www.maledatimes.com ዲሞክራሲያዊ /የመድብለ ፓርቲ/ማስመሰል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ዲሞክራሲያዊ /የመድብለ ፓርቲ/ማስመሰል

By   /   October 27, 2012  /   Comments Off on ዲሞክራሲያዊ /የመድብለ ፓርቲ/ማስመሰል

    Print       Email
0 0
Read Time:23 Minute, 16 Second

በዳዊት ታደሰ – የአዲስ ታይምስ

አዶልፍሂትለር ወደመንበረ ዙፋኑ ከወጣ በኋላ አውሮፓ እረፍትና እንቅልፍ ካጣች አመታት ተቆጠሩ፡፡  በዚህ ሰው ቀጭን ትእዛዝ የተላኩ ነፍጠኞች በደረሱበት ሁሉ እልቂት ትርፋቸው ሆነ፡፡ ህጻን-አዋቂ፤ ወንድ-ሴት ሳይለዩ በክፋት በተገራው አይምሮና በታዛዣቸው አፈሙዝ ብቻ እያሰቡ ህዝቡን ጨፈጨፉት፡፡  ገላጋዮች አርፍደው በደረሱበት በሁለተኛው የአለም ጦርነትም የሀገራት ድንበር ያለምንም ስስት በእነዚህ ወታደሮች ተጣሱ፤ ሂትለርና ጓዶቹ አለምን የፈጣሪ ያህል አዘዙባት፡፡ እስካልደረሰብን ምን ያገባናል ሲሉ የነበሩት ሀያላንም በመጀመሪያ ደንታቢስነትን ቢያሳዩም የኋላኋላ በሌሎች ላይ የተመዘዘው ሰይፍ ለነሱም እንደማይመለስ ሲገባቸው ማውገዝ ጀመሩ፡፡  በመጨረሻ ግን ወደ እልህ አስጨራሹ ጦርነት በጋራ ተቀላቅለው የናዚን ስርአት ታሪክ አደረጉት፡፡  የሆነው ሁሉ ከሆነ በኋላ ከሞት የተረፉ ቁንጮ አመራሮች ለፍርድ ቀርበው ህግ ስለጥፋታቸው ተጠያቂ አደረጋቸው፡፡

ይህ ከሆነ ከሁለት አመት በኋላ ካርል ጃስፐርስ የተባለ ጀርመናዊ ፈላስፋ የመሪዎቹን ያህል ተመሪው ህዝብም የሞራል ተጠያቂ የሚሆንበትን ፅንሰ-ሀሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡  በሰው ልጆች ላይ ለተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ተመሪው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡  ቅጥ ያጣውን የሂትለርን አምባገነንነት በደንታቢስነትና በዝምታ ድጋፍ ሲሰጡ ለነበሩት ጀርመናዊያን የህግ ባይሆንም የሞራል ፍርድ እንደሚገባቸው ፈላስፋው ሞገተ፡፡  በስርአቱ ተገደውም ይሁን በጸጋ ተቀብለው መንግስቱን አበረታተዋል ያላቸውን ጀርመናውያንን በሙሉ ከሞራል ተጠያቂነት እንደማያመልጡ የመከረበት ስራው አለምአቀፍ እውቅናን አላብሶታል፡፡

ለእንዲህ አይነቶቹ የህሊና ፍርደኞች መቀጫው ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ግን መልስ ያላገኘ ጥያቄ እንደሆነ እስካሁን አለ፡፡  አረመኔ መንግስታትን ያበቀለ ማህበረሰብ፤ ጭካኔ ስጋ ለብሶና አይን አውጥቶ ገዢ ሲሆን እያየ አፉን ለጉሞ ያበረታታ ምን ቢቀጣ ስህተቱን ላይደግመው ይችላል? እራሱን እየጎዳ ገዳዮቹን የሚያፋፋስ በምን አይነት መንገድ ከተበዳዮች ጋር ገበታ ሊቀርብ ይገባዋል? የሂትለር ቡድን አለምን ወደአዘቅት ሲሸኛት በአካል ያየው ጀርመናዊ ግን ገዢዎቹን “ኸረ በህግ” ብሎ ቢያስቆም ኖሮ ይሄ ሁሉ ተቀጥላ ስም ባልወጣለ ትነበር፡፡

