ኑሯቸውን በተለያዩ የውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ የህወሓት እጅ ውስጥ እየገባ እንዳልሆነ አንድ መረጃ አመለከተ፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረገው ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ተቋም፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሚልኩት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 78 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ፣ በህገ ወጥ መንገዶች እንደሚገባ አስታውቋል፡፡ ይህ የገንዘብ አላላክ ዘዴ ከህወሓት ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ለተመታው የህወሓት ኢኮኖሚ ሌላ ፈተና እየሆነ መምጣቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ማለትም ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ አብዛኛው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ከህወሓት ቁጥጥር ውጭ በሆኑ መንገዶች በመሆኑ፣ የህወሓት መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ እየገጠመው እንደሚገኝ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በበዓላት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ ቁጥሩ ከፍተኛ ቢሆንም፣ በቀጥተኛ የባንክ አገልግሎት የሚላከው ገንዘብ ግን እጅግ የተመናመነ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንደ ዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ተቋም መረጃ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው በአሜሪካ፣ በጣልያን እና በእንግሊዝ ካሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆን፣ ሆኖም መንግስት አብዛኛውን የውጭ ምንዛሬ ወደ ካዝናው ገቢ እያደረገ አይደለም፡፡ ከተጠቀሱት ሀገራት ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገራቸው የሚልኩት በአረብ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዛሬ ዓመት አካባቢ በመላው ኢትዮጵያ ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የህወሓትን አገዛዝ ለማዳከም ሲባል፣ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በቀጥታ በባንክ እንዳይልኩ ጥሪ መተላለፉ ይታወሳል፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት የህወሓት አገዛዝ ከኢኮኖሚ ድቅት እና ከመሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ተመናምኗል፡፡
BBN News August 24, 2017
Average Rating