እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ የተጣለባት ኤርትራ፣ ማዕቀቡን በመጣሷ ምክንያት ምክር ቤቱ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ሊልክ መሆኑ ታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ በተደጋጋሚ ጊዜ እየጣሰች መሆኑን ኢትዮጵያ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ ጊዜ ስታጋልጥ ቆይታለች፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ሊልክ መሆኑን ደግሞ ምንጮች ለሪፖርተር አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ የኤርትራን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ይፋ መሆኑንና በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤትን ለአንድ ወር ፕሬዚዳንትነት እንደምታገኝ አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡ ከመስከረም ወር ጀምሮ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ከግብፅ እንደምትረከብ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ በተለምዶ ኒውዮርክ ይካሄድ የነበረው ስብሰባም ከጳጉሜን 2 እስከ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ ቋሚና ተለዋጭ አባል አገሮች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካና የተመድ የምክክር ስብሰባ ኢትዮጵያ የሁለቱን ምክር ቤቶች ሰብሳቢ እንደምትሆንም አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባዔ የአፍሪካ ኅብረትና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የጋራ ውይይት እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፣ 15 የምክር ቤቱ አባላት በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር እንደሚገናኙም ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ ኃላፊነቷን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በፕሬዚዳንትነቷ ወቅት ሁለት ዓበይት ፕሮግራሞችን እንደምትመራ የተገለጸ ሲሆን፣ እነሱም ከጳጉሜን 2 እስከ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በኒውዮርክ የሚካሄዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚካሄደው ስብሰባ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በቻድ ሐይቅ አካባቢ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለዓለም የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች፣ በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ መካከል ስላለው ትብብር ምክክር እንደሚደረግ አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡
መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በኒውዮርክ የሚደረገውን ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንደሚመሩት፣ ስብሰባው በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮና በቀጣይ መከናወን በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ጠቁመዋል፡፡
ስብሰባው በአዲስ አበባ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ብዙ ጥቅሞችን ልታገኝ እንደምትችል አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ማሳደግና አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ማረጋገጥ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏንም አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔዎችን ማስፈጸም፣ የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለመፍታት ኢጋድ ስለሚያደርጋቸው ጥረቶች የፀጥታው ምክር ቤት ጠንካራ ድጋፍ እንዲኖረው መደረጉ፣ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ድጋፍ እንዲጠናከር፣ የሰላም ማስከበር ሥራ ማስገንዘብና የሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት ዕልባት ሊያገኝ የሚችለው በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ማስረዳት መቻሏን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሦስተኛ ጊዜ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗ ይታወሳል፡፡
Average Rating