ከብሔር ልዩነት ይልቅ ጥልቅ ድህነት አንድ ያደረገን እኛ ኢትዮጵያውያን በገዢዎቻችን ፊረማ ለደረሰው፤ እየደረሰ ላለውና ሊደርስ ካለው ጣጣ ከተጠያቂነት ለመዳን ምን እያደረግን እና ለሀገራዊ መከራውስ ምላሽ እንዲሆን የሰራነውስ በቂ ነው ወይንስ ይቀረዋል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡  ሁልጊዜም ቢሆን ተጨማሪ ተከታዮችን እንጂ አዳዲስ መሪ ሀሳቦችንና ግለሰቦችን ለማፍራት ዝግጁ ያልሆነ ስርአት ለሁለት አስርታት ራሱን ሲያደራጅ እንደነበር መናገር የረፈደበት ትርክት ነው የሚሆነው፡፡  የደንታቢስነታችንን መርገምት ሰብረን ያገባኛል ልንል ስንል አገዛዙ ሊቀፈድደን በራችን ላይ እንዳለ ያስማማናል፡፡  እነሱም ፍጹም “ሰላም” ብለው የሚያሞካሹት “መረጋጋት” በዚህ ተግባራቸው የመጣ ነው፡፡  ሰልፋችንን በሰይፎቻቸው እንደሚበትኑም ታሪክ አሳይቶናል፡፡  ስህተት አና ወንጀል እየተሰራ እያዩ በዝምታ ማለፍ ያልቻሉት ቀዳሚዎቻችንም ዕጣፈንታቸው እስርና ሞት ነበር፡፡  ህልሞቻችን በግዴለሽነት ንፋስ እንደጉም ተበትነዋል፤ መማራችንም መከራችንን የሚያባብስ ሆኗል፡፡  መጪው ትውልድ ለመውጣት ወደሚከብድ የክህደት መቃብር እየተገፋ እንደሆነም ታዝበናል፡፡  ክፉ ግለሰቦች በአምላካዊ ክብር ሲሸለሙም እንድናይ ገዢዎች አስገድደውናል ለነዚህ ሁሉ ሀገራዊ ኪሳራዎች መቆጠር ጥቂቶች የህግ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ራሳቸው ጥቂቶቹም ያውቁታል፡፡  እኛም አብዛኞቹ ከሚመጣው ትውልድ “ይሄ ሁሊ ሲሆን የት ነበራችሁ?” ስንባል መልስ ለመስጠት እና ከሞራል ተጠያቂነት ለማምለጥ ሳይረፍድብን ሰውን ከሌላው እንዲለይ ወዳደረገው ማንነታችን ተመልሰን መጠየቅ ለነገው የማንተወው የቤት ስራችን ነው፡፡

ኤሊ ቪይሰል የተባለ ከኦሽዊትዝ ማጎሪያ ቅጥር የተረፈ አይሁዳዊ ደንታቢስነትን “በብርሃንና ጨለማ፤ በአመሻሽና ንጋት፤ በወንጀልና ቅጣት፤ በጭካኔና ርህራሄ፤ በክፉና ደግ መካከል ያሉ መስመሮች የደበዘዙበት እንግዳ እና ኢ-ተፈጥሮአዊ ኑባሬ ነው” ይለዋል፡፡  አለም በዙሪያችን እንዲህ ስትታመስ እንደው የውስጥ ሰላምን ላለማጣት ያህል፤ መደበኛ ኑሮን ለመኖር ያህል፤ መልካም ምግብና የወይን ጠጅ ለማጣጣም ያህል ደንታቢስነትን መተግበር ግድ ነው ወይ? ብሎም ጠይቆ ነበር፡፡ የደንታቢስነት መጨረሻው የሰዋዊ ስሜት መሰለብና በዙሪያችን ለሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ምላሽ አልባ መሆን ነው፡፡  ነጋዴው ትርፍ ከመሰብሰብ ውጪ ለሌሎች ሰዋዊ እሴቶች ግድ የማይሰጠው ከሆነና የማህበረሰቡ/የደንበኞቹ/ ሰብአዊነት በመንግስት አካላት ሲጣስ እያየ እንዳላየ ካለፈ ለገቢው ዘላቂነት መተማመኛው ምኑ ላይ ነው? ተማሪውስ “ትምህርቴን ጨርሼ…” ከሚለው መቋመጥ ባሻገር መፍትሄ የሚፈልጉ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውዥንብሮችን ይስተካከልልኝ ብሎ ተፈጥሮአዊ መብቱን ባለመጠየቁ ምክንያት ብቻ የጓጓለትን ስራ ሲያጣው ከራሱ ውጪ ማንንም ተጠያቂ ለማድረግ የተሟላ ብቃት ሊኖረው አይችልም፡፡  ህይወት አቋራጭ መንገድ የላትም፡፡  ሊወገዱ ሲገባቸው ዘለን ያመለጥናቸው እንቅፋቶች ከኋላ ለሚከተሉን መሰናክሎች ናቸው፡፡  ጋዜጠኛውም ቢሆን ሀገር ስትፈርስ ተመልክቶ እንደ ሙያው “ሀገሪቷን አፈረሷት” ከሚለው ሀተታ በኋላ እንደዜጋ ሀገሪቷን ለመታደግ ቢንጠራራ ዛሬ ለደረስንበት የሞራል ክስረት ላይ ባልተዘፈቅን ነበር፡፡  ምሁሩስ! እድሜውን ሁሉ ለእውቀት የባከነው ልጆቹ በሰላም እንዲያድጉ ሲል ለገዢዎች  ሎሌ ለመሆን ነው?  በችጋር እየረገፈ ላስተማረው ህዝብስ ምላሹ ለመከራው ጀርባውን መስጠት ነውን?  ለዚህ እንዳልሆነ ራሱም ያውቀዋል፡፡  ብንወደውም ብንጠላውም ግን መሃል መንገድ ላይ ቆማ ወዴት ልሂድ ለምትለው ሀገር ፖለቲካዊ ህይወት ቀጣይነት ሁላችንም ተጠያቂዎች ከመሆን አንድንም፡፡  በተጨቆነ ማህበረሰብ መካከል እየኖሩ ግድ የለሽ መሆን ጨቋኞችን የበለጠ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡  የዜጎች ደንታቢስነት ሲስፋፋ ማህበረሰባዊ ድንዛዜን ይፈጥራል፡፡ ይህ ደግሞ ራስን ለበረታ አምባገነንነት አመቻችቶ መስጠት ይሆናል፡፡  የደነዘዘ ማህበረሰብ ለመብቶቹ እንዴት ይገደዋል?

