source Horn affair
በዘንድሮው ዓመት በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር መከሰቱ ይታወቃል። የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል። በዚህ አጋጣሚ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በዜጎች ላይ የአካል ጉዳት፣ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት ደርሷል። በመሆኑም፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚከተሉትን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ያሻል፡፡
1ኛ፡- ነፃ ምርጫ በማካሄድ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ፣
2ኛ፡- ገለልተኛ የምርጫ አካሄድ መዘርጋት፣
3ኛ፡- ለታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ምህረት ማድረግና የፖሊቲካ እስረኞችን መፍታት፣
4ኛ፡- የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ማሻሻል፣
5ኛ፡- የፕሬስና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን ማረጋገጥ፣
6ኛ፡- በየአከባቢው ከፖለቲካ ነፃ የሆነ አደረጃጀትና አስተዳደር ለመዘርጋት፣
7ኛ፡- በኃላፊነትና በመግባባት ላይ የተመሰረተ የፓርቲ ፖለቲካ፣ እና
8ኛ፡- በማህበራዊ ግንኙነት ረገድ ያሉ ግድፈቶች በማስወገድ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር ማስቻል።
ከላይ የቀረቡት ስምንት ነጥቦች ዛሬ ላይ በኢትዮጲያ ላለው ችግር ትክክለኛ መፍትሄዎች ቢሆንም እኛ ግን ለእንደዚህ ዓይነት የሰለጠነ ፖለቲካዊ መፍትሄ አልታደልንም። ይህ “June 29 Proposal” በመባል የሚታወቀው የመፍትሄ ሃሳብ የቀረበው እ.አ.አ. ሰኔ 29/ 1987 ዓ.ም በደቡብ ኮሪያው ገዢ ፓርቲ “Democratic Justice Party” ዋና ሊቀመንበር በነበሩት “Roh Tae Woo” ነበር። በእርግጥ በወቅቱ ደቡብ ኮሪያ የገጠማት ችግር አሁን ኢትዮጲያ ከገጣማት ችግር ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነበር። ከተወሰነ የአውድ ልዩነት በስተቀር የመፍትሄ ሃሳቡም ተመሳሳይ እንደሆነ በፅሁፉ መጨረሻ ካለው እንግሊዘኛ ቅጂ ጋር ማመሣከር ይቻላል።
ከግዜና ቦታ በስተቀር በደቡብ ኮሪያ እና በኢትዮጲያ የተነሳው ጥያቄ ልዩነት የለውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ልማታዊ መንግስትና የ3ኛው ምዕራፍ መንታ መንገድ በሚል ርዕስ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቼበታለሁ። ስለዚህ፣ በዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረቴ በልማታዊ ዴሞክራሲ አቅጣጫን በሚከተሉት ሁለቱ ፓርቲዎች ለተመሳሳይ ችግር ባቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ይሆናል። ከላይ የተጠቀሱትን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ በማድረጉ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲያዊነት፣ ሀገሪቱን ከታዳጊነት ወደ የበለፀጉ ሀገራት ተርታ አሸጋግሯታል። ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ውስጥ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ግን ራሱንና ሀገሪቷ ለባሰ ውድቀት የሚዳርግ ነው፡-
“… በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ …. መላ የአገራችን ህዝቦች …በዚህ ወቅት በድርጅትና በመንግስት አካላት ዘንድ የታየው ይህ ስህተት ተስፋቸውን እንዳያጨልመው ያደረጉትን ትግል ከታላቅ አክብሮት ጋር ይመለከተዋል። …እነሆ ዛሬ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሰረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግስትና በድርጅት ማዕቀፍ እንደሚታይ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቦ ይህንኑ ለማስተካከል የሚያስችል እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡”
በመሰረቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግምገማ ውጤት፡- የችግሩ መንስዔና መፍትሄ ፍፁም ስህተት ነው። ሕዝቡ ላደረገው ትግል “ታላቅ አክብሮት” እንዳለው መግለፁም ቢሆን “የአዞ እምባ” ነው። ምክንያቱም፣ አሁን ሀገሪቷ ያጋጠሟት ችግሮች መሰረታዊ መንስዔና መፍትሄ ከላይ በፅሁፉ መጀመሪያ ላይ በተጠቀሱት ስምንት ነጥቦች ያለው ነው። ስለዚህ፣ ያለ ምንም መዛነፍ፣ በእነዚህ ስምንት ነጥቦች ላይ ተገቢው ምላሽ እስካልተሰጠ ድረስ ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ ይሄዳል። ምክንያቱም፣ “ልማታዊ መንግስትና የ3ኛው ምዕራፍ መንታ መንገድ”በሚለው ፅሁፌ በዝርዝር ለማብራራት እንደሞከርኩት፣ እ.አ.አ. በ1987 ዓ.ም በደቡብ ኮሪያ የነበረውና ዛሬ ላይ በኢትዮጲያ እየታየ ያለው የሕዝብ እንቅስቃሴ መነሻውና መድረሻው መዋቅራዊ ለውጥ (structural change) ነው።
በእርግጥ ላለፉት ስምንት ወራት ተከታታይ ፅሁፎችን በማውጣት የኢህአዴግ መንግስትን ስመክርና ስተች ነበር። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፤ “የአብዮት እና የዴሞክራሲ ትውልድ ግጭት” የተቃውሞ እንቅስቃሴው የተወሰኑ ቡድኖች ጥያቄ ሳይሆን የትውልድ ጥያቄ እንደሆነ፣ “ኢህአዴግና ፅንፈኞች፡- ባሉበት የቆሙና ባለፈው የቆዘሙ” በሚል ርዕስ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ከአዲሱ ትውልድ ጋር አብሮ መሄድ እንደተሳነው፤ “ኢህአዴግ፡ አፍን ይዞ ከኋላ መጫን ለማፈንዳት” የ2007ቱን ምርጫ ውጤት አመፅ ቀስቃሽ እንደሆነ፤ “ኢህአዴግ፡ ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ”፣ ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ እና አርሶ-አደርን ከመሬቱ ከማስነሳት ይልቅ ማጠጋጋት” በሚሉት ፅሁፎች ደግሞ ኢህአዴግ ከሕዝቡ ለሚነሱ የመብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄቆች ምላሽ መስጠት እንደተሳነው፤ “ሕገ-መንግስታዊ ፅንፈኝነት በኢትዮጲያ” በሕገ-መንግስት ስም የዜጎችን መብትና ነፃነት እየጣሰ እንደሆነ፤“ኢህአዴግና የሰይጣን ጠበቆች እናከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ፡ ክፍል-3 የአሸባሪዎች ሕግ” የፕሬስና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት፤ ኢህአዴግ አሸነፈም ተሸነፈም ለውጥ አይመጣምእና የደሞወዝ እድገት ቀርቶብኝ የአካዳሚክ ነፃነቴን ስጡኝ” የማህበራት አደረጃጀትና የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ከገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ስር ነፃ እንዲወጣ፣…ወዘተ።
