በነዚያ የነጠቡ ብዕሮች “ተራራውን ያንቀጠቀጠ” እየተባሉ ሲወደሱ የነበሩ ሁሉ እነሆ በአንድ ብላቴና ሲንቀጠቀጡ ከማየት የበለጠ ምስክር ከየትም ሊመጣ አይችልም። የ”ኢትዮጵያ” ስም ሲጠራ ብርክ እንደያዘው የሚሽመደመዱ፤ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት እየልን በጣት የምንቆጥራቸው የጥላቻና የበቀል ጉግማንጉጎች ለመሆናቸውም ትውልድን ደፍሮ ይናገርላቸዋል። የዚህ ቡድን አባላት ከመጠን ያለፉ ጭቃዎች መሆናቸውን እንኳ ለማወቅ ራሳቸውን በመስታወት የሚመለከቱ አይመስልም።
100 ሚሊዮን ሕዝብ እየመራ ያለው ይህ ቡድን በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ አርቆ ማሰብ እና አስተዋይነት ይጎድለዋል። አስተዋይነት ደግሞ የታላላቆች ውድ ስጦታ ስለሆነ ከርካሽ ሰዎች አይጠበቅም።
አበው ትተውልን ያለፉት አንድ ቅርስ፣ ያቺ የቀስተደመና ተምሳለት፣ ያቺ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ስትነሳ አጋንንት እንደለከፈው እርያ የሚክለፈለፉ የዘመናችን ጉዶች…. አንድ ነገር እንዳላቸው አንክድም። የበተ-መንግስቱ ታራ ደርሷቸው የተቀመጡት ትንሾች ያላቸው አንድያ ነገር መሃይምነት ብቻ ነው።ግና ኮንሰርት በመከልከል ቴዲን የጎዱ እየመሰላቸው ይልቅ ተወዳጅነቱን በእጥፍ ጨመሩለት።
አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ቴዲ አፍሮ ሲያርበተብታቸው አየን። በጩኸት ሳይሆን በዝምታ፣ በሰይፍ ሳይሆን በዘለሰኛ፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ብቻ የሚሰባብራቸው፣ ሰባብሮም ድል የሚያደርግ ጀግና። እንግዲህ በዚህ አይነት እጅግ በወረደ ተራ ነገር ይህን ድምጻዊ በገንዘብ ሊጎዱት ይችሉ ይሆናል። የህይወት ስንቅ የሆነው ፍቅር ግን ወዲህ ነው። የማይለወጥ የሚሊዮኖችን ፍቅር። እነ ደብረጽዮን አቅሙ ኖሯቸው ይህንን ቢነፍጉት ኖሮ ቴዲ ሊጎዳ ይችል ነበር። አንድ በቀነሱበት ቁጥር፣ በመቶ እጥፍ እንደሚጨመርበት ግን መቼም ሊያስተውሉት አይችሉም።
አያሌ እንቅፋቶችን አልፎ ዛሬ ምሽት ላይ በሂልተን ሆቴል ሊደረግ የነበረው የ”ኢትዮጵያ” አልበም ምረቃ ባይስተጓጎል ነበር የሚገርመን። ምክንያቱም አልበሙ “ኢትዮጵያ”፣ መልእክቱም ፍቅር እና አንድነት ነዋ! ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ሳይወድዷት ለሚገዙዋት ራስ ምታት ነው። ባንዲራዋን የሚጠሉ ሁሉ የሶስቱ ቀለማት መውለብለብ ያሳምማቸዋል።
ቴዲ አፍሮ፣ ፓርቲ ሳያቋቁም፣ በሶስትም ሆነ ባራት ሳይደራጅ፣ በአንዲት አልበም ብቻ ቤተ-መንግስቱን ያሸበረና የነቀነቀበት ምስጢር ይኸው ነው። የፈሪ ዱላቸውን የመምዘዛቸው ምስጢርም ኢትዮጵያዊነትን የመስበኩ ወንጀል ነው። አንድ ዜማ ወደ ፍርሃት ጥግ ሲገፋቸው የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ አሳጣቸው። ኮንሰርቱን ሲያግዱ፣ የምርቃቱን ዝግጅት ሲከለክሉ፣ የባንዱን አባል ከሃገር ሲያባርሩ…
እርግጥ ነው። ብላቴናው ላውንቸር ወይንም ሚሳየል ሳይሆን ኢትዮጵያን ከጀርባው ይዟል። ዛሬ በዙፋን ሆነው ይፈርዳሉ። የግዜ ጀግኖች አሁንም በንጹሃን ዜጎች በድፍረት ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ይበይናሉ። በዚህ ሁኔታ ለዘልዓለም የሚዘልቁም ይመስላቸዋል። ይህንን ሲያድደርጉ የሚተማመኑበት አንድ ነገር አለ። ፋጣሪን አይደለም። ሕዝብንም አይደለም። ጠመንጃቸውን ነው የታመኑበት። “የቆሙ የመሰለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ይላልና ቃሉ የዛሬ ፈራጆች ነገ እንደማይወድቁ ምንም ዋስትና የለም። በእርግጠኝነት የምንናገረው አንድ ነገር አለ። ትውልድ አምጿል። ልብ በሉ! በመጭው አመት አንድ አዲስ ነገር እናያለን። ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ይጠብቅ።
Average Rating