የአምባገነን ስርአት ለዲሞክራሲና ለመቻቻል ጊዜም ቦታም የለውም፡፡  ለማውራት እንጂ ለማዳመጥ ትሁት አይደለም፡፡  ለመዳንም ለማዳንም፤ ለማመንም ለማሳመንም አልበሰለም፡፡  እውቀት ጠላቱ ነው፡፡  ችሎት የኖረውን ህዝብ ማዋረድና ክብር ማሳጣት የተለምዶ ተግባሩ ነው፡፡  በወንበሩ ላይ የመቆየቱ ሚስጥር ከማህበረሰባዊ በጎ ፈቃደኝነት የተቸረው መሆኑን አያስተውልም፡፡  ከመወደድ ይልቅ ለመፈራት ይቸኩላል፡፡  ይሄ እንዲሆንለት ደግሞ ያፍናል፤ ያስራል፤ ያፈናቅላል፤ ይገድላል፡፡  በአለማችን መጨቆን ብቸኛ የስልጣን መቆያ መፍትሔ የመሰላቸው መንግስታት ይሄንን ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡  ግዴለሽ ተገዢዎች ግን ከጀርባቸው ነበሩ፡፡  ባይስማማንም እኛም የዚህን መሰል ስርአት በጫንቃችን ደግፈን በእኛው ላይ እንዲሰለጥን ፈቅደንለታል፡፡  የጋምቤላ ነዋሪዎች መግቢያ ሲጠፋቸው፤ የኦጋዴን ሰዎች ሲሰቃዩ፤ የጉራፈርዳ አርሶ አደሮች ሲፈናቀሉና የኦሮሚያ ወጣቶች እስር ቤት መታጎራቸውን እየሰማን የተቀረነው ግን አሁንም በአርምሞ ውስጥ ነን፡፡  ሙስሊም ወዳጆቻችን መብቶቻቸውን ስለጠየቁ ሲታፈኑና በገፍ ሲታሰሩ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ስለምን የአያገባኝም ደንታቢስነታችን ውስጥ ተሸሸግን?  እርምጃው ትክክል ነበር ብለን ተስማምተን ይሆን? ነው ወይንስ ጉዳያችን አይደለም ብለን? ገዢዎቻችንስ ቢሆኑ በአለቃቸው በአቶ መለስ ሞት የነሱን ያህል (ምናልባትም  ከነርሱ በላይ) ያዘንን እንድንመስል ሲያስገድዱን ለአኝዋክ ብላቴኖችም ሆነ በአዋሳ ጎዳናዎች ላይ ላለቁ የሲዳማ ወንድሞቻችን እንዳናለቅስ ለምን ከለከሉን? ሆን ብለው ከሚኮረኩሙን ብዙ ባንጠብቅም ከመከራ አቻዎቻችን ግን ሰብአዊነትን የተላበሰ የመቆርቆር ስሜት እንጂ ደንታቢስነትን አንጠብቅም፡፡  የፍትህ ጋዜጣና ባልደረቦች ለፕሬስ ነጻነትና ለዲሞክራሲያዊ ህላዊነት እንዲያ ሲዋትቱ ለደረሰባቸው እንግልት የሌሎች ጋዜጦች ቸልተኝነትስ ከአፋኞች ጋር መተባበርን አያመለክትም?

