ይድነቃቸው በካፍ ፕሬዘዳንትነት
በ1965ቱ የያዉንዴ ጠቅላላ ጉባዔ ይድነቃቸው የሱዳኑን ዶ/ር አብዱልሃሊም መሃመድ 15 ለ 12 በሆነ የድምፅ ብልጫ በማሸነፍ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ሆነው ተመረጡ። ምንም እንኳን በምርጫው በአስተባባሪነት የሰሩት የወቅቱ የፊፋ ፕሬዘዳንት ስታንሊ ሮውስ ለዶ/ር አብዱልሃሊም ድጋፋቸውን ቢገልፁም ይድነቃቸው ይህንን በመቋቋም ምርጫውን አሸንፈዋል። በካፍ ፕሬዘዳንትነት በሰሩባቸው 15 ዓመታት የተፈጠሩት ለውጦች በብዙዎች አስተሳሰብ እስካሁን ካየናቸው የአፍሪካ እግርኳስ መሪዎች ሁሉ የበለጠ ስኬታማ አድርጓቸዋል።
በይድነቃቸው የካፍ አመራር ስር በርካታ ፈር ቀዳጅ ስራዎች ተከናውነዋል። የመጀመሪያው የአፍሪካ የወጣቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ የዋንጫ አሸናፊ ክለቦች ውድድር (የአሁኑ የኮንፌዴሬሽኖች ዋንጫ) በይድነቃቸው ጠንሳሽነት የተጀመሩ ውድድሮች ናቸው። የካፍ ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ በ1974ቱ የሊቢያ የአፍሪካ ዋንጫ የቴሌቪዥን እና ስርጭት መብት ታይቶ በማይታወቅ ትርፍ ለመሸጥ ተችሏል።
ይድነቃቸው የአፍሪካ እግርኳስ በዓለም ያለውን ስፍራ ለማሳደግም በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል። ለዚህ አላማቸው ቁልፍ መሳሪያ አድርገው የተጠቀሙት ደግሞ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ኮንፌዴሬሽኖች መሃል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነበር። በብራዚል የነፃነት ድል ማክበሪያ ውድድር ላይ ከአፍሪካ ሃገራት የተወጣጣ ቡድን እንዲሳተፍ ማድረጋቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ብራዚላዊው ጆ ሃቫላንጅ እንግሊዛዊውን ስታንሊ ሮውስ በማሸነፍ የፊፋ ፕሬዘዳንት ሲሆን የይድነቃቸው ሚና ቀላል አልነበረም። በተለይ መጪውን የፊፋ ምርጫ እንደመሳሪያ በመጠቀም አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ አዘጋጅታው ከነበረ ዓለም ዓቀፍ የእግርኳስ ውድድር ብራዚል ራሷን እንድታገል ያደረጉበት ሂደት የሚረሳ አይደለም። እንግሊዛዊው የወቅቱ የፊፋ ፕሬዘዳንት ስታንሊ ሮውስ በፃፈው ደብዳቤ ሁኔታውን እንዲህ መዝግቦታል፤
“ከታማኝ ምንጮች እንደሰማሁት ከሆነ ብራዚላውያኑ ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉት የአፍሪካው ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ይድነቃቸው ተሰማ ብራዚል በውድድሩ ከተሳተፈች ጆ ሃቫላንጅ ከእኔ ጋር ለፊፋ ፕሬዘዳንትነት በሚያደርገው ፉክክር የአፍሪካን ድምፅ እንደሚያጣ ገልፆ ስላስፈራራው ነው።”
ፖል ዳርቢ Africa, football, and FIFA: Politics, Colonialism and Resistance በሚለው አስደናቂ መፅሃፉ የይድነቃቸውን ዘዴ እንዲህ ሲል ነበር ያብራራው፤
“ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካን ድጋፍ እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ ጆ ሃቫላንጅን ማስፈራራት መቻሉ ካፍ በራስ መተማመኑ ማደጉን እና ያለው ትልቅ የአባላት ቁጥር የሰጠውን የመምረጥ ሃይል መጠቀም መጀመሩን ያሳያል። ከዚህ የ1974ቱ (እ.ኤ.አ) የፊፋ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ አፍሪካውያኑ በስልጣን ቅርምት ውስጥ ያሉ ተመልካቾች ሳይሆኑ ራሳቸውን የስልጣኑ ባለቤቶች አድርገው እንዲመለከቱ በር ከፍቶላቸዋል።”
በዚሁ የፊፋ ስብሰባ ይድነቃቸው ያቀረቡት እግርኳሱ ከዘር፣ ቀለም እና ሃይማኖት መድልዎ ነፃ እንደሆንና ይህን ያልተገበረ ማንኛውም ሀገር ከአባልነቱ እንዲሰረዝ የሚጠይቀው ህግ እንዲፀድቅ ተደርጓል። ይህም አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ በፊፋ ከተጣለባት ቅጣት እንድትመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ እንደ ስታንሊ ሮውስ ያሉ ሰዎችን ተስፋ መና አስቀርቷል። ከ2 ዓመታትም በኋላ በጆ ሃቫላንጅ አመራር ስር ደቡብ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ ከፊፋ ታግዳለች።
በ1971 ዓ.ም. አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ያላት ኮታ እንዲጨምር ጥያቄዋን አቀረበች። ጥያቄውም በአብዛኛው የፊፋ አባላት ተቀባይነት በማግኘቱ ከ1974ቱ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ የአፍሪካ ኮታ ወደ 2 እንዲያድግ ተፈቅዷል፡፡
የይድነቃቸው ተሰማ ልጅ የሆኑትና ታሪካቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማሳወቅ ጥረት የሚያደርጉት አቶ ታደለ ይድነቃቸው የጆአኦ ሀቫላንጅን ከዚህ አለም በሞት መለየት አስመልክቶ በፃፉት ፅሁፍ ስለ ይድነቃቸው እና ሀቫላንጅ ግንኙነት ይህንን ብለው ነበር፡፡
” ሃቨላንጅ ከይድነቃቸው ጋር በርካታ ዓመታት በፊፋና በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሲሠሩ በብዙ የዓለም ስፖርት ጉዳዮች ላይ አይስማሙም ነበር፡፡ በተለይ አፍሪካ በፊፋ ዓለም ዋንጫ ሊኖራት በሚገባ የውክልና ቁጥርና ከፊፋ ገንዘብ ሊኖራት በሚገባ ድርሻ ላይ ተወዛግበዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሃቨላንጅ እኤአ በ1978 አክራ – ጋና በተደረገ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጉባኤ ላይ አባላቱን አሳድመው ይድነቃቸውን ከኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት ለማውረድና ከጭቅጭቅ ለመገላገል ሞክረው ነበር፡፡ ይህ ሙከራ ባይሳካላቸውም ይድነቃቸው የአፍሪካ ተወካይ ሆኖ ፊፋ ሥራ አስፈጻሚ እንዳይገባባቸው ማድረግ ችለዋል፡፡ ስለዚህም በእርሳቸው ዘመን የፊፋ ሥራ አስፈጻሚ አባል መሆን ያልቻለ ብቸኛ የኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ይድነቃቸው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ሁለቱም ላለመስማማት መስማማት የሚችሉ ሥልጡን ጓደኛሞች ስለነበሩ ይድነቃቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ በሚስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ አብረው ሠርተዋል፡፡ ሃቨላንጅን እጅግ የማደንቃቸው በታሪክ ላይ የማይዋሹ ሰው ስለነበሩ ነው፡፡ ይድነቃቸው በሞት ከተለየ በኋላ ሊጎዳቸውም ሊጠቅማቸውም እንደማይችል እያወቁ ቀደም ሲል የነበሯቸውን አለመግባባቶች ሁሉ ወደጎን ትተው ባገኙት መድረክ ሁሉ ለሥራዎቹ እውነተኛ ምሥክርነት ይሰጡ ነበር፡፡
” ይድነቃቸውና ሀቨላንጅ የማይስማሙባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ቀደም ባለ ጽሁፍ ገልጫለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ምንም አልሠሩም ማለት አይደለም፡፡ እኤአ በ1976 በአዲስ አበባ የተጀመረውን የሥልጠና ፕሮጀክት በሁሉም የአፍሪካ ዞኖች በፊፋ ገንዘብ አጠናክረው በተከታታይ በማስቀጠል በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ዳኞች፣ አሠልጣኞች፣ የእግር ኳስ አስተዳደር፣ ሕክምና ወዘተ ባለሙያዎች አሠልጥነዋል፡፡ በዋናው ጉዳይ ማለትም በአፍሪካ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ላይ በቁጥር አነሰ በዛ ይጋጩ እንጂ አፍሪካ ሃቨላንጅ ከመምጣታቸው ከአራት ዓመታት በፊት በብዙ ትግል ያገኘችው ከ16 ተካፋዮች አንድ ቦታ ለማሳደግ እኤአ በ1980 የፊፋ አፍሪካ መመካከሪያ ዓመታዊ መድረክ ፈጥረው እኤአ በ1982 ከ24 ተካፋዮች ሁለት ቦታ እንድታገኝ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የነበሩትን ጭማሪዎች ይድነቃቸው ባያያቸውም ሃቨላንጅ ቃላቸውን ጠብቀው እኤአ ለ1994 ዓለም ዋንጫ ከ24 ሦስት ቦታ ሰጥተዋል፡፡ ለ1998 ከ32 ተካፋዮች አምስት ቦታ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ እንደ ቀላል መታየት የለባቸውም፡፡ በተለይ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ የዛሬው የኢትዮጵያ ቡድን ከ10 የአፍሪካ ቡድኖች አንዱ ሆኖ ለ2014 ብራዚል የመጨረሻ ማጣሪያ ለመጫወት የበቃው በዚህ ጥረት በተገኘ የቁጥር ጭማሪ ነው፡፡ ”
ለአፍሪካ እግርኳስ የይድነቃቸውን ያህል ዋጋ የከፈሉ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ይድነቃቸው ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ እግርኳስ እንዳደረጉት አስተዋፅኦ መጠን በእግርኳስ የታሪክ መዝገብ የተሰጣቸው ስፍራ እጅግ ያንስባቸዋል። እኛም ከአፍሪካ አልፎ በዓለም እግርኳስ ላይ ተፅእኖ መፍጠር የሚችል መሪ ከምድራችን ዳግም እስኪነሳ በተስፋ እንጠብቃለን።
Average Rating