ይልቅ ወሬ ልንገራችሁ
ታሪካዊው የአቡነ ጴጥሮስ ሬዲዮ ጣቢያ ስለመፍረሱ
ቅ ፅ 16 ቁጥር 310 ነሀ ሴ 2009
መቼም አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ አጠገብ የሚገኘውን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ህንፃ ታውቀዋለህ አይደል? ህንፃው ታሪካዊ ንግግሮችና የህዝብ መልዕክቶች የተላለፉበት የሬዲዮ ጣቢያ እንደነበር መቼም አትዘነጋውም፤ ምን ምን? ምነው የአፄ ኃይለስላሴ ከስልጣን መውረድ የተነገረው በዚሁ ጣቢያ ስቱዲዮ ነበር፤ ሌላስ? ሌላውማ ያው የግንቦት 20 ቀን 1983 የደርግ መንግስት መፍረስ የተነገረው በዚሁ ስቱዲዮ ውስጥ ነበር፡፡
ከስልሳ ኣመታት በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቸኛ የሬዲዮ ድምጽ ሆኖ ያገለገለውና በርካታ አንጋፋ ጋዜጠኞች አሻራቸውን ያሳረፉበት ይህ ስቱዲዮ ዛሬ በህይውት የሌሉ ታላላቅ ሰዎች ድምፅ የተቀረፀበትና ታሪካዊ ሁነቶች የተቀረፀበት ህንጻ ነው፡፡
እናስ? እናማ ይህ ታሪካዊ ሬዲዮ ጣቢያ ከ15 ዓመታት በፊት ለአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቶ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ት/ቤት ሆኖ ነበር፡፡ እናስ? እና ሰሞኑን የአዲስ አባ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ስምንት ዓመታት ‹ሳስጠና ቆየሁ› ባለው እቅድ መሠረት 800 ሚሊዮን ብር በጀት ይዞ ታሪካዊውን ህንፃና ስቱዲዮ በማፍረስ አዲስ ህንፃ ልገነባበት ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ለመሆኑ ይህ ታሪካዊ ህንፃ በቅርስነት ተመዝግቦ ቢቀመጥ ለታሪክም ሆነ ለገብኝዎች ፋይዳ እንዳለው ለዩኒቨርሲቲው የነገረው የለም ወይ አልክ? ያለ አለ፤ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሬዲዮ ጣቢያውን ‹አፍርሼ አዲስ ህንፃ ልገነባበት ነው› ሲል ጆሮው ላይ ተኝቶ ህንፃው ታሪካዊ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን የሚያጣራ አንድ ኮሚቴ አቋቁሚያለሁ ስለማለቱ ተነተግሯል፡፡
እርግጥ ነው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዩኒቨርሲቲው ህንፃውን እንዳያፈርስ የሚጠይቅ ደብዳቤ ልኮለት ነበር፡፡ እናስ? እና ዩኒቨርሲቲው ለደብዳቤው ምን የሚል ምላሽ የሰጠ መሰለህ? ‹አንድ ህንጻ ካረጀ መፍረስ አለበት፤ይህ ህንፃ መፍረስ የለበትም የሚል አስተሳሰብ ካለ ግን ለሚሰራው ልማት እንቅፋት መሆን ነው› ስለማለቱ አዲስ አመን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ለመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ራሱ ስለ አንድ ቅርስ ምንነት ጠፍቶት ነው ወይ ይህንን ያለው አልክ? እሱ አልጠፋውም፤ የጉዳዩ አወዛጋቢነት ታይቶ የመጨረሻ አቤቱታ ለማቅረብ ጉዳዩ የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ጋር ቀርቦ ነበር ተብሏል፡፡
እናስ? እሳቸው ምን አሉ? እንዳይፈርድ ወሰኑ ወይስ? አትድከም ወዳጄ፤ ፕሮፌሰሩ ጉዳዩን በተመለከተ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ አይነት ምላሽ ነው የሰጡት፤ ምን አሉ መሰለህ? ‹ የህንፃውን ታሪካዊነት ለማስታወስ ዘመኑ በሚፈቅደው መንገድ በቪዲዮና በፎቶ መረጃ እንዲያዝ ተደርጎ ከኮንትራክተሩ ጋር ውል ተፈፅሞ ወደ ስራ ተገብቷል›
ለመሆኑ እኝህ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በቅርቡ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል አልተባለም እንዴ አልክ? አንድ ወዳጄ ምን አለ መሰለህ? ‹ልክ ነው አምባሳደር ሆነዋል እንኳንም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ሀላፊ አልሆኑ› በል ቻዎ…
Average Rating