የተቃውሞ ኃይል ጎራዎችም ዜጎች የመከራ አጣብቂኝ ውስጥ መሆናቸውን ሲያውቁ “እንቃወማለን” ከሚለው የተለምዶ መግለጫ /መፈክር/ ባሻገር ባሉት ሰላማዊ ግፊቶች መንግስትን ከክፋት መንገዱ እንዲመለስ ያላስቻሉት በዚሁ በደንታቢስነት አባዜ ካልሆነ በቀር በሌላ በምን ሊሆን ይችላል?  በጠንካራ መሰረት ላይ ሆነን እየሰራን ነው የሚሉን ፓርቲዎች የሀገሪቱ ህግና ነባራዊ ሁኔታዎች የተቃርኖ እንቅስቃሴዎችን እንደማይኮንኑ እያወቁ ባለመጠቀማቸው ብቻ ስርአቱን ዲሞክራሲያዊ /የመድብለ ፓርቲ/ በማስመሰል ላበረከቱት አስተዋፅኦ ኃላፊነታቸውን ከሁሉ አደገኛ ያደርገዋል፡፡  አመራሮቻቸው በማይገባ ምክንያት ሲታሰሩ በአደባባይ ወጥቶ እስከመጮህ የሚደርስ ህጋዊ ፈቃድ የተቸራቸው ቢሆንም አጥጋቢ ያልሆኑ ሰበቦችን በመደርደር ለሚያሳዩት ቸልተኝነት ግን የሞራል ተጠያቂነትን ሸክም በግላቸው ይወስዱታል፡፡  በህይወት ስለመኖራቸው ማሳያ የሚሆነው ከዚህ ድንዛዜ በመንቃት የእውቀትና የጥበብ መስመሮችን ለመከተል ሲሞክሩ ብቻ ነው፡፡

መልካም ስማችንንና ታሪካችንን ከግድፈት ለመታደግ ከግል ምልከታችን ፈቅ ማለት ጊዜው ያስቀመጠልን ዕዳ ነው፡፡  አንድን ህጻን በውሃ ከመስጠም ለማዳን እጃችንን መዘርጋት ብቻ በቂ እኮ ነው፡፡  ምነው ከህጻኑ ነፍስ ይልቅ ለልብሳችን በውሃ መበስበስ አሰብን?

በቪየትናም ጦርነት ወቅት የተከሰተው የማይ ላይ ጭፍጨፋ የወቅቱ ተጠቃሽ ክስተት ነው፡፡  በዘመኑ የአሜሪካን ወታደሮች መረን ባጣ ቅጣት ሴትና ህጻናትን ሳይለዩ ይረሽኑ ነበር፡፡  ኸግ ቶምሰን የተባለ አሜሪካዊ የሄሊኮፕተር አብራሪ ግዳጅ ተሰጥቶት ቅኝት ላይ እያለ አሰቃቂውን ኩነት ተመለከተ፡፡  ወዲያውም በገዳይ ጓዶቹ እና በተገዳይ ንጹሐን መካከል ሄሊኮፕተሯን አሳርፎ መሀል ሜዳው ላይ በመቆም “ወይ እኔ ላይ ተኩሱ ወይንም እነሱ ላይ መተኮስ አቁሙ” በማለት እጆቹን ወደ ላይ ዘረጋ፡፡ ከመቅጽበት ግድያው ቆመ፡፡  ቶምሰን አደጋው የማይደርስበት ቢሆንም ሌሎችን ለመታደግ ሲል በራሱ ህይወት ቆመረ፡፡  ለሀገሩና ለዜጎቹ ደህንነት ቢያስብም ሰብአዊነት ግን ወደ ንጹሐን አደላ፡፡  የእርሱ አይነት ጥቂቶች በጦሩ ወስጥ ቢኖሩ ኖሮ የቪየትናም ጦርነት ለታላቋ አሜሪካ በደም የተጻፈ ታሪክ ግድፈት ባልሆነ ነበር፡፡  የማይ ላይ ታሪክ የትም ሊፈጠር ይችላል፡፡  መልኩ ይቀየር እንጂ እኛም ጋር በእለት ተእለት ኑሯችን የምናስተውለው ነው፡፡  ታዲያ ይህን መሰሉን ክስተት እየተመለከትን ምላሻችን ምንድን ሆነ? አስቀድሞ ስለመብቶቻቸው የጠየቁ ዜጎችን በግድያ፤ በእስርና በስደት ከአደባበዩ የሚያርቅ የዚህ አይነቱ ስርአት በመጨረሻም የአፈና እጆቹን ስለሌሎች መከራ ደንታቢስ ወደነበሩት ያዞራል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 27, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 27, 2012 @ 6:58 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar