽ ኮታ ብቻ ነበረው። የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ እና የእስያ ዋንጫ አሸናፊ እርስበርስ ተጫውተው ከሁለቱ ያሸነፈው ቡድን ብቻ ዓለም ዋንጫውን ይቀላቀል ነበር። የማጣሪያ ሂደቱ ርዝመት፣ ከፍተኛ ወጪ እና የማለፍ የተመናመነ ተስፋ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በማጣሪያው እንዳይሳተፉ አደረጋቸው። የፊፋ አመራሮችም ይህንን ተጠቅመው የአፍሪካ ሃገራት ያላቸውን ድምፅ ብዛት ለመቀነስ ተንቀሳቀሱ፤ “በሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ወይም የኦሎምፒክ ማጣሪያዎች ላይ ያልተሳተፈ ፌዴሬሽን በፊፋ ስብሰባዎች ላይ የመምረጥ መብት የለውም የሚል ሃሳብ ያለው ህግም ማርቀቅ ጀመሩ።”
በዚህ ወቅት ነበር ይድነቃቸው ተሰማ እና የአፍሪካ እግርኳስ መሪዎች በጋናው ፕሬዘዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ድጋፍ ራሳቸውን ከ1959ኙ የእንግሊዝ ዓለም ዋንጫ ያገለሉት፤ በቀጣይ የዓለም ዋንጫዎችም ለአፍሪካ አንድ ሙሉ ኮታ ካልተሰጣት በቀር እንደማይሳተፉ ገለፁ። ፊፋ በመጀመሪያ የአፍሪካ ፌዴሬሽኖች ይህንን በማድረጋቸው እያንዳንዳቸው 5000 ፍራንክ ቅጣት እንዲከፍሉ ትእዛዝ ቢያስተላልፍም በመጨረሻ በጉዳዩ በመስማማት ለአፍሪካ አንድ የዓለም ዋንጫ ኮታ መደበ። ሞሮኮም በ1963ቱ የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሃገር ሆነች።
በዚህ የፊፋ ውሳኔ በርካታ አውሮፓውያን ደስተኛ አልነበሩም። እስከ አሁን ድረስ ለወርልድ ሶከር መፅሄት የሚፅፈው እንግሊዛዊ ፀሃፊ ብራያን ግላንቪል በወቅቱ የነበረውን ስሜት እንዲህ ሲል ገልፆ ነበር፤
“እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ውስጥ ያለው እግርኳስ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እንደሚነቃቃ ግልፅ ነው። ነገር ግን የነዚህ ሀገራት በዓለም ዋንጫው መሳተፍ የውድድሩን ዋጋ የሚያረክስ እና ደረጃውን የሚቀንስ ነው። ውድድሩ የዓለማችን እግርኳስ ትልቁ መድረክ እንደመሆኑ ይህ መፈቀድ የለበትም።”
Average Rating