በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበባት ኮሌጅ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት በተደጋጋሚ በዳይሬክተርነት ያገለገሉት የትራምፔቱ መምህር ሰሎሞን፣ የትምህርት ቤቱን ሥርዓተ ትምህርት በየጊዜው ከሌሎች መምህራን ጋር በመመርመርና ዕድገቱን ጠብቆ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ በኩላቸውን ሚና መጫወታቸው ይወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ይዘት፣ ዕድገትና ደረጃ እንዲኖረው ካላቸው ዓላማ አኳያ በመነሳት ሁለት የሲምፎኒ አርኬስትራ ሙዚቃዎችን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅኝት ላይ የተመሠረቱ ደርሰው በማቀነባበር፣ በቀድሞው የሶቪየት ኅብረት የሙዚቃ ደራስያን ማኅበር ሥራቸው ተገምግሞ ብቃቱ በመረጋገጡ፣ ‹‹የካቲት›› የተባለው የሲምፎኒ ሙዚቃ ድርሰታቸው በሶቪየት ኅብረት የዓለም አቀፍ ሙዚቃ ማኅበር ኮንፍራንስ ላይ በታላቁ የሲምፎኒ ኦርኬስትራ እንዲጫወትላቸው ተደርጎ አድናቆትን ማግኘቱ ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በአገር ውስጥም የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሲምፎኒ ኦርኬስትራ በትምህርት ቤቱና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በየጊዜው ያቀረቡ ሲሆን በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ተዘጋጅተው በነበሩ ታላላቅ የሙዚቃ ዝግጅቶች ውስጥም የሳቸው አሻራ አለበት፡፡ በደራሲነትና በሙዚቃ አቀነባባሪነት ከሌሎች ሙያተኞች ጋር በጋራና በተናጠል የተሳተፉባቸው ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት የሚፈጁ ሙዚቃዊ ድራማዎች፣ ማይም ዳንሶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከእነዚህም እንደ ‹‹ደማችን››፣ ‹‹በኮሚኒስቶች አንድነት››፣ ‹‹ዶግዓሊ›› እና ሌሎችም በወቅቱ ከፍተኛና ተወዳዳሪ የሌላቸው የሙዚቃ ድርሰት ሥራዎች እንደነበሩ ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
አቶ ሰሎሞን ሉሉ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ማኅበር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ኮሚቴዎችም ተመድበው ለሙያው ዕድገትና የሙያተኛውን መብት ለማስከበር የጎላ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡
ከእናታቸው ከወ/ሮ አሰገደች በላቸውና ከአባታቸው ከአቶ ሉሉ ምትኩ በቀድሞው አጠራር በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ሐረር ከተማ በ1939 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ሰሎሞን፣ የመጀመርያ ደረጃን በተወለዱበት ከተማና በአዲስ አበባ መድኃኔ ዓለም ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን በዳግማዊ ምኒልክ ተከታትለዋል፡፡
አቶ ሰሎሞን ገና በወጣትነታቸው በትራምፔትና በድራም ተጫዋችነት ሠልጥነው፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ባንድና ኦርኬስትራ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ከባንዱ አባላት ጋር ያደረጉት አስተዋጽኦ በትምህርት ቤቱ ታሪክ ውስጥ ሲታወስ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
አቶ ሰሎሞን በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ በትራምፔት የማስትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት በቡልጋሪያ ነው፡፡
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ የቆዩት አቶ ሰሎሞን፣ በተወለዱ በ70 ዓመታቸው ነሐሴ 21 ቀን 2009 አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ነሐሴ 23 ቀን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ነፍስ ኄር ሰሎሞን ሉሉ ባለትዳርና የሦስት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡
Average Rating