ልክ እንደ እኔ ኢህአዴግን ብዙ ሰዎች መክረውታል። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ያወጣውን መግለጫ ስመለከት ግን የእኔም ሆነ የሌሎች ሰዎች ምክር ውሃ እንደበላው ነው ተሰማኝ። መጀመሪያ ላይ ችግሩ ሲነገረው ሳይቀበል ይቆይና፣ የብዙ ሰው ሕይወትና ንብረት ከጠፋ በኋላ ልክ እንደ ሰሞኑ፤ “ጥፋቱ የእኔ መሆኑን ተቀብዬለሁ” ብሎ መግለጫ ይሰጣል። “ከዘገየም በኋላ ቢሆን ጥፋትህን መቀበልህ ጥሩ፣ መፍትሄው ደግሞ ይኸውልህ…” ሲባል ደግሞ አይሰማም። በራሱ መፍትሄ ነው ያለው ነገር ሌላ ስህተት ይሆንና፣ እንደገና የብዙ ሰው ሕይወትና ንብረት ከጠፋ በኋላ፣ “በመጀመሪያ የወሰድኩት የመፍትሄ እርምጃ በጥናት ላይ የተመሰረተ አልነበረም” ይላል። እንዲህ እያለ፣ በስህተቱ ላይ ሌላ ስህተት እየደገመ ሀገሪቷን ለከፋ ውድቀት ሊዳርጋት ተቃርቧል። “ይኼ ምን የሚሉት አባዜ ነው?” እያልኩ ሳስብ የሚከተለው ውይይት ትዝ አለኝ።
“ጃንሆይ ሩሲያን ለመጎብኘት ሲሄዱ አብሬ ሄጄ ነበር፡፡ ከዚያም በባቡር ከሌኒንግራድ ወደ ሞስኮ ከተማ ለመሔድ ብዙ ሰዓት የፈጀ ጉዞ በማድረግ ላይ እንዳለን ጃንሆይን ብቻቸውን በቂ ጊዜ አግኝቼ ያነጋገርኩበት መልካም አጋጣሚ ስለነበር፤ በአገራችን በአስተዳደር፣ በፍርድ፣ በምጣኔ ሀብትና በመሬት ስሪቱ ያለውን ብልሽትና ባለስልጣኖች በጠቅላላው በህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን በደል በሠፊው ዘርዝሬ ገለጽኩላቸው፡፡
ከዚያም ይህ ሁኔታ ቶሎ መግቻ ካልተደረገበት የጉዳቱ ብዛት ይህ ነው የማይባል እልቂት የሚያመጣ፣ የብዙ ሰው ህይወት የሚያጠፋ፣ ብዙ ደም የሚያፋስስ፣ ንብረት የሚያወድም፣ የግርማዊነቶን ታሪክ የሚያጎድፍና የዘውድ አስተዳደር ቀጣይነት ገትቶ ለውጥ የሚያመጣ ብርቱ እንቅስቃሴ ስለሚያስነሳ፤ ግርማዊነቶ ይህን ሥርዓት አንስቶ ሥልጣኑን ለአልጋ ወራሹ ሰጥቶ ግርማዊነቶ ከኋላ ሆኖ በመምከርና በመቆጣጠር፣ እንደ እንግሊዝና ጃፓን ያለ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት በኢትዮጵያ ቢዘረጋ፤ ዘውዳዊውን ሥርዓት የሚያስቀጥልና ኢትዮጵያን ከጥፋት በማዳን ስምዎ፣ ክብርዎና ታሪክዎ እንደተወደደና እንደተከበረ ለዘላለም እንዲኖር የሚረዳ ነው፡፡ እንዲህ ቢያደርጉ ኢትዮጵያን ከመከራና ከብጥብጥ ያድኗታል ብዬ ንግግሬን ሳቆም፤
ዝም ብለው ቆይተው ‘አይ ! አይ! ወርቅነህ! እኔ የበሰልክ ይመስለኝ ነበር፤ ለካስ ልጅ ነህ! ከልጅ ጋር ነው የምንሰራው! እግዚአብሔር የሰጠንን ሥልጣን እስካለን እንሰራበታለን፡፡ ከዚያ በኀላ እሱ እንደፈለገ ያድርጋት፡፡ ለመሆኑ ማን ስልጣኑን ለሌላ አሳልፎ የሰጠ አይተሀል?’ አሉኝ፡፡” – (ብርሃኑ አስረስ – የታህሳሱ ግርግርና መዘዙ፡ ገጽ 145)
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የኮ/ል ወርቅነህ ገበየሁን ምክር ስላልሰሙ፤ በመጀመሪያ እንደ ጄ/ል መንግስቱ ነዋይ ያለ ቀባሪ መጣባቸውና ለትንሽ ተረፉ። ብዙም ሳይቆዩ ግን ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም መጥቶ ቀበራቸው። መንግስቱ ኃይለማሪያም ስልጣኑን እንደ ተቆጣጠረ በዙሪያው እንደ ኢህአፓና ሚኢሶን ያሉ መከሪዎች ነበሩት። በኋላ ላይ ኢህአፓ በጥይት ሊቀብረው መሞከሩን ተከትሎ በሀገሪቱ ያሉትን የተማሩ ሰዎች ለሞት፣ ለስደት፣ ለጦርነትና ለእስር-ቤት በመዳረግ ሀገሪቷን ምሁር-አልባ አደረጋት። ከእነዚህ ውስጥ በሕይወት የተረፉት በወቅቱ ቀድመው የትጥቅ ትግል የጀመሩት እና ከሀገር የተሰደዱት ወጣቶች ብቻ ነበሩ። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከታህሳሱ ግርግር በኋላ እንዳደረጉት፣ ደርግም በቀይ-ሽብር ወቅት መካሪዎቹን ገድሎና አስሮ ሲጨርስ ኢህአዴግ ሊቀብረው መጣ።
ከኢህአዴግ በፊት የነበሩት ዘውዳዊው አገዛዝና ደርግ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ለፖለቲካ ልሂቃን (Political Elites) ያላቸው ጥላቻ ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ የዳበረ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመገንባቱ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን የማይተካ ሚና አላቸው። ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ልሂቃን ባሉበት ሀገር በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የጋራ ዕውቀት (shared knowledge) እና ሀገራዊ መግባባት ይዳብራል። ቀይ-ሽብር በመንግስት እና ሕዝብ መካከል ያለው የመተማመን መንፈስ (social contract) እንዳይኖር አደረገው። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ላይ የፍርሃት ድባብ በማስፈን በጋራ ጉዳዮች ላይ ግልፅ የውይይት የማድረግ ባህልን ሙሉ-ለሙሉ አጠፋው።
የተማሩ ልጆቿን ለሞት፣ ለስደት፣ ለጦርነትና ለእስር-ቤት በመዳረግ ኢትዮጲያን የወላድ መሃን ያደረጋትን ደርግ ያስወገደው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣ ሁለተኛ ዓመት ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው? ከደርግ ጭፍጨፋና እስር የተረፉትን ከ40 በላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ከሥራ በማባረር መካሪዎቹን ማጥፋት ጀመረ። የኢህአዴግን መንግስት ሲተቹትና ሲቃወሙት የነበሩትን ቀስ-በቀስ ለእስርና ስደት ሲዳርግ ከከረመ በኋላ በ1997 ዓ.ም ቅንጅት የሚባል ቀባሪ መጣበት። እንደ አፄ ኃይለስላሴ እና መንግስቱ ኃይለማሪያም የመጀመሪያውን ሙከራ እንደ ምንም ተንገዳግዶ ተረፈ። ከዚያ በኋላ፣ እሱን የሚቃወም ፖለቲከኛ እና የሚተች ጋዜጠኞች አንድ በአንድ ለእስርና ስደት ከዳረገ በኋላ፣ ይኼው ዛሬ ላይ ኢህአዴግ ቢጠሩት አይሰማ፣ ቢመክሩት አይለማ። መካሪዎቹን አባሮና አስሮ ቀባሪዎቹን እየጠበቀ ነው። እንደው በቃ ግን ሁሉም የኢትዮጲያ መንግስታት ቀባሪ እንጂ መካሪ አይሹም?
አባሪ፡- June 29 Proposal
“(1) the peaceful transition of government through a direct presidential election based on new constitution; (2) fair election procedures; (3) amnesty of a popular opposition leader Kim Dae•Jung and the restoration of his rights and the release of political prisoners; (4) enhancement of human rights; (5) freedom of speech and press; (6) formation of local assembly and democratization of university administration; (7) responsible and harmonious party politics; (8) social purification for a healthy society.” Hankuk Daily Newspaper. special issue. June 29, 1987.
ማጣቀሻዎች
* Abbink, J. (1995), The Impact of Violence: the Ethiopian ‘Red terror’ as a social phenomenon.
* Ethiopian Red Terror Documentation and Research Center: A Brief History of The Ethiopian Terror
Average Rating